• Slider One

  የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

 • Slider Two

  የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

 • Sldier Three

  የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ሸገር ወሬዎች እና ልዩ ወሬዎች

በአመቱ ባደረገው ጥናትና ድንገተኛ ፍተሻ ከ1 ሺ 445 በላይ የንግድ ድርጀቶች ህገ-ወጥ ንግድና የታክስ ማጭበርበር ተግባር...

በአመቱ ባደረገው ጥናትና ድንገተኛ ፍተሻ ከ1 ሺ 445 በላይ የንግድ ድርጀቶች ህገ-ወጥ ንግድና የታክስ ማጭበርበር ተግባር መፈፀማቸውን ደርሼበታለሁ ያለው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ነው፡፡የንግድ ማጭበርበር፣ የታክስ ስወራ፣ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያን ህጉ በማይፈቅደው መልኩ መጠቀም፣ ለቀረጥ ነፃ የተሰጠ መብትን ያለ አግባብ መጠቀምና ሌሎችንም ህገ-ወጥ ተግባራት ፈፅመዋል ያላቸውን ከ1 ሺ 445 በላይ የንግድ ድርጅቶች ላይም ድርጅቱን ከማሸግ ጀምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዱን በዓመቱ የሥራ አፈፃፀም ሪፖርቱ አስፍሯል፡፡

ከመካከላቸውም የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢ ሆነው ደረሰኝ የማይቆርጡ 927 ድርጅቶች ተጠርጣሪዎችም ተይዘው ጉዳያቸው ለተጨማሪ የወንጀል ምርመራ ለሚመለከተው አካል ተላልፏል ተብሏል፡፡ሌሎች 42 ድርጅቶችም ከሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ጋር ተያይዞ ማስታወቂያ ባለመለጠፋቸውና 33 ድርጅቶችም አመታዊ የቴክኒክ ምርመራ ባለማድረጋቸው ጉዳያቸው ለአስተዳደራዊ ቅጣት ለሚመለከተው ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ተልኳል፡፡38 ድርጅቶችም ያለንግድ ፈቃድ ሲሰሩ ተገኝተው እንዲታሸጉ መደረጉን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የንግድ ገቢ ግብር ሲሰበስብ ተደጋጋሚ ኪሣራ የሚያሳውቁ ምንም የንግድ እንቅስቃሴ አልነበረንም ብለው ሪፖርት የሚያደርጉና አነስተኛ የንግድ ትርፍ በሚያሣውቁ በ483 ድርጅቶች ላይ ጥናትና የመረጃ ማሰባሰብ ሥራም ከውኗል፡፡በ109 ድርጅቶች ላይ ድንገተኛ የሠነድ ምርመራ በማካሄድም ለኦዲት ጠቃሚ የሆኑ ሰነዶችን ማግኘቱንና የ106ቱን ለሂሣብ ምርመራ ወደ ኦዲት መላኩን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በሪፖርቱ ተናግሯል፡፡

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ህገ-ወጦችን በመያዝና መንግሥት ሊያጣ የነበረውን ገቢ በማሰባሰብ ተግባሩ ከጠቋሚዎች ያገኘው መረጃ 91 በመቶ ውጤታማ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብሏል፡፡ለጠቋሚዎቹም በዚህ ዓመት ብቻ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ እንደከፈለ ተናግሯል፡፡

ትዕግስት ዘሪሁን

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ነሐሴ 17፣2009 የሸገር ወሬዎቻችን

 • የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር አቅም የሌላቸው ሴቶች በራሳቸው ፍትህ እንዲያገኙ የሚረዳ ሥርዓት ልፈጥር ነው አለ፡፡ (ምህረት ስዩም)
 • የኢትዮጵያ ገቢያዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሥነ-ምግባር ችግር አሳይተዋል ያላቸውን ሰባ ሰባት ሠራተኞቹን ከሥራ ማባረሩን ተናገረ፡፡ (ትዕግሥት ዘሪሁን)
 • በ2009 በጀት አመት ከ5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ንፁህ ውሃ እንዲጠጡ አድርጌአለሁ ሲል የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ተናገረ፡፡ (ምህረት ስዩም)
 • በመላ ሃገሪቱ በ150 ወባማ ወረዳዎች የፀረ ወባ መድሐኒት ርጭት እየተካሄደ እንደሆነ ተነገረ፡፡ (አስፋው ስለሺ)
 • የምሥራቅ ኢትዮጵያን የህክምና ፍላጐት ለማሟላት የተገነባው የራዲዮ ቴራፒ (የካንሰር ህክምና ማዕከል) ግንባታው ተጠናቋል ተባለ፡፡ (ምሥክር አወል)
 • ከ1 ሺ 400 የሚበልጡ የንግድ ድርጅቶች በህገ-ወጥ ተግባራት ተሰማርተው በመገኘታቸው እርምጃ ተወስዶባቸዋል ተባለ፡፡ (ትዕግሥት ዘሪሁን)
 • ብሔራዊ ሎተሪ ያሰበውን ያህል ገቢ ዘንድሮ ማግኘት አልቻለም ተባለ፡፡ (ዮሐንስ የኋላወርቅ)
 • ሳሪስ የሚገኘው የአቦ አደባባይ ሊፈርስ ነው ተባለ፡፡ (ንጋቱ ሙሉ)
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የኮድ 3 ሚኒባስ ተሽከርካሪዎች በተመደቡበት መስመር ሳያቆራርጡ አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላል የተባለው የብረት ታፔላ ተቀየረ

የኮድ 3 ሚኒባስ ተሽከርካሪዎች በተመደቡበት መስመር ሳያቆራርጡ አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላል የተባለው የብረት ታፔላ ተቀየረ፡፡የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን በከተማዋ የታክሲ አገልግሎት ለሚሰጡ የኮድ-3 ሚኒባስ ተሽከርካሪዎች ታፔላውን የቀየርኩት ተሽከርካሪዎቹ እንደሌሎች ታክሲዎች ለእይታ በሚመች መልኩ እንዲሰቅሉት ነው ብሏል፡፡

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ምክትል ኃላፊ የሆኑት አቶ ምትኩ አስማረ የታፔላው መየቀር ለቁጥጥር ሥራው ምቹ ከመሆኑም በላይ ተሣፋሪዎችም የታክሲውን መሥመር በቀላሉ እንዲለዩት ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡ታፔላ የመቀየሩ አገልግሎትም ከነሐሴ 17 እስከ ነሐሴ 30 2009 ዓ.ም አንደሚሰጥም ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ተናግሯል፡፡

በፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን የትራንስፖርት አገልግሎት ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ተስፋዬ በላቸው በበኩላቸው ታፔላ የሚሰጣቸው ተሽከርካሪዎች ከተሰጣቸው ስምሪት ውጪ ወደ ክልል ከተሞች መሄድ አንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡

በየነ ወልዴ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

በኦሮሚያ ክልል በሐሰተኛ መንጃ ፈቃድ የሚያሽከረክሩ አሽከርካሪዎች የትራፊክ አደጋ ስጋት መሆናቸውን ቀጥለዋል ተባለ

በኦሮሚያ ክልል በሐሰተኛ መንጃ ፈቃድ የሚያሽከረክሩ አሽከርካሪዎች የትራፊክ አደጋ ስጋት መሆናቸውን ቀጥለዋል ተባለ፡፡ይህን ያለው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ነው፡፡የፖሊስ ኮሚሽኑ የትራፊክ ፖሊስ ደህንነትና ቁጥጥር የሥራ ሂደት ባለሙያ ምክትል ኮማንደር ንጉሴ ግርማ እንደተናገሩት የአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ዞኖችን ጨምሮ በተለይ ምስራቅ ሀረርጌና ወለጋ በሐሰተኛ መንጃ ፈቃድ የሚያሽከረክሩ ሰዎች አሁንም በብዛት አሉ፤ አደጋ ካደረሱም በኋላ ይሰወራሉ ብለዋል፡፡

በሐሰተኛ መንጃ ፈቃድ የሚያሽከረክሩትን የክልሉ ፖሊስ በተቻለው መጠን እየያዘ በፍርድ ቤት እንዲቀጡ እያደረገ ነው ያሉት ምክትል ኮማንደር ንጉሴ ግርማ የመንጃ ፈቃድ ቋት ወጥ የሆነና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ካልሆነ በስተቀር ችግሩን ለመቅረፍ ይቸግራል ብለዋል፡፡ሐሰተኛ መንጃ ፈቃድን ለመቆጣጠርም ሆነ ሌሎች የትራፊክ ደንብ ጥሰቶችን ለመቆጣጠር ቋሚ የፍተሻ ጣቢያ በክልሉ በተመረጡ ቦታዎች ለማድረግ እቅድ መኖሩን ባለሙያው ነግረውናል፡፡ በዚህ ዓመት በኦሮሚያ ክልል በደረሱ የትራፊክ አደጋዎች ከ1 ሺ 900 በላይ ሰዎች ህይወት የተቀጠፈ ሲሆን ካለፈው ዓመት ተመሣሣይ ወቅት ጋር ሲመሣከር በ280 ቅናሽ እንዳለው ሰምተናል፡፡

ንጋቱ ሙሉ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ነሐሴ 16፣2009 የሸገር ወሬዎቻችን

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

 • በኦሮሚያ ክልል በሐሰተኛ የመንጃ ፈቃድ የሚያሽከረክሩ ሰዎች አደጋ ካደረሱ በኋላ እንደሚጠፉ ተነገረ፡፡ (ንጋቱ ሙሉ)
 • በከፍተኛ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ውስጥ 26ቱ ትላንት ፖሊስ የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀዶለታል፡፡ (እሸቴ አሰፋ)
 • መረጃ ባለመሟላቱ ምክንያት በአዲስ አበባ ከ14 ሺ በላይ ይዞታዎች ለምዝገባ ብቁ ሣይሆኑ ቀርተዋል ተባለ፡፡ (ምህረት ስዩም)
 • የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ያሰብኩትን ገቢ ሙሉ በሙሉ መሰብሰብ አልቻልኩም አለ፡፡ (ትዕግሥት  ዘሪሁን)
 • የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ለፆም ፍቺ በዛ ያሉ በሬዎችን አረድኩ አለ፡፡ (ወንድሙ ኃይሉ)
 • የኮድ 3 ሚኒባስ ተሽከርካሪዎች በተመደቡበት መስመር ሳያቆራርጡ አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላል የተባለው የብረት ታፔላ ተቀየረ፡፡ (በየነ ወልዴ)
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የበጎ አድራጐት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ በዚህ ዓመት 27 በጎ አድራጊ ድርጅቶችና ማህበራት መዘጋታቸውን ተናገረ

የበጎ አድራጐት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ በዚህ ዓመት 27 በጎ አድራጊ ድርጅቶችና ማህበራት መዘጋታቸውን ተናገረ፡፡ብዙዎቹ የመንቀሣቀሻ ገንዘብ ስለሌላቸውና በተለያየ ምክንያት በራሳቸው የድርጅታችን ይዘጋልን ጥያቄ ያቀረቡ መሆናቸውን ኤጀንሲው ለሸገር ተናግሯል፡፡በዚህ ዓመትና በ2008 ዓ.ም የተዘጉ 73 የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ንብረትም ተመሣሣይ ሥራ ለሚሰሩ በጎ አድራጊዎች መተላለፉን ሰምተናል፡፡

በአካውንታቸው የተገኘ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብርም ወደ ኤጀንሲው የባንክ ሂሣብ ገብቶ ከተዘጉ ድርጅቶችና ማኅበራት ጋር ለተያያዙ ወጪዎች እያዋለው መሆኑን በኤጀንሲው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መስፍን ታደሰ ለሸገር ተናግረዋል፡፡የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ በበጀት ዓመቱ ህግን ባለማክበራቸው ከተዘጉና የማይጠቀሙበትን ንብረት በሽያጭ ይወገድልን ያሉ ድርጅቶችን ንብረት በሽያጭ በማስወገድም 28 ሚሊየን ብር ተገኝቷል ብሏል፡፡

ከተሸጡ ንብረቶች መካከልም ኬር ኢትዮጵያ የተሰኘው ድርጅት የማይገለገልባቸውን ተሽከርካሪዎች፣ የተለያዩ ማሽኖችና ሌሎችንም ንብረቶች ኤጀንሲው በሽያጭ አስወግዶ ያገኘውን 24 ሚሊየን ብር መልሶ ወደ ኬር ኢትዮጵያ ዝግ አካውንት ማስገባቱን አቶ መስፍን ነግረውናል፡፡በሽያጭ ከተወገደው ንብረት የተገኘውን 24 ሚሊየን ብርም ኬር ኢትዮጵያ የሥራ ክንውን እቅድ ለኤጀንሲው አቅርቦ ከፀደቀለት በኋላ ለአላማ ማስፈፀሚያ ብቻ መዋል እንደሚችል ሰምተናል፡፡

የበጎ አድራጐት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ በተጠናቀቀው የ2009 በጀት ዓመት የ222 በጎ አድራጊ ድርጅቶችና ማህበራትን ደረጃም አውጥቶላቸዋል ተብሏል፡፡እቅድና የሂሣብ ምርመራ ውጤታቸውን በወቅቱ የሚያቀርቡ፣ ከተፈቀደላቸው አላማ ውጪ የማይሰሩ፣ በገቢ አሰባሰብና በወጪ አወጣጥ ህግን ተከትለዋል ተብለው የ“A”ን ደረጃ ያገኙት በጎ አድራጊ ድርጅቶች 34 ብቻ መሆናቸውን ሰምተናል፡፡

ትዕግስት ዘሪሁን

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

በውስጡ ባለው ከፍተኛ ፍሎራይድ ምክንያት ለመጠጥነት እንዳይውል ያልኩት ውሃ ገና በጉድጓድ ያለ እንጂ በቧንቧ መሰራጨት የጀመረ አይደለም ሲል የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ተናገረ

በውስጡ ባለው ከፍተኛ ፍሎራይድ ምክንያት ለመጠጥነት እንዳይውል ያልኩት ውሃ ገና በጉድጓድ ያለ እንጂ በቧንቧ መሰራጨት የጀመረ አይደለም ሲል የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ተናገረ፡፡የአዲስ አበባን የውሃ አቅርቦት እንዲያቃልሉ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ከተቆፈሩ ጥልቅ ጉድጓዶች መካከል አንዱ የሆነው በለገሃር ምድር ባቡር ጣቢያ ውስጥ የተቆፈረው ጥልቅ ጉድጓድ ከፍተኛ ፍሎራይድና ሶዲየም በውሃ ውስጥ በመገኘቱ ውሃው ለመጠጥ አገልግሎት እንዳይውል መደረጉን የባለሥልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እስጢፋኖስ ብስራት አስታውሰዋል፡፡

ውሃው በውስጡ ባለው ከፍተኛ ፍሎራይድና ሶዲየም ምክንያት ለመጠጥ አገልግሎት ቢውል ለአጥንት መሳሳትና ለጥርስ መበላሸት እንደሚዳርግም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ይሁን እንጂ ውሃው ችግር እንደሚያስከስት ቢነገርም አንዳንድ ሰዎች ውሃውን ለመጠጥ እንደሚጠቀሙት አቶ እስጢፋኖስ ነግረውናል፡፡

ለገሃር ምድር ባቡር ጣቢያ ግቢ ውስጥ ተቆፍሮ በተገኘ ውሃ ምክንያት ውሃውን እንዳትጠቀሙ የሚል ማስጠንቀቂያ በመሰጠቱ የባንቧ ውሃ አትጠጡ ነው ወይ የተባለው የሚል ግርታ የተፈጠረባቸው አድማጮች አሉ ያልናቸው አቶ እሥጢፋኖስ የቧንቧ ውሃን አይመለከትም ብለዋል፡፡በለገሃር ምድር ባቡር ጣቢያ ውስጥ ተቆፍሮ የተገኘውን ውሃ ጥቅም ላይ ለማዋል ሌላ ኬሚካል ያስፈልጋል ያሉት አቶ እሥጢፋኖስ ኬሚካሉ በሃገር ውስጥ ባለመኖሩ ወደፊት ኬሚካሉ ከውጭ ሀገር ሲገዛ ውሃው ጥቅም ላይ ይውላል ብለዋል፡፡

ንጋቱ ሙሉ

አስተያየት ይፃፉ (1 Comment)

ሳማ ሳሌም በተባለው የኩዌት አካባቢ ትኖር የነበረችና ከአሰሪዋ ጥቃት ለማምለጥ ከ7ኛ ፎቅ ላይ ወድቃ ከባድ ጉዳት የደረሰባት ኢትዮጵያዊት አገግማ ዛሬ ሀገር ቤት መድረሷ ተሠማ

ሳማ ሳሌም በተባለው የኩዌት አካባቢ ትኖር የነበረችና ከአሰሪዋ ጥቃት ለማምለጥ ከ7ኛ ፎቅ ላይ ወድቃ ከባድ ጉዳት የደረሰባት ኢትዮጵያዊት አገግማ ዛሬ ሀገር ቤት መድረሷ ተሠማ፡፡ከውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት እንደሰማነው ከ7ኛ ፎቅ ወድቃ ህይወቷ በተአምር የተረፈው አደሰች ሳዲቅ ለረጅም ጊዜ ሙባረክ አልከቢር በተባለ ሆስፒታል ውስጥ በህክምና ስትረዳ ቆይታለች፡፡በኩዌት ከአሰሪዋ ጥቃት ለማምለጥ ብላ በመስኮት ከ7ኛ ፎቅ ላይ የዘለለችው አደሰች ሳዲቅ በእጅና ጀርባዋ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባት እንደነበር ተወርቷል፡፡

አደሰች ሳዲቅ በመስኮት ስትዘል አሰሪዋ አደሰችን ከመርዳት ይልቅ በቪዲዮ ትቀርፃት እንደነበርና በዚህ ወንጀሏም ተከሣለች መባሉን ሠምተናል፡፡የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች ዛሬ ማለዳ ላይ አደሰች ሳዲቅን እንደተቀበሏት ተነግሯል፡፡ባለፉት ወራት በኩዌት በተለያዩ ወንጀሎች ተከሰው እሥር ቤት የሚገኙ ሰዎች ምህረት እንዲደረግላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት በጠየቀው መሠረት የኩዌት ንጉስ በመፍቀዳቸው ጉዳያቸው በሂደት ላይ ነው መባሉንም ሰምተናል፡፡

የኔነህ ሲሳይ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ነሐሴ 15፣2009 የሸገር ወሬዎቻችን

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

 • ከአሰሪዋ ጥቃት ለመሸሽ ብላ ከ7ተኛ ፎቅ ወድቃ የነበረችው ኢትዮጵያዊት ወደ ሀገሯ ገባች፡፡ (የኔነህ ሲሣይ)
 • ለመጠጥ እንዳይውል የተባለው የለገሃር አካባቢ ጥልቅ ጉድጓድ ውሃ በቧንቧ መሰራጨት የጀመረ አይደለም ተባለ፡፡ (ንጋቱ ሙሉ)
 • በአዲስ አበባ ከተማ ከተካሄደው የቀን ገቢ ግብር ትመና ወደ አርባ በመቶ የሚጠጋው ችግር እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሣለኝ ተናገሩ፡፡ ነጋዴዎችን አወያያተናል በሚል ሃሰተኛ ሪፖርት በትመናው ዙሪያ በቂ መረጃ ሳይሰጥ እንደቀረም ተረድተናል ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ከግሉ ዘርፍ ተወካዮች ጋር ባለፈው ቅዳሜ በሸራተን አዲስ ሆቴል ተወያይተዋል፡፡ (ንጋቱ ረጋሣ)
 • የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ከፍተኛ መስመር ተሰብሮብኝ ጥገና ላይ ነኝ አለ፡፡ (ወንድሙ ኃይሉ)
 • የሀዋሳ ኤርፖርት በ2009 ከ48 ሺ በላይ መንገደኞችን አመላልሷል ተባለ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በርካቶቹ ቱሪስቶች መሆናቸውን አየር መንገዱ ተናግሯል፡፡ (አስፋው ስለሺ)
 • የሌሴቶው ንጉስ ከዛሬ ጀመሮ ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ ተባለ፡፡ (ንጋቱ ሙሉ)
 • በተጠናቀቀው የ2009 በጀት ዓመት 27 የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ተዘግተዋል ተባለ፡፡ (ትዕግሥት ዘሪሁን)
 • የሰሜን ሸዋ ዞን በውስጡ የሚገኙ የቱሪዝም ሀብቶች ከምንጊዜውም በላይ እንዲታወቁልን እሠሰራለሁ ብሏል፡፡ (ምሥክር አወል)
 • ዘንድሮ 173 ሺ ከረጢት ደም ከለጋሾች ተሰብስቧል ተባለ፡፡ (ወንድሙ ኃይሉ)
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ከእንግዲህ በኋላ የተሰሩ መንገዶችና ሌሎች የመሠረተ ልማቶች በተሰሩበት ቅፅበት ባለመናበብ ምክንያት የሚፈርሱበት ምክንያት አይኖርም ተባለ

ከእንግዲህ በኋላ የተሰሩ መንገዶችና ሌሎች የመሠረተ ልማቶች በተሰሩበት ቅፅበት ባለመናበብ ምክንያት የሚፈርሱበት ምክንያት አይኖርም ተባለ፡፡ይህን ያሉት በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በቅርቡ ውሃን፣ ቴሌን፣ መብራትንና መንገዶችን ተናበው እንዲሰሩ የሀገርንና የህዝብን ገንዘብ በግዴለሽነት እንዳያባክኑ የተቋቋመው የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይሉ ወልደሥላሴ ናቸው፡፡አቶ ኃይሉ አደረጃጀትና መመሪያ ከወጡለት በኋላ በቀጣይ ዓመት እየተናበቡ እንዲሰሩ ይደረጋል ብለዋል፡፡

አንዳንድ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችና ገንቢዎች በፌዴራሉ መንግሥት ሥር ያሉ ናቸው ያሉት አቶ ኃይሉ ከከተማ መስተዳድሩ ጋር ተቀናጅተው የሚሰሩበትን መንገድ እናጤነዋለን ብለዋል፡፡በተለያዩ የወሬ ጊዜያችን በሰራናቸው ወሬዎች አንዱ የሰራውን ሥራ አጠናቆ እቃውን ሳይሰበስብ ሌላኛው እየቆፈረው ይህም ነዋሪዎችን ለአካል ጉዳት፣ ለትራንስፖርት እጥረት፣ ለውሃ፣ ለመብራትና ለተለያዩ አገልግሎቶች ችግር ሲያጋልጡት መክረማቸውን አውርተናል፡፡

እንደ አዲሱ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ምክትል ኃላፊ ከእንግዲህ ካለፈቃድ በየፊናቸው ያ አይደረግም ተብሏል፡፡በተለይ መብራት፣ ውሃ፣ መንገድና ቴሌ አንዱ የሰራውን ሌላኛው ሲያፈርሰውና ሀገርን ለሌላ ወጪ ሲዳርግ ተመልክተናል፡፡አሁን ግን ፈቃድ ወስደው ሲፀድቅላቸው ቁጥጥር ተደርጎባቸው ይተገበራሉ አሁን ባይፀድቅም በአዋጅ ደረጃ አለ ብለዋል ምክትል ኃላፊው አቶ ኃይሉ፡፡

ለእግረኛ ትኩረት የሚሰጥ ሰፋፊ የልማት ሥራዎችን ያካተተ መዋቅራዊ ፕላን መዘጋጀቱን የተናገሩት ምክትል ኃላፊው እነዚህ ተቋማት ተናበው፣ ተግባብተው እንዲሰሩ በማስፈለጉ ባለሥልጣኑ መቋቋሙን ለሸገር ተናግረዋል፡፡

ምሥክር አወል

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የቻይና ኤግዚም ባንክ የሰሜን አዲስ አበባን የውሃ ችግር ለመቀነስ እንዲቻል የገንዘብ ብድር ሰጠ ተባለ

የቻይና ኤግዚም ባንክ የሰሜን አዲስ አበባን የውሃ ችግር ለመቀነስ እንዲቻል የገንዘብ ብድር ሰጠ ተባለ፡፡ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ እሥጢፋኖስ ብሥራት ዛሬ ለሸገር ሲናገሩ የቻይና ኤግዚም ባንክ የ146 ሚሊየን ዶላር ብድር የሰጠ ሲሆን ገንዘቡ ለገርቢ ግድብ ግንባታ ይውላል ብለዋል፡፡

በሌላ የውሃ ወሬ የኩዬ ፈቼ ቂሊንጦ ፕሮጀክት 50 ሺ ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ የሚያመነጭ ሲሆን በታህሣስ 2010 ተጠናቆ ሥራ ይጀምራል፡፡በተለይ ለሰፋፊ የኮንዶሙኒየም ፕሮጀክቶች የውሃ አቅርቦት ይሰጣል ሲሉ አቶ እስጢፋኖስ ነግረውናል፡፡በፈረቃ የሚዳረሰውን የአዲስ አበባ ውሃ አገልግሎት በ2011 ሙሉ ለሙሉ ከፈረቃ ለማውጣትና ሁሌም ለሁሉም ውሃ ለማቅረብ መታሰቡን ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሰምተናል፡፡

ወንድሙ ኃይሉ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)
Sheger 102.1 AudioNow Numbers