• Slider One

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Slider Two

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Sldier Three

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ነሐሴ 12, 2005:ታሪክን የኋሊት

ነሐሴ 12, 2005

ላቲቪያ ለበርካታ ምዕተ ዓመት በሩሲያ ኃላም በሶቪየት ህብረት ተፅዕኖ ስር ቆይታ ነፃነቷን ያወጀችው የዛሬ 22 ዓመት በዛሬዋ እለት ነው፡፡ላቲቪያ እንደ ጐረቤቶቿ ኢስቶኒያና ሊትዌንያ ከ200 ዓመታት በላይ በሩሲያ የተፅዕኖ ክልልነትና ቅኝነት ቆይታለች፡፡ በ1ኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ሩሲያ ከጀርመን ጋር ውጊያ ላይ በነበረችበት ክፍተት ባጋጠማት ምቹ ሁኔታ ከ94 ዓመታት በፊት ነፃነቷን አወጀች፡፡ ይሁንና የዚያን ጊዜ የላቲቪያ ነፃነት ሩቅ ሊጓዝ አልቻለም፡፡ የ2ኛው የዓለም ጦርነት መፈንዳት በላቲቪያ ነፃነት ላይ ፈተና ጋረጠባት፡፡ ናዚዎች ፖላንድን በመውረር የ2ኛው የዓለም ጦርነት ጅማሬ ከመሆኑ 1 ሳምንት አስቀድሞ በጀርመንና የሶቪየት ህብረት መካከል ሚስጥራዊ ስምምነት ተደረሰ፡፡

ነሐሴ 10, 2005:ታሪክን የኋሊት

ነሐሴ 10, 2005

አውሮፕላን የተፈለሰፈው በ20ኛ ክፍል ዘመን መጀመሪያ ነው፡፡ አውሮፕላን ከመፈልሰፉ ብዙም ሳይዘገይ ቴክኖሎጂውን ለውድድር ዓላማ የማዋል ሙከራዎች ነበሩ፡፡ የውድድር ዓላማ ኖሯቸው ከተዘጋጁት የአውሮፕላን በረራ ውድድሮች የዶል ውድድር የሚባለው አንዱ ነው፡፡ከተወዳዳሪዎቹ አብዛኞቹ ክፉ እጣ የገጠማቸው የዛሬ 86 ዓመት በዛሬዋ እለት ነበር፡፡ ውድድሩ ከሰሜናዊ ካሊፎርኒያ እስከ ሃዋይ የሚዘልቀውን 3 ሺ 870 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ነበር፡፡ የአትላንቲክ ውቅያኖስን ስለሚያቋርጥም የትራስ አትላንቲክ ውድድር በመባልም ይታወቃል፡፡ከኦክላንድ ካሊፎርኒያ እስከ ሃዋይ ሆኖሉሉ ለተደረገው ለዚህ አትላንቲክ አቋራጭ የበረራ ውድድር እስከ 18 አውሮፕላኖች በተፎካከሪነት ተመዘገቡ፡፡ ከመካከላቸውም አስራ አንዱ  መወዳደር የሚያስችላቸውን ማረጋገጫ አገኙ፡፡
ከዚህ ውድድር ከጥቂት ወሮች አስቀድሞ ቻርልስ ሊንድበርግ በተሳካ ሁኔታ ይሄን ርቀት መሸፈኑ ለውድድሩ መነቃቂያ ነበር፡፡
ጀምስ ዶል የተባለው የሐዋይ ከበርቴ ለውድድሩ የማበረታቻ ሽልማት የሚውል  35 ሺህ ዶላር  መደበ፡፡ 1ኛ ለሚወጣ 25 ሺህ ዶላር፤ 2ኛ ሆኖ ለሚያጠናቅቅ 10 ሺህ ዶላር ሽልማቱ አብራሪዎቹን ሳባቸው፡፡

ነሐሴ 09, 2005:ታሪክን የኋሊት

ነሐሴ 09, 2005

የፓናማ ቦይ በካሪቢያን ቀጠና ሰው ሰራሽ የመርከቦች መተላለፊያ መስመር ነው፡፡የሰላማዊና የአትላንቲክ ውቂያኖሶችን የሚገናኝና በአካባቢው  የመርከቦች ማቋረጫና የሰሜንና ደቡብ አሜሪካ መገናኛ ነው፡፡የፓናማ ቦይ ቁፋሮና ግንባታው ተጠናቆ ለመርከቦች ምልልስ ክፍት ከሆነ ዛሬ ልክ 99ኛ ዓመቱን ደፈነ፡፡82 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው ቦይ የሀገሪቱን የየብስ አካል በመክፈል  ለመርከቦች መመላለሻነት ለመብቃት የ31 ዓመታት የግንባታ ጥረት ጠይቋል፡፡ከቦዩ መቀደድ በፊት በአካባቢው መርከቦች እንዲህ እንዳሁኑ አቋራጭ ሳይኖራቸው ካሻቸው ስፍራ ለመድረስ በላቲን አሜሪካ ደቡባዊ ጫፍ ዙሪያ ጥምጥም መጓዝ ያስፈልጋቸው ነበር፡፡

የቦዩ መቀደድ ጊዜውንም የቦታ ርቀቱንም ጐምዶ አስቀርቷል፡፡የቦዩ መንገባት በቦታ ርቀት ሲለካ መርከቦች 13 ሺህ ኪሎ ሜትር እንዲቀንሱ አስችሏል፡፡ከአትላንቲክ ወደ ሰላማዊ ውቅያኖስና በተቃራኒው የሚደረገውን የምልልስ ጊዜ በግማሽ ቀንሶታል፡፡የፓናማ ቦይ መጀመሪያ በኮሎምቢያ ከዚያም በፈረንሳዮች ቀጥሎም በአሜሪካውያን ይዞታ ስር ቆይቷል፡፡

ሐምሌ 16,2005:ታሪክን የኋሊት

ሐምሌ 16,2005

በግብፅ ከ2ኛው የዓለም ጦርነት በኋላ እንደ ብዙዎቹ የዓለማችንም ሆነ የዓረቡ ክፍል ለውጥ የሚያሻቸው የበረከቱ ፖከቲካዊ ምጣኔ ሐብታዊና ማህበራዊ ችግሮች ተንሠራፍተውባት ነበር፡፡ ለውጥ አስፈለገ፡፡ የንጉስ ፋሩቅ አገዛዝ ለዚህ ለውጥ አቅሙም፤ፈቃደኝነቱም ችሎታውም አልነበረወም፡፡ በዛ ላይ እስራኤል እንደ ሀገር እንደተመሠረተች በጐርጐሮሳዊው የዘመን ቆጠራ በ1948 በተካሄደው የአረቦችና የእስራኤል ጦርነት በግብፅ ጦር ላይ የደረሰው ሽንፈት ሐፍረትም ፈጠረ፡፡ የነፃው መኮንኖች ንቅናቄ የተሠኘው የመኮንኖች ስብስብ በለውጥ አራማጅነት ብቅ አለ፡፡ የለውጥ ውጥኑን ኃላ ላይ በዓረቡ ዓለም እንደ ጀግና መሪና ተራማጅ አስተሳስብ አቀንቃኝ የተቆጠሩት ጋማል አብድልናሰር ፈር አስያዙት፡፡

መኮንኖቹ የንጉስ ፋሩቅን መንግስት አሽቀነጠሩት፡፡ የግብፅ አብዮት ተባለ፡፡ ይሄ ከሆነ ዛሬ ልክ 61ኛ ዓመቱን ደፈነ፡፡ የአብዮቱ አውታር ዋነኛ ዘዋሪ አድራጊ ፈጣሪው ኮሎኔል ጋማል አብድል ናስር ቢሆኑም ገልባጮቹ መኮንኖች ጄኔራል ሙሐመድ ናጊብን ወደ መድረኩ ፊት ለፊት አመጧቸው፡፡ ግብፅ ሪፖብሊካዊት፤ ናጊብ ደግሞ ፕሬዝዳንት ሆኑ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ፕሬዘዳንት ናጊብ በተግባር የአብዮቱ መሪ ከነበሩት ናስር ጋር በአመራር ዘይቤ አለመግባባት ፈጠሩ፡፡ 

ሐምሌ 25, 2005:ታሪክን የኋሊት

ሐምሌ 25, 2005

ከ99 ዓመት በፊት አውሮፓ የጦርነት ዳመና አንዣቦባት ነበር፡፡ ታላላቆቹ ሀገሮች የጥቅም፣የገዢነት ስሜትና የተፅዕኖ አሳዳሪነት ፉክክራቸው ጣራ ነካ፡፡ በቡድን በቡድን ጐራ ለዩ፡፡ ሽርክና ፈጠሩ፡፡

ጀርመን፣ ኦስትሪያ ሐንጋሪ፣ የቱርክ አቶማን ግዛትና ቡልጋሪያ በአንድ ወገን ሆኑ፡፡ ፈረንሳይ፣ ብሪታንያና ሩሲያ በሌላው ወገን ተሰለፉ፡፡ እነዚህ ዋነኞቹ ቢሆኑም ሁለቱም ጐራዎች ሌሎች ትናንሽ መንግስታትን በአጫፋሪነት አሠለፉ፡፡ ቅራኔው ከረረ ተካረረ፡፡

እያበጠ እያበጠ መጥቶም መፈንጃው ተቃረበ፡፡ እንደጐርጐሮሳዊው የዘመን አቆጣጠር በሰኔ መጨረሻ 1914 የኦስትሪያ ሐንጋሪው አልጋወራሽ መስፍን ፍራንዝ ፈርዲናንድ ሰራይቮ ውስጥ በሰርብ ብሔረተኛ ተገደለ፡፡ ለጦርነቱ ዋነኛው ምክንያት ባይሆንም ጥሩ ሰበብ ሆነ፡፡ ኦስትሪያ ሐንጋሪ በሰርቢያ ላይ ጦርነት አወጀች፡፡ የአንደኛው የዓለም ጦርነት ፊሽካ ተነፋ፡፡ ይሄ የሆነው የዛሬ 99 ዓመት በዛሬዋ እለት ነበር፡፡ ጀርመን የሰርቢያ አጋር በሆነችው ሩሲያ ላይ ሩሲያም በጀርመን ላይ ጦርነት አወጁ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ...

አስተያየት ይፃፉ (1 Comment)
Sheger 102.1 AudioNow Numbers