• Slider One

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Slider Two

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Sldier Three

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ሸገር ወሬዎች እና ልዩ ወሬዎች

አርብ አርብ ይካሄድ የነበረው የካቢኔ ስብሰባ ወደ ቅዳሜ መዛወሩን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ

ዶክተር አብይ ከሚኒስትሮች ፤ ሚኒስትር ዴኤታዎችና ዋና ዳይሬክተሮች ጋር ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ውይይት አድርገዋል፤ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በፊት በየሳምንቱ አርብ ጠዋት በስራ ሰዓት ሲካሄድ የነበረው የካቢኔ ስብሰባ ወደ ቅዳሜ ጠዋት መዛወሩን በውይይቱ ላይ ተናግረዋል፤በስብሰባ ላይ በማይገባ ክርክርና ጭቅጭቅ የሚባክኑ ሰዓቶችን ለመቀነስ ጥረት እንደሚደረግ መናገራቸውንም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት መረጃ አስፍሯል

ሚኒስትሮች አርብ በስብሰባ ስም ጊዜ ማባካን እንደሌለባቸው ማሳሰባቸውን ደግሞ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጽፏል፤እያንዳንዱ ሚኒስትር ከዚህ በኋላ ለስብሰባ ሲመጣ በቂ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባው የተናገሩት ዶክተር አብይ፤ “ሚኒስትር ሃሳብ አመንጪ እንጂ አቃቂር አውጭ አይደለም” ብለው መናገራቸው ተሠምቷል

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የስብሰባዎች መብዛትና መንዛዛት የመንግስት የስራ ጊዜ ላይ ተጽዕኖ እንዳለው ከዚህ ቀደም መናገራቸው ይታወሳል።በውጭ ሀገራት ባንኮች *የባንክ ሂሳብ* ወይም አካውንት ያላቸው ባለስልጣናት በአካውንቶቻቸው ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋልየባለስልጣናቱን አካውንት በማጣራቱ ተግባር ሀገራትም እየተባበሩ ናቸው ብለዋል

በቀጣይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልዩ ልዩ ቋሚ ኮሚቴዎች ከሚመለከታቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር የስራ ስምምነት እንዲፈጽሙ እና ስራውን በዚሁ አግባብ እንዲሰሩ አዘዋል፤
እያንዳንዱ የመንግስት ተሿሚ አሰራሩን ግልጽና ለህዝብ የማይደበቅ ማድረግ አለበትም ብለዋልጠቅላይ ሚኒስትሩ በውይይቱ ላይ የራሳቸውን ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርበዋል የተባለ ሲሆን የአመራር ጥበብን የተመለከተ ገለጻ ማድረጋቸውንም ሠምተናል

ባቀረቡት ጽሁፍ ላይ ስራን ከማቀድ ጀምሮ እስከሚጠናቀቅበት ጊዜ ድረስ በምን ያህል ጊዜና ወጪ መስራት እንደሚገባ አብራረተዋል ተብላል፤ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለስልጣናት ኢትዮጵያ አድጋለች ከማለት ባሻገር በተጨባጭ ህዝቡ ምን ያህል ተጠቅሟል የሚለውን መፈተሽና ማረጋገጥ እንዳለባቸው አሳስበዋል

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከውይይቱ በሁዋላ ባለስልጣናቱን በአጼ ሚኒሊክ፣ በአጼ ኃይለሥላሴ እና በደርግ ዘመን የተለያዩ ታሪካዊ ድርጊቶች የተፈጸሙባቸውና በቤተመንግስት የሚገኙ- እስካሁንም ድረስ ዝግ የነበሩ የተለያዩ ክፍሎችን አስከፍተው እንዲጎበኙ አድርገዋል።በዚህም ባለስልጣናቱ የነገስታቱን የግብር ቤቶች፣ አጼ ሀይለስላሴ የተገደሉበትንና የደርግ ጄኔራሎች የተረሸኑባቸውን ክፍሎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት ጎብኝተዋል።

ንጋቱ ረጋሳ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

አምስት የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ጡረታ ወጡ፡፡

ጡረታ እንደወጡ ከተጠቀሱት መካከል ጎምቱ የህወሀት መስራችና የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዮት ዋና ዳሬክተር ጄነራል አቶ ስብሃት ነጋ እንደሚገኙበት የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት አስታውቋል፡፡
 
ፅ/ቤቱ ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችው ማሻሻያ /ሪፎርም/ የተሳካ እንደሆነ የማድረጉ ስራ እንዲሁም ለህዝብ የልማትና ለውጥ ፍላጎት ተገቢ ምላሽ የመስጠቱ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያግዙ እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሚገኙ ጠቅሷል፡፡ከነዚህ እርምጃዎች መካከል ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ እያካሄዱት ያለው የካቢኔ ለውጥ ይገኝበታል ብሏል፡፡
 
ዶ/ር አብይ የተለያዩ የመንግስት ተቋማት በአዳዲስ ሀላፊዎች እንዲመሩ እያደረጉ ይገኛሉ ያለው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ከዚህ ስራ ጋር በተያያዘም ለበርካታ አመታት በመንግስት ሀላፊነት ቦታዎች ያገለገሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች በጡረታ እንዳያርፉ እየተደረገ ይገኛል ሲል ተነግሯል፡፡
 
በጡረታ እንዲያርፉ የተደረጉትም የህወሀት መስራች የነበሩትና የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዮት ዋና ዳሬክተር ጀነራል የሆኑት አቶ ስብሃት ነጋ/አብይ ስብሃትን ጨምሮ አምስት ናቸው፡፡ እነሱም ከፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ዶክተር ካሱ ኢላላ ፣ ከተቀናጀ የመሬት አጠቃቀም እቅድና ፖሊሲ ዝግጅት ፕሮጀክት አቶ በለጠ ተፈራ ፣ ከንግድና ኢንዱስትሪ የፖሊሱ ዕቅድ አፈፃፀም ክትትል አቶ ታደሰ ሀይሌ እንዲሁም ከፖሊስ ምርምር ማዕከል አቶ መኮንን ማንያዘዋል መሆናቸው ተገልፃል፡፡
 
ወደፊትም ለረጅም ጊዜ በመንግስት ሀላፊነት እየሰሩ ያሉ ሀላፊዎች በጡረታ እንዲያርፉ የማድረጉ ስራ ይቀጥላል ሲል ጽ/ቤቱ ተናግሯል፡፡

ንጋቱ ሙሉ
 
 
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

በኢትዮጵያና በቼክ ሪፐብሊክ መካከል ባለው የንግድ ግንኙነት የኢትዮጵያ ድርሻ ዝቅተኛ መሆኑ ተነገረ

በቼክ ኤምባሲ በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት እና በቼክ ሪፐብሊክ ንግድ ምክር ቤት ትብብር በተዘጋጀ የንግድ ልውውጥ መድረክ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ኤልያስ ገነቴ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ ወደ ቼክ ሪፐብሊክ ያደላ መሆኑ ተናግረዋል፡፡

ቼክ ከኢትዮጵያ የተቆላ ቡና ፣ የተፈተገ ሰሊጥ እና ሌሎችም ምርቶችን በብዛት ብትፈልግም ኢትዮጵያውያን አምራቾችና ላኪዎች ደረጃውን የጠበቀ አለም አቀፉን መስፈርት የሚያሟላ አቅርቦት ስለሌላቸው ሊገኝ የሚችለውን የውጪ ምንዛሬ እንዳያስገቡ እንቅፋት ሆኖባቸዋል ብለዋል ፕሬዝዳንቱ ፡፡የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አምራቾችና ላኪዎች የሚጠበቅባቸውን መስፈርት እንዲያሟሉ ለማስቻል እየሰራ መሆኑንም አቶ ኤልያስ ተናግረዋል፡፡

በማኒፋክቸሪግ ዘርፍ በአለም ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸው የቼክ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያደርጉ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤትና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተባብረው ሊሰሩ ይገባል ተብሏል፡፡በዝግጅቱ ላይ የተለያዩ የቼክ ሪፐብሊክ ኩባንያዎች ልምዳቸውን ያካፈሉ ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ለመስራት ያላቸውን ቀጥተኛ ፍላጎት አሳይተዋል፡፡

ማህሌት ታደሰ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ኒውትሪሽን ኢንተርናሽናል የተባለው አለም አቀፍ ድርጅት ዛሬ በሂልተን ሆቴል ኢትዮጵያ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ስኬትና ወደፊት ተስፋዎችን በተመለከተ ውይይት አካሂዷል

ኢትዮጵያ ሴቶች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ እና ጤናቸው እንዲጠበቅ የምታደርገውን ጥረት በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር የሆኑት ፊሊፕ ቤከር አድንቀዋል፡፡ የአንዲት አገር ዜጎች ጤናማና የዳበሩ ሆነው መገኘት ለተቀረው አለም ስኬት ነው ያሉት አምባሳደሩ ይህም የሚሳካው የተመጣጠነ ምግብ ለዜጎች በማቅረብ ነው ብለዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ከአምባሳደሩ በተጨማሪ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የእናቶችና የህፃናት ጤናና የተመጣጠነ ምግብ ዳይሬክተር ዶ/ር ኤፍሬም ታከለም ኢትዮጵያ በድህነት ቅነሳና የህፃናት ሞት ዙሪያ አመርቂ ስራዎችን ብትሰራም የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ግን መቀነስ አልቻለችም ብለዋል፡፡ ከአራት እናቶች አንዷ አሁንም ደም ማነስ እንደሚይዛት ተናግረዋል፡፡

ይህንንም በብሄራዊ የተመጣጠነ ምግብ ፕሮግራም ለመቀነስ መንግስት ቁርጥ አቋም ይዟል ብለዋል፡፡ኒውትሪሽን ኢንተርናሽናል ለዜጎች የተሻለ የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት እያደረገ ያለው ድጋፍም አድንቀዋል፡፡ኒውትሪሽን ኢንተርናሽናል እ.ኤ.አ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ቢሮውን በአዲስ አበባ ከከፈተ ወዲህ ከ90 ሚሊዮን የካናዳ ዶላር በላይ ድጋፍ እንዳደረገ ተናግሯል፡፡ኢትዮጵያ ኒውትሪሽን ኢንተርናሽናል ከተባለው ድርጅት ጋር በጥምረት መስራት ከጀመረች 20 አመታት ተቆጥሯል፡፡

ቴዎድሮስ ብርሃኑ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የኦሮሚያ ክልል የአሽከርካሪዎችና የቴክኒሽያኖች ብቃት ማረጋገጫ ማዕከል ከኦሮምኛ እና አማርኛ በተጨማሪ በሌሎች የአገራችን ቋንቋዎች ስልጠና ለመስጠት ዝግጅቴን ጨርሻለሁ አለ

የኦሮሚያ ክልል የአሽከርካሪዎችና የቴክኒሻኖች ብቃት ማረጋገጫ ማዕከል በአዳማ ስራ ጀምሯል፡፡በክልሉ እንዲቋቋሙ ለታሰቡ ሌሎች የአሽከርካሪዎችና የቴክኒሻኖች ብቃት ማረጋገጫ ማዕከላት እንደሙከራ እንዲያገለግል ታስቦ ስራ መጀመሩ ተነግሯል፤ተጨማሪ ማዕከላትን ሻሸመኔ ፤ ጅማ እና ነቀምት ላይ የማቋቋም ዕቅድ እንዳለ ሠምተናል፡፡የኦሮሚያ ክልል የአሽከርካሪዎችና የቴክኒሻኖች ብቃት ማረጋገጫ ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ አሠፋ እንዳሉት ማዕከላቱን በከተሞቹ ለማቋቋም የመሬት ርክክብን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

የአዳማው ማዕከል ለአሽከርካሪዎችና ቴክኒሻኖች ስልጠናውን እየሰጠ ያለው በአማርኛ እና ኦሮምኛ ቋንቋ እንደሆነ አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል፤ወደፊት ግን ስልጠናው የሚሰጥባቸውን ቋንቋዎች እናበዛለን ብለዋል፤በአዳማው ማዕከል እስከ አሁን በሶስት ዙር ለአሽከርካሪዎችና ቴክኒሻኖች ስልጠና መሰጠቱን ሠምተናል፡፡

ንጋቱ ረጋሳ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

በኢትዮጵያ የቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ወጪ ንግድ እየጨመረ ቢሆንም ከአመት አመት የሚያሳየው ጭማሪ ግን ቀርፋፋ መሆኑ ተሰማ

ይህ የተሰማው የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የ9 ወራት የስራ አፈፃፀሙን የተመለከተ ሪፖርት ዛሬ ለሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት ነው፡፡የቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ንግድ የጥራት ደረጃውን ጠብቆ ለውጪ ገበያ እንዲላክ ቢደረግም የሚላከው መጠን ግን ከአመት አመት አጥጋቢ የሆነ ጭማሪ አያሳይም ተብሏል፡፡

የምርጥ ዘርና የኢንዱስትሪ ግብአት የአቅርቦት ችግር ፣ ሕገ-ወጥ የንግድ ዝውውር መኖር ለቡናና ሻይ ወጪ ንግዱ በተፈለገው መጠን እድገት አለማሳየት ምክንያቶች እንደሆኑ ተነግሯል፡፡በ2010 በጀት አመት 9 ወራት ከ159 ሺ ቶን በላይ ቡና ለውጪ ገበያ ተልኮ ከ560 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል ተብሏል፡፡የቡና ወጪ ንግዱ ካለፈው አመት ጋር ሲመሳከር በመጠንና በገቢ ጭማሪ ማሳየቱ ተነግሯል፡፡

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በ9 ወራት ሪፖርቱ ከ1 ሺ 364 ቶን በላይ የሻይ ምርት ደግሞ ለውጪ ገበያ መላኩንና በዚህም ከ2 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱን ለቋሚ ኮሚቴ ተናግሯል፡፡በበጀት አመቱ የቅመማ ቅመም ወጪ ንግድ ከ8 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ቢገኝም የቅመማ ቅመም ምርቱ በመጠንም ሆነ በገቢ ቅናሽ የታየበት ነው ተብሏል፡፡

በተለይ የቡና ምርታማነት መቀነስ ላይ ያረጀ ቡና የመሬት ሽፋን መጨመር ፣ የበሽታ ስርጭት መጨመር ፣ አዳዲስ የቡና ችግኞችን አለመጠቀምና ሌሎችም ምክንያቶች ናቸው ተብሏል፡፡በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለችግሮቹ ማስተካከያ ለማድረግ ምን ታስቧል የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎች በቋሚ ኮሚቴ አባላት ተነስቷል፡፡የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የስራ ሀላፊዎች በቋሚ ኮሚቴው ተገኝተው ምላሽ እየሰጡ ነው፡፡

ምህረት ስዩም
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ኢትዮ ቴሌኮም ጂቱጂ ለተባለ አገር በቀል ኩባንያ የኢንተርኔት አቅራቢነት ፈቃድ መስጠቱን ዛሬ ተናግሯል

ኩባንያው በኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሰርቨር ስር በመጠቀም ለተቋማት፣ መኖሪያ ቤቶች እና ለግለሰቦች ኢንተርኔት እንዲያቀርብ ስምምነት ተደርጓል፡፡በአዲስ አበባ በ7 አካባቢዎች ማለትም በቦሌ ፣ አያት ፣ ሲኤምሲ፣ ሃያ ሁለት እና በሌሎች አካባቢዎችም የኢንተርኔት አገልግሎቶችን መስጠት የሚያስችለውን ስምምነት ፈፅሟል፡፡

የኔነህ ሲሳይ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

በኢትዮጵያ የተገነቡ ወጣት ማዕከላት የታቀደላውን ሥራ እየሰሩ አይደለም ተባለ

በ2002 ለወጣቶች ማዕከላት የወጣው አገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ አሁን ያለውን የወጣቱን አስተሳሰብና ፍላጎት እንደማይመጥን ተነግሯል፡፡ይህን የሰማነው ዛሬ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር በወጣቶች ስብዕና ግንባታ ዙሪያ በየደረጃው ካሉ አመራሮችና ከተወካዮች ምክር ቤት ማህበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር እያደረገ ባለው ውይይት ነው፡፡

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተደረገ የዳሰሳ ጥናት እንዳሳየው ከሆነ የተገነቡ ወጣት ማዕከላት የአገልግሎት ደረጃ አሰጣጣቸው ብቻ ሳይሆን የግንባታ ዲዛይናቸው ላይ ችግር አለበት ብሏል፡፡ወደፊት የሚገነቡት የወጣት ማዕከላት ዲዛይናቸው መሻሻል እንዳለበትም ጥናቱ አመላክቷል፡፡

አገልግሎት አሰጣጡም በደረጃ የተከፈለ፣ ቴክኖሎጂን ያካተተና የወጣቶችን የፈጠራ ስራ የሚያበረታታ መሆን አለበትም ብሏል፡፡በኢትዮጵያ ከ9 መቶ በላይ ወጣት ማዕከላት ቢኖሩም በአግባቡ ወጣቶችን እያገለገሉ እንዳልሆኑ ሰምተናል፡፡

ከአዲስ አበባ ውስጥ ካሉት በስተቀር በክልል ያሉት ወጣት ማዕከላት ቋሚ ሰራተኞች እንደሌላቸውም በጥናቱ ቀርቧል፡፡ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ማዕከላቱ ያለባቸውን ችግሮች ይቀርፋል የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃቸውንም ከፍ ያደረጋል ያለውን የመፍትሄ ሀሳብ አቅርቦ እያወያየበት ይገኛል፡፡

አስፋው ስለሺ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም የህክምና ኮሌጅ በብቸኝነት የሚሰጠው የኩላሊት ህክምና እና ንቅለ ተከላ ከአሁን በኋላ ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ...

በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም የህክምና ኮሌጅ በብቸኝነት የሚሰጠው የኩላሊት ህክምና እና ንቅለ ተከላ ከአሁን በኋላ ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ የህክምና ባለሙያዎች ይደረጋል ተባለ፡፡ከ2 አመት 9 ወራት በፊት በዚሁ ሆስፒታል የተጀመረው የኩላሊት እጥበት እንዲሁም የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምናው ይሰጥ የነበረው ከአሜሪካው ሚችጋን ዩኒቨርሲቲ የመጡ ሀኪሞች ከኢትዮጵያውያን ጋር በጋራ በመሆን ነበር፡፡

ህክምናው ሙሉ በሙሉ በሀገር ቤት ሀኪሞች እንዲደረግም በኩላሊት ህክምና ተጨማሪ ትምህርት በመውሰድ ስፔሻላይዝድ ያደረጉ ሀኪሞች ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ስራ መግባታቸውን አቶ ንዋይ ፀጋዬ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም የህክምና ኮሌጅ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ለሸገር ተናግረዋል፡፡የኩላሊት ህክምናና ንቅለ ተከላ ማዕከሉ በኢትዮጵያ እንዲጀመር አስተዋጽኦ ያበረከቱ ግለሰቦችም እና ሀላፊዎችም ሆስፒታሉ እውቅና መስጠቱን አቶ ነዋይ ነግረውናል፡፡

ሆስፒታሉ የኩላሊት ህክምናው በሌሎች ሆስፒታሎችም እንዲጀመር ተጨማሪ ሐኪሞች እና ነርሶች እያሰለጠነ እንደሆነም ተነግሯል፡፡የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም የህክምና ኮሌጅ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ማዕከል ህክምና ከጀመረ ጊዜ አንስቶ እስካሁን በሆስፒታሉ ከ80 በላይ ለሆኑ ሰዎች የኩላሊት ንቅለ ተከላ ማድረጉን ሰምተናል፡፡

ምህረት ሥዩም

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የተሻሻለው የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ ከአሽከርካሪዎች በተጨማሪ ሌሎች አጥፊዎችንም በተለያየ መንገድ የሚቀጣ ነው ተባለ

አጥፊ እግረኞች፣ የትራፊክ ተቆጣጣሪዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ከአሽከርካሪዎች ውጪ ያሉ ደንቡ የሚቀጣቸው ናቸው ተብሏል፡፡በዚሁ ደንብ መሰረት እንስሳትን በመንገድ ላይ የነዳ ሰው 2 መቶ ብር ይቀጣል፡፡የእግረኛ መንገድ በሌለበት መንገድ ላይ ቀኝ ጠርዝን ይዞ መጓዝ እና ለእግረኛ ተብሎ ከተከለለ መንገድ ውጪ መጓዝም እያንዳንዳቸው 40 ብር የሚያስቀጡ ጥፋቶች እንደሆኑ ተነግሯል፡፡

ተገቢውን ጥንቃቄ ሳያደርግ ወይም የጆሮ ማዳመጫ በማድረግ መንገድ ያቋረጠ ሰው 80 ብር እንደሚቀጣ የፌዴራል የትራንስፖት ባለስልጣን ዘርፉን አስመልክቶ በአዳማ ከተማ ባዘጋጀው ስልጠና ላይ ሲነገር ሰምተናል፡፡በብረት ወይም በግንብ ተለይተው የታጠሩ መንገዶችን ዘሎ ማቋረጥም እንዲሁ 80 ብር ያስቀጣል ተብሏል፡፡

በእግረኛ መሄጃ መንገድ ላይ ንግድ ያከናወነ ወይም ቁሳቁስ በማስቀመጥ ለእንቅስቃሴ እንቅፋት የሆነ ሰው ደግሞ 40 ብር እንደሚቀጣ ደንቡ ይጠቅሳል፡፡እነዚህን ጥፋቶች ፈፅሞ ቅጣቱን በገንዘብ መክፈል የማይችል ሰው ተመጣጣኝ የሆነ የማህበራዊ አገልግሎት እንደሚሰጥ በአዲሱ የትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ ሰፍሯል፡፡አትክልት መኮትኮትና የትራፊክ ማስተናበር ስራ ከእነዚህ ማህበራዊ አገልግሎቶች መካከል ናቸው ተብሏል፡፡

የትራፊክ ቁጥጥር ተግባሩን ሲያከናውን ለመንገድ ተጠቃሚዎችና ለደንብ ተላላፊዎች ተገቢውን አክብሮት ያላሳየ የትራፊክ ተቆጣጣሪም የመጨረሻው የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እንደሚሰጠው ሰምተናል፡፡ጉቦ የተቀበለው ወይም የጠየቀ የትራፊክ ተቆጣጣሪ ደግሞ ከሀላፊነቱ እንዲነሳ በደንቡ ሰፍሯል፡፡እነዚህን ጥፋቶች የፈፀመ የትራፊክ ተቆጣጣሪ በህግ ጭምር ተጠያቂ እንደሚሆን ሰምተናል፡፡

ንጋቱ ረጋሳ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

በእናት ስም የተሰየመው እናት ባንክ በተመሰረተ በ5 አመቱ ሴቶችን በፋይናንስ ተጠቃሚ በማድረግ በኩል ስኬታማ ነበርኩኝ ሲል ተናገረ

ይህም የብሔራዊ ባንክን ህግ በጠበቀ መልኩ ሴቶችን ተጠቃሚ በማድረግ ማስያዣ ሳያስፈልግ ብድር ሲሰጥ መክረሙን የባንኩ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ኤርሚያስ አንዳርጌ ነግረውናል፡፡ለዚህም ከባንኩ ባለ ድርሻዎች ትርፍ 5 በመቶ እየተቀመጠ ሴቶች እንዲበደሩ እና በባንክ ተቀማጭ ያላቸው ፈቃደኛ ሰዎች ገንዘብ እንደ ተያዥ በመሆን ለሴቶች የብድር አገልግሎት የሚያገኙበትን መንገድ ሲተገብር እንደቆየ ሰምተናል፡፡

ባንኩ አሁን ላይ 41 ቅርንጫፎች እንዳሉት የተናገሩት አቶ ኤርሚያስ እኛ ማገዝ ያለብን ነገር ግን ከቅርንጫፎቻችን ለራቁ ሴቶች ለ3 ብድርና ቁጠባ ተቋማት 15 ሚሊዮን ብር በመስጠት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓልም ብለዋል፡፡እናት ባንክ በአ.አ የሚገኙ ቅርንጫፎችን ለሀገርና ማህበረሰብ ትልቅ ስራ በሰሩ ሴቶች ስም እንደሚሰይም የተናገሩት ምክትል ፕሬዝዳንቱ በየዘርፉ በርካታ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ለማፍራት ያለመ ስለመሆኑ ነግረውናል፡፡

ሴቶችን ለማበርታት የተቋቋመው የፋይናንስ ተቋም በተመሰረተ የመጀመሪያ አመት ለአባላቱ ትርፍ ያከፋፈለ ባንክ እንደሆነም ተነግሯል፡፡ባንኩ ሀገራዊ ግዴታን በመወጣት በኩሉም ለታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ እና ለሌሎች የልማት ፕጀክቶች የ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የቦንድ ግዢ ከብሔራዊ ባንክ መፈፀሙን ተናግሯል፡፡

ባንኩ ትናንት ምሽት በካፒታል ሆቴል ባዘጋጀው ፕሮግራሙ የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊን በወ/ሮ ሀና ጥላሁን መቀየሩን ይፋ አድርጓል፡፡350 ቋሚና 350 ጊዜያዊ ሰራተኖች እንዳሉት የተናገረው ባንኩ በባንኩ ገንዘብ ከሚያገቡት ውስጥ 56 በመቶዎች ሴቶች መሆናቸው ሲነገር ሰምተናል፡፡

ምስክር አወል

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)
Sheger 102.1 AudioNow Numbers