• United Bank S.C.

    ሕብረት ባንክ አ.ማ.

  • Slider Two

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Sldier Three

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ሸገር | ወግ

የዓለም ዋንጫ…የእግር ኳስ ጥበብ፣ የፖለቲካ ትርምስ፣ የነውጠኝነት ስጋት

የሩስያው የዓለም ዋንጫ ደርሷል፡፡ በቢሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ይከታለዋል ተብሎ ነው የሚጠበቀው፡፡ ያለፈውን የብራዚል የዓለም ዋንጫ ወደ 3.2 ቢሊዮን ህዝብ አይቶታል ነው የሚባለው፡፡ በነገራችን ላይ ያለፈው የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ጀርመን ካሸነፈች እያንዳንዱ ተጫዋች 350‚000 ዩሮ ጉርሻ ያገኛል፡፡

ኔይማር ደግሞ ከብራዚል ጋር ዋንጫ ካሸነፈ ናይኪ 50‚000 ዶላር ይከፈለዋል ተብሏል፡፡ በተጨማሪም የውድድሩ ምርጥ ተጫዋች ከሆነ ሌላ 200‚000 ዶላር ያገኛል፡፡ በእርግጥ ያጓጓል፡፡

በነገራችን ላይ በሩስያው የዓለም ዋንጫ አንድም እንግሊዛዊ ዳኛ የለም፡፡ አንድም! ፕሬሚየር ሊግ አንድም ለዓለም ዋንጫ የሚበቃ ዳኛ ይጣ! በቀድሞው ዘመን እኛም አኮ ለዓለም ዋንጫ ዳኛ ልከን ነበር! እንዲሁ ‘ነበር’ን ለለማብዛት እንለፈው እንጂ!

እግረ መንገድ…ያለፉት ውድድሮች እንደሚጠቁሙት ከሆን በዓለም ዋንጫው የተነሳ የሩስያ ህዝብ ብዛት ከዘጠኝ ወር በኋላ በጥቂተ መቶ ሺዎች ሊጨምር ይችላል፡፡ ምክንያቱም ከደቡብ አፍሪካ የዓለም ዋንጫ ዘጠኝ ወራት በኋላ በአገሪቷ የውልደት መጠኑ አሻቅቦ ነበርና፡፡

በ2006 ጀርመን ያዘጋጀች ጊዜም እንዲሁ በአንዳንድ የአገሪቱ ከፍሎች የውልደት መጠኑ በ30% አድጎ ነበር፡፡ እንግዲህ… ቤት ተቀምጦ ኳስ ሲያዩ ማምሸትና ውጪ ድራፍት ሲጨልጡ በማምሸት መሀል ያለው ልዩነት ማለት ነው፡፡ ይህ ግኝት እኛንም የሚመለከት ከሆነ ምን ማድረግ ይቻላል!… “ባሎች ቁጥራችን እንዳይጨምር ደጅ አምሹ፣” አይባል ነገር!

እንግዲህ በዓለም ዋንጫ ወቅት ገር፣ ገር የሆኑ ነገሮችን የምንጠብቅ ቢሆንም…ህይወት ኳስ ቦታም ይሁን የትም ስፍራ በአበቦች መሀል ሽርሽር አይደለችምና፡፡ የቴክኒኩን፣ የታክቲኩንና የመሳሰለውን ነገሮች ለባለሙያዎቹ ለስፖርት ጋዜጠኞች እንተወው፡፡ የዓለም ዋንጫ ግን እርካታ የሚፈጥረውን ያህል ደስ የማይሉ ክስተቶችም በየጊዜው ይታዩበታል…ጦር እስከማማዘዝ የደረሱ ክስተቶች፡፡

እጅግ አስቀያሚ የተባለው የቺሊው ዓለም ዋንጫ በእግር ኳስ ላይ የማይለቅ ጥቁር ነጥብ የተወ ነው ይባላል፡፡ ይህ የዓለም ዋንጫ እጅግ አስቀያሚና ከእግር ኳስ ጥበብ ይልቅ ቅልጥም ሰበራ የበዛበት ነው ተብሏል፡፡ በወቅቱ ‘ዘ ኤክስፕሬስ’ የተባለው የእንግሊዝ ጋዜጣ “ከስፍራው የሚመጡ ዘገባዎች ከጦር ሜዳ የሚላኩ ይመስላሉ፣” ብሎ ነበር፡፡

ለምሳሌ የጣልያንና የጀርመን ግጥሚያ ‘ነጻ ትግልና ጦርነት’ ነው የተባለው፡፡ “ተጫዋቾች ከመጫወት ይልቅ እግራቸውን ለማትረፍ ኳሷን እየሸሹ ይዘሉ የነበሩበት ጨዋታ ነው፣” ብሏል ጋዜጣው፡፡ ተጫዋቾች የሚሄዱት ለኳስ መሆኑ ቀርቶ ለእግር ነበር፡፡ በመጀመሪያ ሁለት ቀናት በተደረጉ ስምንት ግጥሚያዎች ብቻ አራት ቀይ ካርዶች ነው የተሰጡት፡፡

 

በተጨማሪም በአርጀንቲናና በቡልጋሪያ መካከል በተደረገው ግጥሚያ ብቻ ዳኛው 69 ቅጣም ምቶች ሰጥቷል፣ ይህም በየ78 ሴከንዱ አንድ ቅጣት ምት ማለት ነበር፡፡

ከሁሉ በላይ ግን በአዘጋጇ ቺሊና በጣልያን መካከል የተደረገው ግጥሚያ በዲስፕሊን ረገድ ከአስከፊነቱ የተነሳ ‘ዘ ባትል ኦፍ ሳንቲያጎ’ በሚል ይታወሳል፡፡ ከግጥሚያው በፊት ‘ክላሪን’ የተባለው የአገሪቱ ጋዜጣ “ይህ የዓለም ዋንጫ ሳይሆን የዓለም ጦርነት ነው፣” ብሎ ጽፎ ነበር፡፡

‘ዘ ኤክስፕሬስ’ም… “ይህ ውድድር አስቀያሚና ደም የሚጎርፈበት እንደሚሆን ምልክቶች አሉ” ብሎ ጽፎ ነበር፡፡ ከችግሩ መነሻዎች ዋናው ከግጥሚያው በፊት የጣልያን ጋዜጦች ቺሊ ላይ ይጽፏቸው የነበሩ አዋራጅ የተባሉ ዘገባዎች ናቸው፡፡

“ውድድሩ ቺሊ መደረጉ እብደት ነው፣” ብለዋል ጋዜጦቹ፡፡ “ስልኮች አይሠሩም፣ እንደ ታማኝ ባሎች ሁሉ ታክሲዎችም በመከራ ነው የሚገኙት፣ ወደ አውሮፓ ቴሌግራም ለመላክ ዋጋው ኪስ ያራቁታል፣ አንድ ደብዳቤ ለተላከለት ለመድረስ አምስት ቀናት ይፈጅበታል፡፡ ህዝቡም በምግብ እጥረት፣ መሃይምነት፣ በአልኮል ሱሰኝነትና በድህነት የተያዘ ነው፡፡

ሳንቲያጎ አሰቃቂ ነች፡፡ ሙሉ መንደሮች ለግልጽ ሴተኛ አዳሪነት የተሰጡ ናቸው፡፡” ብዙ፣ ብዙ ተጻፈ፡፡ እነዚህ ዘገባዎች ውቅያኖሶችን አቋርጠው ቺሊያውያን ጆሮ ይደርሳሉ… ጥርሳቸውንም ነከሱ፡፡ ቺሊ ሆነው እነዚህን ዘገባዎች የላኩት ጋዜጠኞች ወደ አውሮፓ እግሬ አውጪኝ አሉ፡፡

ግጥሚያው ሲጀመር ቺሊያውያኑ ጣልያን ተጫዋቾች ላይ ይተፉባቸው፣ ይጎነትሏቸውና ይረግጧቸው ጀመር፡፡ ጣልያኖቹ ምላሽ ሲሰጡ ካርድ የሚመዘዘው ለእነሱ ሆኑ፡፡

የመጀመሪያው ቅጣት ምት የተሰጠው ገና በ12ኛው ሴከንድ ነበር፡፡ በአራተኛው ደቂቃ ደግሞ የመጀመሪያው ቀይ ካርድ ጣልያናዊው ጂዮርጂዮ ፌሪኒ ላይ ተመዘዘ፡፡ እሱ ግን አልወጣም አለ፡፡ ከአስር ደቂቃ ጭቅጭቅ በኋላ የታጠቁ ፖሊሶች ናቸው አጅበው የወጡት፡፡ ‘ዘ ሚረር’ ጋዜጣ “የእግር ኳስ ሜዳው በአንድ ጊዜ ወደ ጦር ሜዳነት ተለወጠ፣” ነበር ያለው፡፡

የፕሮፌሽናል ቦክስኛ ልጅ የሆነው የቺሊው ሌኦኔል ሳንቼዝ የጣልያኑን አምበል ሆምቤርቶ ማሺዮን አፍንጫ በቦክስ ሰበረው፡፡ ማስጠንቀቂያ እንኳን አልተሰጠውም፡፡ ቀጠለና ሌላውን የጣልያን ተጫዋች ማሪዮ ዴቪድን የቀኝ ቡጢ አሳረፈበት፡፡ ዴቪድ ምላሹን ሲሰጥም በቀይ ወጣና ቡድኑ በዘጠኝ ሰው ቀረ፡፡ ቺሊ አሸነፈች፡፡ በነገራችን ላይ ዘንድሮ ጣልያን የለችም፡፡ የጂያንሉካ ቡፎን አገር ከ1958 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ሳታልፍ ቀርታለች፡፡

ስለዓለም ዋንጫ ጨለማ ክስተቶች በተነሳ ቁጥር በየጊዜው የሚነሳ ሌላ የደቡብ አሜሪካ ታሪክ አለ፡፡ ሆንዱራስና ኤል ሳልቫዶር ለረጅም ዘመናት ሲወዛገቡ የኖሩ ሀገራት ነበሩ፡፡ ለ1970 ሜክሲኮ ዓለም ዋንጫ ለማለፍ ማጣሪያ ላይ ተገናኙ፡፡ በሆንዱራስ ዋና ከተማ ቴጉቺጋልፓ በተደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ሆንዱራስ 1—0 ታሸንፋለች፡፡ የደጋፊዎች ብጥብጥም ሆነ፡፡

በኤል ሳልቫዶር ዋና ከተማ ሳን ሳልቫዶር በተደረገው የመልስ ግጥሚያ ኤል ሳልቫዶር 3—0 ታሸንፋለች፡፡ እዚህም ቅልጥ ያለ ጠብ ሆነ፡፡ ሁለቱም እኩል ሦስት ነጥብ ስለነበሩ በጊዜው ህግ መለያ ግጥሚያ መደረግ ነበረበት፡፡ ይኸው ግጥሚያ ሜከሲኮ ሲቲ ውስጥ ተደርጎ ኤል ሳልቫዶር በተጨማሪ ሰዓት 3—2 አሸነፈች፡፡

የሳልቫዶር ደጋፊዎች የሆንዱራስ ቡድን ያረፈበትን ሆቴል ከበው ሌሊቱን ሙሉ ሲጮሁ ያድራሉ፡፡ ይህ ወሬ ሆንዱራስ ውስጥ ሲሰማ ቀውጢ ሆነ፡፡ የሳልቫዶር ዜጎች ከየቤታቸው እየተጎተቱ ተደበደቡ፣ ከሥራቸው ተፈናቀሉ፣ ከአገር ተባረሩ፡፡ ከዚህ አመጽ ጀርባ የሆንዱራስ መንግሥት ይሁንታ ነበረበት ነው የሚባለው፡፡

ኤል ሳልቫዶር ወዲያው ነበር ከሆንዱራስ ጋር የነበራትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ ያቋረጠችው፡፡ ብዙም ሳይቆይ አየር ሀይሏ ሀንዱራስ ላይ የቦምብ ናዳ አወረደ፡፡ እግረኛ ጦሩም ድንበር ተሻግሮ ገባ…ቅልጥ ያለ ጦርነትም ሆነ፡፡ አራት ቀናት በፈጀውና ‘የመቶ ሰዓቱ ጦርነት’ ተብሎ በሚታወቀው ኳስ በቀሰቀሰው ውጊያ ሁለቱም ወገኖች እያንዳንዳቸው ከ2‚000 ሰው በላይ ሲያልቅ 300‚000 ሳልቫዶራውያንም ከሆንዱራስ ተባረሩ፡፡

ዓለም ዋንጫ ከውበቱ እና ለአንድ ወር ያሀል ከሚሰጠው ደስታ ባለፈ በርካታ የሜዳ ውስጥና የሜዳ ውጪ ችግሮች በርካታ ናቸው፡፡ በ1958 ስዊድንና ጀርመን በግማሽ ፍጻሜ ተገናኙና ስዊድን 3—1 አሸነፈች፡፡ ይሄኔ ሀምቡርግ ውስጥ የሚገኙ የስዊድን መኪኖች ጎማዎች ተሸረከቱ፡፡ በጀርመን ምግብ ቤቶች ተወዳጅ የነበረ የስዊድን ምግብም ከሜኑዎች ላይ ተሰረዘ፡፡

በ1966 የእንግሊዝ ዓለም ዋንጫ በጀርመንና እንግሊዝ መካከል በነበረው የመጨረሻ ግጥሚያ 2—2 ያልቅና ተጨማሪ ሰዓት ውስጥ ይገባሉ፡፡ በተጨማሪው ሰዓት በአሥራ አንደኛው ደቂቃ ላይ የእንግሊዙ ጄኦፍ ኸርስት የመታት ኳስ የግቡን አግዳሚ መትታ ግቡ መስመር አከባቢ ትነጥራለች፡፡ የእንግሊዝ ተጫዋቾች ግብ ነች አሉ፡፡

ካዛክስታናዊ የመስመር ዳኛ ቶፊክ ባክራሞቭ “አዎ ግብ ነች” አሉ፡፡ በኋላ የተቀረጸው ሲታይ ግን ግብ አለመሆኑ ታይቷል፡፡ እንግሊዝ አራተኛ ግብ አስቆጥራ ዋንጫውን ወሰደች፡፡ የመስመር ዳኛው ሆነ ብለው ያደረጉት ነው ይባላል፡፡ ይቺን ዓለም ሊሰናበቱ ሲሉ “ለምን እንዲህ አደረግህ?” ተብለው ተጠየቁ፡፡

አንድ ቃል ብቻ ነው የተናገሩት… “ስታሊንግራድ!” አሉ ይባላል፡፡ በእሳቸው ቤት የሁለተኛው የዓለም ጦርነት የሂትለርን ወረራ መበቀላቸው መሆኑ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ታሪክ ግን እስካሁን በአስተማማኝ አልተረጋገጠም፡፡

የዓለም ዋንጫ የተጫዋች ህይወትም አስከፍሏል፡፡ በአሜሪካው የዓለም ዋንጫ አሜሪካና ኮሎምቢያ ይገናኙና አሜሪካ 2—1 ታሸንፋለች፡፡ የመጀመሪያዋን የአሜሪካ ግብ የኮሎምቢያው ተከላካይ አንድሬስ ኤስኮባር በራሱ ግብ ላይ ያገባት ነበረች፡፡ ጦሰኛ ግብ ነበረች፡፡

ኤስኮባር አገሩ ተመልሶ ሜደሊን ውስጥ ከሴት ጓደኛው ጋር ከሬስቱራንት ሲወጣ ሦስት ሰዎች ቀርበውት ትንሽ ይጨቃጨቃሉ፡፡ ከዚያም ተኩስ ከፍተውበት በአሥራ ሁለት ጥይት ይጥሉታል፡፡ ከገዳዮቹ አንዱ… “በራስህ ላይ ላገባኸው ግብ እናመሰግናለን፣” ብሎታል ይባላል፡፡

ሌላ በዓለም ዋንጫ እጅግ አስቀያሚ ቅሌቶች ከተባሉት መሀል በ1982 የስፔይን የዓለም ዋንጫ ጀርመንና ኦስትርያ ያደረጉት ጨዋታ ነው፡፡ ጀርመን በአንድ ወይም ሁለት ጐል ካሸነፈች ሁለቱ ተያይዘው ያልፉና ቀደም ሲል ጀርመንን ያሸነፈችው አልጄሪያ ትወድቃለች፡፡

ጨዋታው በተጀመረ አስረኛው ደቂቃ ጀርመን አስቆጥራ አንድ ለዜሮ መምራት ጀመረች፡፡ ከዛ በኋላ ሁለቱም ቡድኖች ምንም እዚህ ግባ የሚባል የጎል ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው አለቀ…ተያይዘውም አለፉ፡፡ ሁለቱ ቡድኖች ሆነ ብለው እንዳደረጉት ወቀሳ ቢጎርፍም ፊፋ ሁለቱም ቡድኖች ምንም ጥፋት አልፈጸሙም አለ፡፡ ሆኖ ያ ጨዋታ በአውሮፓ እግር ኳስ ላይ ትልቅ ጥቁር ነጥብ ጥሎ ያለፈ ነው፡፡

ቀደም ባለው ጊዜ በ1978 አርጀንቲና ለፍጻሜው ለማለፍ ፔሩን በአራት ግብ ልዩነት ማሸነፍ ነበረባት፡፡ እንደተባለው ለፔሩ ባልስጣናት ስኳር አስላሷቸውና ፔሩዎች ለቅቀው አርጀንቲና 6—0 አሸነፈች፡፡ በመጨረሻውም ኔዘርላንድን 3—1 አሸንፋ ዋንጫ ወሰደች፡፡

በ1982 በሲቪል፣ ሰፔይን የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ የጀርመኑ ግብ ጠባቂ ሃራልድ ሹማቸር የፈረንሳዩን ፓትሪክ ባቲስተንን ግብ ሊያገባ ሲል አስቀያሚ ታክል ይሠራበትና በጎኑ ፊቱን ይመታዋል፡፡ ባቲስተን ራሱን ይስታል፡፡ ሜዳ ውስጥ ኦከሲጂን ተሰጥቶት ነው የነቃው፡፡ ሆኖም ሦስት ጥርሶቹን አጥቷል፡፡ ዳኛው ግን ምንም ውሳኔ ሳይሰጡ ጨዋታው በመልስ ምት እንዲቀጥል ነው ያደረጉት፡፡

ባቲስቲን ራሱን ስቶ ተከቦ እያለ ሹማቸር ኳሷን ለመምታት አመቻችቶ ምንም እንዳልተፈጸመ ማስቲካ ያኝክ ነበር በሚል ጀርመናዊው የስድብ ናዳ ወርዶበታል፡፡ በሌላ በኩል ላልተገባ ጨዋታ ሁለቱም ቀይ ካርድ አይተው በመውጣት ላይ እያሉ ፍራንክ ራያካርድ በጀርመኑ ሩዲ ቮለር ላይ በካሜራዎች ፊት የተፋበት ከዓለም ዋንጫ አስቀያሚ ድርጊቶች መሀል ነው ተብሏል፡፡

በ2006 የጀርመኑ ዓለም ዋንጫ ፖርቱጋል ኔዘርላንድን ያሸነፈችበት ጨዋታ ከፍተኛ የዲሲፕሊን ችግር የታየበት ሲሆን ‘ዘ ባትል ኦፍ ኑረምበርግ’ ወይም ‘የኑረምበርግ ጦርነት’ በሚል ይታወቃል፡፡ አራት ቀይ ካርዶችና አስራ ስድስት ቢጫ ካርዶች የታዩበት ጨዋታ ነበር፡፡ በ2006 የበርሊኑ ፍጻሜ ግጥሚያ ዚነዲን ዚዳን የጣልያኑን ማርኮ ማቴራዚን በቴስታ ምንጣፍ ያደረገበት የሚረሳ አይሆንም፡፡ ዚዳን እንደዛ ያደረገው ማቴራዚ እህቱን ሰድቦበት ነው ተብሏል፡፡

የዚዳን ድርጊት በእግር ኳስ ህግ ከፍተኛ ጥፋት ቢሆንም በወቅቱ ደጋፊዎችም ነበሩት፡፡ በአደባባይ “ደግ አደረገ፣” ያሉ ብዙ ናቸው፡፡ ሆኖም በዛ ድርጊት ዚዳን ለረጅም ጊዜ ውግዘት ሲዘንብበት ኖሯል፡፡

አስገራሚ ከሚባሉ የዳኞች ውሳኔዎች መካካል ፈገግ የሚያሰኙም አሉ፡፡ በ1982 ፈረንሳይ ከኩዌት ጋር ስትጫወት ፈረንሳዮች የመጀመሪያዋን ግብ ያገባሉ፡፡ የኩዌት እግር ኳስ ፌዴሬሽን መሪ የነበሩት ሼክ ፋሃድ አል አሃማድ አለ ሳባህ “ከተመልካች መሀል የተነፋ ፊኽካ የልጆቼን ሀሳብ ሰርቆት ነው፣” አሉ፡፡ ሜዳም ገቡና የኩዌትን ተጫዋቾች “ኑ ውጡ!” አሏቸው፡፡ ዩክሬንያዊው ዳኛ ሚሮስላቭ ስቱፓር ግቧን ሻሯት፡፡ ፈረንሳይ 4—1 አሸነፈች፡፡

በነገራችን ላይ ከሜዳው ውስጥ ፍልሚያ ውጪ የፊፋ አመራር መጠነ ሰፊ የሙስና ቅሌትም በውቡ ስፖርት ላይ ደማቅ ጥቁር ነጥብ ነው የተዉበት፡፡ የስዊስ ፖሊስ ዙሪክ የሚገኝ የቅንጦት ሆቴል ላይ ወረራ አካሂዶ ሰባት የፊፋ አመራሮችን ያዘ፡፡ እስራቱ ከኤፍ፡ቢ፡አይ፡ ጋር ለበርካታ ዓመታት ሲካሄድ የነበረ ምርምራ ውጤት ነው ተብሏል፡፡ እስራቶቹ የሴፕ ብላተርና የሚሼል ፐላቲኒን የስልጣን ዘመን ወደ ፍጻሜው አምጥቶታል፡፡

ሌላም ታሪክ አለ… ከሙስናው ባሻገር ሴፕ ብላተር የፊፋ ዋና ጸሀፊ ከነበሩት ሄልሙት ኬሰር ጋር የነበራቸው ግንኙነት የተበላሸ ነበር፡፡ ምንድነው የሆነው… ብላተር ዕድሜዋ የእሳቸውን ግማሽ የሆነችውን የኬሰር ልጅ ይከጅሏታል፡፡ ኬሰር ደግሞ “እንዴት ሆኖ!” በሚል ይበሳጫሉ፡፡ ምንም ሊያደርጉ ግን አልቻሉም፡፡ ብላተር ባርባራን ጠቀለሉ፡፡ እንደተወራው ከሆነ ኬሰር “ወንድ ብቻውን ነው የሚያለቅስ…” እንደሚባለው ተደብቀው ሳይሆን ሰው ባለበት ስቅስቅ ብለው አለቀሱ፡፡ በሰርጉም አልተገኙም፡፡

አሁን እነብላተር የሉም…የዓለም ዋንጫ ግን አለ፡፡ ትናንትና እና ከትናንት ወዲያ ውድድሩን ሲያጠይሙት የነበሩ የነውጠኝነት፣ የዘረኝነትና የመሳሰሉት ክስተቶች እንዳሉ ሆነው አሁን ደግሞ ፖለቲካ በስፖርቱ ላይ ከሚያስፈልገው በላይ ጫና እያሳደረ ነው፡፡የሩስያ ዓለም ዋንጫም የሚካሄደው በእነዚህ ሁሉ ስጋቶች ተከቦ ነው፡፡

በማኅበረ ሰብ ገጾች ያጋሩ

Submit to FacebookSubmit to Google PlusSubmit to TwitterSubmit to LinkedIn
Sheger 102.1 AudioNow Numbers