• United Bank S.C.

    ሕብረት ባንክ አ.ማ.

  • Slider Two

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Sldier Three

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ሸገር | ወግ

ውሸት ለመናገር አትሻም ምላሴ

እናት ልጇን… 

“ማሙሽ፣ ሂድና ከሸምሱ ሱቅ ስኳር፣ እጣንና፣ ሰንደል ገዝተህልኝ ና፡፡”
“እሺ፣ እማዬ፡፡”

ልጅ ይሄዳል፡፡ ተመልሶ ሲመጣ የያዘው ስኳርና ሰንደሉን ብቻ ነው፡፡ እንባ ህቅ፣ ህቅ ይለዋል፡፡

“እጣንም ግዛ ብዬህ አልነበር እንዴ፣ የት አደረግኸው?”
“እ..እማዬ፣ ልጆቹ ፍራንኩን ነጠቁኝ፡፡” የፓስቴው ዘይት እኮ ገና ሙሉ ለሙሉ ከከንፈሩ አልተጠረገም፡፡

እናት ጭኑ ስር ትገባና ልምዝግ… “ይሄን ውሸት ተው አላልኩህም! እ!... መዋሸት ይለምድብሀል አላልኩም!”

ቁንጥጫ ካልሠራ ቅጣቱ ወደ አለንጋ ‘አፕግሬድ’ ይደረጋል፣ በአለንጋም ካልሆነ ምን ችግር አለው… ያኔ በርበሬ እኮ በልተነውም ስለሚተርፈን እንደዕጣን ነገርም እንጠቀምበት ነበር፡፡

ቅጣቶቹ እንተዋቸውና... ትልቁ ነገር ግን ውሸት መናገር ምን ያሀል አስከፊ እንደነበር የሚያሳይ ነው፡፡ “መዋሸት ያድግብሀል አላልኩህም!” ከማለት የተሻለ ማገረጋገጫ ምን አለ!
እንደ ዘንድሮ ሳይሆን፣ “እከሌ ውሸታም ነው” ከተባለ እኮ መንደር ሙሉ ጣት ሲቀሳሰርበት፣ ከጀርባው ሲንሾካሾክበት ነው የሚውለው፡፡

“እከሊት የለየላት ቀጣፊ ነች፣” ከተባለች በቡናውም፣ በእድር እቃ አጠባውም በምናምኑም ስሟ ሲነሳና ሲወድቅ ነው የሚኖረው፡፡ የዛሬን አያድርገውና ውሸት እንዲህ ያስጠላ ነበር… ጊዜ ተለውጦ ከውሽት ጋር እንዲህ ከመዋደዳችን በፊት! ግን ውሸት ብዙ ነገር እያጠፋ ነው፡፡

የውሸት መግለጫና ማብራሪያ፣ የሀሰት መሀላ፣ የሀሰት ምስክርነት፣ የሀሰት ሰነድ፣ የሀሰት ማስታወቂያ፣ የሀሰት ምርት…ብዙ ነገሮች እየተበላሹ ነው፡፡

እንዲህ ሆኖ ታዲያ ውሸት…ተቀብለነው፣ ተግባብተነው አብረነው የምንኖረው አይነት ነገር እየሆነ ይመስላል፡፡ ከምናምናቸው ነገሮች የማናምናቸው ነገሮች እየበዙ ነው፡፡ እንዲህም ሆኖ “ምን ይደረግ፣ ጊዜው ነው፣ እያልን እናልፋቸዋለን፡፡

“ስሚ ያ የባንኩ ጉረኛ ከሚስቱ ሊፋታ ነው አሉ፡፡”
“በምን አወቅሽ?”
“ሰው ነገረኝ፡፡”
“ማን ነው የነገረሽ?”
“ያቺ ጎረቤቴ ነቻ…”

“ምነው! ምነው! እሷን ሰው ብለሽ የምትልሽን እሺ ብለሽ ትቀበያለሽ! አገር ያወቃት ቀዳዳ አይደለች እንዴ!”

ውሸት እንዲህ ያስጠላ ነበር…ዛሬ፣ ዛሬ ከማስወቀስ ይልቅ እሱ ነው ኖሮን ያወቀበት አስብሎ ኒሻን የሚያስጭን እየሆነ ነው እንጂ!

ውሸት ለመናገር አትሻም ምላሴ
ለእውነት እሞታለሁ አልሳሳም ለነፍሴ

ተብሎም ተዘፍኖ ነበር… ውሸት መናገር ነውር በነበረበት ዘመን፣ እውነተኝነት በያስከብርበት ዘመን፣ “እሱ እኮ የለየለት ቀጣፊ ነው” ከመባል የጠቆረ የስም ጥላሸት ያልነበረበት ዘመን፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ: ውሸት ለመናገር አትሻም ምላሴ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ከሐርላዎች ግፍ ምን እንማራለን…?

ሸገር ልዩ ወሬ፣ ‘ሐርላዎችን ያየ በእንጀራ ግፍ አይሰራም...’

ሐርላ በምስራቅ ኢትዮጵያ በአንድ ወቅት የነበረች ስልጡን ከተማ ነበረች፡፡ ቢያንስ ከ10ኛው ክፍለዘመን ጀምሮ ገናና የነበሩት ሐርላዎች በ16ኛው ክፍለዘመን እንደጠፉ ይነገርላቸዋል፡፡

አርኪዮሎጂስቶች በቅርቡ በቁፋሮ በርካታ ግንባታዎችና ከማዳጋስካር እስከ ቻይና ድረስ የመጡ ጌጣጌጦች የተገኙባት ሐርላ ሚስጥራዊ ነች፡፡ ስለሐርላውያንም በዝርዝር የሚታወቅ ነገር እምብዛም የለም፡፡

በምስራቅ ኢትዮጵያ በስፋት የሚነገረውና ስለሐርላውያን አጠፋፍ የሚገልፀው አፈታሪክ ግን የሐርላውያን መጥፋት ሰበቡ ግፍ ነው ይላል፡፡

አካላቸው ግዙፍ እና እጅግ ሐብታም ነበሩ የሚባሉት ሐርላዎች የመጥፋታቸው ሰበብ በሰርግ ድግሳቸው ላይ እንጀራ አንጥፈው ሰርገኛው በእንጀራው ላይ እየተራመደ እንዲሄድ ማድረጋቸው ነው የሚለው አፈታሪክ በዚህ ሳቢያ ፈጣሪ ተቆጥቶ ምድር ተገልብጣ ዋጠቻቸው ይላል፡፡

ለመሆኑ እውን የእነዚህ ድንገት ከታሪክ ገፅ የጠፉ ጥንታዊ ገናና ሕዝቦች ታሪክ ምን ይሆን ሲል የሸገሩ ወንድሙ ኃይሉ ይህን አጠናቅሯል…

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ዳቦ አዳዩ ብርሃኑ ! – “አዬዬ … ዛሬስ ዳቦዬን የሚወስድልኝ የለም”

በሸገር ልዩ ወሬው ወንድሙ ኃይሉ ላለፉት 4 ዓመታት በየቀኑ ከሌሊቱ 11 ሰዓት እየተነሳ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዳቦዎችን ለነዳያን፣ ለጎዳና ተዳዳሪዎችና ለጎዳና ውሾች ስለሚያድለው ብርሃኑ ያጫውተናል፡፡ባለትዳርና የ2 ልጆች አባት የሆነው ብርሃኑ መርካቶ ውስጥ በድለላና ተዛማጅ ሥራዎች የተሰማራ ነው፡፡

መሳለሚያ አካባቢ ከሚገኝ ዳቦ ቤት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዳቦዎች ገዝቶ በራሱ ነጭ ሚኒባስ እየተዘዋወረ ለችግረኞች ዳቦ የሚያድለው ብርሃኑ ይሄን ካላደረግኩ ቀኑን ደስ ብሎኝ አላሳልፍም ይላል፡፡የብርሃኑን ነጭ ሚኒባስ የጎዳና ውሾችና የጎዳና ተዳዳሪዎች ያውቋታልና ወደ እሷ ይፈጥናሉ፡፡ አንዳንድ ጓደኞቹም በገንዘብ እንደሚግፉት የሚናገረው ብርሃኑ አንዳንድ ቀናት መንገድ ተዘጋግቶ ወይም በሌላ ምክንያት ትንሽ ዘግየት ካለ ነዳያኑ ይቆጡታል ይለናል ወንድሙ…

የበዓል ዕለት ብርሃኑ እንደተለመደው ዳቦውን ይዞ አንድ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ ሲደርስ በበዓል ለነዳያን ምድብ የሚያበሉ ሰዎችን ሲያይ አይይ ዛሬስ ዳቦዬን የሚወስድልኝ የለም ብሎ አዝኖ ነበር ይለናል ወንድሙ…ቢሆንም ግን ነዳያኑ አላሳፈሩትም … “ሁሉንም ጣጥለው ወደ እኔ መጥተው ዳቦዬን ወሰዱ…” 


Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.


አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

“ብዕር ቢሰበርም ይፅፋል…” - ኤደን ገነትና “ሰባራ ብዕር”

ኤደን ገነት ተስፋ አትቆርጥም…

የፈረንሳይ ለጋሲዮኗ ኤደን ገነት የ24 ዓመት ወጣት ናት፡፡ በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ፣ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ በዲግሪ ፕሮግራም ጤና መኮንንነት እየተማረች ሳለ፣ ልትመረቅ አንድ ዓመት ሲቀራት፣ አንድ ችግር ገጠማት፡፡አንዳች ሕመም ጀርባዋን ሰቅዞ ያዛት፡፡ መጀመሪያ ማደካከም፣ ሲቀጥል ማንከስ ባስ ሲልም ፈፅሞ መራመድ የማትችልበት ደረጃ ላይ አደረሳት…ትምህርቷን ለማቋረጥ ተገደደች፡፡

ቢሆንም ግን ፈፅሞ ተስፋ የማትቆርጠው ኤደን ቤት ተመልሳ፣ ልጆች በማስጠናት ገቢዋን እየደጎመች … በተልዕኮ ትምህርት ከቅድስተ ማርያም ዩኒቨርሲቲ በዲግሪ የማኔጅመነትት ትምህርት እየተማረች ልትመረቅ አንድ ሴሚስተር ከግማሽ ብቻ ነው የቀራት የሚለን ኤደን ገነትን ያነጋገራት የሸገሩ ወንድሙ ኃይሉ፣ ኤደን ገነት መፅሐፍም አሳትማለች ይለናል…

ድንገት ሳታስበው የደረሰባትን ችግር አስመልክታ ስንኝ መቋጠር የጀመረችው ኤደን ገነት እነሆ … “ሰባራ ብዕር…” የተሰኘ የግጥም መድብሏን በፈረንሳይ ለጋሲዮን ወጣቶች ትብብርና በብድር አሳትማለች፡፡ ኤደንን ለመደገፍ የተነሳሱት የፈንሳይ ለጋሲዮን ወጣቶችም 1 000 ኮፒ የታተመውን የኤደን ገነትን “ሰባራ ብዕር” የግጥም መድብል በየመንገዱ፣ በየሱቁና በየቡቲኩ በ100 ብር እየሸጡ ነው…

ተጨማሪ ያንብቡ: “ብዕር ቢሰበርም ይፅፋል…” - ኤደን ገነትና “ሰባራ ብዕር”

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ወጣትነት … ሱስና … ዩኒቨርሲቲ

የ12ኛ ክፍል የመሰናዶ ትምህርት ቤት ፈተና ማጠናቀቂያ ዕለት እንደዋዛ በጠጣችው ወይን እና ባጨሰቻት ሲጃራ ሱስን ሀ ብላ የጀመረችው ወጣት … ዩኒቨርሲቲ ስትገባ ደግሞ ለየላት … የ28 ዓመቷ ወጣት የ10 ዓመታት አስከፊ የሱስ ሕይወቷን አስመልክታ ለሸገር ተናግራለች…

ከቤተሰብ ርቃ ከአዲስ አበባ ውጪ ባለ ዩኒቨርሲቲ የተመደበችው ይህች ወጣት ያኔ ሙሉ ለሙሉ በመጠጥ ሱስ ውስጥ መዘፈቋን ትናገራለች፡፡ እሷ እና መሰል ጓደኞቿ የመጠጫ ገንዘብ ለማግኘት ፓርቲ ያዘጋጁ ነበር፡፡ የሱስ ፍላጎትን ማርኪያ ገንዘብ ፍለጋም በእድሜ ገፋ ላሉ ሰዎች ገላን መሸጡ የመጣው ከዚህ በኋላ ነው ስትል የምታስታውሰው ይህች ወጣት፣ የዩኒቨርሲቲ የወንድ ጓደኞቻቸው ገንዘብ ከየትም እንዲያመጡ ስለሚገፋፏቸው ወደዚህ ተግባር ለመግባት ግፊት ሆኖብናል ትላለች፡፡ በዚያ በሱስ በነፈዙበት ወቅት ወሲብ ላይ ምንም አይነት ጥንቃቄ ያደርጉ እንዳልነበር የምትናገረው ይህች ወጣት ሌሎች ወጣቶች ከእሷ ስህተት ይማሩ ዘንድ ታሪኳን ያጋራችን በቅርቡ ዲ ኬ ቲ ኢትዮጵያ አካሂዶት በነበረው የምክክር መድረክ ላይ ነበር…

ከዩኒቨርሲቲ ተመርቃ ከወጣችና ስራ ከጀመረች በኋላም የመጠጥ ሱሷ ጭራሹኑ ባሰባት፡፡ በምሳ ሰዓት መጠጣት አለባት፡፡ ከጓደኞቼ፣ ከቤተሰቦቼ አራራቀኝ፣ ብዙ ነገሬን አሳጣኝ የምትለው የመጠጥ ሱሷ ቀስ በቀስ ከቢራ ወደ ጂን ተዘዋወረ - ሕይወቷ ምስቅልቅሉ ወጣ - ከሰው ራቀች !!

በስተመጨረሻ ከዚህ ሱሷ ለመውጣት የሕክምና እርዳታ እንደሚያስፈልጋት የተረዳችው ይህች ወጣት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒል ስር ወደሚገኘው ድንቅነሽ ማገገሚያ እና ማጎልበቻ ማዕከል አመራች፡፡ ላለፉት 3 ወራት ሕክምና ተደርጎላት ከሱስ እያገገመች ያለችው ወጣት ለሸገሩ ንጋቱ ሙሉ ታሪኳን አጫውታዋለች…

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)
Sheger 102.1 AudioNow Numbers