ማስታወቂያ

programs top mid size ad

ነሐሴ 08, 2005:ታሪክን የኋሊት

ነሐሴ 08, 2005

ምዕራባዊያን እንደ ቀንደኛ አሸባሪ፤ ግራ ክንፈኞችና ፍልስጤማውያን ደግሞ እንደ ዓለም አቀፍ ተዋጊ የሚቆጥሩት ካርሎስ ቀበሮ በፈረንሳይ የደህንነት ኃይሎች  የተያዘው የዛሬ 19 ዓመት በዛሬዋ ዕለት ነበር፡፡ ሰውየው ሲወለድ እናት አባቱ ያወጡለት ስም ኤሊች ራሚሬዝ ሳንቼዝ ይባላል፡፡ ይህን ቬንዙዌላዊ ግራ ክንፈኛ በአብዛኛው ዓለም የሚያውቀው ካርሎስ ቀበሮ በተሰኘው ቅፅል ስሙ ነው፡፡

ካርሎስ ቀበሮ የሚል ቅፅል ያወጡለት በብረት ትግል የተጐዳኛቸው የፍልስጤም ፖፑላር ፍሮንት የደፈጣ ተዋጊዎች ናቸው፡፡ የምዕራቡ ዓለም እስከ አልቃይዳው መስራች ኦሳማ ቢን ላዴን ዘመን ካርሎስ ቀበሮን በቀንደኛ አሸባሪነት ሲያየው ቆይቷል፡፡ የሕግ ባለሙያው የካርሎስ አባት ግራ ክንፈኛ ዝንባሌ የነበራቸውና የቮልሼቪክ  ፓርቲ መሪውና የሶቪየት ህብረት መስራች የቭላድሚር ኤሊች ሌኒን አድናቂም የፍልስፍና ዘይቤም ተከታይ ነበሩ፡፡ ከሌኒን ስም ተወሰውም ልጃቸውን ኤሊች የሚል ስም ያወጡለት በዚሁ መነሻ ነው ይባላል፡፡ ኤሊች ራሚሬዝ ሳንቼዝም የአባቱን የፍልስፍና መንገድ ወረሰ፡፡ በኩባም በሩሲያም እየተዘዋወረ ተማረ፡፡

ፖፑላር ፍሮንት፣ የተሠኘውን የፍልስጤም የደፈጣ ተዋጊ ቡድን፣ ተቀላቀለ፡፡ ወደ ማሰልጠኛቸውም ገብቶ፣ በፈንጂ ማፈንዳትና በሌላ ሌላውም የደፈጣ የውጊያ ጥበብ ተካነ፡፡

ምዕራባውያኑ፣ እንደ አለም አቀፍ አሸባሪ አርገው ሲቆጠሩት፤ ግራ ክንፈኞችና የፍልስጤም ተዋጊዎች፣ እንደ ዓለም አቀፍ የነፃነት ንቅናቄ አርበኛ አዩት፡፡

በእሱ የተመራ ቡድን፣ በቬየና ኦስትሪያ የነዳጅ አምራችና ላኪ አገራት ድርጅት /ኦፔክ/ ጽህፈት ቤትን ወረረ፡፡
የቡድኑ አባላት ካገቷቸው ከ60 የማያንሱ ሰዎች መካከል ሦስቱን ገደሉ፡፡
የተረፉትን ታጋቾች፣ ለመልቀቅ ካርሎስ ከ20 እሰከ 50 ሚሊዮን ዶላር የቤዛ ክፍያ መቀበሉ ይነገራል፡፡

ከዚያ በኋላ፣ በአውሮፓ የፍልስጤም የደፈጣ ተዋጊዎችንና ግራ ክንፈኞችን ይቀናቀናሉ ባሏቸው የበረከቱ ተቋማትና ግለሰቦች ላይ አደጋ ሲጥሉ፣ በአብዛኛው የካርሎስ ቀበሮ እጅ ነበረበት፡፡

ጥቃቱ የምዕራቡን ዓለም ያማረረ ሆነ፡፡

ካርሎስ የልቡን እየሠራ በተለያዩ የምስራቅ አውሮፓ ሶሻሊስት ሀገሮች መሸሸጉን ተያያዘው፡፡

አልተሳካላትም እንጂ የፈረንሳዩን የኒኩሊየር ተቋም በሮኬት ለማንጐድም ሞክሯል፡፡

የምዕራቡ ዓለም የደህንነት መስሪያ ቤቶች ካርሎስን ለመያዝ ዱካውን ማነፍነፍ ያዙ፡፡
ያዝነው ሲሉ ከመዳፋቸው ሲያፈተልክ ቆየ፡፡

ሊይዙት የተቃረቡትን ሁለት የፈረንሳይ የደህንነት ክፍል ሠራተኞች ገድሎ አመለጠ፡፡

ፓሪስ በንዴት ጦፈች፡፡

ቀበሮው ከቦታ ቦታ እየለዋወጠና አድራሻውን እየቀያየረ፣ ከምስራቅ አውሮፓ ወደ መካከለኛው ምስራቅ እየተዘዋወረ ለአዳኞቹ አልያዝ አልጨበጥ አለ፡፡

ዘመን እየተለወጠ የቀድሞ የምስራቅ አውሮፓ ሽርኮቹ፣ ሂድልን አታስወቅሰን ብለው እየገፉት መጡ፡፡

ሶሪያ -ገባ፡፡ አልተመቸውም፡፡ ወደ ሱዳን አመራ፡፡
ሱዳን እንደ እጆቿን ዘርግታ ቤት ለእንግዳ አለችው፡፡
ታመመ፡፡ ሆስፒታል ተኛ፡፡  አዳኞችህ እንዳይመጡ ቪላ ተዘጋጅቶልሃል አሉት፡፡

አመነ እሺ አላቸው፡፡
ታሞ በተኛበት ማደንዘዣ መርፌ ወጉት፡፡
እንዲህ እንደሆነ የፈረንሳይ የደህንነት ሠራተኞች ይዘው፣ በአውሮፕላን አንከብክበው ወደ ፈረንሳይ ይዘወት ሄዱ፡፡ ይሄ ከሆነ ዛሬ 19ኛ ዓመት ሆነው፡፡

ካርሎስ ፈፅሟል፣ በተባለው ወንጀል የእድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት፡፡ ይሄን ሳይወጣ ሌላ የእድሜ ልክ እስር ተጨመረለት፡፡
እንደሚባለው፣ ሱዳን ካርሎስ ቀበሮውን አሳልፋ የሰጠችው ስሟን ከአሜሪካው የሸብርተኞች ደጋፊ መንግስታት ጥቁር መዝገብ ለማስፋቅ በእጅ መንሻነት ነው ይባላል፡፡
ቁልፍ ቃላት
ምላሽ