• United Bank S.C.

    ሕብረት ባንክ አ.ማ.

  • Slider Two

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Sldier Three

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ሸገር | ወግ

“የገላጋይ ያለህ!”

ባለፈው ዘመን የሆነ ነው፡፡ በሁለት ጎረቤታም ሰፈሮች ልጆች መሀል ከፍተኛ ጠብ ነበር፡፡ ዝም ብሎ መቧቀስ ብቻ ሳይሆን በስለት እስከመጎዳዳት የደረሰ ጠብ…፡፡ ከመካረሩ የተነሳ አይደለም ወጣቶቹ፣ የአንዱ ሰፈር ሰው በሌላኛው ሰፈር ማለፍ የማይችልበት ደረጃ ይደረሳል … ልክ የሁለት አገሮች ጠብ ይመስል፡፡ “የገላጋይ ያለህ…” የሚያስብል ጠብ፡፡

ደግነቱ ጠቡ ከቁጥጥር ውጪ ከመሆኑ በፊት ገላጋይ አልጠፋም … የሁለቱ ሰፈር የሀገር ሽማግሌዎች ተሰባስበው ገሰጹ፣ መከሩ - “አንተም ተው፣ አንተም ተው” አሉ፡፡ የሁለቱ ሰፈር ወጣቶች በየአካባቢው ህዝብ ተከበው በአቅራቢያ በሚገኝ ድልድይ ላይ ተገናኙ፣ ተቃቀፉ፣ ተሳሳሙ፣ ታረቁ - የምዕራባውያኑን ምሳሌያዊ አነጋገር ለመዋስ ‘ቆንጨራቸውን ቀበሩ’

አለቀ…

ኧረ “የገላጋይ ያለህ…” ሲባል የአገር ሽማግሌዎችም “እኛ እያለን ሌላ ገላጋይ ከየት ሊመጣ ነው!” በሚል መንፈስ ህብረተሰቡ በባህልም፣ በታሪክም የሚጠብቅባቸውን ሚና ተወጡ፡፡

አሁንም “የገላጋይ ያለህ፣” እያልን ነው… “እኛ እያለን ሌላ ገላጋይ ከየት ሊመጣ ነው!” የሚል ውብ ዜማ መስማት እየናፈቀን ነው፡፡ የሀገር ሽማግሌዎቻችን የት ጠፉ ! ከሰማያዊ ቃል በታች ከቃላቸው ዝንፍ የማንለው ጎምቱዎቻችን የት ጠፉ ! ይህ ህብረተሰብ እኮ ለሀገር ሽማግሌዎች ታላቅ ክብር የነበረው ነው፡፡ የእነሱ ቃል “እናንተ ካላችሁ ይሁን !”

የሚባል ነበር፡፡ የሀገር ሸማግሌዎች “እኔ ምን አገባኝ” ብለው በካፖርትና በጋቢያቸው የሚጠቀለሉ ሳይሆኑ ከራሳቸው ምቾት ይልቅ ለህብረተሰብ ጥቅም የቆሙ ነበሩ፡፡ በታሪካችን በአገር ሽማግሌዎች ጣልቃ ገብነት እኮ ብዙ ሰናይ ነገሮች ተከስተዋል፡፡

 

“እኔ አልቻልኩም፣ የሀገር ሽማግሌዎች ይጠሩልኝ፣” የምትል እማወራ እኮ የምታንጸባረቀው የሀገርን ዘመናት የከረመ እምነት ነው፡፡ “ይሄ አለመግባባታችን በሀገር ሽማግሌዎች ይፈታ!” የሚል የንግድ ሸሪክ እኮ የሚያንጸባርቀው የሀገርን ዘመናት የከረመ እምነት ነው፡፡ እንዲህ ሆኖ ታዲያ በታሪካችን ከምንጊዜውም በላይ በምንፈልጋቸው በዚሀ ሰዓት የት ጠፉ!

በነገራችን ላይ የሀገር ሽማግሌዎች ስንል ሁልጊዜም ከስማቸው ፊት የሆነ የስልጣን ጉትቻ የተቀጠለላቸው፣ በሆነ ባልሆነውም የቴሌቪዥን መስኮት የሚያጣብቡትን ብቻ አይደለም፡፡ በየሰፈሩ፣ በየመንደሩ የቴሌቪዥን ካሜራ የማያውቃቸው፣ ከስማቸው ፊት ከአቶ የዘለለ ተቀጥላ የሌላቸው፣ ምናልባት እዛች ጥግ ሆነው የተቀዳደ ልብስ በስፌት መኪና የሚጠግኑ፣ እዚህኛው መጋዘን በጥበቃ ሥራ የሚያገለግሉ አይነቶቹንም ማለታችን ነው፡፡

ህብረተሰቡ መሀል ሆነው የችግሩ ተካፋዮችና የችግሩን እውነተኛ ስዕል የሚያውቁ ማለታችን ነው፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያገለለ የሀገር ሽማግሌነት ለሚዲያ ፍጆታ ካልሆነ በስተቀር የችግሮችን መፍቻ የወርቅ ቁልፍ አይደለም! የአገር ሽማግሌነትን ከተቋም መሪነት ለይተን ማየት መቻል አለብን፡፡

በትላልቅ ሆቴልና የስብሰባ አዳራሽ በባንዲራና በመፈክር አሸብርቆ የሚካሄድ አይነት የ‘ሰበር ዜና’ ሽምግልና ሳይሆን በየመንደሩ፣ በየዛፉ ስር፣ በየገላጣው ሜዳ፣ በየግቢው ጓሮ፣ በየቤተዘመዱ ጉባኤ የሚካሄዱ ሽምግልናዎች ለመፍትሄው ይበልጥ ቅርብ ናቸው፡፡ እና በየመንደሩ ነገሮች አስከፊ ደረጃ ሲደርሱ ምነው ድምጻቸው ጠፋ!

“እስቲ ሁላችሁም አደብ ግዙና እንምከር!” የሚል የተስፋ አንደበታቸው ምነው ተለጎመ! ችግሮች ሲነሱ ጣልቃ ገብተው የተጣመመውን የሚያቃኑ፣ የቂም በቀል ፍም ከመንቀልቀሉ በፊት ውህ የሚደፉባት በርካታ የሀገር ሽማግሌዎች ያስፈልጉናል… ሀገር “የገላጋይ ያለህ!” እያለች ነው! - “ምክር ከሽማግሌ ነው፣ መሻገር ከጎበዝ ነው” ይላል የሀገሬ ሰው፡፡

የሀይማኖት አባቶቻችንስ ቢሆኑ የት ናቸው ! “ጸልዩ፣ ለፈጣሪ አቤቱታ አቅርቡ፣” ማለቱ እኮ ህዝቡ “ጸልይ” ባይባልም “ያለን የመጨረሻ አማራጭ ነው፣” ብሎ እየጸለየ ነው፡፡ እንባውን እየረጨ ነው እኮ፡፡

“አቤቱ፣ ወዴት ትወስደን ይሆን?” እያለ ነው እኮ! ምነዋ 
ምእመኖቻቸው መሀል ገብተው “ተዉ ይሄ ነገር ለማንም አይበጅም!” የማይሉትሳ! 
በየደረጃው ያሉ የሀይማኖት አባቶች በየአካባቢያቸው “ተዉ፣ እንዲህ አይሆንም፣” ብሎ መምከር፣ ብሎም መገሰጽ ምነው ተሳናቸው! “ለሁሉም ነገር ሰላማዊ መፍትሄ አለው፡፡ ወንድም በወንድሙ ላይ እጁን አያንሳ፣ የእስካሁኑ ይበቃል!” ለማለት ቀዳሚ መሆን ነበረባቸው እኮ! ራሳቸውን ለፈጣሪ አገልግሎት ሰጥተው የለም እንዴ! የምእመናኑ እረኞች አይደሉም እንዴ! እና፣ ሀገር እዚህ ሁሉ እልቂትና ጥፋት ደረጃ ላይ ስትደርስ ዝምታው ምነው በዛ?

ይህ ሁሉ ጥፋት ደርሶ፣ በርካታ ህይወት ከጠፋ፣ ለቁጥር የሚያዳግት ህዝብ በገዛ ሀገሩ ከመኖሪያው ከተሳደደ በኋላ አስር ደቂቃም ሆነ አስር ቀንም የፈጀ መግለጫ ማውጣት “እነሱም ብለው ነበር፣” ለማለት ካልሆነ በስተቀር መፍትሄ አይሆንም፡፡

ህዝባችን ለሀይማኖት አባቶች ከፍተኛ ከበሬታ አለው፡፡ እነሱ የተናገሩት ነገር መሬት ጠብ አይልም፡፡ “ይሁን? ያሉት ይሆናል፣ “አይሁን” ያሉት አይሆንም፡፡ አለቀ፡፡ ከሀይማኖት አባቶች አንደበት የሚወጣውን ከፈጣሪ እንደተላከ የሚቆጥር ህብረተሰብ ነው፡፡

ምንም እንኳን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በየሀይማኖቶቹ አካባቢ በሚያየውና በሚሰማው ነገር ግራ ቢገባውም…የነፍስና የሥጋ መለያ መስመር ብትደበዝዝበትም ህዝቡ እንደፈጣሪ ወኪሎች በሚያያቸው ተቋማትና አገልጋዮች አካባቢ ሀይማኖታዊ ያልሆኑ ድርጊቶች ሲያይ፣ መንፈሳዊ ተልእኮን ከማሳካት ይልቅ ወደ ምድራዊ ዓለም ምቾቶች ሲያዘነብሉ ሲያይ ግራ ቢገባውም… አሁንም ቢሆን በየደረጃው ላሉ የሀይማኖት አገልጋዮች አክብሮቱ እንዳለ ነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ላይ “ጴጥሮስ ጌታን ወንድሜ ቢበደልኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው? እስከ ሰባት ነውን ቢለው እስከ ሰባት አልልህም ሰባቱን አንድ እያልክ እስከ ሰባ ነው እንጂ” የሚል ሰፍሯል፡፡ በቅዱስ ቁርአን ደግሞ “ተበድለህ እንኳን ቢሆን ከሦስት ቀናት በላይ አታኩርፍ፣ ታረቅ፣ እርቁ ደግሞ ከልብህ ይሁን” የሚል አለ፡፡

እኛ እኮ፣ አይደለም በራሳችን ጉዳይ፣ አባት አያቶቻችንን እያነሳን አሁንም ድረስ “በደሉ/አልበደሉም” እየተባባልን የምናኳረፍ ሰዎች ነን እኮ! ነገራችን ሁሌም “ሊጣላ የመጣ ሰበብ አያጣም፣” አይነት ሆኗል፡፡

እነኚህን የቅዱሳኑ መጽሐፍት ቃሎች ቀድመው የሚያደርሱልን አቧሯው ጨሶ አገሩ ከተሸፈነ በኋላ ሳይሆን አቧራው ከመጨሱ በፊት “ተዉ፣” ብለው የሚገስጹን አባቶች ምነው በብዛት ማግኘት ተሳነን! ይሄን ሁሉ ወራት እስኪናፍቁን ድረስ ምነው ጠፉ! ዋናዎቹ እምነቶች ለደግ እስከሆነ ድረስ ዋሽቶ ማስታረቅን ይደግፋሉ፡፡ እነዚህን ቃላት ወደ ህብረተሰቡ የሚያወርዱ፣ “መጣላት መኳረፍ ሀራም ነው!” “መጣላት፣ መኳረፍ ሀጢአት ነው!” ብለው ሊያስተምሩ የሚገባቸው አባቶች ሲጠፉብን “የገላጋይ ያለህ!” ብንል ምን ይገርማል!

ቀድመው የሙሴ በትርን ይዘው መንገድ ሊመሩን ይገባቸው የነበሩ ክፍሎች አካባቢ “ምን አገባኝ” አይነት ዝምታ ስናይ ምነዋ ተስፋ አንቆርጥ!

እኔ ምን አገባኝ የምትሉት ሀረግ
እሱ ነው ሃገሬን ያረዳት እንደ በግ፣
የሚል ግጥም ልጽፍ ብድግ አልኩኝና
ምን አገባኝ ብዬ ቁጭ አልኩ እንደገና 
ይላል ኑረዲን ኢሳ...

ክብር የሚሰጣቸው፣ የተናገሩት መሬት ጠብ የማይል አባቶች ሲኖሩ ቃላቶቹ አይደለም የተቆጡና በደመ ነፍስ ብቻ የሚመሩ ቡድኖችን፣ ሳንጃ በአፈሙዝ የሰካ ጦርን ባለበት ቀጥ የሚያደርግ ሀይል ነበራቸው እኮ! ቢያንስ፣ ቢያንስ ነገሮች ተረጋግተው ሁሉም ወደ ልቦናው እንዲመለስ ጊዜ ይሰጥ ነበር፡፡

ምናልባት ራሱን ችሎ የማይቆመው ፖለቲካችን፣ በየጊዜው እየተፈነጣጠረ ይህንንም፣ ያንንም የሚነካካ ፖለቲካችን የእምነት አካባቢዎችን ቢነካም አሁንም ህዝቡ በየእምነቱ ከፈጣሪው አልራቀም፡፡ በተለያዩ ሀይማኖታዊ ክብረ በዓላት ላይ እኮ በሚተምመው ህዝብ ብዛት የሚታይ ነው፡፡

ምሁራኑስ! ምሁራኖቻችን የታሉ! ተወደደም፣ ተጠላም አንዳንዴ ነገር ማሳመሪያ የምናደርገው ቢመስልም እውነቱ ግን የተማሩት በህዝብ ገንዘብ ነው፡፡ እዳ አለባቸው፡፡ የጂ ፕላስ ምናምን ቤትና የቶዮታ ኤክስኪዩቲቭ እዳ ማለታችን ሳይሆን የህዝብ እዳ አለባቸው፡፡ እዳቸውን ይሄን ጊዜ ካልከፈሉት መቼ ነው የሚከፍሉት!

በባዶ እግሩ እየሄደ፣ በለቶ መጥገበና ለብሶ መሟሟቅ ሳያምረው ያስተማራቸው ሰው አኮ ነው አሁን በየስፍራው ችግር ላይ የወደቀው፡፡ የሚሳደደው እኮ እሱና የእሱ ልጆች ናቸው፡፡ ትላንት በግብርም በምኑም ለእነሱ ትምህርት ሲገፈግፍ የኖረው ምስኪኑ ነው እኮ አሁን ሀይ ባይ ጠፈቶ በወጣበት አየቀረ ያለው፡፡

አገራችን “በምሁራኖቿ አልታደለችም” የሚለው አመለካከት ትንሽ አንፌይር የሚሉት አይነት ቢሆንም እርግጡ ነገር ህዝቡ ምሁራኖቹን በሚፈልጋቸው ጊዜ አላገኛቸውም - እንደ አሁኑ ጊዜ ማለት ነው፡፡ እዳ ደግሞ መከፈል አለበት !! እውን እዳቸውን እየከፈሉ ነውን ?

ሀያና ሠላሳ ገጽ የትንተና ጽሁፍ በኮክቴል ግብዣ ለሚጠናቀቅ ወርከሾፕ ማቅረብ አንድ ነገር ነው፡፡ ካሜራና ማይክራፎን ፊት ነገር ማሳመር አንደ ነገር ነው፡፡ ህዝቡ መሀል ገብቶ ሀያ ሠላሳ ደቂቃ መመካከር ግን ሌላ ነገር ነው፡፡ ያጣነው ይህነኑ ነው፡፡ አሁን ትንታኔ አይደለም የቸገረን … በመቶ የሚቆጠር ህይወት እየጠፋ፣ በመቶ ሺዎች በገዛ አገራቸው ተፈናቅለው የእርዳታ ፈላጊ በሆኑበት - የቸገረን ትንታኔ አይደለም፡፡

ላለፉት በርካታ አስርት ዓመታት ስንሰማው ኖረናል፡፡ ከምድጃው መለዋወጥ በስተቀር አሁንም በጉሮሯችን የሚርደው ያው የምናውቀው ጣዕም የለሽ ወጥ ነው፡፡ አሁን የሚያስፈልገው መጨራረሱን የሚያረግብ፣ መፈናቀሉን የሚያስቆም፣ ደመ መቀባባቱን የሚያስቀር ተግባር ነው !!! - አዎን ይሄን ነው የምንፈልገው፡፡

ሰዋችን ከጥንት ጀምሮ “የተማረ ይግደለኝ” ይል የነበረው “የተማረ ሰው ከችግር ያወጣኛል፣ ከመከራ ያድነኛል፣” ብሎ ስለሚያምን ነበር፡፡ የተማረ ሰው ላይ ያለውን እምነት ሀያልነት እያሳየ ነው፡፡ ሊበራል ቅብጥርስዮ፣ አብዮታዊ ምንትስዮ ማለት አኮ አሁን፣ አሁን ጆሮ ያም እንደሁ እንጂ እሱን የምንስማበት ጉልበቱንም፣ ትእግስቱንም እያጣን ነው፡፡ 
የዛሬው መሰረት እየሸሸ፣ የዛሬው መስሶ እየተነቃነቀ አሁንም ትናንትና እና ከትናንት ወዲያን መኮነን ከጭቅጭቅነት አያልፍም፡፡ ለኩነናው ያደርስናል … መጀመሪያ ያንዣበበንብን ጥቁር ደመና እስከወዲያኛው እንዳይመለስ ማጥፋት አለብን፡፡ ለኩነናው ያኔ ጊዜ ይኖረናል…

እና ገዥዎቻችን ከርመው፣ ከርመው በዛ ሰሞን “አዎ የእኛ ድክመት ነው፣ ለችግሩ የእኛም የአመራር ድክመት አለበት” አይነት ቃና ያለው መግለጫ አወጡ፡፡ ወዲያውኑ ዝም ብለው የከረሙት ክፍሎች … ድምጻቸው ጮክ ብሎ መሰማት ጀመረ፡፡ ፈረንጅ እንደሚለው “የባህር ዳርቻ ሰላም” መሆኑን አረጋገጧ ! መቼም ገዥዎች በራሳቸው አንደበት “አጥፍተናል” ካሉ በኋላ “ተቸኸን፣” “እንዴት ብትደፍረን ነው እንዲሀ የምትለን!” ብለው እንደማይቆጡ እርግጠኛ ሆኑዋ! ያሰተዛዝባል፡፡

‘መጣ ዝም በሉ፣ ሄደ ተናገሩ’ አይነት ነገር ነው፡፡ ዝም ተብሎ ተከርሞ ገዥዎች “ለተፈጠረው ችግር የእኛም ድክመት አለበት፣” ሲሉ…ከየጎሬው መውጣት ምናልባት ለእኛ ለተራዎች ሊሆን ይችላል - ለአገር ሽማግሌዎችና ለሀይማኖት አባቶች ግን አይሆንም፡፡ “መንግሥት ተሳስቻለሁ ስላለ የልባችንን ብንነጋርም ሸቤ የሚከተን የለም” የሚለው ለእኛ ለምስኪኖቹ ይሆን ይሆናል እንጂ… “መንግሥትም ሀላፊነቱን መወጣት አለበት…” አይነት ሲሉ የሆነ የድል አጥብያ አርበኝነት ሊመስል ይችላል፡፡

“ተዉ፣ እስቲ ተረጋጉና እንምከር” ማለት… ይሄን ፖለቲከኛ መደገፍ፣ ያንን መቃወም አይደለም፡፡ ግጭትን መከላከል፣ የሰው ህይወት መጥፋትን፣ መፈናቀልን፣ መጉላላትን ለማስቀረት መሞከር እኮ ፖለቲካዊ ጉሮሮ መተናነቅ አይደለም፡፡ “የምናምን ናፋቂዎች፣ ነብር አየን በሉ!” የሚያሰኝ አይደለም እኮ! የዛሬ ፖለቲከኛ ነገ ይሄዳል፡፡ የዛሬ ፖለቲካዊ አስተሳሰቦችም ነገ ጊዜ ያልፍባቸዋል፣ አሁን እያለፈባቸው እንዳሉ የፖለቲካ አስተሳሰቦች ማለት ነው፡፡ ምንም እንኳን ይህን ያልገባቸው፣ ወይም ሊገባቸው የማይፈልጉ ፖለቲከኞች ቢኖሩንም ማለት ነው፡፡

የቀደሞ ንጉሥ አንድ ጊዜ “እናንተ ለሕዝብ ተሰጣችሁ እንጂ ሕዝብ ለእናንተ አልተሰጠም፣” ብለው ነበር ይባላል፡፡ ሕዝብ ለእነሱ የተሰጠ የሚመስላቸው ፖለቲከኞችም ልብ ይግዙ፡፡

“ገላጋይ አጥቼ ግልገሌን በላኋት” ይላል የአገሬ ሰው፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እንደዛ እየሆነ ነው ያለው፡፡ ገላጋይ ጠፍቶ ግልገልን የመብላት ነገር፡፡ ጭርሱን እኮ ከምእራብ መዲናዎች ሆኗል “እረፉ!” ምናምን የሚባለው፡፡ በገዛ ጉዳያችን፣ በገዛ ጉዳታችን፣ እኛው በእኛው ለተጎዳዳነው የፈረንጅ አስታራቂ መምጣት አለበት እንዴ! የአውሮፓ ህብረት “ሁላችሁም በአንድ ጠረጴዛ ተወያዩ” አለ፡፡ የአሜሪካ ኤምባሲ “ተነጋገሩ አለ”…ጉዳያችን እኮ የእኛ ነው!!!

“የእንትን የቀድሞ ባለስልጣን ኢትዮጵያውያን በጠረጴዛ ዙሪያ ችግሮቻቸውን መፍታት እንዳለባቸው አሳሰቡ…” አይነት ነገር ይባልልኛል፡፡

አይ የእኛ የአገር ሽማግሌዎች እስቲ ተሳባሰቡና እንነጋገር ማለት ይቻላል እኮ፡፡

እነሱ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ “እንዲህ ካልሆናችሁ ዋ!” ሊሉን ይገባል እንዴ ! ዘላለማችንን አቁማዳችንን ይዘን በራቸው ላይ የቆምን ይመስል “ዋ አቁማዳህን ባዶዋን ይዘህ ትመለሳታለህ!” የሚል የውስጥ አዋቂ ማስጠንቀቂያ ሊሰጠን ይገባል እንዴ! ራሳችን በራሳችን ችግራችንን ለመፍታት እንደበቀደሙ የአሜሪካ “በእየሩሳሌም ጉዳይ የእኛን ውሳኔ የምትቃወሚ አገር ሁሉ ነብር አየኝ በይ” አይነት ልክ የሰፈር ልጅ “ጠዋት መቶ ብር ካላመጣሽ ጥርስሽን ነው የማራግፈው!” አይነት ዛቻ ከውጪ እንዲላክልን ይገባል እንዴ!

ያለችን አኮ ይቺው ሀገር ነች፡፡ ፓስፖርት ልንለውጥ እንችላለን፣ ስማችንን ከከበደ ወደ ኮልበርት ከአረጋሽ ወደ አንጀሊና ልንለውጥ አንችላለን፡፡ በዚህም ሆነ በዛ ግን ያለችን ይቺው ሀገር ናት፡፡ አለቀ፡፡ “የገላጋይ ያለህ!” የምንልበትን ጊዜ ያሳጥርልን!

ኤፍሬም እንዳለ

በማኅበረ ሰብ ገጾች ያጋሩ

Submit to FacebookSubmit to Google PlusSubmit to TwitterSubmit to LinkedIn
Sheger 102.1 AudioNow Numbers