• Slider One

  የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

 • Slider Two

  የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

 • Sldier Three

  የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ሸገር ወሬዎች እና ልዩ ወሬዎች

ከእንግዲህ በኋላ የተሰሩ መንገዶችና ሌሎች የመሠረተ ልማቶች በተሰሩበት ቅፅበት ባለመናበብ ምክንያት የሚፈርሱበት ምክንያት አይኖርም ተባለ

ከእንግዲህ በኋላ የተሰሩ መንገዶችና ሌሎች የመሠረተ ልማቶች በተሰሩበት ቅፅበት ባለመናበብ ምክንያት የሚፈርሱበት ምክንያት አይኖርም ተባለ፡፡ይህን ያሉት በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በቅርቡ ውሃን፣ ቴሌን፣ መብራትንና መንገዶችን ተናበው እንዲሰሩ የሀገርንና የህዝብን ገንዘብ በግዴለሽነት እንዳያባክኑ የተቋቋመው የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይሉ ወልደሥላሴ ናቸው፡፡አቶ ኃይሉ አደረጃጀትና መመሪያ ከወጡለት በኋላ በቀጣይ ዓመት እየተናበቡ እንዲሰሩ ይደረጋል ብለዋል፡፡

አንዳንድ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችና ገንቢዎች በፌዴራሉ መንግሥት ሥር ያሉ ናቸው ያሉት አቶ ኃይሉ ከከተማ መስተዳድሩ ጋር ተቀናጅተው የሚሰሩበትን መንገድ እናጤነዋለን ብለዋል፡፡በተለያዩ የወሬ ጊዜያችን በሰራናቸው ወሬዎች አንዱ የሰራውን ሥራ አጠናቆ እቃውን ሳይሰበስብ ሌላኛው እየቆፈረው ይህም ነዋሪዎችን ለአካል ጉዳት፣ ለትራንስፖርት እጥረት፣ ለውሃ፣ ለመብራትና ለተለያዩ አገልግሎቶች ችግር ሲያጋልጡት መክረማቸውን አውርተናል፡፡

እንደ አዲሱ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ምክትል ኃላፊ ከእንግዲህ ካለፈቃድ በየፊናቸው ያ አይደረግም ተብሏል፡፡በተለይ መብራት፣ ውሃ፣ መንገድና ቴሌ አንዱ የሰራውን ሌላኛው ሲያፈርሰውና ሀገርን ለሌላ ወጪ ሲዳርግ ተመልክተናል፡፡አሁን ግን ፈቃድ ወስደው ሲፀድቅላቸው ቁጥጥር ተደርጎባቸው ይተገበራሉ አሁን ባይፀድቅም በአዋጅ ደረጃ አለ ብለዋል ምክትል ኃላፊው አቶ ኃይሉ፡፡

ለእግረኛ ትኩረት የሚሰጥ ሰፋፊ የልማት ሥራዎችን ያካተተ መዋቅራዊ ፕላን መዘጋጀቱን የተናገሩት ምክትል ኃላፊው እነዚህ ተቋማት ተናበው፣ ተግባብተው እንዲሰሩ በማስፈለጉ ባለሥልጣኑ መቋቋሙን ለሸገር ተናግረዋል፡፡

ምሥክር አወል

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የቻይና ኤግዚም ባንክ የሰሜን አዲስ አበባን የውሃ ችግር ለመቀነስ እንዲቻል የገንዘብ ብድር ሰጠ ተባለ

የቻይና ኤግዚም ባንክ የሰሜን አዲስ አበባን የውሃ ችግር ለመቀነስ እንዲቻል የገንዘብ ብድር ሰጠ ተባለ፡፡ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ እሥጢፋኖስ ብሥራት ዛሬ ለሸገር ሲናገሩ የቻይና ኤግዚም ባንክ የ146 ሚሊየን ዶላር ብድር የሰጠ ሲሆን ገንዘቡ ለገርቢ ግድብ ግንባታ ይውላል ብለዋል፡፡

በሌላ የውሃ ወሬ የኩዬ ፈቼ ቂሊንጦ ፕሮጀክት 50 ሺ ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ የሚያመነጭ ሲሆን በታህሣስ 2010 ተጠናቆ ሥራ ይጀምራል፡፡በተለይ ለሰፋፊ የኮንዶሙኒየም ፕሮጀክቶች የውሃ አቅርቦት ይሰጣል ሲሉ አቶ እስጢፋኖስ ነግረውናል፡፡በፈረቃ የሚዳረሰውን የአዲስ አበባ ውሃ አገልግሎት በ2011 ሙሉ ለሙሉ ከፈረቃ ለማውጣትና ሁሌም ለሁሉም ውሃ ለማቅረብ መታሰቡን ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሰምተናል፡፡

ወንድሙ ኃይሉ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ነሐሴ 11፣2009 የሸገር ወሬዎቻችን

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

 • በህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችና ደላሎች ላይ የሚደረገው ዘመቻ ቀጥሏል ተባለ፡፡ (የኔነህ ሲሣይ)
 • ቀደም ሲል ታውጀው ያተዘጉ እና በከፊል ላልተረጋገጡ ይዞታዎች ወሰን ተካሏል ተባለ፡፡ (ምህረት ስዩም)
 • ኢትዮጵያ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶቿን ልኬት ስታትስቲክስ የሚያሳይ ጥናታዊ መረጃ እንደሌላት ተነገረ፡፡ (ቴዎድሮስ ብርሃኑ)
 • የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲስ በረራውን ዛሬ ወደ ባህሬን ይጀምራል ተባለ፡፡ (የኔነህ ሲሣይ)
 • ብሔራዊ የደረጃዎች ምክር ቤት ከዘጠኝ መቶ የሚበልጡ የኢትዮጵያ ደረጃዎችን አፀደቀ፡፡ (ንጋቱ ርጋሣ)
 • በአዲስ አበባ የተቋማትን የሥራ መጣጣም የሚከታተል መሥሪያ ቤት በመቋቋሙ ከእንግዲህ አንዱ ሲገነባ ሌላው የሚያፈርስበት አጋጣሚ አይኖርም ተባለ፡፡ (ምሥክር አወል)
 • የቻይናው ኤግዚም ባንክ ለሰሜን አዲስ አበባ የውሃ አቅርቦት ችግር ማቃለያ ለሚከናወን ሥራ የሚውል የ146 ሚሊዮን ዶላር ብድር ሰጠ፡፡ (ወንድሙ ኃይሉ)
 • ሱዳን የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ የተለያዩ ቦታዎችን መጐብኘታቸው ተነገረ፡፡ (የኔነህ ሲሣይ)
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ለዛ የምሳ ሰዓት ፕሮግራም ነሐሴ 9፣2009

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

በክረምት ዝግ ሆነው የሚቆዩት ፍርድ ቤቶች አስቸኳይ ጉዳዮች ላይ የዳኝነት አገልግሎት ይሰጣሉ ተባለ

በክረምት ዝግ ሆነው የሚቆዩት ፍርድ ቤቶች አስቸኳይ ጉዳዮች ላይ የዳኝነት አገልግሎት ይሰጣሉ ተባለ፡፡የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንደተናገረው ፍርድ ቤቶች የዜጎችን መብት የሚጥሱ አስቸኳይ ጉዳዮች ከገጠሙ በክረምቱ በመደበኛ እንዲሁም ተረኛ ችሎቶች የዳኝነት አገልግሎት ይሰጣሉ ብሏል፡፡

በክረምቱ ጊዜ በከፍተኛ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዲሁም የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች የሚያገለግሉ ዳኞች የረፍት ጊዜያቸው በመሆኑ የዳኝነት አገልግሎት አይኖርም ተብሏል፡፡ነገር ግን የዜጎችን መብት የሚጥሱና በሀገሪቱ ሰላምና ፀጥታ ላይ ለሚገጥሙ አስቸኳይ የፍርድ ጉዳዮች ፍርድ ቤቶቹ በመደበኛ እንዲሁም ተረኛ ችሎቶች ጉዳዮችን ይመለከታሉ ተብሏል፡፡የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በክረምቱ ጊዜ የሙስና፣ ሽብር፣ ግድያ፣ ታክስ፣ አደንዛዥ ዕፅ፣ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ሌሎች ከባድ ወንጀሎችን እንደሚመለከት ተናግሯል፡፡

የእጅ ከፍንጅ ወንጀሎች፣ የመያዣና የብርበራ ትዕዛዞች በክረምቱ መደበኛ የዳኝነት ችሎት የሚታዩ ጉዳዮች ሲሆኑ የጊዜ ቀጠሮ፣ የእምነት ቃል መቀበል ትዕዛዝ፣ የፍትሐ-ብሔር ጉዳዮች ከዋስትና ጋር የተያያዙ አቤቱታዎችና የእግድ ጉዳዮች በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በተረኛ ችሎት ይስተናገዳሉ ተብሏል፡፡የህፃናትን ጥቅማ ጥቅምና ደህንነት የሚመለከቱ ጉዳዮችም በሀገሪቱ በሚገኙ በ11 የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ምድብ ችሎቶች በክረምቱ ሳይቋረጡ የሚስተናገዱ የዳኝነት ጉዳዮች እንደሆኑ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ተናግሯል፡፡

በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለሰበር የሚቀርቡ አቤቱታዎች እስከ ነሐሴ 21 ቀን 2009 ዓ.ም የሚስተናገዱ ናቸው ፤ ከዚህ ውጭ ያሉ ባለጉዳዮች ግን እስከ መስከረም 21 ቀን 2010 ዓ.ም የማትስተናገዱ መሆኑን እወቁት ተብላችኋል፡፡

ምህረት ሥዩም
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የ2008 ዓ.ም የሥነ-ሕዝብ ጤና ጥናት ውጤትን ዛሬ ይፋ አድርጓል

ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የ2008 ዓ.ም የሥነ-ሕዝብ ጤና ጥናት ውጤትን ዛሬ ይፋ አድርጓል፡፡ ጥናቱ የሀገሪቱን ጤና እና ጤና ነክ ማለትም የውልደት መጠን፣ የጋብቻ፣ የቤተሰብ ምጣኔ፣ ሥነ-ምግብ፣ የህፃናት ሞት፣ የሴት ልጅ ግርዛት፣ ኤች አይ ቪ፣ የአባላዘር በሽታዎችንና ሌሎችንም ያካተተ መሆኑን ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዛሬ ጥናቱን በሂልተን ሆቴል ይፋ ሲያደርጉ ተገኝተን ሰምተናል፡፡

በ9 ክልሎችና በሁለት ከተማ መስተዳድሮች በገጠርና ከተማ የሚገኙ እድሜያቸው ከ15-49 ያሉ 15 ሺ 683 ሴቶችና እድሜያቸው ከ15-59 የሆኑ 12 ሺ 688 ወንዶች በተመረጡ 16 ሺ 650 ቤተሰቦች መረጃ መሰብሰቡ ተነግሯል፡፡የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ የሥነ-ሕዝብ ጤና ውጤቱ ለመንግሥት፣ ለጥናት አድራጊዎችና ተመራማሪዎች፣ ለለጋሾች እንዲሁም ለፖሊሲና ስትራቴጂ አውጪዎች ትልቅ ግብዓት ይሆናል ሲሉ እምነታቸውን ተናግረዋል፡፡ተገኙ ከተባሉ የሥነ-ሕዝብና የጤና ጥናት ውጤቶች መካከል በፈረንጆቹ  አቆጣጠር 2000 ላይ 5 ነጥብ 5 ልጅ በአማካይ የነበረው የአንዲት ኢትዮጵያዊ እናት የውልደት መጠን አሁን በጥናቱ ወደ 4 ነጥብ 6 ልጅ በአማካይ ወርዷል ተብሏል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ...

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ትናንት አንዲት እናትና ሁለት ልጆቿ የመኪና አደጋ ገጠማቸው

አሳዛኝነው፡፡

ትናንት አንዲት እናትና ሁለት ልጆቿ የመኪና አደጋ ገጠማቸው፡፡

በሰንዳፋ በኬ ከተማ ጂላ ወንዝ ተብሎ በሚጠራው አቅራቢያ አንዲት እናት የ4 ወሯን ህፃን አዝላ የ12 ዓመቷን ልጇን ደግሞ እጇን ይዛ በመጓዝ ላይ ሳለች በቪትስ የቤት አውቶሞቢል ተገጭታ ወደቀች፡፡በአደጋው የታዘለው የ4 ወሩ ጨቅላ ህይወት ወዲያው ሲያልፍ እናቲቱ እና የ12 ዓመቷ ሴት ልጅ ከባድ የአካል ጉዳት አጋጥሟቸው ለህክምና ወደ አዲስ አበባ ተልከዋል ሲሉ የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ፖሊስ የመረጃ ባለሙያው ኢንስፔክተር አዲሱ አበራ ለሸገር ተናግረዋል፡፡

በሌላ የአደጋ ወሬ በወልመራ ወረዳ መናገሻ ከተማ ትናንት ከጠዋቱ 1 ሰዓት ከ40 ደቂቃ ከአዲስ አበባ ወደ ሆለታ እየተጓዘ የነበረ ቶዮታ ፒካፕ መኪና ርቀቱን መጠበቅ ባለመቻሉ ከፊት ለፊቱ የነበረን ሲኖ ትራክ ገጭቶ የቶዮታ ፒካፑ ሾፌር ለከባድ የአካል ጉዳት ተዳርጓል ተብሏል፡፡

በዚህ አደጋ 650 ሺ ብር የተገመተ ንብረት መውደሙንም ኢንስፔክተሩ ነግረውናል፡፡

ወንድሙ ኃይሉ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ነሐሴ 9፣2009 የሸገር ወሬዎቻችን

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

 • በኢትዮጵያ የውልደት መጠኑ እየቀነሰ መሆኑን ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ እወቁልኝ አለ፡፡ (ምሥክርአወል)
 • የፌዴራሉ ትራንስፖርት ባለሥልጣን በዚህ ዓመት ወደ ሀገር ውስጥ ለገቡ ከ80 ሺ በላይ ተሽከርካሪዎች ፍተሻ በማድረግ ፈቃድ መስጠቱን ተናገረ፡፡ (ምህረትስዩም)
 • ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ ወደ ካርቱም መሄዳቸው ተሠማ፡፡ (የኔነህሲሣይ)
 • ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ጌጣጌጦች በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው ሲጓጓዙ መያዛቸው ተሠማ፡፡ (ንጋቱሙሉ)
 • ከመጋቢት ወር ወዲህ 577 አሽከርካሪዎች በደማቸው ውስጥ መኖር ከሚፈቀደው የአልኮል መጠጥ በላይ ወስደው ሲያሽከረክሩ ተገኝተው መቀጣታቸው ተሠማ፡፡ (ወንድሙኃይሉ)
 • የአይሻ ሁለት የንፋስ ኃይል ማመንጫ በ257 ሚሊየን ዶላር ግንባታው ተጀመረ፡፡ (ዮሐንስየኋላወርቅ)
 • የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአራት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ካፒታል እንዲስተካከል ወሰነ፡፡ (ንጋቱረጋሣ)
 • በዚህ ዓመት በአዲስ አበባ መገንባት ከነበረባቸው 84 መንገዶች ግማሾቹ የወሰን ማስከበር ሥራ አላለቀላቸውም፤ ለተገነቡት 42 መንገዶች ግን ከ1 ሺ በላይ ቤቶች ፈርሰዋል ተባለ፡፡ (ትዕግሥትዘሪሁን)
 • ፍርድ ቤቶች በክረምቱ ዝግ ሆነው ቢሰነብቱም አጣዳፊ ጉዳዮች መታየታቸው አይስተጓጐልም ተባለ፡፡ (ምህረትስዩም)
 • ትናንት አንዲት እናትና ሁለት ልጆቿ የመኪና አደጋ ገጠማቸው፡፡ (ወንድሙ ኃይሉ)
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

በመጪዎቹ ስድስት ቀናት በክረምቱ ተጠቃሚ በሚሆኑ አካባቢዎች ጠንከር ያለ ዝናብ ይኖራል ሲል የብሔራዊ ሚትዬሮሎጂ ኤጀንሲ ተናገረ

በመጪዎቹ ስድስት ቀናት በክረምቱ ተጠቃሚ በሚሆኑ አካባቢዎች ጠንከር ያለ ዝናብ ይኖራል ሲል የብሔራዊ ሚትዬሮሎጂ ኤጀንሲ ተናገረ፡፡በክረምቱ ዝናብ የሚያገኙ አካባቢዎች ላይ ዝናብ ሰጪ የሚትዬሮሎጂ ገፅታዎች ተጠናክረው በመቀጠላቸው በመጪዎቹ ስድስት ቀናት በወንዞች ሙላት፣ በጎርፍና በረባዳ ቦታዎች ላይ በሚተኛ ውሃ ጉዳት ሊከሰት ስለሚችልም ጥንቃቄ አድርጉ ሲል ኤጀንሲው አሳስቧል፡፡

መደበኛና ከመደበኛ በላይ ከባድ ዝናብ፣ የወንዝ ሙላትና ቅፅበታዊ ጎርፍ ሊከሰትባቸው ይችላል ከተባሉት የሀገሪቱ አካባቢዎች ውስጥ አባይ፣ ተከዜ፣ ባሮ አኮቦ፣ አፋርና አዋሽ፣ የላይኛውና መካከለኛው ስምጥ ሸለቆ፣ ኦሞ ጊቤ ይገኙበታል በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎችም ሊጠነቀቁ ይገባል ተብሏል፡፡አማራ፣ ትግራይ፣  ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ደቡብ፣ ጋምቤላና ኦሮሚያ ክልሎች የሚገኙ አካባቢዎችም በመጪዎቹ ስድስት ቀናት የተጠናከረ ዝናብ ያገኛሉ ተብሏል፡፡

አዲስ አበባን ጨምሮ በደቡብ የተለያዩ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ ዝናብ የሚያገኙ አካባቢዎች ሲሆኑ ምዕራብና ምሥራቅ ሀረርጌ፣ ድሬዳዋና ሐረሪ እንዲሁም ሶማሌ ክልል ደግሞ አነስተኛ የዝናብ ሥርጭት የሚያገኙ አካባቢዎች እንደሆኑ ተነግሯል፡፡ባለፉት አሥር ቀናት በዝናብ ሰጪ የአየር ትንበያ ገፅታዎች በቂ እርጥበት ያላገኙ የአማራ፣ ኦሮሚያና ደቡብ እንዲሁም ትግራይ ክልሎች በእነዚህ ስድስት ቀናት የተሻለ እርጥበት እንደሚያገኙ ይጠበቃል ተብሏል፡፡

ጠንካራ የደመና ክምችት በሚኖርባቸው ሌሎች የሀገሪቱ የተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ደግሞ ከባድ ዝናብ ሊኖር ይችላልና ጥንቃቄ አይለያችሁ ሲል የብሔራዊ ሚትዬሮሎጂ ኤጀንሲ አሳስቧል፡፡

ምህረት ሥዩም
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ነሐሴ 10፣2009 የሸገር ወሬዎቻችን

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

 • በመጪዎቹ ስድስት ቀናት በክረምቱ ዝናብ የሚያገኙ አካባቢዎች ላይ ጠንከር ያለ ዝናብ ሊኖር ስለሚችል ጥንቃቄ አድርጉ ሲል የብሔራዊ ሜትዮሮሎጂ ኤጀንሲ አሳሰበ፡፡ (ምህረት ስዩም)
 • ለደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች የተሰጠው ተጨማሪ 10 ቀናት ዛሬ ይጠናቀቃል፡፡ እስከ ዛሬ ያልከፈሉ ከነገ ጀምሮ ቅጣት ይጠብቃቸዋል ተብሏል፡፡ (ንጋቱ ሙሉ)
 • በካርቱም በሥራ ጉብኝት ላይ የሚገኙት የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ ለሁለተኛ ቀን ከካርቱም መሪዎች ጋር እየመከሩ ይገኛሉ፡፡ (የኔነህ ሲሣይ)
 • ከ5 ዓመት በታች በሆኑ ኢትዮጵያውያን ህፃናት ላይ የደም ማነስ ችግር መጨመር ታይቷል ተባለ፡፡ (ምሥክር አወል)
 • በሐምሌ ወር ከእንስሣት ክትባት ሽያጭ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ተገኘ፡፡ (ወንድሙ ኃይሉ)
 • የጀርመን መንግሥት ከሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ለተነሱ ሰዎች ድጋፍ አደርጋለሁ አለ ተባለ፡፡ (ወንድሙ ኃይሉ)
 • በኢትዮጵያ የኩላሊት ንቅለ ተከላ የሚመራና የሚተዳደርበትን ሕግ የማርቀቅ ኃሣብ እንዳለ ተሠማ፡፡ (ንጋቱ ሙሉ)
 • ኤርፖርቶች ድርጅቶች 5 አዳዲስ አውሮፕላን ማረፊያዎችን ለመገንባት ቦታ መረጣ ላይ ነኝ አለ፡፡ (ወንድሙ ኃይሉ)
 • ለሀጅ ጉዞ ወደ ሳዑዲ የሚሄደው የልዑካን ቡድን ውጡልን የተባሉና በዚያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ለማግባባት ጥረት ያደርጋል ተባለ፡፡ (ዮሐንስ የኋላወርቅ)
 • በኦሮሚያ ክልል የወንዝ ሙላትና ጐርፍ ያሰጋቸው ወደ 1 ሺ የሚጠጉ አባወራዎች ወደ ጊዜያዊ መጠለያ እንዲገቡ ተደረገ፡፡ (ንጋቱ ረጋሣ)
 • ዓለም አቀፉ ድርጅት ለአንኮበር ወረዳ አልዩ አምባ ዙሪያ ቀበሌ ልማት ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ፡፡ (ወንድሙ ኃይሉ)
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ኢትዮጵያ ለጐረቤት ሀገር ልካ ከሸጠችው ኤሌክትሪክ ኃይል ከ1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቷ ተሰማ

ኢትዮጵያ ለጐረቤት ሀገር ልካ ከሸጠችው ኤሌክትሪክ ኃይል ከ1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቷ ተሰማ፡፡ከውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ ከአቶ ብዙነህ ቶልቻ እንደተሰማው ሱዳን በወር በአማካይ ከ92 ሜጋ ዋት በላይ ኤሌክትሪክ ኃይል ገዝታ 73 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ከፍላለች፡፡

ለጅቡቲም 33 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ ከ56 ሜጋ ዋት በላይ ኤሌክትሪክ ኃይል የተሸጠላት መሆኑንም ሰምተናል፡፡ጅቡቲም ተጨማሪ ኃይል ከኢትዮጵያ መግዛት እፈልጋለሁ ያለች ሲሆን ተጨማሪ ኃይል ለመስጠት የሚያስችል መስመር ለመዘርጋት ጥናት እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያ በ2011 አጋማሽ ለኬንያ 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ ቅድመ ዝግጅት እያደረገች መሆኑም ታውቋል፡፡ዘንድሮ ለሀገር ውስጥ ከኤሌክትሪክ ሽያጭ 5 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 4 ነጥብ 66 ቢሊየን ብር ተሰብስቧል ተብሏል፡፡

ዮሐንስ የኋላወርቅ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)
Sheger 102.1 AudioNow Numbers