• United Bank S.C.

    ሕብረት ባንክ አ.ማ.

  • Slider Two

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Sldier Three

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ሸገር | ወግ

ስሜን ያየ!

ዝም ብሎ መተራመስ ምንድነው?
የአዲስ አበባን ውሎ ማወቅ የፈለገ በስራ ቀን ቢሮ መግባቱን ትቶ አንዱ ኢንተርኔት ካፌ ጎራ ይበል፡፡ ለካ ስንት ነገር አምልጦኛልና የሚል ቁጭት ይፈጠርበታል፡፡ ትላንት ሰኞ ግንቦት 26 በእረፍት ስም ቢሮ ሳልገባ ብውል ሀገሪቱን እና ህዝቦቿን ስታዘባቸው ዋልኩ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ከሳምንታት በፊት ባንክ ሄጄ መታወቂያዬን አዩና ሌላ የሚረባ መታወቂያ ካለሽ አምጪ ይሄኛው ሳይታደስ 2 ዓመት ያለፈበት ነው ተባልኩ፡፡ መቼ ወደ ቀበሌ መሄድ እንዳለብኝ የመከረኝ ደህና ዘመድ ስላልነበረኝ ከዛሬ የተሻለ ቀኝ አላገኝም አልኩና ሰኞ ወደ ከሰዓት በኋላ ከቤት ወጣሁ፡፡ አስቸኳይ  ፎቶ ተነሳሁ፡፡(‹አስቸኳይ ፎቶ አለ?› ተብለው ሲጠየቁ ‹አለ ግን ለዛሬ አይደርስም› የሚሉ ፎቶ ቤቶች አሉ ብለው ካሳቁኝ ሳምንት አልሞላውም፡፡ የኔው ከ35 ደቂቃ በኋላ የሚደርስ ነበር) እስከዛው ኢንተርኔት ካፌ ልቆይ ወሰንኩ፡፡ ቤቴ ለፎቶ ቤቱ ይቀርባል፡፡ ኢንተርኔት ካፌው ደግሞ ለፎቶ ቤቱ ይቀርባል፡፡ ከኢንተርኔት ካፌው በቅርብ ርቀት ላይ ውዱ ቀበሌአችን ይገኛል፡፡
ሳላስበው ለአንድ ሰዓት ተኩል አካባቢ በኢንተርኔት ካፌው ስቆይ ሰዎች እየመጡ እንዲህ ይጠይቁ ነበር፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ: ስሜን ያየ!

አስተያየት ይፃፉ (4 Comments)

የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ኢንተርኔት

ዓለም ከ50 ዓመታት በኋላ እንዴት ትሆን?..ይሄ ገሎበላይዜሽን (Globalization) አሁን የምናውቃትን ዓለም የፈጠረውን የዘር፣ የቋንቋ፣ የባህልና ምናልባትም የቀለም ልዩነቶች እያደበዘዛቸው ነው፡፡ በአንጻሩም የአንድ ዓለም…የአንድ ህዝብ…የአንድ ባህል ፍልስፍና እየጠነከረና እየደመቀ ነው፡፡ ይኼም በየቀኑ ኢንተርኔት ስጎለጉል ይበልጥ ይታየኛል፡፡ ኢንተርኔት ሙሉ ለሙሉ ማለት ይቻላል በእንግሊዘኛ ተጀምሮ አሁን ላይ ወደ ሌሎች ቋንቋዎች እየተስፋፋ ቢመጣም አሁንም በ 'ሌሎች' ቋንቋዎችና በእንግሊዘኛ መሃል ያለው የመጠን ልዩነት ግዙፍ ነው፡፡ በመላው ዓለም ከሚነገሩ 6000 በላይ ቋንቋዎች እንግሊዘኛ የአንበሳውን ድርሻ ይዟል በኢንተርኔት፡፡ ለነገሩ መጀመሪያ እኒህ ከ6000 የበለጡ የንግግር ቋንቋዎች የጽሁፍም ቋንቋዎች አለመሆናቸውን ልብ ማለት ያሻል፡፡ ራሳቸው የቋንቋ ባለሙያዎችም ቢሆኑ በቁጥሩ ዙሪያ የተስማሙበት አይደለም፡፡ ይሁንና እኛ ለጨዋታችን እንዲረዳን ከ6000 ቋንቋዎች ግማሹ ያህል የጽሁፍ ቋንቋም ናቸው ብለን እናስብ፡፡ በነገራችን ላይ አንድ ቋንቋ የጽሁፍም ለመሆን የግድ የራሱ ፊደላት እንዲኖሩት አያስፈልግም፡፡ ለምሳሌ ከሃገራችን እንኳ የላቲን ፊደላትን የሚጠቀሙትን የኦሮምኛ እና የሶማሊኛ ቋንቋዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ወደ ኢንተርኔታችን እንመለስ፡፡ ከነዚህ ከ3000 ሺ የበለጡ  ቋንቋዎች እንግሊዘኛ 57 በመቶ ያህሉን ድርሻ ይዟል፡፡ ከዚህ የተረፈውን ደግሞ ራሺያን፣ ጀርመን፣ ስፓኒሽ፣ ቻይኒዝ፣ ፍሬንች፣ ጃፕኒዝ…እያልን መቀጠል እንችላለን፡፡ ቀጥለን ቀጥለን ግን 2900 በላይ የአለም ቋንቋዎች ከ0.1 በመቶ በታች ድርሻ ነው ያላቸው በኢንተርኔት ውስጥ፡፡ ከነዚህ መሃል አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግረኛና ሌሎችም የሃገራችን ቋንቋዎች ይገኛሉ፡፡ ይህ የእንግሊዘኛ ገንኖ መውጣት አሁን አሁን ላይ እየቀነሰ እየመጣ ቢሆንም ያለው ድርሻ ግን እንዲሁ በቀላሉ የሚነጠቅ አይሆንም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ: የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ኢንተርኔት

አስተያየት ይፃፉ (1 Comment)

እንከን አይወጣለትም

የማወራችሁ ስለ 11 አመት ታዳጊ ነው፡፡ የኔ ግምት 8 ወይም 9 ነው፡፡ እሱ 11 ነኝ ስላለኝ ተጠቀምኩት እንጂ፡፡
 
    ከፒያሳ ወደ አዲሱ ገበያ መስመር ላይ በተለያዩ ታክሲዎች ላይ ወያላ ሆኖ ይሠራል፡፡
የመጀመሪያ ቀን ፒያሳ "አዲሱ ገበያ ሰሜን ሆቴል የሞላ የሞላ 2 ሠው"እያለ ደጋግሞ ሲጠራ ይህ ልጅ ወያላ ነው ለማለት ተቸግሬ ነበር፡፡ ታክሲ ውስጥ ያለው ሁሉ በአግራሞት እያየው ከንፈር ይመጣል፡፡
 
     ታዳጊው ከእድሜው በታች በጣም ቀጫጫ ነው፡፡ ጉዞ ጀምረን ገንዘብ ሲሰብሰብ እጁ ዝርዝር ሳንቲሞች ለመያዝ ተቸግሮ አሁንም አሁንም ኪስ ወደ ተሞላች ሱሪው እጁን ይሠዳል፡፡ ድንገት ስራውን ዘንግቶ በታክሲ ካሉት ህፃናት ጋር ይጫወታል፡፡ ደግሞ መለስ ይላል፡፡ ታክሲ ውስጥ ካሉት አብዛኛዎቹ ያላቸውን መልስ ሳይቀበሉ ትተው ወረዱ፡፡ከዛ በኋላ ከአማኑኤል ጋር ደጋግመን ተገናኝተናል፡፡
 
እንዲህ ያለውን አቅምና እድሜን ያላገናዘበ የጉልበት ስራ ለኢትዮጵያ እድሜያቸው ከ5 እስከ 14 የሆኑ 60 በመቶ ህፃናት ይጋሩታል፡፡ያውም በከፋ መንገድ፡፡  
 
     ይህ በአለም የህፃናት ጉልበት ከሚበዘበዝባቸው 10 ፊት አውራሪ የአለም አገሮች ኢትዮጵያን አንዷ  አድርጓታል፡፡
በሒልተን ሆቴል በተዘጋጀ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛን የተመለከተ ስብሠባ ላይ እንድሳተፍ ተጠራሁ፡፡ እንደ ጋዜጠኛ ብዙ ልሠማ ሄድኩ…ግን ብዙ እንድናወራ የሚጠበቅበት ሆኖ አገኘሁት፡፡ ‹‹ቶክሾው›› መሆኑ ነው፡፡
ፕሮግራሙን የሚመራው ጋዜጠኛ ... (አሁን ስም ምን ያደርጋል?) ይህ የሚያክል ትልቅ ሀሳብ በ3 ደቂቃ እንዲገባደድ የሚናገሩትን ጋዜጠኞችና ‹ባለድርሻ አካላት
(የሚመለከታቸው እንደማለት ነው)፤ አፍ አፋቸውን ይላል፡፡ የሚጀመር እንጂ የሚያልቅ ሀሳብ ጠፍቷል፡፡  ባለሙያዎቹ እንዲህ አይነት ጥፋተኞችን ለመቅጣት በቂ ኧረ እንደውም ከዛ በላይ ህግ ወጥቷል ግን ተፈፃሚ አይደለም ይላሉ፡፡ አብዛኛው ሰው ግን የግንዛቤ እጥረት›› የምትለው ሃሳብ ላይ የሙጠኝ ብሎ ይዘምራታል፡፡
 
 ወይ ጣጣ
     ‹‹የግንዛቤ እጥረት የግንዛቤ እጥረት "የግንዛቤ እጥረት"  ይላል፡፡ እንዴት እጅ እጅ ይላል ይህ ቃል? በግንዛቤ እጥረት የተናገሩት ይሆናል ብልን እንለፈው፡፡ እኛ ሀገር ሁሉም ነገር በግንዛቤ እጥረት የመጣ ነው፡፡
 
እድሜያቸው ከ15 አመት በታች የሆኑ ልጆችን ከባባድ ስራ ማሰማራት ያስቀጣል፡፡ በህግ ተደንጓል! አንቀጽ ወጥቶለታል! ወንጀል ነው!
በየቤታችን አንድ ለልጅ አቃፊ፣ አንድ እግር አጣቢ፣ እያልን ህፃናትን ከገጠር ስንመለምል ወይም ሽሮሜዳን ያጥለቀለቁትን የሚታዩና የማይታዮ ህፃናትን ጉልበት ስንበዘብዝ እንታያለን፡፡ ድርጊቱን የሚፈፅሙት እየተጠቀሙበት ነው፡፡ ወጪ ለመቆጠብ፤ የፍላጐት ያህል ጉልበት ለመበዝበዝ፤ ትርፍ ለማጋበስ ይህ ሁሉ ጥቅም ነው፡፡
ሲጋራ ማጨስ እንደሚጐዳ አጫሹ ያወቀዋል ግን ያደርገዋል፡፡ ተያያዥ የሆነ  አካባቢያዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሊኖርውም፣ ይህ ሰው የሚጐዳው ራሱን መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህን አጫሽ የግንዛቤ እጥረት አለበት ማለት ይቻል ይሆናል፡፡ በሌሎች ህይወትና ሬሳ ላይ ቤቱን የሚያቆምና ህንፃ የሚሠራን እንዴት ግንዛቤ  አጥሮት ነው ተብሎ "እንከን አይወጣለትም"የተባለ ህግ ሳይፈፀም ይቀራል?
አታምርሪ እንደምትሉኝ አውቃለሁ፡፡ ግን ልቀጥል ትንሽ እድል ስጡኝ፡፡
ሌላው ተደጋግሞ ሲነሳ የነበረው ምን መሰላችሁ? "ህብረተሰቡን ለወንጀል ተባባሪ ሆነ ጥፋተኛን አያጋልጥም" የሚል ወቀሳ ነው››
ሀገር ያወቀው ፀሃይ የሞቀው የአደባባይ ጉዳይ ከህዝቤ ካልሠማሁ አላምንም የሚል ከአይኑ ይልቅ ህዝቡን የሚያምን ብቸኛ መንግስት የኛ ሃገሩ ይመስለኛል፡፡
 
ስለ ኢትዮጵያ ማውራት ይቅር .... አዲስ አበባ ላይ ሰብሰብ እንበል፡፡ ስለሽሮ ሜዳዎቹ ህፃናትም አናንሳ .... በየቤቱ ተጫውተው ሳይጠግቡ አጫዋች የሆኑ፣ ቤታችንን ቀጥ አድርገው የሚያስተዳድሩ፣ የንዴትና ብስጭታችን ማራገፊያ የሆኑ ህፃናት ጉዳይንም ተዉት፡፡  
..... የወያላዎቹንም ህፃናት ጉዳይ አታንሱት፡፡ ሁሉንም እርሱት፡፡

ብር ይዞ ይመጣል

ከአመታት በፊት በአንድ አጋጣሚ በአውሮጳ በአንዱ ከተማ ለጥቂት ቀናት ያገኘነው ወጣት እጅግ ለጋስ በሆነው በአገራችን ልጆች መስተንግዶ ካስተናገደን በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ ዶላሮች አውጥቶ ለአባቴ ስጡልኝ አለን፡፡ የወጣቱን ልጅ ኑሮና እጅግ የበረታ የሥራ ድካም በሁለት ቀን ዕድሜ ጥሩ አድርገን አይተነው ነበርና ምነው አይበዛም? አንተ እዚህ አልተመቸህ? አልነው በማያገባን ገብተን፡፡ አባቴ የአሥራ ሁለተኛ ክፍል ውጤት ጥሩ ስላልመጣልኝ ለዓመታት እቤት ውስጥ እውል ነበርና፤ እግቢያችን ውስጥ ያለውን የኰክ ዛፍ እያሳየ “አንተና ይሄ የኮክ ዛፍ አንድ ናችሁ አታፈሩም”! ይለኝ ስለነበር እዚህ መጥቼ ያጠራቀምኩትን የመጀመሪያ ገንዘብ ማፍራቴን እንዲያይ መላኬ ነው፡፡ ማለቱን መቼም አልረሣውም ፡፡
 
   በየአገሩ የተበተኑት ኢትዮጵያውያን ከያሉበት አገር ወደ አገር ቤት ገንዘብ ሲልኩ ስሰማም ሆነ ሳይ የዚያ የወጣት አነጋገር በሃሳቤ ይመጣል፡፡ በየጊዜው የሞራል ስብራት ያደረስንባቸው ልጆቻችን የልጅነት ወዛቸውንና ጉልበታቸውን እያፈሰሱ ያላቸውን ጥሪት እየላኩ የሞራል ስብራታቸውን እየጠገኑ፣ ቁጭታቸውን እየተወጡ ይሆን?
 
   የአለም ባንክ የቅርብ  ጊዜ መረጃ 215 ሚሊዮን ሰዎች ከትውልድ አገራቸው ውጪ ይኖራሉ ይላል፡፡ ከእነዚህ ሰዎች ወደየትውልድ አገራቸው የሚላከው ገንዘብ ከተለያዩ አገሮች በልማት ስም ከሚሰጠው ዕርዳታ በሦስት እጅ ይበልጣልም ይላል፡፡ ይሄም በገንዘብ ሲሰላ በ2011 ብቻ 372 ቢሊዮን ዶላር በ2012 530 ቢሊዮን እንደደረሰ የአለም ባንክ ሪፖርት ያመለክታል፡፡ ቁጥሩም በየዓመቱ እየጨመረ እንደሚሄድ ያሳያል፡፡ ይሄ እንግዲህ እንደ አለም ባንክ መረጃ፤ ፀሐይ ሞቆት አገር አውቆት በባንክ በኩል የሚካሄደውን የገንዘብ ዝውውር እንጂ የአድርሱልኙንና ሌላ ሌላውን አይጨምርም፡፡
 
 
  ይሄን መረጃ መነሻ አድርገው የኤኮኖሚ ባለሙያዎች ከበለፀጉ አገሮች ከሚላከው የገንዘብ እርዳታ ይልቅ በየአገሩ ኗሪ ከሆኑ ስደተኞች የሚላከው ገንዘብ ከዕርዳታው ድጐማ በሦስት እጥፍ የሚበልጥ ከሆነ የትኛው አማራጭ ይበጃል? እያሉ ነው፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ የሚበጀው በብዙ የእርዳታ ውለታ የማይታሠረው የአገር ልጆች በፈቃዳቸው የሚልኩት ገንዘብ ይመስለኛል፡፡

ቁጭ በል-ካ በመሬት

ጊዜው ትንሽ ረዘም ብሏል የደርግ ጊዜ በመባል የሚታወቀው ወቅት ነው፡፡ ሁኔታው የተፈጠረው ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ድሬዳዋ በሚሄድ ባቡር ላይ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ከአዲስ አበባ ድሬዳዋ ጅቡቲ መንገደኛ ይዞ የሚጓዝ ባቡር ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም ሲልም የማታው ባቡር መኘታም ነበረው፡፡ ለማንኛውም መነሻቸውን ከአዲስ አበባ ያደረጉ ተሳፋሪዎች በዋዜማው በአዲስ አበባው ላጋር ባቡር ጣቢያ ቲኬታቸውን ረጅም ሠልፍ ተሰልፈው ቆርጠው በመሄጃቸው ቀን ሌሊት በ11 ሰዓት ሄደው ተሣፍረው ናዝሬት ደረሱ፡፡  የትዕዩንቱ ባለታሪኮች አንዲት ሴትና ሕፃን ልጇ፣ አንድ ወጣት፣ ሌሎች ተሣፋሪዎች፣ እንዲሁም ፈንጠር ብለው የተቀመጡ የአደሬ አዛውንት ናቸው፡፡ ወጣቱና እመጫቷ አንድ ወንበር የተጋሩ ቢሆንም ወጣቱ ለእመጫቷ ከነልጇ እንዲመቻት ወንበሩን ለቆ በፉርጐው በራፍ ላይ ቆሟል፡፡ ባቡሩ ናዝሬት ላይ ሲቆም አንድ ተሣፋሪ በዚህኛው ፉርጐ ይገባል፡፡ ዙሪያ ገባውን ይመለከታል፡፡ ትርፍ ወንበር ያጣል፡፡ ትርፍ ነው ብሎ የገመተውን ቦታ እናቲቱና ልጅ የያዙትን
 
                  “ልጅሽን እቀፊና እኔ ወንበሩ ላይ ልቀመጥ” ይላል፡፡
    በዚህ ጊዜ ቦታውን የለቀቀው ወጣት ፈጠን ብሎ ጠጋ ይልና “እኔ እንዲመቻት ብዬ ነው የለቀቀሁላት እንጂ ለመቀመጥማ ቦታው የኔ ነው ይላል፡፡ አንድ ሁለት ሲባባሉ ጠቡ የሁሉም የባቡር ተሣፋሪ ጉዳይ ይሆናል፡፡ ተሣፋሪው ግለሰብ በየዘመኑ በአገራችን ብቅ የሚሉና “የዘመኑ ሰው” በመባል የሚታወቁ ልበ ሙሉዎች አንዱ መሆኑን በጐኑ የታጠቀው መሣሪያ ኮቱን ገለጥ አድርጐ በማሳየት በሕብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ቦታ በቃል ብቻ ሳይሆን በድርጊት ያሳያል፡፡ አብዛኛው ገላጋይ ድምፁን እየቀነሠ ይሄዳል፡፡ ፍጥጫው ባለወንበሩ ወጣት፣ የሕፃኑ እናትና በባለ ሽጉጡ ልበ ሙሉ መካከል ይጦፋል፡፡ እስካሁን ቃላቻውን ያልሰጡት በመስኮት ወሬ እያዩ ጥርሳቸውን የሚፍቁት አዛውንት “የኔ ወንድም” ብለው ጉሮሮአቸውን አጥርተው በጉዳዩ ለመጀመሪያ ጊዜ ጣልቃ ይገባሉ፡፡
 
                        “እስቲ ና ወዲህም” ይላሉ፡፡
Sheger 102.1 AudioNow Numbers