• United Bank S.C.

    ሕብረት ባንክ አ.ማ.

  • Slider Two

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Sldier Three

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ሸገር | ወግ

የ‘ብላክ ፓንተርሷ’ ዋካንዳ እና የእኛዋ ኢትዮዽያ

ድፍን አፍሪካ ዳር እስከ ዳር ደስ ብሏታል፣ በ‘ብላክ ፓንተር’ ፊልም፡፡ ለምን ደስ አይበላት! ለምን “ኩራት፣ ኩራት አይልሽም ወይ?” አያሰኛት! ሆሊዉድ አፍሪካን በበጎ የመሳል ታሪክም የለውም…ያውም ጀግኖች አድርጎ፣ ያውም በቴክኖሎጂ የበለጸጉ አድርጎ! አፍሪካን በተመለከተ በቅኝ አለመያዝ፣ በቴክኖሎጂ መበልጸግ፣ ጀግነነት በሆሊዉድ ፊልሞች ላይ በአንድ አረፍተ ነገር ውስጥ የሚገቡ ቃላት አልነበሩም፡፡ ‘ብላክ ፓንተር’ ይህን ሁሉ ይለውጠው ይሆናል፡፡

በዚህም ተባለ በዛ የ‘ብላክ ፓንተር’ ነገር ዓለም አቀፍ ዝና ማግኘቱ፣ ገቢ በኩንታል መዛቁሸ አንዲትን ምናባዊ የአፍሪካ አገር ታስቦ በማያውቅ ሁኔታ በበጎና፣ በሚያስጨበጭብ መልክ ማቅረቡ ብቻ አይደለም…በተጨማሪ አትዮዽያን እንደገና በበጎ በዓለም አቀፍ መልኩ ስሟን እንዲነሳ ማድረጉም እንጂ፣ የጥንቷና በጊዜዋ ገናና የነበረችው ኢትዮዽያ ማንነትና ምንነት እንደገና ዓለም አቀፍ መወያያ እንድትሆን ማስቻሉ እንጂ፣ ታላቁ የአድዋ ድልና እምዬ ምኒልክ እንደገና በዝርዝር እንዲወሱና እንዲዘከሩ ማድረጉ እንጂ፡፡

በነገረችን ላይ ከበርካታ ወራት ዓለመ አቀፍ የእለቂትና የትርምስ ወሬ መለስ ብሎ አገራችንን እንዲህ ከፍ፣ ከፍ የሚያደርጉ ወሬዎች መስማት መቻላችን እፎይታ ነገርም አለው፣ ምንም እንኳን ጊዜያዊ ሊሆን ቢችልም፡፡ የክርክሩ ዙር እየከረረ ነው…የ‘ብላክ ፓንተሯ’ ምናባዊና ቅኝ ተይዛ የማታውቅ፣ የበለጸገችና በቴክኖሎጂ እጅግ የመጠቀች አገር መነሻ ሀሳብ ከየት ነው የመጣው የሚለው ክርክር፡፡

“ፊልሙን ያዩ ኢትዮዽያውያን ለ‘ዋካንዳ ሀሳብ’ ምንጭ የሆነችው አገራቸው እንደሆነች ይናገራሉ፣” ይላል የ‘ዋሽንግተን ፖስት’ ጽሁፍ፡፡ “እንደ አውነቱ” ሲል ጽሁፉ ይቀጥላል፣ “ኢትዮዽያ፣ ወይም በአንድ ወቅት ትታወቅ እንደነበረው አቢሲንያ፣ በመካከለኛዎቹ ክፍለ ዘመናት ለአውሮፓውያን እንቆቅልሽ የሆነች፣ እጅግ የበለጸገች እንቆቀቅልሽ የሆነች ክርስቲያናዊ አገር፣ በክፉ በሚያዩዋት የሙስሊም ሀገራት የተከበበች፣ ከተራሮች ጀርባ የተሸሸገችና የመናኙ ዮሀንስ (ፕሬስተር ጆን) አገር ነበረች፡፡”

“እንዲህ አይነት ገጸ ባሀሪያትን ብዙ ጊዜ ጥቁር ሲጨወታቸው የምታያቸው አይደሉም፣” ሲል የህግ ባለሙያዋ ብሌን ሳህሉን ይጠቅሳታል፡፡ በተለይም ብሌን የሹሪን ገጸ ባሀሪይ ትጠቅስለታለች፡፡ “የእሷ ሚና ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነች፣ ምን ያህል ብልህ እንደሆነች… ብላክ ፓንተር የሚጠቀመው ቴክኖሎጂ በእሷ አእምሮ የተፈጠረ ነው፡፡”

 

በነገራችን ላይ ለኤድና ሞል ሲኒማም አኪር ቆሞለታል ነው የሚባለው፡፡ ጋዜጣው የሲኒማ ቤቱን ሃላፊ ጠቅሶ በቀን አምስት ጊዜ በሚቀርቡት የ‘ብላክ ፓንተር’ ትርኢቶች ሲኒማ ቤቱ ጢም እንደሚልና ከአቫታር ወዲህ በገቢ ከፍተኛ መሆኑን እንደገለጸለት አስፍሮታል፡፡ 
የ‘ዋካንዳ’ ሀሳብ ከኢትዮዽያ ነው የተቀዳው ብለው የሚከራከሩት በተለይም የኢትዮዽያን የጥንት ታላቅነት ያነሳሉ፡፡

እዚህ ላይ የታሪክ ድርሳናት ለመጥቀስ ያህል “ኢትዮዽያዊ ታላቅ ዘር ነው፣ ምናልባትም ከሁሉም ቀዳሚው፡፡ በችግር ምክንያት የሚያልቅ ዘር ነው፣” ትላላች ኢትዮዽያ የስልጣኔ መጀመሪያ ስለመሆኗ በ1930ዎቹ መጽሀፍ የጻፈች አፍሪካዊት አሜሪካዊት ጸሀፊ፣ ድሩስላ ደንጂ ሂዩስተን፡፡ “የጥንት ጸሃፊዎች ግብጽ የተጠፈጠፈችው ከኢትዮዽያ እየታጠበ በሄደ ጭቃ ነው ይላሉ፡፡

ኢትዮዽያውያን ዓለም ላይ ለመኖር የመጀመሪያ ህዝቦች ናቸው፣ አማልክትን የማምለክና መስዋእት የማቅርብ ለማዶች… ግብጽ የኢትዮዽያ ቅኝ ነበረች፣ ለዚህም ነው የሁለቱ ሀገራት ህጎች ተመሳሳይ የነበሩት፣” ትላለች፡፡

በእነኛ የኋለኛ ዘመናት ግብጽ በኢትዮዽያ አገዛዝ ስር ነበረች፡፡ ‘ሳይክሎፒደያ ኦፍ ቢብሊካል ሊትሬቸር’ ላይ እንዲሀ ይላል፣ “ነቢዩ ኢሳያስ ኢትዮዽያና ግብጽን ቅርብ ፖለቲካዊ ግንኙነት አዳላቸው፡፡ ኢትዮዽያ የሚለው ስም ለግብጽ ብሔራዊና ዘውዳዊ ስም ሆኖ አገልግሏል፡፡ መጀመሪያ ላይ ግብጽ የምትመራው ከኢትዮዽያ ነበር፡፡ ኢትዮዽያ ግን ከግብጽ ጋር ባደረገቻቸው ጦርነቶች ራሷ ተጎዳች፣” ይላል፡፡

‘ሳይክሎፒዲያ ኦፍ ቢብሊካል’ ሊትሬቸር ደግሞ ጥያቄዎች ይደረድሯል፡፡ “ግብጽ ሬሳዎች እንዳይበሰብሱ የምትጠቀምባቸውን ሽቶዎችና መድሀኒቶች ከየት ነው ያገኘችው? በማምለኪያ ስፈራዎቻቸው የሚጨሰው እጣን ከየት መጣ? ህዝቦቿ ይዋቡበት የነበረውንኗ የእሷ አፈር ይህን ያህል የማያመርተውን ከፍተኛ የሆነ ጥጥ ከየት አመጣች? በይሁዲ ገጣምያንና ጥንታዊ ግሪካውያን የሚወደሰው ኢትዮዽያ የሚለው ስም ከየት መጣ?” እንዲህ እያለ በርካታ ጥያቄዎች ይደረድርና እነኚህ ሁሉ ነገሮች ኢትዮዽያ ማእከል በሆነችበት ዓለም አቀፍ የንግድ ልውውጥ የመጡ ናቸው ይላል፡፡

እንግዲህ የኢትዮዽያን ጥንታዊ ታላቅነት የሚጠቅሱ ድርሳናት በየቦታው ተወሸቀዋል፡፡ አይደለም ይሄ ብቻ…ቅርሶቿ እንኳን በሌላ አገር ስም ስር ይጠራሉ፡፡ ይህን በተመለከተ ከፍ ብለን የጠቀስናት ሂዩስተን እንዲህ ትላለች፡፡ “አሁን ተጎሳቁላ ያለችውን ኢትዮዽያ በማየት አገር አሳሾች፣ ከርሰ ምድር ተመራማሪዎችና የሰው ዘር አመጣጥ ተመራማሪዎች የሚያቀርቧቸውን ድምዳሜዎች ለመቀበል አስቸጋሪ ይሆነባቸዋል፣” ትላለች ሂዩስተን፡፡

በመሃል ያለው ረጀም ጊዜ የእነኛን ስልጣኔዎች ምልክቶች ሁሉ አጥፍቷቸዋል፡፡ በዓለም አካባቢ ያሉ ቤተመዘክሮች ያሉና የግብጽ ናቸው የሚባሉት ቅርሶች እንደ እውነቱ የኢትዮዽያ ናቸው፡፡” ይህ ቀላል መረጃ አይደለም፡ በተላይ ለታሪካዊ ቅርሶች የሚሰጠው ትኩረት በፖለቲካና በመንደርተኝነት አስተሳሰብ በተዥጎረጎረበት በአሁኑ ጊዜ ምን ያህል ታሪካችን እንደተወሰደብን ማሰቡ በእርግጥም ያስቆጫል፡፡

እንግዲህ እነዚሀ ሁሉ ባሉበት የ‘ብላክ ፓንተር’ መነሻ ሀሳብ ኢትዮዽያ ነች ብሎ መከራረኩ ጉንጭ ማልፋት ብቻ ላይሆን ይችላል፡፡ የሚነሱት ማመሳከሪያዎች የዋዛ አይደሉም፡፡ “በብሉ ናይል አምባ ላይ ያሉት ህዝቦች ያለፈ አንጸባራቂ ታሪካቸውን ያውቃሉ፣ ራሳቸውንም በኩራት ኢትዮዽያውያን ብለው ይጠራሉ፡፡ በቀድሞ ጊዜያት የአካባቢው የአየር ሁኔታ ክፍተኛ የሆነ ስልጣኔ ለማዳበር የተመቸ ከመሆኑ በላይ ኢትዮዽያውያኑን የጥንት ሰዎች “ከጥንታዊው ዓለም ካሉ ወንዶች ሁሉ እጅግ መልከ መልካሞቹ፣” ብለዋቸዋል፡፡

ይህ ሁሉ ተብሎ ግን ቅራኔው (ወይም ‘ኮንትራዲክሽን’ የምንለው ነገር) የሚመጣው የአሁኗን የደካከመች ኢትዮዽያን በቀድሞው ዘመን ከነበረችው ታላቋ ኢትዮዽያ ጋር ለማመሳሰል ሲሞከር ነው፡፣ ሥራችንን ባለመሥራታችንና በሚያሳዝን መልኩ ይህ በብዙ መስኮች ውስጥ የሚታይ ነው፣ አገራችን ከተፈጠረች ጀምሮ ሁልጊዜም እንዲህ የችግር ምድር ሆና እንደኖረች የሚያስቡ አሉ፡፡

ምክነያታዊ ያለሆነ አስተሳስብ ነው፡፡ በእርግጥ አገራችን በጥንቱ ጊዜ እንደሚወራላት ከነበረች የቁልቁለት መንሸራተቷ መቼ ነው የጀመረው፣ ለምንስ ነው ውደቀቷ ፈጣን የሆነው፣ ለምንስ ነው እዚሀ ደረጃ የደረሰው…የመሳሰሉ ሞጋች ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ እዚሀ ላይ እንደ ሂሳብ የሚጣፋ ነገር የለም፣፡

የዛሬው ደካማነቷ የትናንት ጥንካሬዋን አጣፍቶ ዜሮ ሊያመጣው አይችልም፡፡ 
ስለሆነም…በ‘ደብርሀን ብሎግፖስት’ ላይ ሀሳባቸውን ያሰፈሩ አንድ ጸሃፊ በርካታ መመሳሰሎችን ይጠቅሳሉ፡፡ ‘ብላክ ፓንተር’ ላይ ትቻላ በልጅነቱ ታፍኖ ከመወሰዱም በላይ አገሩን ከቅኝ ገዛትነት ለመከላከል የአውሮፓ ወራሪዎችን ድል ነስቷል፡፡ ዳግማዊ ምንሊክም በልጅነታቸው በአጼ ቴዎድሮስ ታስረው የነበሩ ሲሆን የጣልያንንየ ቅኝ ግዛት ምኞት አምክነዋል፡፡

‘ብላክ ፓንተር’ ላይ በንጉሥ ትቻላ ጥረት ‘ዋካንዳ’ በቴክኖሎጂ የመጠቀች አገር ነች፡፡ በሌላ በኩል ምኒልክ በአሥራ ዘጠነኛው ክፍለ መባቻ ለአገራቸውና ለህዝባቸው በወቅቱ የመጠቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ያስታወቁ የመጀመሪያው ኢትዮዽያዊና አፍሪካዊ መሪ ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገራት ነገር ባልነበራቸው ወቅት ምኒልክ ህዘባቸው የመብራት ሀይል፣ ስልክ፣ ባቡር፣ ሆቴሎች፣ ሲኒማ፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች አና ቴሌኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት እንዲያገኝ አድርገዋል፡፡

አንዳንድ ጸሃፊዎች ኢትዮዽያ በዳግማዊ ምኒልክ መሪነት የጣልያን ወረራን መመከትንና በቴክኖሎጂ በኩል መገስገሷን ይጠቅሳሉ፡፡ “ይህ የሆነው ኢትዮዽያ ከአውሮፓ አገዛዝ ነጻ በመሆኗ የአውሮፓን ቴከኖሎጂ በሚጠቅማት መንገድ ለመጠቀም ነጻ የነበረች መሆኗ ነው፣” ይላሉ፡፡

“ብላክ ፓንተር ላይ ያለችው ዋካንዳ የተባለችው አገር “አፍሪካ በቅኝ ግዛት ባትያዝ ኖሮ ልትደርስ ትችል የነበረበትን የሚያሳይና፣ እንዲሁም ትክክለኛውን አመራር ካገኘች ወደፊት ለምትድረስበት ተምሳሌት ነው፣” ብሏል አንድ ጸሀፊ፡፡

ስለሆነም የ‘ብላክ ፓንተሩ’ ትቻላ ባህሪያት በአብዛኛው ከኢትዮዽያው ዳግማዊ ምኒልክ ባህሪያት ናቸው የሚል መከራከሪያ አለ፡፡ እንደውም ‘ብላክ ፓንተር’ የታሪኮቹን ሀሳቦች ላገኘባቸው ስፍራዎች በግልጽ እውቅና ባለመስጠቱ የኮፒራይት ስህተት አለበት ይላሉ፡፡
በነገራችን ላይ የአሁኗ ዓለማችን ቀድማ ከነበረችውም የባሰባት የሸፍጥና የክፋት ዓለም ነች፣ በጣም የባሰባት፡፡ ይሄን ለማለት የአርማጌዶን ሰባኪ መሆን አያስፈልግም፡፡

በቀድሞዎቹ ዘመናት ታሪካችንን በዝምታ ሊያፍኑ እንደሞከሩ ሁሉ አሁንም ቢሆን እንዲህ አይነት ዓለም ያነቃነቀ ሥራ ሀሳብ የመጣው ከኢትዮዽያ ታሪክ መሆኑን አይደለም መቀበል ማሰቡ እንኳን ይተናቃቸው ይሆናል፡፡

በሌላው ዓለም በተለይ በምእራቡ ዓለም አፍሪካንና ኢትዮዽያን በበጎ የሚያሳዩ በተለየ ታሪካዊ ድርጊቶችን ሆነ ብሎ ችላ የማለት ነገር በግልጽ የምናየው ነው፡፡ ይህ የታሪክ ሽሚያ አይደለም፡፡ ይህ በልብወለድ መልክ ተጽፎ እንደ እውነተኛ ታሪክነት ስለሚቀርብ ነገር አይደለም፡፡ ይህ እውቀትን ስለመፈለግ ነው፡፡

ከምንጊዜውም በላይ ተመራማሪዎቻችንን የምንፈልገበት ጊዜ ነው፡፡ ከምንጊዜውም በላይ የእኛ የሆነውን ካለበት ቆፍረው የሚያወጡልንን፣፡ እውነተኛ የጥንት ምስላችንን እንዳናይ የወረዱ የፖለቲካና የመነደረተኝነት አስተሳሰቦች ሙያቸውን ያላዥጎረጎረባቸውን ተመራማሪ ልጆቿን የምትፈልግበት ዘመን ነው፡፡

የ‘ብላክ ፓንተር’ ሀሳብ የመጣው ከኢትዮዽያ ነው አይደለም የሚለው ክርክር ሊቀጥል ይችላል፡፡ ምናልባትም አይደለም የሚለው ሰራዊት ድምጹ ሊጎላ ይችል ይሆናል….ምክንያቱን ህብረተሳበችብ ‘ኔይሴየርስ’ የሚሏቸው አይነት በራሳቸው ቡድናዊና ግለሰባዊ እምነት እውነት ሊሆን የሚችለውን ነገር ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆኑ ብዙ አሉና፡፡ የማመን የማሳመን ነገር ላይኖር ይችላል፣ አያስፈልግምም፡፡

ግነ ‘ብላከ ፓንተር’ ከሁሉም በላይ ኪነጥበብ አካባቢ ላሉ የአገር ልጆች ትልቅ ጥያቄ የሚፈጥርና ፈተናዎችም የሚደቅን ነው፡፡ “እኛስ ምን ሠራን?” የሚያስብል ነው፡፡ ትንሿን ምልክት ይዘው ይሄን ያሀል ዓለምን ቁጭ፣ ብድግ የሚያደርግ የጥበብ ሥራ ሲያደርግ እኛ ዘላለም… “እኛን ማለቱ ነው፣” “ከእኛ ታሪክ የተቀዳ ነው፣” እያልን ልንቀጥል አንችልም፡፡ ምን ያክል ሥራችንን እንዳልሠራን፣ ምን ያህል ከማንነታችን እየራቅን እንድንሄድ እንደተደረገ፣ ምን ያህል ቀስ በቀስ ማንነታችን እንዳልነበር የማድረጉ ጥረት ሳናውቀው ምን ያሀል ባዶ ሜዳ ላይ (‘ኖ ማንስ ላንድ’) የሚሉት አይነት ላይ ሊጥለን እንደቀረበ የማስጠንቀቂያ ደወሉን የሚያንቃጭል መሆን አለበት፡፡

በሰሞኑ በአድዋ በዓል አከባቢ አንድ ጎልቶ የወጣ ነገር ቢኖር በስነጥበባትና በመሳሰሉት አድዋን ለመዘከር ያደረግናቸው ጥረቶች እዚህ ግቡ የሚባሉ አለመሆናቸው ነው፡፡ እንደዛ ብቻ ሳይሆን የሚያስወቅስም ነው፡፡ አድዋ በኢትዮዽያ ስነ ጥበብ — ሙዚቃ፣ ፊልም፣ ልብ ወለድና ስነ ግጥም — ያለው ስፍራ እጅግ አናሳ ነው፡፡ በፊልም ደረጃ የሚጠቀሰው ብቸኛ ስራ የፕሮፌሰር ሀይሌ ገሪማ ‘አድዋ፣ አን አፍሪካን ቪክትሪ’ ነው፡፡ ይህም ቢሆን አሜሪካ ውስጥ የተሠራ ነው፡፡ በሙዚቃም ቢሆን በዋነኝነት የሚጠቀሱት የጀጂና የቴዲ አፍሮ ሥራዎች ናቸው፡፡

በነገራችን ላይ መጀመሪያ የምንላቸው ብዙ፣ ብዙ ነገሮች አሉ…መጀመሪያ ጊዜ መኪና የነዳ አፍሪካዊ መሪ ንጉሥ ምኒልክ ናቸው፣ የፓን አፍሪካኒዝም የትውድል ስፍራ ኢትዮዽያ ነች፣ የራሷ የቀን መቁጠሪያ ያላት፣ ከአረቦቹ በስተቀር አፍሪካ ውስጥ የራሷ የጽሁፍ ቋንቋ ያላት ኢትዮዽያ ብቻ ነች፣ በዓለም የታወቀች የመጀመሪያዋ ሴት አፍሪካዊት መሪ ንግሥት ዘውዲቱ ነበሩ፣ አውሮፕላን በማብረር የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ሴት አብራሪ ኢትዮዽያዊት ነች፡፡ አርባ ጊዜ ያሀል በመጽሀፍ ቅዱስ የምትጠቀሰው ኢትዮዽያ በመጽሐፍ ቅዱስም፣ በቁራንም፣ በሆመር ኦዲሴና በሌሎች በርካታ የጥንት መጻህፍት ሁሉ ከተጠቀሱት ጥቂት አገራት አንዷ ነች…መቀጠለ ይቻላል፡፡

በነገራችን ላይ ለመረጃ ያህል… ‘አላሞ ድራፍትሀውስ’ የተባለ ምግብ ቤት ‘የብላክ ፓንተር ስፔሻል’ ማዘጋጀቱን በድረ ገጹ ሲያስተዋውቅ ነበር፡፡ “እንደ ንጉሥ ወይም እንድ ንግሥት ተመገቡ፣ ይላል፡፡ ምግብ አብሳዩ ሼፍ ብራድ ሶረንሰን የኢትዮዽያን በርበሬ ቅመምና ንጥር ቅቤ በመጠቀም ልዩ ምግብ ማዘጋጀቱን ገልጿል፡፡

በንጥር ቅቤ የተጠበሰ ፈንድሻ፣ በበርበሬ የተጠበሰ የዶሮ ክንፍ፣ ዳቦ ቆሎ…እንዲመገቡ ይመክርና “ንጉሥ ትቻላ በእነኚህ ምግቦች እንደሚደሰት እናምናለን፡፡ እናንተም እንደምትደሰቱ እናምናለን፣” ይላል፡፡ እንግዲህ በዚህ፣ በዚህ በ‘ብላክ ፓንተርስ’ የተነሳ የኢትዮዽያ ስም የሚነሳባቸው ሁኔታዎች ዘርፈ ብዙ መሆናቸውን ማየት ይቻላል፡፡

ሰለሆነም የ‘ብላክ ፓንተርስ’ መነሻ ሀሳብ ከየት እንደተገኘ የሚካሄደው ምልልስ ጊዜያዊ ሊሆን ይችላል፡፡ የአንድ ሰሞን የሚዲያ ላይ ሞቅ፣ ሞቅ ሊሆን ይችላል፡፡ እውነቱ ግን ከምጊዜውም በላይ ኢትዮዽያ የሚለውን ስም በዓለም ጓዳዎች አስገበቶታል፡፡

አሁን ያለችው ኢትዮዽያ የሁልጊዜም ኢትዮዽያ እንዳልሆነች ለማያውቁት ቢያንስ ምክልክት ሰጥቷቸዋል፡፡ በእርግጠኝነትም ስለ ትናንትናዋ ኢትዮዽያ ለማወቅ የሚኖረው ፍላጎት መጨመሩ አይቀርም፡፡ በዛው ልክ እኛ ላይ የቤት ሥራው በበዙ እጥፍ ይጨምራል፡፡ 
እውን የቤት ሥራውን በብቃት እንወጣው እንደሆነ ጊዜ የሚለየው ይሆናል፡፡

ኢትዮዽያ ለዘለዓለም ትኑር!

በማኅበረ ሰብ ገጾች ያጋሩ

Submit to FacebookSubmit to Google PlusSubmit to TwitterSubmit to LinkedIn
Sheger 102.1 AudioNow Numbers