• United Bank S.C.

    ሕብረት ባንክ አ.ማ.

  • Slider Two

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Sldier Three

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ሸገር | ወግ

የቻይናው መሪ የዢ ጂን ፒንግ ነገር…

“በበጎ ምግባር የሚያስተዳድር እንደ ሰሜናዊቷ ኮከብ ነው”

ማን ያውቃል አሁን “የእኔ ልጅ እኮ ቦስተን ነች” ተብሎ ሴቶች እድር ላይ እንደሚፎከረው ከዓመታት በኋላ “የእኔ ልጅ እኮ ቤይጂንግ ነች” ተብሎ ይፎከር ይሆናል፡፡

“የህልሜ ደረሰ፣ ልመናዬን ሰማኝ፡፡ 
“ምን ተገኝቶ ነው?”
“ልጄ ቻይና ሊሄድልኝ ነው”
“አትለኝም!” 
“ሙት ስልህ፣ እሁድ ማታ ነው የሚበረው”
“እግዜሐር ይወድሃለ ማለት ነው - በጣም እድለኛ ሰው ነህ”

ግዴላችሁም…ከዓመታት በኋላ እንዲሀ አይነት ምልልሶች የድራፍት ጠረጴዛዎችን የማይቆጣጣሩበት ምክንያት የለም፡፡

ጉዞ ወደ ቻይና ሆኗል፡፡ ለዘመናት “አሜሪካ፣ አሜሪካ” ሲባል እንደነበረው አሁን “ቻይና፣ ቻይና” ማለትን መለማማድ ጀምረናል፡፡ እንደውም እንደሚባለው ከሆነ ልክ እንደ አሜሪካ ጉዞ ሁሉ ወላጆች ልጆቻቸውን ቻይና ለመላከ ምንም አይነት ገንዘብ ለመክፈል ፈቃደኛ እየሆኑ ናቸው ተብሏል፡፡

አብዮተኞቹ በማኦ ዜዱንግ፣ የፊልም ወዳጆቹ ደግሞ በእነ ጃኪ ቻንና ጄት ሊ የሚያውቋት ቻይና የሚያቃጥል ጫማ ብቻ አይደለችም፡፡ አራት ቀን በርቶ፣ በአምስተኛው ቀን ጭል ጭል ብሎ በስድስተኛው ቀን ውድም እንደሚለው አምፖል ብቻ አይደለችም፡፡ እሱ፣ እሱ የእኛ የጥራት ቁጥጥር ጉዳይ ነው፡፡ የአሁኗ ቻይና “ስም ሲያወጡ ሸክላ ሳህን ድንጋይ ላይ እየከሰከሱ በሚወጣው ድምጽ መሰረት ነው” ብለን የምንቀልድባት የትላንቷ ቻይና አይደለችም፡፡

ታዲያ… ለአሁኗ ፈጣን ግስጋሴዋ በርካታ ምክንያቶች መዘርዘር ቢቻልም በዋንኝነት ከሚጠቀሱት መሀል አንድ ሰው አሉ … የአሁኑ መሪ ዢ ጂን ፒንግ፡፡ ጠንካራ መሪዎች በሀገር እድገት ላይ የሚያሳድሩት ተጽእኖ ምሳሌ ናቸው ነው የሚባለው፡፡

እንዲህ ሆኖ ታዲያ ሰውየው እጅግ ኋላ ቀር ከሆነች የገጠር መንደር እስከተንጣለለው የቤይጂንግ የስልጣን ማማ የነበራቸው ጉዞ ቀላል አልነበረም፡፡

ከአምስት አስርት ዓመታት በፊት ቻይና አየተናጠች ነበር - የባህል አብዮት ባሉት የማኦ ዘመቻ፡፡ ዢ ጂን ፒንግ 15 ዓመታቸው ነበር፡፡ በሀገሪቱ ገደላማ ሸለቆዎችና ተራሮች ከባዱን የገጠር ኑሮ እየተፋለሙ ነበር፡፡ የእርሻ ሥራቸውን ያካሂዱባት የነበረችው ያናን የተባለችው ስፍራ በእርስ በእርስ ጦርነቱ ጊዜ የኮሚኒስቶቹ መናኸሪያ ነበረች፡፡ እንደውም ያናን ራሷን “የቻይና አብዮት ቅድስት ስፍራ” ብላ ትጠራ ነበር፡፡

የዢ ታሪክ ታድሷል፣ አብዛኛዎቹ የቻይና ገጠራማ ስፍራዎች በሚያስደንቅ ፍጥነት ወደከተማነት ሲለወጡ እሳቸው ያደጉባት መንደር ለኮሚኒስት ፓርቲው አፍቃሪዎች የመንፈሳዊ አይነት ጉዞ መዳረሻ ሆናለች፡፡

በ1968 ማኦ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶች ከከተማ ወደ ገጠር ዘምተው ከአርሶ አደሮች ከባድ ህይወት ልምድ እንዲቀስሙ አዘዙ፡፡ “በ15 ዓመቴ ስደርስ ያልተረጋጋሁና ግራ የተጋባሁ ነበርኩ፣” ይላሉ ዢ፡፡ “በ22 ዓመቴ ለቅቄ ስሄድ የህይወቴ ግቦች ጠንካራ የሆኑና በራስ መተማመንም የተሞላሁ ነበርኩ፡፡”

በወጣትነታቸው የመጀመሪያ ዓመታት ዢ መልካም የሚባል አስተዳደግ ነበራቸው፡፡ አባታቸው የኮሚኒስቱ አብዮት ጀግና ነበሩና፡፡ ሆኖም በ1960ዎቹ ሁሉም ነገር የእምቧይ ካብ ሆነና አረፈው፡፡ የማኦ ተጠራጣሪነትና የበቀል ስሜት ጣራ ነካ፣ የአብዮቱ ጠላቶች የሚሏቸው ላይም ከባድ በትራቸውን ሰነዘሩ፡፡ ድፍን ቻይና ተርበደበደች፡፡

ብዙዎችም ሰለባ ሆኑ፡፡ በትሩ የዢ አባትንም አልማረም፡፡ መጀመሪያ ከፓርቲው ተባረሩ፣ ከዚያም ወደ ዘብጥያ፡፡ ቤተሰባቸውም በአደባባይ ተዋረደ፡፡ እንደውም አንድ እህታቸው ህይወቷ አለፈ፡፡ ምናልባትም በብስጭት ራሷን አጥፍታ ሊሆን ይችላል የሚል መላ ምት ነበር፣ ማንም አላረጋገጠም እንጂ፡፡

ዢ 13 ዓመት ሲሞላቸው ሳይወዱ መደበኛ ትምህርታቸውን አቆሙ፣ ምክንያቱም በድፍን ቤይጂንግ ትምህርት ቆሞ ነበርና ! ነገሩ አብዮት ልጇቿን ትበላለች ነበርና ትምህርት እንዲቆም የተደረገው ተማሪዎች አስተማሪዎቻቸውን እንዲተቹ፣ እንዲደበድቡና ብሎም እንዲገድሉ ለማስቻል ነበር ይላሉ የቻይናን ታሪክ በቅርበት የሚከታተሉ፡፡

 

ዢ በየመንገዱ የባህላዊ አብዮቱን የጅምላ ፍርድ ከሚያስፈጽሙ ቀይ ዘቦች የሚከላከልላቸው ወላጆችና ጓደኞች ስላልነበራቸው የግድያና የእስር ዛቻ እየተሰነዘረባቸው ሁለተኛው የቤይጂንግ ኑሯቸውን ተያይዘውት ነበር፡፡ ሁኔታውን ከብዙ ጊዜ በኋላ ለአንድ ጋዜጠኛ ተርከውለት ነበር፡፡

“ገና 14 ዓመቴ ነበር፡፡ ቀይ ዘቦቹ ‘ወንጀሎችህ ምን ያህል ከባድ ናቸው ትላለህ?” ብለው ጠየቁኝ፡፡
“እኔም ‘እናንተ መገመት ትችላላችሁ፣፡ አኔን ለማስገደል በቂ ነው?” አልኳቸው፡፡
“‘መቶ ጊዜ ልንገድልህ እንችላላን’ አሉኝ፡፡
“እንደ እኔ ከሆነ መቶ ጊዜ በመገደልና አንድ ጊዜ በመገደል መሀል ልዩነት የለም፣” አልኳቸው፡፡

በ1960ዎቿ ቻይና የመንደር ኑሮ በጣም ከባድ ነበር፡፡ የኤሌክትሪክ ሀይል አልነበረም፣ የሞተር ትራንስፖርት፣ ወይም ሜካኒካል መሳሪያዎች አልነበሩም፡፡ በአስራዎቹ እድሜ ውስጥ የነበሩት ዢ ፍግ መሸከም፣ ግድቦች መገንባትና መንገዶችን መጠገን ለመዱ፡፡

ዋሻዎች ውስጥ በትኋን የተሞላ አልጋቸውን ከሌሎች ሦስት ሰዎች ጋር በጋራ ነበር የሚጠቀሙበት፡፡ አንደኛው ሉ ሀውሼንግ የተባሉ አርሶ አደር እንዲህ ብለዋል፣ “በዛን ወቅት የምንበላው ገንፎ፣ ቅጠላ ቅጠልና የመሳሰሉትን ነበር፡፡ “ከራበህ ምን በላህ ምን፣ ግድ አይኖርህም፣” ነው ያሉት አርሶ አደሩ፡፡

እንዲህም ሆኖ ግን ዢ ጊዜያቸውን በንጭንጭ አያጠፉም ነበር፡፡ ምሽት ላይ ዢ ዋሻቸው ውስጥ በኩራዝ ብርሀን ንባብ ላይ ናቸው፡፡ የለየላቸው አንባቢና ሲጋራ ላይ በላይ የሚያጨሱ እንደነበሩም ይነገርላቸዋል፡፡ ለነገሩ በቅርቡ ሲጋራ ማጨስ ማቆማቸውን አስመልክቶ የዓለም የጤና ድርጅት ሲያደንቃቸው ነበር፡፡ 300 ሚሊየን አጫሽ ላለባት ቻይና የመሪዋ ሲጋራ ማጨስ ማቆም ጥሩ ዜና ነው ብሎ ነበር የዓለም የጤና ድርጅት፡፡

አንዳንዶች ደግሞ ማጨስ እንኳን ያቆሙት በ1980ዎቹ ነው ይላሉ፡፡ የማኦን ስብስብ ሥራዎች፣ የማኦን አባባሎችና ጋዜጣ ያነቡ ነበር፡፡ በወቅቱ ከእነኚህ በስተቀር ሌላ የሚነበብ ነገር አልነበረም፡፡

በነገራችን ላይ ዢ ፈገግ የማሰኘትም ሆነ የማሳቅ ባህሪ ‘ሴንስ ኦፍ ሂዩመር’ የሚባለው ክህሎት አልነበራቸውም ይባላል፡፡ ካርታ አይጫወቱም፣ ከጓደኞቻቻው ጋር ወጣ ብለው አይዝናኑም፣ የሴት ጓደኛም አይፈልጉም ነበር ነው የሚባለው፡፡ በ18 ዓመታቸው የኮሚኒስቶችን የወጣቶች ሊግ ተቀላቀሉ፡፡ በ21 ዓመታቸው የፓርቲው አባል ሆኑ፡፡

በእርግጥ ቀላል አልነበረም፡፡ በአባታቸው መታሰርና በቤተሰባቸው መዋረድ የተነሳ በተደጋጋሚ የፓርቲ አባልነት ጥያቄያቸው ውድቅ ሆኖባቸዋል፡፡ 25 ዓመት ሲሞላቸው አባታቸው በተሀድሶ እንደገና ፖለቲካ ውስጥ ገብተው ጉዋንግዶንግን እንዲያስተዳድሩ ተላኩ፡፡ በነገራችን ላይ ዢ በስልጣን መሰላል ላይ ላደረጉት የሽቅብ ጉዞ የአባታቸው እጅ አለበት ነው የሚባለው፡፡

ዢ ጂንፒንግ ከረጅም እና እህል አስጨራሽ ከሚባለው አይነት ጉዞ በኋላ በ2012 የኮሚኒስት ፓርቲው መሪ ሲሆኑ ሁሉም ተደንቆ ነበር፡፡ ሆኖም በተከታዮቹ አምስት ዓመታት የሚመጣውን ማንም አልገመተም፡፡ ስልጣን ላይ ሲወጡ “ሙስና ላይ ጎራዴ እመዛለሁ!” ነበር ያሉት… እንዳሉትም መዘዙት፡፡ አይነኬ የፓርቲ አባላት ሳይቀሩ ካቴና እየገባላቸው ይጎተቱ ጀመር፡፡

በቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ታሪክ በሙስና ችሎት የቀረቡ እጅግ ከፍተኛው ባለስልጣን ዙ ዮንግካንግ ናቸው፡፡ እኚህ በ70ዎቹ እድሜ የሚገኙ ሰው ለዓመታት በቻይና በጣም የተፈሩና ፖሊስን፣ ፓራፓሚሊቴሪዎችን፣ እስር ቤቶችን እና የደህንነት ተቋሞችን የሚቆጣጠሩ ነበሩ፡፡

ዢ እኝህን የሚያክል ትልቅ ባለስልጣን ለፍርድ ማቅረባቸው እርምጃው የዢን ቆራጥናት ማሳያ ነው ተብሏል፡፡ ከላይ እስከ ታች በተለያዩ የፓርቲ ስልጣን ደረጃዎች ላይ የሚገኙ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በሙስና የተነሳ ቅጣት ተላልፎባቸዋል፡፡ ምእራባውያኑ ግን የጸረ ሙስናው ዘመቻ ዋና ዓላማ የዢን የፖለቲካ ተቀናቃኞች ለመመንጠር ነው ይሏቸዋል፡፡

በሌላ በኩልም ሙስናን በተመለከተ የእሳቸው ስም አይነሳም ማለት አይደለም፡፡ በቀጥታ እሳቸውን በሚመለከት ሳይሆን ዘመዶቻቸውን በሚመለከት፡፡ እሳቸው ስልጣን ከመያዛቸው በፊት በነበሩት ዓመታት አንዳንድ ዘመዶቻቸው እጅግ ባለጸጋ ሆነው ነበር፡ ሆኖም እሳቸው የቤተሰባቸውን የንግድ እንቅስቃሴ ለማጎልበት እንቅስቃሴ ለማድረጋቸው የሚያሳይ ምንም ምልክት የለም፡፡

“በበጎ ምግባር የሚያስተዳድር እንደ ሰሜናዊቷ ኮከብ ነው፣” ይላሉ ኮንፊሺየስን በመጥቀሰ፣ “ስፍራዋን አትለቅም፣ በርካታዎቹ ክዋክብትም ክብራቸውን ይግልጹላታል…” ለዢም በርካቶች ክብራቸውን እየገለጹላቸው ነው፡፡

ዢ ስልጣን ላይ በቆዪባቸው ዓመታት ተወዳጅነትንም አትርፈዋል፡፡ በተሰጡ ልብሶች መሀል እየተሽሎከለኩ ደካማ መንደሮች ውስጥ ጠልቀው ገብተዋል፡፡ ለተማሪዎችም “የመጀመሪያዎቹን ጥቂት ቁልፎች በትክክል ካልቆለፉ እንደሚበላሽ ሸሚዝ ሁሉ ሕይወትም እንደዚያው ነች” ሲሉ ነግረዋቸዋል፡፡

ከቺንግሁዋ ዩኒቨርሲቲ በኬሚካል ኢንጂነሪንግ የተመረቁት ዢ የተወጣላቸው የፖለቲካ ቼዝ ተጫዋች ናቸው ይሏቸዋል - ምእራባውያኑ፡፡ የእሳቸው ሀሳቦች ህገ መንግሥት ውስጥ በስማቸው ተጠቅሶ ገብቷል - “የቻይና ባህሪይ ያለው የዢ ጂን ፒንግ የሶሻሊዝም ሀሳብ ለአዲሱ ዘመን” ይላል፡፡

ይህንን ክብር ያገኙት ማኦ ዜዱንግ ብቻ ናቸው፡፡ ይህ ማለት ከእንግዲህ በዢ ጂን ፒንግ ላይ የሚደረግ ማንኛውም ተቃውሞ በኮሚኒስት ፓርቲው ላይ እንደተደረገ ይታያል ማለት ነው፡፡ ሰባት ሰዎች ያሉበት የአመራር ቡድን ወስጥ እሳቸውን ለመተካት ይችላል የሚባል ሰው የለም ነው የሚባለው፡፡ ይህም ማለት ዢ ለተከታዮቹ በርካታ ዓመታት በመሪነታቸው ይቆያሉ ማለት ነው፡፡

ዢ የቀድሞ ህይወታቸውን አስከፊ ተሞከሮዎችና የዋሻ ውስጥ ብቸኝነታቸውን ከህይወታቸው ውስጥ አላወጡትም ነው የሚባለው፡፡ ይህ ቁጥብ የመሆን ባህሪያቸው የባለስልጣን ልጅ ከነበረችው የመጀመሪያ ሚስታቸው እንዲፋቱ አድርጓቸዋል፡፡ በሌላ በኩል እነኚህ ባህሪያት ለፖለቲካ ህይወታቸው አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ የስልጣን ጫፍ እስኪደርሱ ከሌሎች የሚለያቸው ስኬት ብዙም ዓይን ሳይገቡ ወደ ላይ መመንጠቃቸው ነበር፡፡

ሰው ዓይን የገቡት የአሁኗን ሚስታቸውን ሲያገቡ ነው፡፡ ሚስታቸው የታወቀች ዘፋኝ ነበረች፡፡ ብዙ ጊዜ ህብረተሰቡ ውስጥ የሚቀለድ ቀልድ ነበር፡፡
“ዢ ጂንፒንግ ማነው?”
“የፔህግ ሊዩዋን ባል ነው፡፡”

ይህ እንግዲህ ሰውዬው ምን ያሀል ራሳቸውን ከእይታ ማራቅ እንደሚችሉ የሚያሳይ ነው፡፡ 
በቀደመው ጊዜ በቻይና የመሪ ሚስት ከመጋረጃ ጀርባ ነች፣ እንዲች ብሎ አደባባይ መውጣት የለም፡፡ የዢ ሚስት ግን ከፍተኛ የሚዲያ ሽፋን ታገኛለች፡፡ ዢ ሚንግዜ የምትባል ሴት ልጅ አለቻቸው፡፡ እሷም በሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ከመማሯ በስተቀር ብዙም የሚታወቅ ነገር የለም ነው የሚባለው፡፡

በነገራችን ላይ የቻይና ለአንድ ቤተሰብ አንድ ልጅ ብቻ የሚለው ፖሊሲ ከፍተኛ የጾታዎች አለመመጣጠን ፈጥሯል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ቻይና ውስጥ የወጣት ወንዶች ቁጥር ከወጣት ሴቶች ቁጥር በ32 ሚሊዮን ይበልጣል፡፡ ወደፊት በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወንዶች ሚስት አያገኙም ማለት ነው ይባላል፡፡ ይህ ደግሞ አይደለም ለቻይና ለዓለም ሰላምም አስጊ ሊሆን ይችላል ነው የሚባለው፡፡

ዢ ጠላት ላለማፍራት በጣም ይጠነቀቁ ነበር ተብሏል፡፡ በ40ዎቹና 50ዎቹ እድሜያቸው በከፍተኛ የፓርቲ ስልጣን ላይ ሆነው እንኳን ምንጊዜም የሥራ ሰውና መቼም ቢሆን ልታይ፣ ልታይ የማይሉ ነበሩ፡፡

ላለፉት በርካታ አስርት ዓመታት የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ‘ዘ ሞስት ፓወርፉል ማን ኢን ዘ ወርልድ’ ተብለው ነው የሚጠቀሱት፡፡ ‘የዓለም ሀያሉ ሰው’ እንደማለት ነው፡፡ ይህ ስያሜ ግን ምን ያሀል ተጨማሪ አስርት ዓመታት እንደሚዘልቅ አጠራጣሪ ነው፡፡

ቻይና ግስጋሴዋን በያዘችው ፍጥነት ከቀጠለችና ከቡድንና ከግለሰብ ጥቅም የአገር ጥቅም የሚያስቀድሙ እንደ ዢ ጂን ፒንግ አይነት መሪዎች ማፍራቷን ከቀጠለች የዓለም ሀያሉ ሰው ማን እንደሚሆን ያን ጊዜ የምናየው ይሆናል፡፡ “በበጎ ምግባር የሚያስተዳድር እንደ ሰሜናዊቷ ኮከብ ነው፣” ብሎ የለ ኮንፊሺየስ “ስፍራዋን አትለቅም፣ በርካታዎቹ ክዋክብትም ክብራቸውን ይግልጹላታል…”

ብሎ የለ - እንደዚያ ነው…

ኤፍሬም እንዳለ

በማኅበረ ሰብ ገጾች ያጋሩ

Submit to FacebookSubmit to Google PlusSubmit to TwitterSubmit to LinkedIn
Sheger 102.1 AudioNow Numbers