• Slider One

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Slider Two

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Sldier Three

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ሸገር ወሬዎች እና ልዩ ወሬዎች

ሰሞኑን የወጣ አንድ ሪፖርት የሰሜን አውሮፓዊቷን ሐገር ፊንላንድ በዓለማችን ሕዝቦቿ እጅግ ደስተኛ የሆኑባት ሐገር ብሏታል

ሰሞኑን የወጣ አንድ ሪፖርት የሰሜን አውሮፓዊቷን ሐገር ፊንላንድ በዓለማችን ሕዝቦቿ እጅግ ደስተኛ የሆኑባት ሐገር ብሏታል፡፡ የሐገራትን የደስተኝነት ደረጃ የዘረዘረው ሪፖርት ያሳየው ሌላው ነገር በኢኮኖሚ መበልፀግ ለደስተኝነት ማረጋገጫ አለመሆኑንም ነው…ሙሉውን ያዳምጡ…

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ጫት ላይ የሚረጨው ዲዲቲ ነገር

‘ጫቱ ላይ ያለውን ተባይ ለማጥፋት እና ጫቱ ‘ሻይን’ እንዲያደርግ፣ እንዲያምር በሚል ዲዲቲ ይረጭበታል…’ ጫት ላይ የሚረጨው ዲዲቲ ነገር… ለወጣ ትንኝ ማጥፊያ በሚል ወደ ሐገራችን የገባው ዲዲቲ በአሁኑ ወቅት በሐገራችን በሕግ የተከለከለ ኬሚካል ቢሆንም ገበሬው ከሕገወጥ ሻጮች እየገዛ ጫት እና የተለያዩ የጓሮ አትክልቶች ላይ ይረጨዋል ይለናል ይህ የትዕግስት ዘሪሁን ዘገባ… በተለያዩ ሐገራት የተከለከለው ይህ ኬሚካል ለጉበት፣ ለነርቭ፣ ለካንሰር እና ለመሃንነት እንዲሁም የጤና እክል ያለባቸው ሕፃናት እንዲወለዱ ምክንያት ይሆናል ነው የሚባለው፡፡

ዘገባው እንደሚለው ጭራሽ አንዳንድ ገበሬዎች ለረጅም ጊዜ የሚያስቀምጡት በቆሎ ነቀዝ እንዳይበላው በሚል በዲዲቲ አሽተው ያስቀምጡታል… ይህን ለጤና አደገኛ የሆነ ኬሚካልን ገበሬዎች እንደማንኛውም ሸቀጥ በቀላሉ ማግኘት መቻላቸውና እንደልባቸው እንደፀረ-ተባይ ኬሚካል መጠቀማቸው ሊያስከትል የሚችለው ማህበራዊ የጤና ጠንቅ የትየለሌ ነው ነው የሚባለው፡፡

16 ሚሊየን ያህል ኢትዮጵያውያን የሚቅሙት ጫት ላይ ዲዲቲ የመረጨቱ ነገር አሳሳቢ ነው የሚለው ዘገባው፤ ጫቱ ላይ ያለውን ተባይ ለማጥፋት እና ጫቱ ‘ሻይን’ እንዲያደርግ፣ እንዲያምር በሚል ዲዲቲ ይረጭበታል ይላል፡፡ በጫቱ ቅጠል ውስጥ ሰርጎ የሚገባው ዲዲቲ ቢታጠብም አይወጣም የሚሉት ባለሞያ መርዛማው ኬሚካል አፈር ውስጥ ከ15 ዓመት፤ ውሃ ውስጥ ደግሞ ከ150 ዓመታት በላይ ይቆያል ይላሉ…ሙሉውን ያዳምጡ

ትዕግስት ዘሪሁን

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የጉለሌው “በአቅም መኖር” ሰፈር

የጉለሌው “በአቅም መኖር” ሰፈር፣ ግዙፍ ቪላዎች ከደሳሳ ጎጆዎችና ከላስቲክ ቤቶች ጋር ጎን ለጎን የሚኖሩበት ነው፡፡ ጥረው ግረው፣ በቀን ሥራ እና ቅጠል በመልቀም የሚተዳደሩት የሰፈሯ ነዋሪዎች ፈፅሞ ዝቅተኝነት አይሰማንም - ከሰራን እኛም የምንፈልግበት መድረሳችን አይቀርም ባይ ናቸው…

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የአዲስ አበባ የላዳ ታክሲ ባለቤቶችንና ሾፌሮችን ሰብስቦ ዛሬ ረፋድ መከራቸው

የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የአዲስ አበባ የላዳ ታክሲ ባለቤቶችንና ሾፌሮችን ሰብስቦ ዛሬ ረፋድ መከራቸው፡፡በባለስልጣኑ መስሪያ ቤቱ የመንገድ ደህንነት ትምህርትና ግንዛቤ ዳይሬክተሩ አቶ ዮሐንስ ለማ ለሸገር ሲናገሩ ላዳ ታክሲዎች ከመደበኛው የከተማው ትራንስፖርት አገልግሎታቸው ባለፈ በርካታ የውጪ ሀገር ዜጎችን ከኤርፖርት፣ ሆቴል፣ ከቦታ ቦታ የሚያዘዋውሩ በመሆናቸው የሾፌሮቻቸው ሥነ ምግባርና የታክሲዮቹ የቴክኒክ ብቃት የተስተካከለ መሆን ስላለበት ነው ለባለቤቶቻቸውና ለሾፌሮቻቸው ምክር መስጠት ያስፈለገው ብለዋል፡፡

በከተማው የአንዳንድ ላዳ ታክሲ ሾፌሮች መጠጥን በውሃ መያዣ ላስቲኮች በመያዝ፣ ጫት በመቃም በሌሎችም የባህሪ ችግሮች ውስጥ ሆነው መኪኖቹን ማሽከርከራቸው አሮጌና የቴክኒክ እክል የበዛባቸው ላዳዎች መብዛታቸው ለዛሬው የምክር ፕሮግራም መነሻ ሆኗል ሲሉ ለሸገር ተናግረዋል፡፡

ሾፌሮቹ ቀንም ሌሊትም መንዳታቸው ለትራፊክ መንስኤ እየሆነ ነው ተብሏል፡፡ በፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን አዳራሻ ዛሬ ለግማሽ ቀን በተከናወነ ፕሮግራም ላይ 1 ሺ የሚሆኑ የላዳ ባለንብረቶችና ሾፌሮችም የተገኙ ቢሆንም፤ በቂ አይደለም እንዲህ ያለው ምክር ወደፊትም ይሰጣል ብለዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከ7 ሺህ በላይ የላዳ ታክሲዎች አሉ ተብሏል፡፡

ወንድሙ ኃይሉ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

11 የሚደርሱ የፌዴራል የመንግስት መስሪያ ቤቶች ሀላፊዎችና ሰራተኞች ሀብት አናስመዘግብም ማለታቸው ተሰማ

11 የሚደርሱ የፌዴራል የመንግስት መስሪያ ቤቶች ሀላፊዎችና ሰራተኞች ሀብት አናስመዘግብም ማለታቸው ተሰማ፡፡የፌዴራል የሥነ-ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በየደረጃው ከሚገኙ የሥነ-ምግባር መኮንኖችና ከክልል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽነሮች ጋር ውይይት ሲያደርግ ነው ይህንን የሰማነው፡፡

በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ያሉ ሀላፊዎች ተባባሪ አለመሆን የፀረ ሙስና ትግሉ ከሚፈለገው ደረጃ ላይ እንዳይደርስ ማድረጉን ተነግሯል፡፡ተቋማዊ ሙስና የመከላከል እስትራቴጅንም ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁነት የላቸውም ተብሏል፡፡

የሥነ ምግባር መኮንኖች የአቅም ማነስና የግንዛቤ ችግሮችም ሌሎቹ የፀረ ሙስና ትግሉ ፈተናዎች መሆናቸውም ተጠቅሷል፡፡የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች ተጠሪነታቸው የሚገኝበት መስሪያ ቤቶች ሀላፊዎች መደረጉ ሙስናን የመከላከል አቅማቸውን የሚያዳክም መሆኑን ተወያዮች አንስተዋል፡፡ 

ተጠሪነታቸው ለሀላፊዎች ከሚሆን ለፌዴራሉ የሥነ-ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን መሆን አለበት ብለዋል፡፡በየደረጃው ያሉ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ሀላፊዎች በሹመት የሚቀመጡ መሆናቸው ሙስናን በሚፈለገው ደረጃ ታግሎ ውጤታማ ማድረግ ይቻላል የሚል እምነት እንደሌላቸውም ተወያዮች ሲናገሩ ሰምተናል፡፡

በውይይቱ ከህብረተሰቡ ጋር ቀን ከቀን ግንኙነት ያላቸው የመንግስት ተቋማቶች ሙስናና ብልሹ አሰራሮች የጎሉ በመሆናቸው ዳግም መታየትና መፈተሽ ይኖርባቸዋል ተብሏል፡፡

በየነ ወልዴ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የአፄ ቴዎድሮስ ህልፈተ ሕይወት 150ኛ አመት ከትውልድ ቦታቸው ቋራ እስከ ተሰዉበት ቦታ መቅደላ በድምቀት በልዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ተናገረ

የአፄ ቴዎድሮስ ህልፈተ ሕይወት 150ኛ አመት ከትውልድ ቦታቸው ቋራ እስከ ተሰዉበት ቦታ መቅደላ በድምቀት በልዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ተናገረ፡፡የቢሮው የኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ ኃይለየሱስ ፍላቴ ከባህልና ቱሪዝም ቢሮው ጋር የጎንደር፣ የደብረ ታቦርና የወሎ ዩኒቨርስቲዎች ለበዓሉ ተባባሪዎች መሆናቸው ለሸገር ተናግረዋል፡፡

በጉብኝትና ሲምፖዚየም የሚከበረው የመይሳው 150ኛ ዓመት ከመጋቢት 11 ጀምሮ እስከ 18 ለአንድ ሳምንት እንደሚዘልቅ ከቢሮው ኮሚኒኬሽን ሀላፊ ሰምተናል፡፡የአንድነት፣ የአርቆ አሳቢነትና የጀግንነት ተምሳሌት የሆኑት አፄ ቴዎድሮስ በ1847 የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሆነው በደራስጌ ማርያም የንጉስ ነገሥትነት አክሊል ደፍተው አንድነትን በመሰነቅ እስከ 1860 ለ13 አመታት መምራታቸውን ታሪክ ያስረዳል፡፡

150ኛ ህልፈተ ሕይወት አመታቸው ሲከበርም ከአፄ ቴዎድሮስ ታሪክ ጋር ትስስር ያላቸው ስፍራዎች ይጎበኛሉ ተብሏል፡፡ከነዚህም መካከል ጉብኝቱ ተወልደው ባደጉባት ቋራ ቸርኬ ማርያም ጀምሮ የነገሱበት ጃን አሞራ ደራስጌ ማርያምን አካቶ ዋና ከተማቸው አድርገዋት የነበረችው ደብረ ታቦርንና የጦር መስሪያ ኢንዱስትሪ መንደራቸው ጋፋትና አካባቢውም ይጎበኛል ተብሏል፡፡

ንጉሠ ነገስቱ ራሳቸው በመሳተፍ ያሰሩትና ሴባስቶፓል መድፍ የተጎተተበት የጉዞ መስመር እንዲሁም የመጨረሻ ቤተ መንግስት ሕይወታቸው ያለፈበት የመቅደላ አምባ እና የንጉሰ ነገሥቱ የጦር ጄኔራል ፊታውራሪ ገብርዬ ከእንግሊዞች ጋር ተዋግተው ህይወታቸው ያለፈበትና አስክሬናቸው ያረፈበት ታሪካዊው የእሮጌ የጦር ሜዳ እንደሚጎበኝ ሰምተናል፡፡

በጉብኝቱ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የመገናኛ ብዙሃን ተሳታፊ እንደሚሆኑም ሰምተናል፡፡ከወራት በፊትም በደብረ ታቦር ከተማ የዘመናዊነት ህልማቸውን የሚያሳይ ሐውልት እንደተሰራላቸው ይታወሳል፡፡አፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መሳፍንትን በመግታት አንድ የዘመነች ኢትዮጵያ እንድትኖርም ስለመልፋታቸው ታሪክ ያስረዳል፡፡

ምስክር አወል
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ኢትዮጵያ ወደፊት በሚስፋፋው የበርበራ ወደብ ተርሚናል 19 በመቶ ባለድርሻ እንድትሆን የሚያስችላትን ስምምነት መፈራረሟ መዘገቡ ይታወቃል

ኢትዮጵያ ወደፊት በሚስፋፋው የበርበራ ወደብ ተርሚናል 19 በመቶ ባለድርሻ እንድትሆን የሚያስችላትን ስምምነት መፈራረሟ መዘገቡ ይታወቃል፡፡ ስምምነቱ በሶማሌያ በኩል ተቃውሞ ሲገጥመው በጅቡቲ በኩል ቅሬታ አሳድሯል፡፡ የእሸቴ አሰፋ ዝግጅት ስምምነቱንና አንደምታውን ይመለከታል፡፡

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ቸል የተባለው የትውልድ ፈተና - ሱሰኝነት

ይህ የሸገር የ“ስንክሳር” ዶክመንተሪ በሐገራችን በአደገኛ ሁኔታ በተዛመተው የሱሰኝነት ጉዳይና ይዞት በመጣው የአእምሮ ሕመም መስፋፋት ላይ ያተኩራል፡፡ ከአራት ኢትዮጵያውያን አንዱ የአእምሮ ሕመም ተጠቂ ነው የሚለው ይህ ዶክመንተሪ ከአእምሮ ሕመም ሰበቦች አንዱ የሱስኝነት መስፋፋት ነው ይለናል…

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

እድሜያቸው ከ10 እስከ 24 ዓመት ከሚሆናቸው ኢትዮጵያውያን ወጣቶች 51 % ያህሉ ጫት ቃሚዎች ናቸው...

እድሜያቸው ከ10 እስከ 24 ዓመት ከሚሆናቸው ኢትዮጵያውያን ወጣቶች 51 % ያህሉ ጫት ቃሚዎች ናቸው - 45.6 %ቱ ደግሞ የአልኮል መጠጥ ይጠጣሉ - ጥናት…የሸገሩ ንጋቱ ሙሉ ዘገባ - ኢትዮጵያ ወጣቶችዋ በሱስ፣ በጤና እክል፣ በሥነ ልቦናዊ እና የሥነ ተዋልዶ ችግሮች ተተብትበዋል ይለናል፡፡ ጫት፣ ሺሻ፣ የአልኮል መጠጦች እና ማሪዋናን የሚወስዱ ወጣቶች ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ ነው፡፡

ከኢትዮጵያውያን ወጣቶች 45.6 ከመቶዎቹ የአልኮል መጠጥ ይጠጣሉ፤ 51 ከመቶዎቹ ደግሞ ጫት ቃሚ ሆነዋል የሚለው ይህ ዘገባ ከቃሚዎቹ መካከል 56.6 ከመቶዎቹ ወንዶች ናቸው ይላል፡፡ከሱሱም በተጨማሪ ኤች አይ ቪ፣ የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽን፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እና ራስን ማጥፋት የበርካታ ወጣቶችን ሕይወት የሚቀጥፉ ሰበቦች ናቸው ተብሏል፡፡

ለችግሩ አስከፊ ደረጃ ላይ መድረስ ዋንኛው ሰበብ ሕጎች ቢኖሩም ሕጎቹን የሚተገብራቸው አካል አለመኖሩ ነው፡፡ወጣቶችንም የመፍትሄው አካል ማድረግ ይገባል ነው የተባለው…

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

አዲስ አበባ በሚገኙ ሥጋ ቤቶች ላይ ከልኬት ጋር የተገናኘ ሰፋ ያለ ችግር እንዳለ ተነገረ

አዲስ አበባ በሚገኙ ሥጋ ቤቶች ላይ ከልኬት ጋር የተገናኘ ሰፋ ያለ ችግር እንዳለ ተነገረ፡፡ ከ1 ኪሎ ሥጋ እስከ 123 ግራም አጉድለው ለተጠቃሚው የሚሸጡ ሥጋ ቤቶች እንዳሉ ሰምተናል፡፡የንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን በተለያዩ ሥጋ ቤቶች ላይ ያካሄደውን ምልከታ ውጤት ዛሬ ይፋ አድርጓል፡፡

ባለስልጣኑ የምልከታ ውጤቱም በኢትዮጵያ ሆቴል ይፋ ያደረገው በአገር አቀፍ ደረጃ ዛሬ በተከበረው የሸማቾች ቀን መድረክ ላይ ነው፡፡ሥጋ ቤቶቹ ለተጠቃሚው የሚሸጡትን ሥጋ በሚለኩበት ሚዛን በየአመቱ ማረጋገጫ ማግኘት እንዳለባቸው ተነግሯል፡፡ምልከታው ከተካሄደባቸው ሥጋ ቤቶች መካከል ግን 64 በመቶው የልኬት ማረጋገጫው የላቸውም ተብሏል፡፡

ችግሩ ለሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራትና በግል ሥጋ ቤቶች የሚታይ እንደሆነም ተነግሯል፡፡በተቃራኒው የግል የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቆች ከልኬት አኳያ የተጋነነ ችግር እንደሌለባቸው ሲነገር ሰምተናል፡፡ባለስልጣኑ ምልከታ ካካሄደባቸው 75 የግል የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቆች 49ኙ ወይም 65 ነጥብ 3 በመቶ ምንም ዓይነት የልኬት ችግር አልተገኘባቸውም ተብሏል፡፡

የተቀሩት ግን ደረጃው ቢለያይም የልኬት ችግር እንዳለባቸው ታውቋል፡፡የዘንድሮ የሸማቾች ቀን በአገራችን የተከበረው “በተደራጀው የህብረተሰብ ተሳትፎ የምርት ጥራት ይረጋገጣል” በሚል መሪ ሀሳብ ነው፡፡

ንጋቱ ረጋሳ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

በጅቡቲና በኢትዮጵያ ድንበር አስተዳዳሪዎች መካከል በተደረገው የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ላይ ስምምነቶች መደረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ተናገሩ

በጅቡቲና በኢትዮጵያ ድንበር አስተዳዳሪዎች መካከል በተደረገው የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ላይ ስምምነቶች መደረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ተናገሩ፡፡በአፋር ከተማ ሰመራ የተደረገው የሁለቱ አገራት 24ኛ የድንበር ኮሚሽን ስብሰባ ላይ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስቆም እና ህገ-ወጥ ንግድን ለመቆጣጠርም ሁለቱ የድንበር አስተዳዳሪዎች መስማማታቸው ተነግሯል፡፡

23ኛው የሁለቱ አገራት የድንበር ኮሚሽን ስብሰባ ዲግል ጅቡቲ ውስጥ የተደረገ ሲሆን በወቅቱ የተስማሙባቸው ነጥቦች ከምን እንደደረሱ በዚህ ጉባኤ ላይ መሰማቱ ተነግሯል፡፡ከድንበር በተጨማሪ በኢትዮጵያ እና በጅቡቲ መካከል የወደብ አገልግሎት የተመለከተ ንግግር መደረጉንም ሰምተናል፡፡

በጅቡቲና በኢትዮጵያ መካከል ከ12 እስከ 15 ቢሊዮን ዶላር የመሰረተ ልማት ትስስር እንዳለም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡ከሱማሌላንድ ጋር የኢትዮጵያ መንግስት ያደረገውን የበርበራ ወደብ ስምምነትን የሶማሊያ መንግስት መቃወሙን በተመለከተ ለቃል አቀባዩ ጥያቄ ቀርቦላቸው በሰጡት መልስ ከሱማሌላንድ ጋር ኢትዮጵያ የሚኖራት ግንኙነት የሎጅስቲክ በመሆኑ የሱማሊያና የሶማሌላንድ መንግስት የውስጥ ጉዳይ በመሆኑ አያገባንም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ላለው የህዝብ ቁጥሯ የሚመጥን የወደብ አገልግሎት ስለሚያስፈልጋት ከጅቡቲ በተጨማሪ አማራጭ ወደቦችን መመልከት ግድ ይለናል፡፡ እና በዚያ መሰረት እየሰራነው ሲሉ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ የቃል አቀባይ ጽ/ቤት በመስሪያ ቤቱ የመዋቅር ማስተካከያ ከተደረገ ወዲህ የስራ ክንውኑን በሚመለከት የሚሰጠው መደበኛ ሳምንታዊ መግለጫ 1 አመት እንዳስቆጠረም ቃል አቀባዩ ጨምረው ተናግረዋል፡፡

የኔነህ ሲሳይ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)
Sheger 102.1 AudioNow Numbers