ሸገር ወሬዎች እና ልዩ ወሬዎች
የጥራት መሥፈርታቸውን ያላሟሉ የታሸጉ የመጠጥ ውሃ በሚያቀርቡ አምራቾች ላይ እርምጃ ይወሰድባቸዋል ተባለ
በተለያየ ጊዜ ያልሆኑትን ነን የሚሉና ጥራታቸው የተጓደለ የታሸገ የመጠጥ ውሃዎች እየተለዩ እንደሆኑ ሰማን…
አስገዳጅ የጥራት ደረጃ መሥፈርቶችን አሟልተው ወደ ገበያ መግባት ያለባቸው የታሸጉ ውሃዎች ይሄንን ሳያሟሉ በከተማው እና በተለያዩ የክልል ከተሞች እየተቸበቸቡ ነው ተብሏል፡፡
በዚህ መሠረትም የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ጥራት የጐደላቸው የውሀ አምራች ኩባንያዎች እንዳሉ ስላረጋገጥኩ እርምጃ ለመውሰድ ሥራዬን አጠናቅቄያለሁ ብሏል፡፡
የሚመለከተው መሥሪያ ቤት የጥራታቸውን ጉዳይ አረጋግጦ የላከልኝ የውሃ አምራች ኩባንያዎችንም ቁጥር አውቄያቸዋለው ማለቱን ነግሮናል፡፡
ወሬውን ለሸገር የነገሩት የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የክስ ምርመራና ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሀብታሙ ጥላዬ ናቸው፡፡ ንግድ ቢሮው ጥራታቸውን ሳያሟሉ በገበያው ገብተው የታሸገ ውሃ የሚቸበችቡ አምራቾች ላይም እርምጃ እወስዳለው ብሏል፡፡
በኢትዮጵያ የጥራት ማረጋገጫ ተሰጥቷቸው የታሸገ ውሃ የሚያመርቱ ኩባንያዎች ቁጥር ፈቃድ ከሚሰጠው እና ከሚያረጋገጥው መሥሪያ ቤት ውጪ እንደሚገኙ ንግድ ቢሮው የተናገረ ሲሆን ጥራታቸው የተረጋገጠላቸው የታሸጉ ውሃዎች ዝርዝራቸው በተለያዩ የንግድ ማዕከሎች እና በሚሸጡበት ቦታ ሁሉ ለተጠቃሚው በግልፅ እንደሚለጥፉ ሰምተናል፡፡
ተሕቦ ንጉሴ