• United Bank S.C.

    ሕብረት ባንክ አ.ማ.

  • Slider Two

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Sldier Three

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ሸገር | ወግ

ውሸት ለመናገር አትሻም ምላሴ

እናት ልጇን… 

“ማሙሽ፣ ሂድና ከሸምሱ ሱቅ ስኳር፣ እጣንና፣ ሰንደል ገዝተህልኝ ና፡፡”
“እሺ፣ እማዬ፡፡”

ልጅ ይሄዳል፡፡ ተመልሶ ሲመጣ የያዘው ስኳርና ሰንደሉን ብቻ ነው፡፡ እንባ ህቅ፣ ህቅ ይለዋል፡፡

“እጣንም ግዛ ብዬህ አልነበር እንዴ፣ የት አደረግኸው?”
“እ..እማዬ፣ ልጆቹ ፍራንኩን ነጠቁኝ፡፡” የፓስቴው ዘይት እኮ ገና ሙሉ ለሙሉ ከከንፈሩ አልተጠረገም፡፡

እናት ጭኑ ስር ትገባና ልምዝግ… “ይሄን ውሸት ተው አላልኩህም! እ!... መዋሸት ይለምድብሀል አላልኩም!”

ቁንጥጫ ካልሠራ ቅጣቱ ወደ አለንጋ ‘አፕግሬድ’ ይደረጋል፣ በአለንጋም ካልሆነ ምን ችግር አለው… ያኔ በርበሬ እኮ በልተነውም ስለሚተርፈን እንደዕጣን ነገርም እንጠቀምበት ነበር፡፡

ቅጣቶቹ እንተዋቸውና... ትልቁ ነገር ግን ውሸት መናገር ምን ያሀል አስከፊ እንደነበር የሚያሳይ ነው፡፡ “መዋሸት ያድግብሀል አላልኩህም!” ከማለት የተሻለ ማገረጋገጫ ምን አለ!
እንደ ዘንድሮ ሳይሆን፣ “እከሌ ውሸታም ነው” ከተባለ እኮ መንደር ሙሉ ጣት ሲቀሳሰርበት፣ ከጀርባው ሲንሾካሾክበት ነው የሚውለው፡፡

“እከሊት የለየላት ቀጣፊ ነች፣” ከተባለች በቡናውም፣ በእድር እቃ አጠባውም በምናምኑም ስሟ ሲነሳና ሲወድቅ ነው የሚኖረው፡፡ የዛሬን አያድርገውና ውሸት እንዲህ ያስጠላ ነበር… ጊዜ ተለውጦ ከውሽት ጋር እንዲህ ከመዋደዳችን በፊት! ግን ውሸት ብዙ ነገር እያጠፋ ነው፡፡

የውሸት መግለጫና ማብራሪያ፣ የሀሰት መሀላ፣ የሀሰት ምስክርነት፣ የሀሰት ሰነድ፣ የሀሰት ማስታወቂያ፣ የሀሰት ምርት…ብዙ ነገሮች እየተበላሹ ነው፡፡

እንዲህ ሆኖ ታዲያ ውሸት…ተቀብለነው፣ ተግባብተነው አብረነው የምንኖረው አይነት ነገር እየሆነ ይመስላል፡፡ ከምናምናቸው ነገሮች የማናምናቸው ነገሮች እየበዙ ነው፡፡ እንዲህም ሆኖ “ምን ይደረግ፣ ጊዜው ነው፣ እያልን እናልፋቸዋለን፡፡

“ስሚ ያ የባንኩ ጉረኛ ከሚስቱ ሊፋታ ነው አሉ፡፡”
“በምን አወቅሽ?”
“ሰው ነገረኝ፡፡”
“ማን ነው የነገረሽ?”
“ያቺ ጎረቤቴ ነቻ…”

“ምነው! ምነው! እሷን ሰው ብለሽ የምትልሽን እሺ ብለሽ ትቀበያለሽ! አገር ያወቃት ቀዳዳ አይደለች እንዴ!”

ውሸት እንዲህ ያስጠላ ነበር…ዛሬ፣ ዛሬ ከማስወቀስ ይልቅ እሱ ነው ኖሮን ያወቀበት አስብሎ ኒሻን የሚያስጭን እየሆነ ነው እንጂ!

ውሸት ለመናገር አትሻም ምላሴ
ለእውነት እሞታለሁ አልሳሳም ለነፍሴ

ተብሎም ተዘፍኖ ነበር… ውሸት መናገር ነውር በነበረበት ዘመን፣ እውነተኝነት በያስከብርበት ዘመን፣ “እሱ እኮ የለየለት ቀጣፊ ነው” ከመባል የጠቆረ የስም ጥላሸት ያልነበረበት ዘመን፡፡

 

ዘንድሮ ውሸት… “ችግሩን ለመፍታት ተግተን እየሠራን ነው፣” በምትል መግለጫ ቢጤ ነገር፤ “በደንበኞች ከፍተኛ ተወዳጅነት ያተረፈው ምርታችን” በምትል ማስታወቂያ ቢጤ ነገር…“በህዝብ ጥያቄ መሰረት ደግመን እናቀርበዋለን፣” በምትል የሚዲያ ሽወዳ ቢጤ ነገር…ብቻ በተለያየ አይነት ስሟ እየተቆለጳጰሰ ትመጣለች፡፡

እኛም… “አቤት ውሸት!” ብለን ጭንቅላችንን መያዝ እየረሳን ነዋ! ውሸት ከምግባር ጉድለት ይልቅ የብልጥነት መለያ ሆኗላ! የሚዋሽ ሰው… “እሱ እኮ ኑሮን አውቆበታል” የሚባልበት ጊዜ ነዋ! “እሱ እኮ ውሸታም ነው፣” ተብሎ ሰው ፊት የሚነሳበት ዘመን እየቀረ ነዋ!

በነገራችን ላይ ብዙ ጊዜ በየመሥሪያ ቤታችን የግዳችንን እንድንዋሽ የሚያስገድዱን ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡ “አንድ ሰው ‘በዓለማችን 300 ቢሊዮን ኮከቦች አሉ…’ ስትለው ያምንሀል፡፡ ግን ‘ግድግዳው እርጥብ ስለሆነ አትደገፈው…’ ስትለው አያምንህም፣” የሚሏት ነገር አለች፡፡

ስለሆነም፣ እውነት በምንናገርበት ጊዜ “እሱን እንኳን ተወው!” አይነት ምላሽ ስናገኝ የግድ ሊሰሙ የፈለጉትን እንነግራቸዋለን፡፡ ጠዋት ቢሮ ስንገባ አለቅየው “ምነው እስካሁን አረፈድሽ?” ይላል፡፡ “አውቶብሷ ዘግይታ ነው የመጣችው፣” ወይ “የታክሲው ሰልፍ ረጃጅም ነበር፣” ምናምን ስንል አለቃ “ሂጂና የአርመን ቱሪስት ብዪ፣” አይነት አስተያየት ያየናል፡፡

ስለዚህ “የጎረቤታችን ሰው ሌሊት ታሞ እሱን ይዘን ሆስፒታል ለሆስፒታል ስንዞር ነው ያደርነው፣” እንላለን፣ አለቃም ያምነናል፡፡ ጎረቤትየው እኮ ቢሰማ “ኸረ የሚያዞር ሲያዞርሽ ይደር!” ነገር ይል ነበር፡፡ እንዲህ አይነት ሟርት የወዳጅ አይደለማ! እሱ በዛ ሰዓት የማታውን የዞረ ድምር ለማስታገስ ሦስተኛ ዙር ሹሮ ፍትፍት እየበላ ሊሆን ይችላላ! 
“አንድ አጎቴ ሞቶ ቀብር ነበርኩ፡፡”

“የአንድ አክስቴ አረባ ሆኖ ሥራ ሳግዝ አድሬ ደክሞኝ ነው…፡፡”

እውነተኛውን ምክንያት ስንናገር አንታመን ብለን በውሸት የጨረስናቸው የእውነትና የልብ ወለድ አክስትና አጎቶቻችን ብዛት ራሱ ለጊነስ ሬከርድ የሚበቃ ነው፡፡

ከወራት በፊት የሆነ ነው፡፡ ‘ልጃችሁን ለልጃችን’ ‘ልጃችሁን ለልጃችን’ ሊሉ የሄዱ ሽማግሌዎች ከበድ ያለ ጥያቄ ይቀርብላቸዋል፡፡

“ለመሆኑ መጠጥ ላይ እንዴት ነው?”

“እሱ መጠጥ በዞረበትም አይዞር፡፡ ከውሀ በስተቀር ንክች አያደርግም፣” ሲሉ ከአሥራ ምናምን ዓመት በላይ ለሆኑ ሊከለከል የሚገባውን ውሸት የሰባ ምናምን ዓመት አዛውንቶቹ ተናገሩ፡፡ አዛውንቶቹ ዘላለማቸውን እየዋሹ ቢመጡ እንኳን በዛ እድሜ “አቤቱ ለእስከዛሬው ይቅር በለኝ!” ምናምን የሚሉበት ወቅት ነበር፡፡ “ውሸት ለመናገር አትሻም ምላሴ፣” የሚሉበት ወቅት ነበር፡ አልሆነም እንጂ፡፡

ጊዜው ነዋ! “አሁን ማን ይሙት፣ ዘንድሮ አንድ ሁለት ቢራ እንኳን የማይቀምስ ወንድ አለና ነው!” ብሎ የሚያፋጥጥ የሴት ወገን የለማ! እጩ ሙሽራው እኮ የየጠዋቱን ራስ ምታት ስላልቻለው ውጪ ላሉት ጓደኞቹ “ኸረ እባካችሁ የዞረ ድምር ማስታገሻ ኪኒን ላኩልኝ!” ብሎ እየተማጸነ ነው፡፡

ድርጅታዊና ተቋማዊ ውሸት አስቸግሮናል፡፡ ከላይ ጀምሮ ውሸት ስሙን እየቀያየረ ይመጣል፡፡ “ጉዳዩን ለማስተካከል ኮሚቴ አዋቅረን እየሠራን ያለንበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡” ከዛም ከስብሳው በኋላ አንዱን ጠርቶ “ስማ… ወይ ኮሚቴ አቋቁምና የሆነ ነገር አድርግ፣” ይባላል፡፡ አንድ ትልቅ ባለስልጣን ጋዜጠኞች ሰብስቦ መግለጫ ሲሰጥ የት ቦታ እንደዋሸ በየቤቱ ያለ ሰው እንደሚያውቅ አለመጠርጠር ቅሽምና ነው፡፡

ሪል ስቴቶቹ ምን የመሰለ በኮምፒዩተር ምስል የታጀበ ማስታወቂያ ለቀው “ገንዘብ ካለስ እዚሀ መኖር ነው!” ምናምን ያስበላል፡፡ በቦታው ሄዶ ሲታይ ግን…ያ መለስተኛ ድግስ ማስተናገድ ያስችላል የተባለው ሳሎን ሰዉ ከግድግዳው ጋር “አቦ አትግፋኝ!” እየተባባለ የሚያልፍበት ሊመስል ምንም አይቀረው፡፡ ስለዚህ በማስታወቂያው አላሳሳቱንም፣ ቅልጥ አድርግው ዋሹን እንጂ፡፡

ያልተደረገውን ተደርጓል ብለው የሚነግሩን ባለስልጣናት… እየዋሹን ነው፡፡ የሆነ ቁጥር በመቶኛ ሲነገር ሀያ በመቶ የማይሞላውን ቁጥር “ወደ ሰባ በመቶ እየተጠጋ ነው፣” ብሎ ነገር…የፖለቲካ ብልጥነት ሳይሆን ውሸት ነው፡፡

ውሸት የ‘ስትራቴጂ’ ጉዳይ ሲሆን አስቸጋሪ ነው፡፡ ማስታወቂያዎች ላይ ማግነን ያለ ነው፡፡ ‘ሀያ አራት ሰዓት እሠራለሁ’ የሚለው ክሊኒክ አንድ ሰዓት ላይ ሰትሄዱ ተዘግቶ ስታገኙት የማሳሳት ጉዳይ ሳይሆን ‘የፈጠጠ’ የሚሉት አይነት ውሸት ነው፡፡

ግን “አቤት ውሸታቸው!” የሚል የለም፡፡ “ኸረ እነሱ ዝም ብለው ሲዘባርቁ ነው፣ አንድ ሰዓት ነው የሚዘጉት፣” ይባላል እንጂ፣ “ምን አይነቶቹ ቀጣፊዎች ናቸው፣ እንዲህ ይዋሹናል!” አይባልም፡፡

‘የተሳሳተ መረጃ’ የሚሏት ነገር አለች፡፡ የመሥሪያ ቤቱ አለቃ ቋፍ ላይ ያለው ድርጀቱን “የሠራተኞቹ የሥራ መንፈስ በጣም የሚያስደስት ነው፣” ምናምን ብሎ ሪፖርት ማሳመሪያ ቢያቀርብ ‘የተሳሳተ መረጃ’ ብቻ የሚባል ሳይሆን፣ ክንፍ ያወጣ ውሸት ነው፡፡

ለባለ አንድ መኝታ ቤት ኮንዶሚኒየም ስንት ዓመት ሲገፈግፉ ኖረው በመጨረሻ “አንድ መኝታ ነው! ሲያምራችሁ ይቅር፣” ማለት ምንድነው!

ውሸትን የማያውቅ እውነተኛ ሰው ነው
ተብዬ መጠራት ታላቅ ኩራቴ ነው
ተብሎ ተዘፍኖ ነበር፡፡

እግረ መንገድ… “ቅዳሜና እሁድ ውሀ በእንትን፣ በእንትንና እንትን ሰፈር ስለሚቋረጥ ጥንቃቄ አድርጉ፣” ይባላል፡፡ ነገራችን አንዳንዴ ያልተከፈለበት ስታንድአፕ ኮሜዲም ሊመስል ምንም አይቀረው፡፡

ከተጠቀሱት ሰፈሮች አንድ ሁለቱ እኮ ውሀ ከጠፋባቸው አስር ቀን አልፎ አሥራ አንደኛውን ይዘዋል! እና ‘ለቅዳሜና እሁድ ተጠንቀቁ’ አይነት ነገር…አስር ቀን ሙሉ ጉሮሯቸው ለደረቀባቸው ቆሽት የምታበግን ነገር ነች፡፡

“ለመሆኑ ምን እየሠራህ ነው?”
“በሀቅ በምሠራት ሀብት ለማግኘት እየሞከርኩ ነው፡፡”
“በሀቅ የምትሠራ ከሆነ ብዙ ተፎካካሪ አይኖርብህም፡፡”

ስለሆነም “እከሌ ሁለት ዓመት እንኳን ሳይሞላ ሀብታም የሆነው በሀቅ ሠርቶ ነው፣” ስንባል ማመን ትተናል፡፡

ስታቲስቲክስ ማመን ትተናል፡፡ ቁጥሮች ትርጉም አልሰጠን ብለዋል፡፡ ማረገጋጫ ሳይሆኑ ማሳሳቻ እየሆኑብን እምነታችንን ሁሉ አሟጠውብናል፡፡ በአጠቀላይ ቁጥር ማመን ትተናል፡፡ የምናምነው ቁጥር ፊት ለፊት የምናየውን ብቻ ሆኗል፡፡ ለምሳሌ ጀርመን ብራዚልን ሰባት ስታጠጣት አይነት ነገር፡፡ “ምርታችን በፐርሰንት አድጓል” ሲሉን ማመን ትተናል፡፡

ፖለቲከኞች ማመን ከተውን ሰንብተን ከርመናል፡፡ መግለጫዎችን ማመን ትተናል፡፡ አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ማመን ትተናል፡፡

ይሄ ሁሉ ሆኖ ግን “እከሌ ውሸታም ነው ሲባል” ብዙ ጊዜ አንሰማም፡፡ ውሸትን ከእነጓዙ፣ ከእነምናምኑ የተቀበልነው ነው የሚመስለው፡፡ ከእነጓዙ ባይሰፍርብን ይህን ያሀል አይበዛም ነበር፡፡

ወይም ውሸት ይህን ያሀል ከተወዳጀን አይቀር አገር አቀፍ መስፈርት ይውጣለትና፡፡ ወርቅ ውሸት፣ ብር ውሸትና መዳብ ውሸት ይባልና ይለይለት፡፡ በአትሌቲክሱ እየተመናመነ የመጣውን የወርቅ ክምችታችንን በዚህ እናሳድገው ነበር፡፡

ሰውየው ስለ አንዱ ሲናገር…“የለየለት ውሸታም ከመሆኑ የተነሳ ምንጊዜም ከጨበጥኩት በኋላ ጣቶቼ በቦታቸው ስለመኖራቸው እቆጥራቸዋለሁ፣” ያለመታመንም ይህን ያህል ነው፡፡

በመጨረሻም… ሰውየው ምን አለ አሉ፣ “‘በዓለም ላይ ከማንም በላይ እወድሀለሁ’ የምትልህን ሴት አትውደድ፡፡ ይሄን ሁሉ ጊዜ ወንዶች ላይ ሙከራ ስታደርግ ቆይታለች ማለት ነው፡፡” ውሸቷን ነው፣ አትመናት…ሙከራውን የማትቀጥልበት ምክንያት የለም ለማለት ነው፡፡

ስትደነብር ኑር ያለው ሰው !

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

በማኅበረ ሰብ ገጾች ያጋሩ

Submit to FacebookSubmit to Google PlusSubmit to TwitterSubmit to LinkedIn
Sheger 102.1 AudioNow Numbers