• United Bank S.C.

    ሕብረት ባንክ አ.ማ.

  • Slider Two

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Sldier Three

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ሸገር ወሬዎች እና ልዩ ወሬዎች

ሀሰተኛ ደረሰኝ ከመጠቀም ጋር ተያይዞ የንግድ ትርፍ ግብራቸውን የሚሰውሩ ነጋዴዎች ቁጥር በመብዛቱ የነጋዴዎችን ሂሳብ ለመመርመር እየተሰናዳ መሆኑን ገቢ ሰብሳቢ መስሪያ ቤት ተናገረ

የገቢዎች ሚኒስቴር ለሸገር እንደተናገረው በተደጋጋሚ ብንነግድም ከስረናል፣ አላተረፍንም እያሉ ሪፖርት የሚያደርጉ 3ሺ 89 ነጋዴዎች ሂሳብ በዝርዝር ሊመረመር ነው፡፡በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ኤፍሬም መኮንን እንደተናገሩት የንግድ ትርፍ ግብር ማሳወቅ ከሚጠበቅባቸው ነጋዴዎች በትክክል ግብራቸውን ከክፍያ ጋር ያሳወቁት 33 በመቶ ብቻ ናቸው ብለዋል፡፡

አብዛኛዎቹ ነጋዴዎች ኪሳራ እና ባዶ በተደጋጋሚ ጊዜ ያሳውቃሉ፡፡ይህም ሀሰተኛ ደረሰኝ ከመጠቀም ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡በቅርቡም ምንም አይነት አገልግሎት እና እቃ የማይሸጡ ሀሰተኛ የንግድ ፈቃድ ያላቸው 124 ድርጅቶች ተገኝተዋል ብለዋል አቶ ኤፍሬም፡፡እነዚህ ድርጅቶች በሀሰተኛ ደረሰኝ ሽያጭ ላይ ብቻ የተሰማሩ ናቸው ብለዋል፡፡ከእነዚህ ድርጅቶች ደረሰኝ ተጠቅመው ግዢ ፈፅሜያለው የሚል ነጋዴም ተቀባይነት እንደማይኖረው አስረድተዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ስጋት ታይቶባቸዋል የተባሉ እና ቀይ ስጋት ውስጥ የገቡ 3ሺ 85 ግብር ከፋዮችን ሂሳብ በዝርዝር ለመመርመር ዝግችታችንን አጠናቅቀናል ብለዋል፡፡በመካከለኛና ዝቅተኛ ስጋት ውስጥ ያሉ ሌሎች ነጋዴዎችም በቅርቡ ተለይተው የሂሳብ ምርመራ እንደሚደረግባቸው አቶ ኤፍሬም ተናግረዋል፡፡

ትዕግስት ዘሪሁን
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ትናንት እና ከትናንት በስቲያ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ 2.6 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸው ተሰማ

የተለያዩ ደህንነት እና ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጡ መድሃኒቶች፣ ሺሻ፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ ልባሽ ጨርቆችና ሞተር ሳይክል ከተያዙት ህገ ወጥ እቃዎች መካከል እንደሆኑ የገቢዎች ሚኒስቴር ለሸገር ተናግሯል፡፡

በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል ደግሞ የአሜሪካ ዶላርን ጨምሮ 264 ሺ ብር የተገመቱ የተለያዩ ሀገር መገበያያ ገንዘቦች ከሀገር ሊወጣ ሲል መያዙን ሰምተናል፡፡በሁለት ቀን ውስጥ በቁጥጥር ስር ውለዋል የተባሉና 2.6 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው እንደ መድሃኒት፣ ሺሻ፣ የመዋቢያ እቃዎችና ሌሎች የኮንትሮባንድ እቃዎች የተያዙት ደግሞ በአዲስ አበባ መርካቶ፣ በሚሌ፣ በአዳማ፣ በጅጅጋና በድሬዳዋ መሆኑን ሰምተናል፡፡

ትዕግስት ዘሪሁን
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የቀድሞው የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ምክትል እና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል አቶ ያሬድ ዘሪሁን በቁጥጥር ስር ዋሉ

የቀድሞው የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ምክትል እና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል አቶ ያሬድ ዘሪሁን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ከጠቅላይ አቃቢ ህግ አቶ ብርሀኑ ፀጋዬ ተመልክተናል።
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የኢሕአዴግ ምክር ቤት ፅ/ቤት ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይን በተመለከተ መግለጫ ማውጣቱን ተመልክተናል

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

ድርጅታችን ኢሕአዴግ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትግል በማስተባበር ዘርፈ ብዙ ለውጦችን ማስመዝገብ የቻለ ድርጅት ነው።ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የሀገራችንን ሕዝቦችና የተለያዩ የህዝብ አደረጃጀቶችን ለቅሬታና ለምሬት የዳረጉ ጥፋቶች በአመራር ዘመኑ እንደተፈጸሙ አበክሮ ይገነዘባል። ለተከታታይ አመታት የጥልቅ ተሃድሶ መድረኮችን በማካሄድ የችግሮቹን ምንጭና መፍትሄዎች ለመለየት ሲሰራ የቆየውም ከዚሁ በመነሳት ነው።ድርጅታችን ቁልፍ የሆነው ችግር መንግስታዊና የፓርቲ ስልጣንን ለህብረተሰባዊ ለውጥ ከማዋል ይልቅ የግል ጥቅምን ለማካበት የማዋል ፍላጎትና ተግባር መሆኑን በጥልቅ ተሃድሶው ግምገማ መለየቱ ይታወሳል።

አሁን ከደረስንበት ለውጥ በመነሳት የህዝባችን ቅሬታ በዚህ መልኩ ምላሽ ሳያገኝ እንዲቆይ ማድረግ የሚቻልበት አንዳችም መንገድ እንደሌለ የተረዳው ድርጅታችን ለህዝቡ በገባው ቃል መሰረት ስር ነቀል የአመራርና የአሰራር ለውጥና ማሻሻያዎች አድርጓል።

የለውጥ ጊዜው አጭር ቢሆንም በስፋቱና በጥልቀቱ ግን በሀገራችን ታሪክ ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ነው። አሁንም የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ዘላቂነት ከማረጋገጥ ጎን ለውጡ ተቋማዊ እንዲሆን ማድረግ የቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶት በድርጅታችን እየተፈፀመ ያለ ተግባር ሆኗል።ከፍተኛ የሕዝብ ቅሬታና እሮሮ ከሚሰማባቸው ውስጥ ሀገራዊ የፍትህ ስርዓቱ በሀገሪቱ የተንሰራፋውን ሌብነትና ብልሹ አሰራር ሊያስቆም አለመቻሉ ይገኝበታል።

የዚህ ዘርፍ ዋነኛ ተልዕኮ ህገ ወጥነትን መከላከልና ሲፈፀምም ህጉን ተከትሎ የእርምት እርምጃ መውሰድ ቢሆንም በፍትህ ስርዓቱ ውስጥ የተደራጁ ሃይሎች በተሰጣቸው ሃላፊነት ልክ ህገ ወጥ ድርጊቶችን ከማስቆም ይልቅ ራሳቸውን የህገ ወጦች ፍላጎት ማስፈፀሚያ መሳሪያ በማድረግ በሀገርና በህዝቦቿ ላይ በደል ሲፈፅሙ ቆይተዋል።

የሀገራችንን ኢኮኖሚ በእጅጉ የሚጎዱ አሻጥሮች ሲፈፀሙ፣ የዜጎችና የቡድኖች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በግላጭ ሲጣሱ እንዲሁም መንግስታዊ ስልጣን ለሽብር ተግባር ማስፈፀሚያ ሲውል ቆይቷል።

ከዚህ በመነሳት ድርጅታችንና መንግስት በዚህ ዘርፍ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚገባ በማመን ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በርካታ ጥናት ሲያደርጉና ርምጃዎችን ሲወስዱ ቆይተዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ...

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በ2002 ዓ.ም በኤርትራ ላይ ጥሎት የነበረውን ማዕቀብ አንስቷል

የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በ2002 ዓ.ም በኤርትራ ላይ ጥሎት የነበረውን ማዕቀብ አንስቷል። የኢትዮጵያ መንግስትም ይህን አስመልክቶ ለኤርትራ መንግስት የእንኳን ደስ አላችሁ እና የምስጋና መልዕክት ለተባበሩት መንግስታት አቅርቧል።
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ፣ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን የስደተኞች፣ የአገር ውስጥና ዜግነት ጉዳዮች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲሚትሪስ አቭራሞፖሎስ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ፣ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን የስደተኞች፣ የአገር ውስጥና ዜግነት ጉዳዮች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲሚትሪስ አቭራሞፖሎስና ልዑካቸውን በዛሬው ዕለት በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው ማነጋገራቸውን ተመልክተናል፡፡ዘመናት ያስቆጠረውን የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ እንደሁም በአፍሪካ እና አውሮፓ መካከል ያለውን ግንኙነት ወደተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ተባብረው ለመስራት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል፡፡
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የሜቴክ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው እና ጋዜጠኛ ፍፁም የሺጥላን ጨምሮ 8 ተጠርጣሪዎች በዛሬው ዕለት በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ የወንጀል ችሎት ቀረቡ

የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው እና ጋዜጠኛ ፍፁም የሺጥላን ጨምሮ 8 ተጠርጣሪዎች በዛሬው ዕለት በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ የወንጀል ችሎት ቀረቡ፡፡ከተጠርጣሪዎቹ መካከል ስድስቱ በሙስና ወንጀል እንዲሁም ሁለቱ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው መያዛቸውን ተመልክተናል፡፡
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ሰማያዊ ፓርቲ:-በኢትዮጵያ የተጀመረው ለውጥ መቀጠል የሚችለው ተቋማዊ ቅርፅ ሲይዝ ብቻ ነው ብሏል

ሰማያዊ ፓርቲ፣ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በዛሬው ዕለት በሰጠው መግለጫው፣ በኢትዮጵያ የተጀመረው ለውጥ መቀጠል የሚችለው ተቋማዊ ቅርፅ ሲይዝ ብቻ ነው ብሏል፡፡ የየኔነህ ሲሳይን ዘገባ ያዳምጡ

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የአፍሪካ ሕብረት አስቸኳይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ የህብረቱ አዳራሽ መካሄድ ጀመረ

የአፍሪካ ሕብረት አስቸኳይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ የህብረቱ አዳራሽ መካሄድ ጀመረ፡፡ የንጋቱ ሙሉን ዘገባ ያዳምጡ

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ጉዞ አድዋ የበጎ አድራጎት ማህበር ትናንት በይፋ ተመስርቶ ስራ መጀመሩ ተነገረ

የማህበሩ መመስረት ታሪክን ከማስጠበቅ ባለፈ ባለፉት አመታት ሲካሄድ የነበሩ የአድዋ መታሰቢያ ጉዞዎች ላይ ይገጥሙ የነበሩ ችግሮችን ለማስቀረት ያስችላል ተብሏል፡፡ትናንት ማምሻውን በኔክሰስ ሆቴል በነበረው የምስረታ ዝግጀት ላይ እንደሰማነው ባለፉት አምስት አመታት የአድዋ ታሪክ በደንብ እውቅና እንዲያገኝ፣ ታሪካዊ ሙዚየም እንዲገነባ በቂ የሚዲያ ሽፋን እንዲኖረውና የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች እንዲገነቡ ጥረት አድርጓል ተብሏል፡፡

የማህበሩ መመስረትንም ተከትሎ በመጭው ጊዜ ጉዞው የሌሎች አገራት ተጓዦችን እንዲያሳትፍ፣ የአድዋ ታሪክ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም እንዲሰጥ በተለያዩ ከተሞችም ታሪኩን የሚዘክሩ ሐውልቶች እንዲቆሙ እንዲሁም መንገዶች እንዲሰየሙ ለማድረግ ይሰራል ተብሏል፡፡በተጨማሪም እየጠፉ ላሉ ሌሎች ቅርሶችም በቂ ትኩረት እንዲሰጥ ማህበሩ ይሰራል መባሉን ሰምተናል፡፡ ጀግኖች አባቶች በአድዋ የፈፀሙትን ገድል ለማሰብ በየካቲት ወር የ3 ኪሎ ሜትር የባዶ እግር የጎዳና ላይ ሩጫ ለማካሄድ መታሰቡንም አዘጋጁ ሆል ኢቨንትስ አስታውቋል፡፡

ቴዎድሮስ ብርሃኑ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ተላላፊ ካልሆኑና በተለይ ከኑሮ ዘይቤ መቀየር ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ስርጭቱ እየጨመረ የመጣውን የስኳር በሽታ እንደሌሎቹ ተላላፊ የሆኑ ህመሞች ትኩረት ያላገኘ በመሆኑ አሁንም በስኳር በሽታ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው ተባለ

በኢትዮጵያ ከአምስት በመቶ በላይ ሕዝብ ወይም ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በስኳር ህመም የተጠቁ መሆናቸው ተነግሯል፡፡ዛሬ በአለም አቀፍ ደረጃ እየታሰበ የሚገኘው የአለም የስኳር ህሙማን ቀን አስመልክቶ በተሰናዳ ምክክር ላይ ተገኝተን እንደሰማነው ከሰሐራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ኢትዮጵያ ከፍተኛ የስኳር ህሙማን ያለባት ቀዳሚ ሀገር ነች ተብሏል፡፡

ከከተሞች መስፋፋት ጋር በተያያዘ እየተለወጠ የመጣው የአኗኗር ዘይቤ፤ እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ የአመጋገብ ሥርዓት መቀየር እና የጤና ምርመራ አለማድረግ ለበሽታው ስርጭት መጨመር ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ተብሏል፡፡በተለይም የቅድመ ስኳር ህመም ያለባቸው ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መምጣቱ የተነገረ ሲሆን 12 ነጥብ 3 በመቶ ሰዎች የስኳር ህመም ስጋት ያለባቸው ናቸው ተብሏል፡፡ዓይነት ሁለት ወይም ታይፕ ቱ የተባለው የስኳር ህመም ተጋላጮች ቁጥር እያሻቀበ በመጣባት ኢትዮጵያ ይህንንም ተከትሎ ለሚከሰቱ የልብ፣ የኩላሊት፣ የደም ግፊትና ሌሎች ተያያዥ ህመሞች የተጋለጡ ሕዝቦቿ ቁጥር አሳሳቢ መሆኑ ተነግሯል፡፡

የአመጋገብ ስርዓትን ማስተካከል፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግና ህመም ቢኖርም ባይኖርም በየጊዜው የጤና ምርመራ ማድረግ 80 በመቶ የስኳር ህመም በሽታን ለመከላከል አማራጭ የሌለው መፍትሄ እንደሆነው ሰምተናል፡፡እስከ 10 አመታት ድረስ ምንም ዓይነት ምልክት ሳያሳይ በደም ውስጥ የስኳር መጠን በመጨመር የሚከሰተው “ዓይነት ሁለት” የስኳር ህመም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ መታወቁ በሽታውን አሳሳቢ ያደርገዋል ተብሏል፡፡በጤና ጥበቃው ዘርፍ ተላላፊ የሆኑ ህመሞች ያገኙትን ያህል ትኩረት ሊሰጠው ይገባል የተባለው የስኳር ህመም በጤና ጥበቃ ዙሪያ የሚሰሩ ተቋማት እንዲሁም ሁሉም ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠውና ተጨማሪ ሰዎች በበሽታው እንዳይያዙ ለማድረግ ሊሰራበት ይገባል መባሉን ሰምተናል፡፡

ምህረት ሥዩም
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)
Sheger 102.1 AudioNow Numbers