• United Bank S.C.

    ሕብረት ባንክ አ.ማ.

  • Slider Two

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Sldier Three

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ሸገር ወሬዎች እና ልዩ ወሬዎች

የፓርቲዎች ጋጋታ ለዲሞክራሲያዊ ምርጫ ምንም አይፈይድም

በአፍሪካ ምርጫን አስመልክቶ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ የሚያመለክተው ነገር ቢኖር ከዲሞክራሲ አንፃር የተጠናከረና ስር የሰደደ አለመሆኑን ነው፡፡የአንድ ፓርቲ ፈላጭ ቆራጭነት እንጂ የብዙኃን ፓርቲ የሚባል ነገር ብዙም አልተለመደም፡፡

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በአህጉረ አፍሪካ የብዙኃን ፓርቲ ፖለቲካ ብቅ ማለት የጀመረው በ1990 ላይ መሆኑን በአፍሪካ የጥናት ማዕከል የተጻፈው መረጃ ያመለክታል፡፡በአፍሪካ የምርጫ ወቅት ባለድርሻ አካላት ከሚባሉት ዋነኞቹ ተዋናዮች ሥልጣን ላይ ያለው ገዢ ፓርቲ ወይንም መንግስት አልያም ሁለቱንም አደባልቀው የያዙ መንግስታት፣ የሲቪል ማህበረሰቡ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ወይንም መንግስት ከመጋረጃ ጀርባ ያደራጃቸው ታማኝ ተቃዋሚዎች መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በአፍሪካ ምርጫን አስመልክተው በተካሄዱ ጥናቶች ባለፉት 15 አመታት ትልቅ መሻሻል እየታየ መጥቷል እየተባለ ነው፡፡በ1990ዎቹ በአፍሪካ ይብዛም ይነስ በፉክክር የታጀቡ ምርጫዎች ደርዘን በሆኑ ሀገሮች ተከናውነዋል፡፡የምርጫ ባለድርሻ አካላት የተሰኙት በምርጫው ሂደት የተሻለ ፍትሃዊ አካሄድ እንዲኖር ካደረጉ፤ ዘላቂ ለሆነ ሰላም የዲሞክራሲ መንገድን በመክፈት በኩል አስተዋፅኦቸው ገንቢ እንደሚሆን እየታመነበት መጥቷል፡፡

ለአብነትም ያህል በጋና፣ በዛምቢያ፣ በሴኔጋል እና በተለየ ሁኔታ በደቡብ አፍሪካ በ1994 የተደረገው የተሳካ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ሊጠናቀቁ መቻላቸው ይታወሳል፡፡ይህ ሲባል ግን በአፍሪካ የሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ምሉዕ በኩሉሄ ወይንም ሙሉ በሙሉ ከችግሮች የፀዳ ነው ማለት አይደለም፡፡በአፍሪካ ምርጫን በሚመለከት ዋነኛ እንቅፋት ተደርገው ከሚጠቀሱት መካከል ቁሩጩ ድሃ በሆኑ ሀገሮች ሳይቀር የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ አሽን የመፍላታቸው ጉዳይ ነው፡፡

ሌላው ደግሞ በጎሳና በሃይማኖት በተከፋፈሉ ሀገሮች የሚደረግ ምርጫ ለበርካታ ሰላማዊ ዜጎች እልቂትና እስራት ምክንያት መሆኑ ነው፡፡በቅርቡ አፍሪካዊቷ ሀገር ዚምባቡዌ የቀድሞውን አንጋፋ መሪዋን ሮበርት ሙጋቤን ጤናማ ነው በሚባል መልኩ በሌላ መሪ ኤመርሰን ምናንጋግዋ መተካቷ የሚታወስ ነው፡፡

ዚምባብዌ እንደሌሎቹ በርካታ ሀገሮች በውስጧ የሚንቀሳቀሱ 107 የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖር ራሷን ያዞሩዋት ይመስላል፡፡ሰሞኑን የዚምባብዌ የምርጫ ኮሚሽን ይህንኑ ጉዳይ በማንሳት ሀገሪቱ ይህን ያህል የፖለቲካ ፓርቲዎች አያስፈልጓትም ባይ ነው፡፡

እነዚሁ ፓርቲዎች በቅርቡ በ2018 በሚካሄደው የሀገሪቱ ምርጫ ላይ የሚወዳደሩ ናቸውም ተብሏል፡፡የፓርቲዎቹ ቁጥር መብዛት ጉዳይ ጎጂ ላይመስል ይችላል፡፡ይሁን እንጂ የዚምባብዌ አብዛኞቹ አነስተኛ ፓርቲዎች የማይጠቅሙና ምናቸውም የማይታወቅ ነገሮች መሆናቸውን የምርጫ ኮሚሽኑን መግለጫ ጠቅሶ ዴይሊ ኒውስ ፅፏል፡፡

የፓርቲዎቹ መብዛት የድምፅ መስጫ ጣቢያዎችን ያጨናንቃሉ፣ የክርክር መድረኮችን የማወላገድና ድምፅ ሰጪዎችን ግራ የማጋባትን ተፅዕኖ ያስከትላሉ ይላል የኮሚሽኑ መግለጫ፡፡የዚህ አይነት 107 የፓርቲዎች ቁጥር በእጅጉ የበዛበት የምርጫ ሥርዓት የማካሄድ በምርጫ ወቅት የማምታታት አሰራር (ሲስተም) የማምጣት ሁኔታን ያስከትላል ነው የሚባለው፡፡

እነዚህ ሁሉ ፓርቲዎች የተቋቋሙት ጥቅል ሀገራዊ ምርቷ 4 ቢሊዮን ዶላር በሆነባት ዚምባቡዌ መመስረታቸው ጉዳይ ነው፡፡እንጥል ለምታህል ሀገር 107 የፓርቲ ጋጋታ መኖር ከጥቅሙ ጉዳቱን በብዙ መልኩ መጥቀስ ይቻላል፡፡በአንፃሩ ጥቅል ሀገራዊ ምርቷ 17.7 ትሪልዮን ዶላር የሆነው ኃያሏ የዓለም መሪ አሜሪካ በውስጧ የሚገኙት የፓርቲዎች ብዛት ዋነኞቹ ሁለት ብቻ ማለትም ዴሞክራቲክ እና ሪፐብሊካን ፓርቲ መሆናቸው ሲታይ የዚምባብዌ ሁኔታ አስገራሚ ይሆናል፡፡

ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች እንዳላት የሚነገርላትን የሀገራችንን ጓዳ ስንፈትሽ ደግሞ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2016 የነበረን ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት 72.32  ቢሊዮን ዶላር መሆኑን እንገነዘባለን፡፡የፖለቲካ ፓርቲዎች ብዛት ደግሞ በ2017 በሀገር አቀፍ ሃያ አንድ ሲሆኑ፤ የክልል ፓርቲዎች ደግሞ 40 መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡በአጠቃላይ 61 ፓርቲዎች አሉን ማለት ነው፡፡
ድህነትን በመዋጋት ላይ ላለች ሀገር የፓርቲ ጋጋታ ምንም አይፈይድላትም የሚል ሂስ ሲሰጥ ይደመጣል፡፡ዴሞክራሲ ስር በሰደደባቸው አሜሪካና እንግሊዝ ሁለት ወይንም ሶስት ፓርቲዎች ብቻ መኖራቸው ለሌሎች ሀገሮች መልካም ተሞክሮ እንደሚሆናቸው ጥርጥር እንደሌለው በሰፊው ይነገራል፡፡

የፓርቲዎች ጋጋታ ብቻውን ዲሞክራሲን ሊያሰፋ እንደማይችል የዚምባቡዌ የፓርላማ አባላት እየተገነዘቡ መምጣት ይገባቸዋል ይላል ፅሁፉ፡፡አሁን በስራ ላይ ያለውን የምርጫ ሕግ በማሻሻልም በምርጫው ወቅት ሊወዳደሩ የሚችሉ ብቃት ያላቸውን እጅግ ቢበዛ አምስት ፓርቲዎች እንዲኖሩ ለማድረግ ቢጥሩ መልካም መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የፓርቲዎች ቁጥርን መመጠን በምርጫ ሰዓት የሚኖረውን ዝብርቅርቅ ሁኔታ ለማስቀረት እንደሚረዳ የዚምባቡዌ የምርጫ አስፈፃሚዎች ሊያውቁት ይገባል እየተባሉ ነው፡፡107 የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሳተፉበትን ምርጫ ማካሄድ ማለት ምን ሊሆን እንደሚቻል ገምታችሁታል ? ፓርቲዎቹን በምርጫው ለማሳተፍ ምን ያህል ወረቀቶች ያስፈልጋሉ ? ይህ ፈጽሞ ሊደረግ የሚገባው ጉዳይ አይደለም በሚል አስተያየት የዚምባቡዌ የምርጫ ኮሚሽን እየተብጠለጠለ መሆኑን ዴይሊ ኒውስ ፅፎታል፡፡

ያም ሆነ ይህ ዚምባቡዌ በአሁኑ ጊዜ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋጋታ እንደማያስፈልጋት በራሷ በምርጫ ኮሚሽኗ እየታመነበት መጥቷል፡፡“የሚያስፈልጓት ነገሮች ቢኖሩ ዋነኛው የመራጮችን ቁጥር መጨመር ነው” በሚል ዴይሊ ኒውስ ፅፏል፡፡በአፍሪካም ሆነ በሌሎች ሀገሮች ሀቀኛ የሀገር መሪዎችን መርጦ ለማስቀመጥ ከ50 እና ከ100 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማፍራት የሥልጣኔ ምልክት አይደለም፡፡

ይልቁንም ለዴሞክራሲ፣ ለፍትህና ዕኩልነት በሀቅ የሚታገሉ በጣት የሚቆጠሩ ፓርቲዎችን ማስተናገድ የተሻለ ሀገርና ዜጋን ለማፍራት እንደሚያስችል በምርጫ አስፈላጊነትና ምንነት ላይ ጥናት ያካሄዱ ጥልቅ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

ጌታቸው ለማ
 

በማኅበረ ሰብ ገጾች ያጋሩ

Submit to FacebookSubmit to Google PlusSubmit to TwitterSubmit to LinkedIn
Sheger 102.1 AudioNow Numbers