• Slider One

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Slider Two

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Sldier Three

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ሸገር ወሬዎች እና ልዩ ወሬዎች

የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ለ10 ወራት የቆየውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንስቶ...

የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ለ10 ወራት የቆየውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንስቶ የ3 ሚኒስትሮችን ሹመት አፅድቋል፡፡የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈፀም የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ዋና ፀሐፊና የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ በየቦታው ጥቃቅን ክስተቶች እያጋጠሙ መሆናቸውንና ያልተቋጩ መለስተኛ ሥራዎች ስለመኖራቸው ተናግረዋል፡፡

ይሁንና ክስተቶቹ በየደረጃው ካሉ የፀጥታ መስተዳድር አካል አቅም በላይ ባለመሆናቸው አዋጁ ተነስቶ ቀሪ ሥራው በመደበኛው የህግ አሰራር እንዲፈፀም የኮማንድ ፖስቱን የውሣኔ ኃሣብ አቅርበው እንደራሴዎቹ  አፅድቀውታል፡፡አቶ ሲራጅ ኮማንድ ፖስቱ ባለፉት 10 ወራት ስለከወናቸው ሥራዎችም ለምክር ቤቱ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡

በሪፖርታቸው በተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን አለመረጋጋት ተከትሎ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ዜጎች ሁከትና ሽብር በመፍጠር ወንጀል ተጠርጥረው 7 ሺ 737 ዜጎች በሰውና በሰነድ ማስረጃ ስለተረጋገጠባቸው በፍርድ ቤት ጉዳያቸውን እየተከታተሉ ነው ብለዋል፡፡ወንጀሉን ስለመፈፀማቸው በማስረጃ ተረጋግጦባቸዋል ከተባሉና በተለያዩ ፍርድ ቤቶች ክርክር ላይ ስለመሆናቸው የተነገረው ከ7 ሺ 700 በላይ ዜጎች መካከል በኦሮሚያ 4 ሺ 136፣ በአማራ 1 ሺ 888፣ በደቡብ ክልል 1 ሺ 166 እና በአዲስ አበባ 547 ዜጎች ይገኙበታል፡፡

ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ነው ከተባሉት መካከልም 709 ያህሉ መሣሪያ ታጥቀው የነበሩ ናቸው ተብሏል፡፡በኮማንድ ፓስቱ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል በሁለት ዙር ሥልጠና ወስደው ወደ ህብረተሰቡ የተቀላቀሉ 21 ሺ ተጠርጣሪዎች እንደነበሩም አቶ ሲራጅ አስታውሰዋል፡፡አክለውም ኮማንድ ፖስቱ ህገ-ወጥ የሰውና የጦር መሣሪያ ዝውውርን ለመቆጣጠር ከነባሮቹ 196 ኬላዎች ፤ 97 አዳዲስ ኬላዎችን በመጨመር 2 ሺ 732 መሣሪያዎችን፣ 181 ቦምቦችንና 2 የግንኙነት ሬዲዮኖችን በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተነግሯዋል፡፡

 

ኮማንድ ፓስቱ ቀሪ ሥራዎች በየአካባቢው ካሉ የፀጥታ ኃይሎችና መስተዳድሮች አቅም በላይ እንዳልሆነ ከየክልልና የፀጥታ ኃይሎች ጋር መክሮበት መግባባት ላይ መደረሱንም ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከዛሬ ጀምሮ እንዲነሣ የቀረበውን የውሣኔ ኃሣብ ከማፅደቅ በተጨማሪ የሚኒስትሮችን ሹመት አፅድቋል፡፡

በቅርቡ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ አንባሳደር አድርገው በሾሟቸው ሚኒስትሮች ምትክ የአዳዲስ ሚኒስትሮች ሹመት ፀድቋል፡፡ አቶ ከበደ ጫኔ የፌዴራልና የአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር፣ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ የትምህርት ሚኒስትር፣ አቶ ሞገስ ባልቻ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በሚኒስትር ማዕረግ ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሹመዋል፡፡

ትዕግስት ዘሪሁን

በማኅበረ ሰብ ገጾች ያጋሩ

Submit to FacebookSubmit to Google PlusSubmit to TwitterSubmit to LinkedIn
Sheger 102.1 AudioNow Numbers