• Slider One

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Slider Two

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Sldier Three

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ታሪክን የኋሊት: ህዳር 03,2006

ህዳር 03,2006

የ20ኛው ክፍለ ዘመን የግራ ክንፈኞች ፖለቲካዊ ጉዳይ ሲነሳ ሊዮን ትሮትስኪም አብሮ ይነሳል፡፡ከቮልሼቪኮቹ መሪ ቭላድሚር ኤሊች ሌኒን ጋር በሚያሳምነው እያመነ የማያምንበትን ፊት ለፊት እየተቃወመ በስምምነትም በልዩነትም ሠርቷል፡፡ ራሱን የሌኒን አልጋ ወራሽ ካደረገው ጆሴፍ ስታሊን ፍፀማዊ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ጋር ስምምነት አልነበረውም፡፡ ሊዮን ትሮትስኪ የጆሴፍ ስታሊንን ሴራና ደባ መቋቋም አልቻለም፡፡ ስታሊን በግራ ክንፈኞቹ ፖለቲካ የገዘፈ ስም ታላቅ ምሁራዊ ተንታኝና የንድፈ ኃሳብ ቀማሪውን ሊዮን ትሮትስኪን ከቮልሼቪክ የኮሚኒስቶች የፖለቲካ ማህበሩ ከእንግዲህ ከኛ ጋር ጉዳይ የለህም ብሎ ያባረረው የዛሬ 86 ዓመት በዛሬዋ እለት ነበር፡፡የሩሲያ ሶሻል ዲሞክራቶች የፖለቲካ ማህበር ፖለቲከኞች ኃሳባቸው ለየቅል ሲሆን ለሁለት ተከፈሉ፡፡በሌኒን የሚመሩት ቮልሼቪኮች ተሠኙ፡፡ ትሮትስኪ ሜንሼቪክ ከተሠኙት ጋር ሆነ፡፡

ኃላም ወደነሌኒን መጣ፡፡
በቮልሼቪኮች የተመራው የጥቅምት አብዮት አፄያዊውን ስርዓተ ሲያስወግድ ትሮትስኪ የጦር ሚኒስትር ሆኖ ተሰየመ፡፡
የጦር ሠራዊቱና የባሕር ኃይሉ የበላይ ሆነ፡፡ በታሪክ ቀዩ ጦር የተሠኘውን የሶቪየት ሠራዊት በሁለት እግሩ አቁመው፡፡ ብዙም ሳይዛገይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም ሆኖ ሠርቷል፡፡
ከሌኒን ሞት በኋላ በእግሩ የተተካው ጆሴፍ ስታሊን ትሮትስኪንና ሌሎች ሻል ሻል ምሁራንና ንድፈ ኃሳብ ቀማሪዎችን ጥርስ ነከሰባቸው፡፡  
በሴራው ወጥመድ ውስጥ ከተታቸው፡፡

ታሪክን የኋሊት: ህዳር 04,2006

ህዳር 04,2006
ኔቫዶ ዴላ ሩዊዝ ከጥንት ጀምሮ የኮሎምቢያ ክፉ ጠላቷ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ኔቫዶ ዴላ ሩዊዝ አደገኛ እሳት ገሞራ ነው፡፡ በየዘመኑ በየጊዜው በአካባቢው ጥፋት ሲያደርስ  ኖሯል፡፡ የአሁንም የወደፊትም ስጋትነቱ አልቀነሰም፡፡ የሩቁን ትተን የቅርቡን ብንጠቅስ እንኳ ኔቫዶ ዴል ሩዊዝ ፈንድቶ አካባቢውን በማዳረስ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የጨረሰውና የከፋ ቁሳዊ ውድመት ያደረሰው የዛሬ 28 ዓመት በዛሬዋ እለት ነው፡፡ የኮሎምቢያ ጠላት የሆነው ኒቫዶ ዴላ ሩዊዝ ከርዕሠ ከተማዋ ቦጐታ በስተምዕራብ በ129 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኙ ሠንሰላታማ ተራሮች ስር ተኝቶ ሲንፈቀፈቅ ሲከፋም እየፈነዳ ጥፋት ሲያደርስ በርካታ ዘመናትን አስቆጥሯል፡፡  
የዛሬ 28 ዓመት በዛሬዋ እለት የፈነዳው እሳተ ገሞራ ሰማይ ምድሩን በቁጣው አዳረሰ፡፡
የእሳተ ገሞራው ትፍና አመድ ሽቅብ ወደ ሰማይ እስከ 30 ኪሎ ሜትር ድረስ ጐነ፡፡
የእሳት ትፍ አመድና ቅላጩ 35 ሚሊዮን ቶን እንደሚጠጋ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
ከዚህ ውስጥ ሌላው ሌላውን ሳይጨምር 700 ሺህ ቶኑ ሰልፈር ዳይ ኦክሳይድ የተሰኘው መርዛማ ንጥረ ነገር ነው፡፡

ታሪክን የኋሊት: ህዳር 02,2006

ህዳር 02,2006

በፍልስጤማውያን የነፃነት ትግል ታላቅ አሻራቸውን ያኖሩት ያሴር አረፋት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የዛሬ 9 ዓመት በዛሬዋ እለት ነበር፡፡ አራፋት ከለጋ ወጣትነታቸው አንስቶ ራሳቸውን የፍልስጤም ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ እንዲወስን ያልሆኑት ፤ ያላደረጉት የለም፡፡የፍልስጤም ነፃ አውጭ ድርድት /PLO/ የትጥቅና የፖለቲካ አንጃ የሆነውን የፋታህ ንቅናቄ በመመሥረት ከእሥራኤል ጋር በጦር መሣሪያ ሲተጋተጉ በፖለቲካ ሲተናነቁ ኖረዋል፡፡ዓላማቸውን ዳር ለማድረስ ብዙ ላይ ታች ብለዋል፡፡ ስደትን ደጋግመውታል፡፡እሥርን አይተውታል፡፡  የቁም እሥር ተደጋግሞባቸዋል፡፡አንዱ ሲያቀርባቸው ሌላው ፊቱን አዙሮባቸዋል፡፡ ብዙ መከራና ብዙ ወጣ ወረድ ተፈራርቆባቸዋል፡፡ነፃይቱን ፍልስጤም ለማየት የነበራቸውን ሕልም ዕውን ለማድረግ ዕድሜ ዘመናቸውን ሰውተዋል፡፡ከ20 ዓመታት በፊት የተፈረመው የኦስሎው ስምምነት ሕልማቸውን ወደ ዕውንነት አቅርቦት ነበር፡፡
                                                         
የኦስሎው ስምምነት መሬት ለሰላም ተባለ፡፡
ከእሥራኤል ጋር ቅርሾ ፣ ጠላትነቱና ቁርቁሶው ማብቃቱን ጠየቀ፡፡
ፍልስጤምን ደረጃ በደረጃ ወደ ነፃ አገርነት የሚያሸጋግረውን መሠረት ጣለ፡፡
ለዚህም ፍልስጤማውያን የከፊል ራስ ገዝ የአስተዳደር መብት አገኙ፡፡
የፍልስጤም ነፃ አውጭ ድርጅት /PLO/ የእስራኤልን ሕልውና በይፋ አውቃለሁ አለ፡፡
እስራኤልም ለPLO እውቅና ሰጠችው፡፡

ታሪክን የኋሊት: ጥቅምት 29,2006

ጥቅምት 29,2006
በጀርመን የናዚዎቹ መሪ አዶልፍ ሂትለር ዓለምን ወደ ጦርነት ሲመራና  ሊያንደረድራት በአዕምሮው ክፉ ኃሳብ ፀንሶ ከተነሳበት ጊዜ አንስቶ ከነ ክፉ ኃሳቡ እንዲጠፋ የበረከቱ የግድያ ሙከራዎች ተደርገውበታል፡፡ ከሙከራዎቹ አንዱ በሙኒክ የተቃጣበት የዛሬ 74 ዓመት በዛሬዋ እለት ነበር፡፡ ሂለትር በሙከራው ወቅት በሙኒኩ አዳራሽ የተገኘው ከዚያን ጊዜ 16 ዓመታት ቀደም ብሎ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ያካሄደበትን 16ኛ ዓመት ከጥፋት እድምተኞቹና ደቀ መዝሙሮቹ ጋር ለማክበር ነበር፡፡ ከዚያ በፊት ሲያደርገው እንደነበረው ሁሉ በቀስቃሽ ስብከቱ ስለ ወደፊቱ እኩይ ዓለማው ስለጀርመን የታላቆች ታላቅነት ሰበከ፡፡ ደስኮረ፡፡ በዚህን ጊዜ በአዳራሹ አስቀድሞ የተጠመደው ቦንብ መፈንጃው ጊዜ ተቃርቦ ሰዓቱ ጢቅ ጢቅ እያለ ነበር፡፡

በጥብቅ የጊዜ ሰሌዳ ከወዲያ ወዲህ ይል የነበረው ሂትለር ንግግሩን ገትቶ ለሚጠብቀው የሽቱትጋርት ጉዞ አዳራሹን ለቆ እንዲወጣ በአጃቢዎቹና ረዳቶቹ ምልክት ተሰጠው፡፡

ሂትለር በአጅብ ተጉዞ ባቡር ጣቢያ እንዲደረሰ ንግግር ያደረገበት አዳራሽ በ12 ደቂቃ ልዩነት በፈንጂ መጐኑ ተሠማ፡፡

በአደጋው ስምንት ሰዎች ተገደሉ፡፡ 60 ያህሉ ደግሞ ክፉኛ ቆሰሉ፡፡

ፈንጂውን አጠመደ የተባለው ጆርግ ኢለር የተባለው ጦርነት ተቃዋሚ ግለሰብ ነው ይባላል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ...

አስተያየት ይፃፉ (1 Comment)

ታሪክን የኋሊት: ጥቅምት 28,2006

ጥቅምት 28,2006
ዶክተር ሪቻርድ ሶርጌይ ከቀንደኛዎቹ የሶቪየት ሰላዮች አንዱ ተደርጐ ይቆጠራል፡፡ ሰላዩ በ2ኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ለዓመታት የጃፓንንና የጦር ተባባሪዎቿን መረጃ እያነፈነፈና እየመነተፈ ለሞስኮ ሲያቀብላት ቆየ፡፡ዶክተር ሶርጌይ በጃፓኖች ተነቅቶበት ከተያዘ በኋላ በስቅላት የተቀጣው የዛሬ 69 ዓመት በዛሬዋ እለት ነበር፡፡ ሶርጌ ወደ ለየለት የሶቪየት ሰላይነት ከመምጣቱ አስቀድሞ በ1ኛው የዓለም ጦርነት በጀርመን ሠራዊት ውስጥ በውትድርና አገልግሏል፡፡ ከጦርነቱ በኋላ ከሃምቡርግ ዩኒቨርስቲ በዶክትሬት ዲግሪ የተመረቀው ሪቻርድ ሶርጌ በ1920ዎቹ መጀመሪያ በሚስጥር ወደ ሶቪየቶች ገባ፡፡ የስለላውን ድርጅት ተቀላቀለ፡፡ የቅድሚያ የሰላይነት ተልዕኮውን በቻይና ተወጣ፡፡

ከቻይና ተልዕኮው በኋላ ለፍራንክፈርት ዛይቱንግ መፅሔት በመስራት ለስለላ ስራው እንዲመቸው የናዚ ፓርቲ አባል ሆነ፡፡

በፍራንክፈርት ዛይቱንግ ጋዜጠኝነቱ ዝነኛና ስመ-ገናና እየሆነ የመጣው ሶርጌ በዚሁ ሙያ አዘጋጁ  ወደ ጃፓን ቶኪዮ እንዲልከው ጠየቀ፡፡
በጥያቄውም መሠረት አዘጋጁ የሰርጌን ጥያቄ ለመመለስ አላመነታም፡፡
በመፅሔቱ ዓለም አቀፍ ወሬ አቀባይነት በቶኪዮ እንዲመደብ አደረገው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ...

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)
Leza Vote Banner
Sheger 102.1 AudioNow Numbers