• United Bank S.C.

    ሕብረት ባንክ አ.ማ.

  • Slider Two

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Sldier Three

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ሸገር ወሬዎች እና ልዩ ወሬዎች

በያዘነው ሰኔ ወር መጨረሻ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ እንደሚወጣ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ተናገረ

በያዘነው ሰኔ ወር መጨረሻ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ እንደሚወጣ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ተናገረ፡፡ግንባታቸው ተጠናቆ በዕጣ ለባለቤቶቹ ይተላለፋሉ ተብሎ ከታቀደላቸው ዓመታትን ያስቆጠሩት የ40/60 የቁጠባ ቤቶች በሰኔ ወር መጨረሻ 2009 ዓ.ም ዕጣ ይወጣባቸዋል ተብሏል፡፡

የግንባታው ሥራቸው ተጠናቋል የተባሉ 1 ሺ 292 ቤቶችን ከንግድ ባንክ ጋር እርክክብ እየተፈፀመ መሆኑን የተናገሩት የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትሩ ዶክተር አንባቸው መኮንን ርክክቡ እየተገባደደ ነው ብለዋል፡፡በመጪው ወር መጨረሻ ዕጣ ይወጣባቸዋል ከተባሉት 1 ሺ 292 የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች በተጨማሪ ሌሎች 20 ሺ 932 ቤቶችም ግንባታቸው 69 በመቶ መድረሱንም ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ የመሥሪያ ቤታቸውን የ10 ወር ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ሲያቀርቡ እንደሰማነው ከ3 ዓመት በፊት ግንባታቸው የተጀመሩ የ20/80 ቤቶች ግንባታ የደረሰበትን ደረጃ ተናግረዋል፡፡እየተገነቡ ካሉ 52 ሺ 651 የ20/80 ቤቶች መካከል 26 ሺ 480 ቤቶች ግንባታቸው 65 በመቶ ደርሷል ፤ የቀሪዎቹን 26 ሺ 171 ቤቶች ግንባታ ደግሞ 48 በመቶ ደርሷል ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ የቤት ልማት ፕሮግራሞች የሚገነቡ ከ170 ሺ በላይ ቤቶችን ማስፈፀሚያ በዚህ ዓመት 8 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ወጪ ተደርጓል ተብሏል፡፡በሁለተኛው የዕቅድ ዘመን 750 ሺ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት የታቀደ ቢሆንም በበጀት አልተደገፈም ያሉት ሚኒስትሩ ዶክተር አንባቸው ይህም ፈተና እንደሆነብን ቀጥሏል ብለዋል፡፡

በ2009 በጀት ዓመት ለአዲስ አበባ ከተማ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ የተፈቀደው ገንዘብ ዘግይቶ በመለቀቁ የሥራ ተቋራጮችና የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋሞች ሥራ አቁመው ተበትነው መቆየታቸውንም አስታውሰዋል፡፡ይህም ለቤቶች ግንባታ መጓተት አንዱ ምክንያት ነው ያሉት ሚኒስትሩ የሥራ ተቋራጮቹን ዳግም ወደ ሥራ ለመመለስ ከከተማ አስተዳደሩ በብድር ገንዘብ መገኘቱንም ተናግረዋል፡፡

በዚህ ዓመት ዕጣ ከወጣባቸው 39 ሺ የጋራ መኖሪያ ቤቶች መካከል 30 በመቶዎቹ ለሴቶች፣ 20 በመቶዎቹን ለመንግሥት ሠራተኞችና 5 በመቶ ለአካል ጉዳተኞች እንደተሰጡም ሰምተናል፡፡ይህም በዕጣ ከተላለፉ ቤቶች 55 በመቶው የተሰጡት በኮታ ለተፈቀደላቸው ነው፡፡

ትዕግሥት ዘሪሁን

በማኅበረ ሰብ ገጾች ያጋሩ

Submit to FacebookSubmit to Google PlusSubmit to TwitterSubmit to LinkedIn
Sheger 102.1 AudioNow Numbers