• United Bank S.C.

    ሕብረት ባንክ አ.ማ.

  • Slider Two

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Sldier Three

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ሸገር ወሬዎች እና ልዩ ወሬዎች

ትንታኔ…

የሶሪያ መንግሥት የኬሚካል ጦር መሣሪያ ጉዳይ አወዛጋቢነት አዲስ አይደለም፡፡ከ3 ዓመት ከመንፈቅ በፊት የሶሪያ የኬሚካል የጦር መሣሪያ ጉዳይ እንዲህ እንደ ሰሞኑ አብይ ዓለም አቀፋዊ መነጋገሪያ ጉዳይ ነበር፡፡በእርግጥም በጊዜው የሶሪያ መንግሥት ከፍተኛ መጠን ያለው የኬሚካል የጦር መሣሪያ ክምችት ነበረው፡፡

በጊዜው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ጆን ኬሪ የፕሬዝዳንት ባሻር አል አሳድ መንግሥት የኬሚካል የጦር መሣሪዎቹን አንዲትም ጠብታ ሳይቀር ካላስረከበ ውርድ ከራሳችን በጦር ይቀመስልህ እንለዋለን ሲሉ አስጠንቅቀውም ነበር፡፡አሜሪካ ያኔ በሶሪያ ላይ የመዘዘችውን ጐራዴ ወደ አፎቱ የመለሰችው በሩሲያ አግባቢነት የሶሪያ መንግሥት የኬሚካል የጦር መሣሪያዎቹን እንዲወድሙ በመስማማቱ ነበር፡፡

ሩሲያም ሁለቱን ወገኖች የማግባባት ሚና ተጫውታለች፡፡ከዚያ ወዲህም የፕሬዝዳንት ባሻር አል አሳድ መንግሥት አሉኝ ብሎ አመኖ ያስረከባቸው ኬሚካሎች በብዛት ወደ ሚወገዱበት ሲጓጓዙ ቆይተዋል፡፡

በሶሪያ የኬሚካል የጦር መሣሪያ ጥቃት ጉዳይ ከሦስት ዓመታት በፊት እንደነበረው ባይጐላም በተለያዩ ጊዜዎች ተፋላሚዎቹን በአንተ ነህ አንተ ነህ እርስ በርስ ማካሰሱ አልቀረም፡፡

ባለፈው ማክሰኞ በአማፂያን ይዞታ ውስጥ በምትገኘው በኢድሊብ ግዛት ካን ሼክሁን ከተማ ከ60 ያላነሱ ሰዎች ያለቁበት የኬሚካል የጦር መሣሪያ ጥቃት ከፍተኛ ዓለም አቀፋዊ ጫጫታና ምሬት ፈጥሯል፡፡

አሜሪካና የቅርብ አጋሮቿ ጥቃቱን የሶሪያ መንግሥት የእጅ ሥራ ነው ለማለት አላቅማሙም፡፡

መቀመጫው በእንግሊዝ ለንደን የሆነው የሶሪያ የሰብዓዊ መብት ተከታታይ አካል ጥቃት አድራሾቹ ሶሪያ አለያም የቅርብ አጋሯ ሩሲያ ሳይሆኑ አይቀሩም ያለው ወዲያውኑ ነው፡፡

 

ሩሲያ እኔ የለሁበትም ከማለቷም በተጨማሪ ይሄ የጭቦ ሥራ የራሳቸው የአማፂያኑ ነው ለማለት አላረፈደችም፡፡

የሶሪያ መንግሥትም ከደሙ ንፁህ ነኝ ባይ ነው፡፡ አሁንም ድረስ፡፡

በካን ሼክሁን ለተፈፀመው ዘግናኝ የኬሚካል የጦር መሣሪያ ጥቃት ከባሻር አል አሳድ መንግሥት ራስ አልወርድም ያለችው አሜሪካ በሆምስ ግዛት የሚገኘውን የሻይራትን አየር ኃይል ሰፈር የቶም ሐውክ ሚሳየሎች ስታዘንብበት አድራለች፡፡

አሜሪካ 60 ያህል ሚሳየሎችን መተኮሷን አልጀዚራ አውርቷል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዝዳነት ዶናልድ ትራምፕ የአገራቸው እርምጃ የሶሪያ መንግሥት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ለፈፀመው ኬሚካላዊ ጥቃት ምላሽ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ትራምፕ በንግግራቸው የሶሪያውን ጦርነት ለማስቆም ስልጡን አገሮች ሊተባበሩ ይገባለ ብለዋል፡፡

አሜሪካ በሆምስ ግዛት የሚገኘውን የሶሪያን መንግሥት የሼይራት የአየር ኃይል ሰፈር የደበደበችው በሜዴትራኒየን ባህር ካሰማራቻት USS ፖርተር የጦር መርከቧ በተተኮሱ ቶም ሐውክ ሚሳየሎች ነው፡፡

ይሁንና ስላደረሱት ጉዳትና ውድመት በዝርዝር የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡

የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት /ፔንታገን/ ሹሞች የድብደባውን የተሟላ ውጤት ለማወቅ ትንሽ ጊዜ ሊጠይቀን ይችላል ማለታቸው ተሠምቷል፡፡

የሶሪያ መንግሥት የአሜሪካን ድብደባ በብርቱ የኮነነው ሲሆን በድብደባው ስለደረሰበት ጉዳት ግን ትንፍሽ አላለም፡፡

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ የአሜሪካን ድብደባ በነፃ ሉዓላዊት አገር ላይ የተፈፀመ ወረራ ነው ሲሉ አውግዘውታል፡፡

ሩሲያ በሶሪያ መንግሥት የጦር አጋርነት ቀጥተኛ ተሳታፊ ከሆነች ከዓመት ከመንፈቅ በላይ ሆኗታል፡፡

የአሜሪካ የቅርብ አጋር ተደርጋ የምትቆጠረው ብሪታንያ ተገቢ እርምጃ ስትል አድንቃለች፡፡

ቀደም ሲል ትራምፕ አሳድን በፀረ I.S ዘመቻ በአጋርነት ሊጠቀሙባቸው እንደሚችሉ ፍንጭ ሲሰጡ ነበር፡፡

የአሁኑ የሻይራት የአየር ኃልል ሰፈር ድብደባ ትራምፕ በሶሪያ ፖሊሲያቸው ላይ ለውጥ ስለማድረጋቸው ፍንጭ ሰጭ እንደሆነ የቢቢሲ የሰሜን አሜሪካ ተንታኝ ጆን ሶፔል ተናግረዋል፡፡

በማኅበረ ሰብ ገጾች ያጋሩ

Submit to FacebookSubmit to Google PlusSubmit to TwitterSubmit to LinkedIn
Sheger 102.1 AudioNow Numbers