• United Bank S.C.

    ሕብረት ባንክ አ.ማ.

  • Slider Two

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Sldier Three

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ሸገር | ወግ

የኮንዶሚኒየም ነገር - “ተዋቸው፣ የኮንዶሚኒየም ልጆች ናቸው”

ልጆቹ የፕሬሚየር ሊግ ኳስ ለማየት አንድ ቤት ገብተዋል፡፡ ቀደም ብለው ገብተው የማያውቁበት ቤት ነው፡፡ የሚደግፉት ቡድን ድንገት ግብ ያስቆጥራል፡፡ ብድግ ብለው ይጮሃሉ፡፡ ይሄኔ ከቤቱ መደበኛ ደንበኞች አንዱ “እባካችሁ ድምጻችሁን ቀንሱ!” ይላል፡፡ እንደዛ አይነት አደጋገፍ እዛ ቤት ውስጥ የተለመደ አልነበረም፡፡ ሌላኛው ሰው ምን ይለዋል፣ “ተዋቸው፣ የኮንዶሚኒየም ልጆች ናቸው…”

የኮንዲሚኒየም ልጆች ?

መቼም ከመሬት ተነስቶ ሰው ላይ በቅጽል ልጠፋ የኤክስፐርት ችግር የለብንም፡፡ ‘የኮንዶሚኒየም ልጆች’ ግን ዝም ብሎ ቅጽል አይደለም፡፡ እንደዛ የተባለው ኮንዶሚኒየም ፎቆች ላይ የሚኖሩ ትናንሽ ልጆች እንደልባቸው መቦረቅ ስለማይመቻቻው … ብዙ ጊዜም ቤት ተቆልፎባቸው ነው የሚያድጉት የሚባል ነገር አለ፡፡

“ተዋቸው፣ የኮንዶሚየም ልጆች ናቸው”… ትንሽ ማጋነን ያለበት ቢመስልም አንድ እውነት ግን አለው፡፡ ልጆች መንደሮች ውስጥ እንደፈለጉት እንደሚሯሯጡት የኮንዶሚኒየም ኑሮ ይህንን ነጻነት አይሰጣቸውም፡፡ ከዓመታት በፊት ከኮንዶሚኒየም ፎቅ ላይ ሰለወደቁ ልጆች ዜና ሰምተናል፡፡

ለነገሩ የኮንዲሚኒየም ወይም የጋራ ቤቶች ኑሮ ይህን ያህል የሚመች ነው እንዴ! እንደስሙ እውነት ተሳስበን በጋራ እየኖረን ነው እንዴ… ለነገሩስ ለጋራ ኑሮ የሚያመቹ ነገሮች ሁሉ የተሟሉ ናቸው እንዴ ! ትናንሾቹ ልጆች ብቻ ሳይሆኑ ሌላውስ በራሱ ላይ ቆልፎ አይደል እንዴ የሚኖረው!

“እዚህ ቤቶች፣ ሰው የለም እንዴ!”
“ኧረ አለን፣ እንደምን አደሩ እትዬ ቦጌ?”
“እግዚአብሔር ይመስገን፣ ነይ ቡና ፈልቷል፡፡”
“እሺ፣ መጣሁ፡፡”
“እግረ መንገድሽን ብርቄንም ነይ በያት፡፡”

 

እንዲህ መባባል ትልቅ እሴት ነበር፣ ትልቅ የጋራ ኑሮ ማሳያ ነበር፡፡ በአጥር ላይ “እባክሽ ሹሮ ስላለቀ በጠሳ ቢጤ ላኪልኝ፣” መባባል እኮ ትልቅ የማህበራዊ ኑሮ እሴት ነበር፡፡ ኮንዶሚኒየም ገባንና ጎናችን ያለው ሰው ማን ይሁን፣ ምን ይምሰል ለዓመታት የማናውቀበት ጊዜ ላይ ደረስን፡፡

በቅርቡ የሆነ ነው፡፡ ልጅት ሦስተኛ ፎቅ ላይ ነው የምትኖረው፡፡ እናም ትሞሸራለች፡፡ ከሌላ ስፍራ የመጡ ወዳጅ፣ ዘመድ፣ አጃቢዎቿ ዘፈኑን አያቀለጡ ይዘዋት ይወጣሉ፡፡ ፎቁን አውርደው መኪና እስኪያስገቧት አንድም ነዋሪ በሩን ከፍቶ ብቅ አላላም፣ ወይም አልሸኘም፡፡ መንደር ቢሆን አኮ አይደለም የነቃው የተኛው ተነስቶ “እልል” እያለ ነበር የሚሸኘው! ሰርግ እና መሰል ነገሮች እኮ ትልቅ የጋራ ኑሮ ማሳያ ነገሮች ነበሩ…

በእርግጥ በኮንዶሚኒየም እንደ መንደር መኖር አይቻል ይሆናል፡፡ የመንደር አይነት ማህበራዊ ኑሮ እንዳለ ማምጣቱ ያስቸግር ይሆናል፡፡ ግን ለምንድንው የሚያጋጩን ነገሮች የሚበዙት! ለምንድነው “እኔ ብቻ…” አይነት መንፈስ የበዛው!

ጥብሱ ይንቻቻል፣ በመጥበሻ ተደርጎ ከሰል ላይ ተጥዶ፡፡ የጥብሱና የከሰሉ ሽታ በየሰዉ ቤት እየገባ ነው፡፡ ደግሞ በዓል ነው፣ ደግሞ የደስታ ጊዜ ነው፣ ደግሞ የፌሽታ ጊዜ ነው፡፡ እና ጥብስ ሲያንሰው ይሆናል፡፡

ግን ችግሩ ይህኛው ጥብስ ይጠበስ የነበረው በአንድ የኮንዶሚኒየም ህንጻ፣ አምስተኛ ፎቅ፣ በመተላለፊያው ወይም ኮሪዶሩ ላይ ነበር፡፡ አዎ፣ አምስተኛ ፎቅ ነዋሪው በሚተላለፍበት ቦታ ላይ! በተለይ በበዓል ጊዜ የአንዳንድ ኮንዶሚኒየሞች ኮሪደሮች ወደ ማእድ ቤትነት ይለወጣሉ ነው የሚባለው፡፡ ዶሮ ወጡ የሚሠራው ብቻ ሳይሆን እድለ ቢሶቹ ዶሮዎች ሁሉ የሚገነጣጠሉት እዛው ነው፡፡ በዚህ የተነሳ በሚፈጠሩ ምልልሶች ብዙ ጊዜ የበዓል መንፈስ ይደፈርሳል፡፡ እንደውም በግ ኮንደሚኒየም በር ላይ አስሮ ሌሊቱን ሁሉ ሲያስጮህ የሚያድር አለ፡፡

ነገሩ ሁሉ፣ “ተዋቸው፣ የኮንዶሚየም ልጆች ናቸው፣” አይነት ሲሆን የተሳሰቱ ነገሮች አሉ ማለት ነው፡፡

“ስማ፣ እንዴት ነው የኮንዶሚየም ኑሮ?”
“ይኸው ይዘነዋል፣ መቼም ውለን እየገባንበት ነው፡፡”
“ሦስት ነው አራት ዓመት ስትቆይ መአት ወዳጅ ሳታፈራ አልቀረህም፡፡”
“ወይ ወዳጅ! ስማ ግራና ቀኜ ያሉ ኮንዶሚኒየሞች ውስጥ እንኳን ያሉትን ሰዎች አላወቃቸውም፡፡” የብዙ ኮንዶሚኒየሞች ነገር እንዲህ ነው፡፡

በነገራችን ላይ፣ በተለይ ከአንድ መንደር የሄዱ ሰዎች አንድ ላይ የሰፈሩባቸው ኮንዶሚኒየሞች ውስጥ የተሻለ ማሀበራዊ ትስስር አለ፡፡ አብዛኞቹ የሚተዋወቁ በመሆናቸውና መንደር ውስጥ የነበራቸውን ትብብር ስላልበጠሱት “አንተ ትብስ/አንቺ” ልምዳቸው እንዳለ ነው፡፡ ክፋቱ ብዙ የጋራ ቤቶች አካባቢ ይህ መንፈስ የለም፡፡

ፎቅ የሚኖር ሰው ነው፡፡ አንድ ቀን ጠዋት ውሀውን ሲከፍት የለም…እንደተለመደው፡፡ ሰውየው በሩን ቆልፎ ወደ ሥራው ይሄዳል፡፡ መሀል ላይ ግን ውሀው ይመጣል፣ መጣና ለሰውየው ለፊቱ ማበሻ የጠፋው ውሀ ለእሱ ቤትና ከእሱ ስር ላሉት ሁሉ ተረፈ…

በመለስተኛ ጎርፍ መልክ፡፡ ለካስ ውሀ መጥፋቱን ሲያውቅ ቧንቧውን እንደመዝጋት ክፍቱን ትቶ ነበር የሄደው፡፡ ምናልባት የውሀ ነገር አስመርሮት “ውሀው ድንገት ቢመጣስ!” የሚል ሀሳብ አእምሮው ውስጥ ስለሌለ ይሆን ይሆናል፡፡ ምናልባትም ሀላፊነት የማይሰማው “እኔ ከሞትኩ…” አይነት ሰው ይሆናል፡፡ በር ቆልፈን የጎረቤት ባይተዋሮች ባንሆን ኖሮ ምናልባትም ይሄን ያህል ግዴለሽነት አይኖር ይሆናል፡፡

ከዚህ የባሰ ደግሞ አለ፡፡ ሰውየው ፎጣውን ተጠቅሞበት በቆሻሻ ውሃ መውረጃው ውስጥ ይወረውረዋል፡፡ ከዚያ ከበላይ ያሉ ነዋሪዎች የሚለቁት ቆሻሻ ውሀ ሁሉ አልሄድ ይላል፡፡ ለካስ ፎጣው መውረጃው ውስጥ ተወትፎ አግቶታል! አሁን ይሄ ሰው ፎጣን የሚያክል ነገር ቧንቧውን መዝጋት እንደሚችል ማወቅ አቅቶት ነው! አንዳንዱ ነገር ደግሞ ለአግራሞት እንኳን ያስቸገራል፡፡ ኮንዶሚኒየም ሳሎን ውስጥ ልጆቹን ኳስ የሚያጫውት አባት ምን ሊባል ይችላል! ትንሹ ነገር እንኳን ኮሽ ሲል በሚያስተጋባበት ህንጻ ውስጥ ኳስ!

ነገሩ ሁሉ፣ “ተዋቸው፣ የኮንዶሚየም ልጆች ናቸው፣” አይነት ሲሆን የተሳሰቱ ነገሮች አሉ ማለት ነው፡፡

አብዛኞቹ የኮንዶሚኒየም ነዋሪዎች ባለቤቶች ሳይሆኑ ተከራዮች ናቸው ይባላል፡፡ ወደ ዘጠና በመቶ ያሰጠጓቸዋል፡፡ በጋራ መኖሪያ በጋራ መኖር ያልተቻለው አንዱም ምክንያት ይሄ ነው የሚሉ አሉ፡፡ ተከራዮች “ነገ ጥዬ ለምሄደው ቦታ ምን አጨናነቀኝ፣” ይላሉ ነው የሚሏቸው፡፡ ግን ተከራይም ሆነ፣ ባለቤት ተሳስቦ፣ አንዱ የሌላውን መብት አክብሮ መኖር “የዛሬ ዓመት፣” “የዛሬ አምስት ዓመት” ተብሎ ቀጠሮ የሚይዙበት ነው እንዴ! ማማሻስ እድሜ አይደለም እንዴ!

ሰላማቸውን የሚነጠቁ የኮንዶሚኒየም ነዋሪዎች አከራዮችንም ይኮንናሉ፡፡ “አንዴ ካከራዩ በኋላ ኪራይ ለመሰብሰበ ካልሆነ ብቅ አይሉም፣” ይሏቸዋል፡፡ የኪራይ ነገር ካነሳን አይቀር የኮንዶሚኒየም ኪራዮችን ፈንድ የሚያደርጉ የዳያስፖራ ወገኖቻችን ናቸው የሚባል ነገር አለ፡፡

እሱ ዳያሰፖራው ለእሷ የአገር ልጅ ኮንዶሚኒየም ይከራይላትና ምናልባት በዓመት አንዴ ብቅ ቢል ነው፡፡ ይሄ ብቅ ለማለት ዓመት የሚፈጀው ነገር አንዳንዴ ግራ የሚያጋባ ነገር አለው፡፡ ነገሩ የአዳምና ሔዋን ግንኙነት መሆኑ አይደል እንዴ! ታዲያ በዓመት አንዴ ኢንቬንትሪ መሆኑ ነው እንዴ ! ምናልባት ከተሞክሯቸው የምንማረው ነገር ካለ ብለን ነው፡፡

እዚህም ሆኖ ስንት ዓመት የቆየ ትዳር፣ ቤተሰብ፣ ልጆችና ፈረስ የሚያስጋልብ ጂ ፕላስ ምናመን ቤት ያላቸው ሰዎችም በተባሉት ዋጋ ኮንዶሚነየም ይከራያሉ ይባላል፡፡ ለኢመርጀንሲ እንዲሆናቸው ማለት ነው፡፡

በአንድ በኩል በግልጽ ለቤተሰባቸው፣ በሌላ በኩል በድብቅ ኮንዶሚኒየም ላስቀመጧቸው ቅምጦች ቀለብ የሚቆርጡ የፈራንክ ችግር የሌለባቸው ብዙ ናቸው፡ እንደውም ለኮንዶሚኒየም ቤቶች ኪራይ ይህን ያህል መወደድ እነሱ የዳያስፖራ አስቀማጮቻችን ምክንያቶች ናቸው የሚባል ነገር አለ፡፡ ፊት ለፊት የምናያት አዲሰ አበባና፣ ከመጋረጃ ጀርባ ያለችው አዲስ አበባ ሁለት የተለያዩ ከተሞች ናቸው እኮ!

አሁን ለምሳሌ መንደር ውስጥ በጠጪነቱ የሚታወቅ ሰው ጥምብዝ ብሎ እየለፈለፈ ሌሊት ቤት መግባት ይህን ያህል ሰበር ዜና አይሆንም፡፡ ግፋ ቢል “ደግሞ ተነሳበት፣” ቢባል ነው፡፡ አንድ ኮንዶሚኒየም ወስጥ የተከራየ እንዲህ አይነት ሰው ነበር፡፡

ከምሽቱ አራት ሰዓት ተኩል አምስት ሰዓት ጥምብዝ ብሎ እየጮኸ ይለፈልፋል፡፡ እሱ ሦስተኛ ፎቅ ሲለፈልፍ ስድስተኛ ፎቅ ያሉ ሰዎች ሰላም ይናጋል፡፡ ሦስተኛ ፎቅ የሚለፈልፈው ስድስተኛ ፎቅ ይረብሻል፡፡ ቢመከር አልሰማ ብሎ ነዋሪዎቹ ለአከራዩ ነግረውት አስወጥተውታል፡፡

ነገሩ ሁሉ፣ “ተዋቸው፣ የኮንዶሚየም ልጆች ናቸው፣” አይነት ሲሆን የተሳሰቱ ነገሮች አሉ ማለት ነው፡፡

ደግሞ ይሄ የአጥር ማጠር ነገር አለ፡፡ ኮንደሚኒየም ፎቆች ላይ አጥር! አምስት የኮንዶሚኒየም ቤቶች በተደረደሩበት ጥግ ያለው አምስተኛው ሰው የእሱን ብቻ ለይቶ ያጥራል… ፊት ለፊት ያለው ሰውዬ በር አጠገብ ድረስ ሄዶ፡፡ አንድ ወዳጄ “አርባ አራት ቁጥር ጫማ የማታክል ስፍራ ነች እኮ!” ብሎኛል፡፡ ከእሱ ቀጥሎ ያለውም እንዲሁ፣ ሌላውም እንዲሁ፡፡ የሚገርም ነገር ነው፡፡

በእነኚህ አይነት ድርጊቶች የተነሳ የሚፈጠሩ ውዝግቦች የጸጥታ ሀይሎችን እስከመጥራት ያዳርሳሉ ይባላል፡፡ በራችንን መከርቸማችን አልበቃ ብሎ እሷንም እንደገና በሌላ አጥር የባቢሎን ግንብ አይነት ለማድረግ መሞከር እስቲ ምን ይባላል ! ኮንዶሚኒየም ላይ ወጥቶ አጥር ማጠር ምን የሚሉት ነገር ነው!…

ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ቤት ተሠርቶ ርክክብ ሲካሄድ እውነት ኮንዶሚኒየሞቹ ነካ፣ ነካ ተደርገው ለመኖር አመቺ ናቸው? እውነት ቁልፍ በተሰጠ ማግስት እቃ ሰብስቦ “ከአትክልት ተራ የቤት እቃ የሚጭን መኪና አምጡልኝ፣” ነገር የሚያስብል ነው ! ምክንያቱም የጋራ መኖሪያ ውጣ ውረድ የሚጀምረው ከቁልፍ መረከብ ጀምሮ ነውና፡፡

“እነ አከሌ፣ እነ እከሌ ኮንዶሚየም ደርሷቸዋል፣” ይባላል፡፡ ከዛ ከጥቂት ወራት ‘ሰስፔንስ’ በኋላ ቁልፍ ይሰጣል፡፡ አለቀ፡፡ በቃ ጣጣው ያለቀ ይመስል ዘወር ብሎ የሚያይ የለም፡፡ …“ቤት ካገኙ አነሳቸው!” አይነት ነገር ነው ሚመሰለው፡፡ ግን እውነት ለመናገር ጣጣው ያኔ ነው የሚጀመርው፡ ሰዎች የደረሳቸውን ኮንዶሚኒየም መኖሪያ ለማድረግ የሚያወጡት ወጪ ባይነሳ ይሻላል፡፡ በዚሀ ላይ የማሰተካከያ ግንባታውን የሚሠሩ ሰዎች ማጨበርበር ሳይረሳ ነው፡፡ አንድ ወዳጄ ጨካኝ የሚለው ቃለ አይገልጻቸውም ነው ያለው፡፡

ገና ደግሞ የስንት ዘመን እዳ ከፈላ አለ፡፡ ይህ ሁሉ ተችሎ ግን የሚፈረፈር ግድግዳ ያለው ኮንዶሚኒየም ሰጥቶ … “ያውልህ ኑርበት!” ማለት ምን ማለት ነው! ከማስረከብ በፊት ቢያንስ፣ ቢያንስ ትንንሿን ነገር እንኳን ለመፈተሽ የሚያስችል እውቀትና አቅም ጎድሎናል እንዴ! ቢያንስ፣ ቢያንስ በእርግጥ ቃል በተገባው መሰረት ተሠርቶ እንደሆነ መፈተሽ አይቻልም ነበር እንዴ !

ቢያንስ፣ ቢያንስ ቧንቧዎችና የኤሌክትሪክ ገመዶች በተገቢውና ደህንነቱ በተረጋጋጠ መንገድ ለመሠራታቸው ማረጋገጥ ይህን ያህል የኳንተም ፊዚክስ እወቀት የሚጠይቅ ነው እንዴ! ገና የእዳ መአት እንዴት እንደሚከፍሉ እንቅልፍ ያሳጣቸው ሰዎች ቧንቧ ለማስተካካል ወለሉን ሁሉ መቆፍረ አለባቸው! የኤሌትሪክ ገመዶችን ለማስተካከል ግድግዳ መፈርፈር አለባቸው!

አንድ ትንሽ ግራ የሚገባ ነገር አለ፣ በእድሜ በጣም ለገፉ አዛውንቶች ሰባተኛ ፎቅ ቤት መስጠት ምን ማለት ነው!… ቢደርሳቸው እንኳን በስምምንት ለማለዋወጥ መሞከር አይቻልም እንዴ ! ሊፍት በሌለበት ! እንደውም ለሊፍት ተብለው የተሠሩ ማለቂያ የሌላቸው የሚመስሉ ጉድጓዶች ተከራይ ያጡ ቤቶች ይመስል አፋቸውን በከፈቱበት፣ ተገጠሙ የተባሉ ሊፍቶችም እንቅስቃሴ ለመጀመር መካከለኛ ገቢ እስክንደርስ የሚጠብቁ በሚመሰሉበት ሰባት ፎቅ መውጣትና መውረድ እንኳን ለአዛውንቶች ለሌላውም ትንፋሽ ጨራሽ ነው፡፡

ድካሙን ስለማይችሉት ወደ ጸሎት ስፍራዎች መሄድ ያቋረጡ መኖራቸውን ሰምተናል፡፡ በሊፍት ጉዳይ ቤቱን የሠራው አካል ክፍቱን ትቷቸው ነዋሪዎቹ ናቸው እያዋጡ በቆርቆሮና በጣውላ ምናምን የሸፈኗቸው፡፡

በነገራችን ላይ ዘመናዊነት ማለት የአኗኗር ጉዳይ እንጂ ፎቅ ላይ መውጣት አይደለም፡፡ ውሀ ጨርሶ በሌለበት ወይም በሳምንት አንድ ቀን ሌሊት በሚመጣበት፣ መብራት ለረጅም ጊዜ ባልገባበት ሰባት ፎቅም ሆነ አስራ ሰባት ዘመናዊ ብሎ ነገር ሊኖር አይችልም፡፡ የጋራ መገልገያዎች በበቂ በሌሉበት፣ ቢኖራቸውም ለበርካታ ወራት ርክክብ ባልተካሄደበት፣ ወይም ርክክብ ተካሂዶ እንኳን ለሌላ አገልግሎት በዋሉበት ዘመናዊ ኑሮ ብሎ ነገር ሊኖር አይችልም!

ሰለጋራ መኖሪያ ቤቶች ብዙ እጅግ በጣም ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ ግን ጎን ለጎን ሆነን ተሳስበን መኖር ያለመሞከራችን ወይም ያለመፈለጋችን ለአገር አቀፍ ቀውሶቻችን አስተዋጽኦ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ምክንያቱም በጋቢና በብርድ ልብስ ተሸፋፍነን አላየሁም፣ አልሰማሁም ብንልም የማንሸሸው ሀቅ … ሀገራዊ ቀውስ ውስጥ መሆናችን ነው፡፡ በጎረቤት ደረጃ አብረን መኖር ካልቻልን እንዴት ነው ሰፋ ባለ ደረጃ አብረን መኖር የምንችለው!

ነገሩ ሁሉ፣ “ተዋቸው፣ የኮንዶሚኒየም ልጆች ናቸው፣” አይነት ሲሆን የተሳሰቱ ነገሮች አሉ ማለት ነው፡፡

ኤፍሬም እንዳለ

በማኅበረ ሰብ ገጾች ያጋሩ

Submit to FacebookSubmit to Google PlusSubmit to TwitterSubmit to LinkedIn
Sheger 102.1 AudioNow Numbers