• United Bank S.C.

  ሕብረት ባንክ አ.ማ.

 • Slider Two

  የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

 • Sldier Three

  የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ሸገር ወሬዎች እና ልዩ ወሬዎች

አዲስ አበባ ለመጪዎቹ ሦስት አመታት የምትመራበት የመንገድ ደህንነት እስትራቴጂ የመተግበሪያ እቅድ ዛሬ ይፋ ተደረገ

አዲስ አበባ ለመጪዎቹ ሦስት አመታት የምትመራበት የመንገድ ደህንነት እስትራቴጂ የመተግበሪያ እቅድ ዛሬ ይፋ ተደረገ፡፡ከተማዋ ለ13 ዓመታት የምትሰራበት የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ በዚህ አመት መጀመሪያ ወራት አካባቢ መፅደቁ ይታወሣል፡፡የ13 ዓመቱን እቅድ መሠረት አድርጐ የተዘጋጀውና ከ2010 እስከ 2012 የሚቆየውን የመተግበሪያ እቅድ ዛሬ በሸራተን ሆቴል ይፋ ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው ናቸው፡፡

በሦስት ዓመቱ የአዲስ አበባ የደህንነት ስትራቴጂ የመተግበሪያ እቅድ ላይ እንደተመለከትነው በከተማዋ የሚደርሰውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ የተለያዩ ሥራዎች እንደሚሰሩ ይዘረዝራል፡፡በአሁኑ ሰዓት 70 በመቶ የሚሆነው አዲስ አበቤ ወዲህ ወዲያ የሚለው በእግሩ እንደሆነ የሚናገረው ሰነዱ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የትራፊክ አደጋ የሚደርስባቸው እግረኞች እንደሆኑም ያትታል፡፡

ስለዚህ ደህንነታቸው የተጠበቁ የእግረኛ መንገዶች ግንባታ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው ነው ተብሏል፡፡ዋና ዋና አደጋ የሚደርስባቸውን መንገዶች ትኩረት ሰጥቶ መሥራት፣ የጠጥቶ ማሽከርከርን ቁጥር መቀነስ እንዲሁም የትራፊክ ደህንነት ትምህርትን ማጠናከር ሌሎች የሦስት ዓመቱ ዋና ዋና ትኩረቶች መሆናቸውን ሰምተናል፡፡

እነዚህን ሥራዎች በመስራትም በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት በአዲስ አበባ የሚደርሰውን የትራፊክ አደጋ ሞት በ30 በመቶ ለመቀነስ ታቅዷል፡፡ጠጥቶ ማሽከርከርና ከፍጥነት በላይ ማሽከርከርን ደግሞ በ50 በመቶ ይቀንሣል ተብሎ ታስቧል፡፡

በአዲስ አበባ በተጠናቀቀው 2009 በጀት ዓመት 463 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን በዚህም መሠረት በአማካይ በቀን 1 ሰው ይሞታል፡፡

ንጋቱ ሙሉ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

አንዳንድ የመንግስት መስሪያ ቤቶች አሽከርካሪዎች ለትራፊክ አስተናባሪዎች እንደማይታዘዙ ተነገረ

አንዳንድ የመንግስት መስሪያ ቤቶች አሽከርካሪዎች ለትራፊክ አስተናባሪዎች እንደማይታዘዙ ተነገረ፡፡ይህን የሰማነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የበጋ ወቅት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን የማበረታቻ የምስክር ወረቀትና ለቀጣይ ስራ ዝጅግት ስልጠና በሰጠበት መድረክ ነው፡፡

አሽከርካሪዎቹ የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን ትዕዛዝ ጥሰው በመሄድ የማስተናበሩን ስራ እንደሚያስተጓጉሉ ነው ወጣቶቹ የተናገሩት፡፡ከእነዚህም ውስጥ የተወሰኑ የመከላከያ ሚንስቴር እና ሌሎች የመንግስት መስሪያ ቤቶች ሾፌሮች እንደሚገኙበት ሰምተናል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የግንባታ ተረፈ ምርቶች መንገድ ላይ መደፋት፣ የመንገድ መቆፋፈር እና በትላልቅ ህንፃዎች አካባቢ የመኪና ማቆሚያ እጥረት መኖሩ የትራፊክ አስተባባሪዎች ስራ የተቀላጠፈ እንዳይሆን ካደረጉት ውስጥ ይገኙበታል ተብሏል፡፡በእለቱ በቀረበ የጥናት ወረቀት የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መኖር ሊደርስ ይችል የነበረውን አደጋ ለመቀነስ እገዛ እንዳደረገ ተጠቅሷል፡፡ከአስሩም ክፍለ ከተሞች ወጣት በጎ ፈቃደኞችን በስነ ምግባር፣ ኃላፊነትን በአግባቡ በመወጣትና የስራ ሰዓትን በማክበር ተመርጠው የሜዳልያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

በየነ ወልዴ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ዛሬ ከ8 ሰዓት በኋላ የመሰናዶ መግቢያ ውጤትን ተፈታኞች መመልከት ይችላሉ ብሏል

ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ዛሬ ከ8 ሰዓት በኋላ የመሰናዶ መግቢያ ውጤትን ተፈታኞች መመልከት ይችላሉ ብሏል፡፡የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዘሪሁን ዱሬሣ እንደነገሩን ተፈታኞች RTN ብለው የመፈተኛ ቁጥራቸውን ወደ 8181 በመላክና በኤጀንሲው ድረ-ገፅ በwww.neaea.gov ማየት ይችላሉ ብለዋል፡፡

በርካታ ተፈታኞች በተመሣይ ሰዓት ሊሞክሩት ስለሚችሉ የኔትወርክ መጨናነቅ ሊፈጠር ይችላል ያሉት ዳይሬክተሩ ተፈታኞች በትግዕሥት ውጤታቸውን እንዲመለከቱ ጠይቀዋል፡፡

ምስክር አወል
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ጷግሜ 1፣2009 የሸገር ወሬዎቻችን

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

 • ሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን መጠቀም ከሚገባቸው የደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮች 34 በመቶዎቹ ማሽኑ የላቸውም ተባለ፡፡ በአስመጪ ድርጅቶች ዘንድም ማሽኑ ተከማችቶ እንደሚገኝ ገቢ ሰብሣቢ መሥሪያ ቤቱ ተናግሯል፡፡ (ትዕግሥትዘሪሁን)
 • በአዲስ አበባ 659 ሄክታር መሬት ወደ መሬት ባንክ ገቢ ተደርጓል ተባለ፡፡ ቀሪ ክፍት ቦታዎችም ከሚቀጥለው ሣምንት ጀምሮ ይለቀማሉ ተብሏል፡፡ (ቴዎድሮስብርሃኑ)
 • ከአመት በፊት በይፋ ተመርቆ ሥራ የጀመረው የስኩል ኔት ፕሮጀክት የተሟላ አገልግሎት እየሰጠ አይደለም ተባለ፡፡ ትምህርት ቢሮ ቴክኒሻኖች ሥራ እየለቀቁ ተቸግሬያለሁ ቢልም አስካሁን ባለሙያ ያልተቀጠረባቸው ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ተሰምተናል፡፡ (ትዕግሥትዘሪሁን)
 • አዲስ አበባ ለመጪዎቹ ሦስት ዓመታት የምትመራበት የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ መተግበሪያ እቅድ ይፋ ሆነ፡፡ (ንጋቱሙሉ)
 • ዓመታዊ የአምባሳደሮች ጉባዔ ከሀዋሳ ዩኒቨርስቲዎች ጋር በዲፕሎማሲው መስክ አብሮ ለመስራት ተነጋገረ፡፡ (የኔነህሲሣይ)
 • አንዳንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አሽከርካሪዎች ለትራፊክ አስተናባሪዎች እንደማይታዘዙ ተነገረ፡፡ (በየነወልዴ)
 • ኢትዮጵያ የብሔራዊ ፓርኮቿን ብዝሃ ህይወትና ሕገ-ወጥ የዱር እንስሣት ዝውወርን ለመቆጣጠር የገንዘብ ድጋፍ አገኘሁ አለች፡፡ (ንጋቱ ሙሉ)
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የአለም የቱሪዝም ቀን መስከረም 17፣2010 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል እንደሚከበር የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ተናግሯል

የአለም የቱሪዝም ቀን መስከረም 17 2010 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል እንደሚከበር የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ተናግሯል፡፡የቱሪዝም ቀኑ በአለም አቀፍ ደረጃ በኳታር ዶሃ ለ38ተኛ ጊዜ ሲከበር በኢትዮጵያ ደግሞ ለ30ኛ ጊዜ እንደሚከበር ሰምተናል፡፡

ቀኑ ሲከበርም መንግሥትና ህዝብ ለቱሪዝም ያላቸው ግንዛቤ እንዲዳብርና ለማህበራዊ፣ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ እሴቶች ያለውን አስተዋፅኦ ለማስገንዘብ ይሰራል ተብሏል፡፡ “ቱሪዝም ለዘላቂ ልማት” የሚል መሪ ኃሣብን ይዞ ይከበራል የተባለው የዘንድሮው የቱሪዝም ቀን ህዝቦች በመስህብ ሀብቶች ላይ የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማቸው ለማድረግና በዘርፉም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያለመ መሆኑን ሰምተናል፡፡

የአለም የቱሪዝም ቀን እንዲከበር የተወሰነው የአለም የቱሪዝም ድርጅት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1970 በስፔን ቶርምሊኖስ ባደረገው ሦስተኛው ጉባዔ መሆኑ ይታወሣል፡፡

ምሥክር አወል

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ የመሰናዶ መግቢያ ውጤት ተሰርዟል እየተባለ በማኅበራዊ ድረ-ገፆች የተሰራጨው ወሬ የተሳሳተ መሆኑን ተናግሯል

ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ የመሰናዶ መግቢያ ውጤት ተሰርዟል እየተባለ በማኅበራዊ ድረ-ገፆች የተሰራጨው ወሬ የተሳሳተ መሆኑን ተናግሯል፡፡የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዘሪሁን ዱሬሣ ለሸገር እንደተናገሩት የፈተና ውጤቱ ይፋ መደረጊያ ቀን የተራዘመው የተማሪዎቹ ቁጥር በርካታ በመሆኑ ወደ ዌብ ሳይትና SMS መልዕክት መመልከቻ ለማስገባት ጊዜ በመጠየቁ ነው ብለዋል፡፡

ሆኖም የኤጀንሲውን ማህተም አስመስሎ የያዘ ደብዳቤ በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲዘዋወር ተመልክተናል፣ ለማወናበድና ድንጋጤ ለመፍጠር የሚሰራው ሥራ አሳዛኝ ነው ብለዋል፡፡ወላጆችም ሆኑ ተማሪዎች እንደዚህ አይነቶች አሳሳች መልዕክቶች ሲሰራጩ ኤጀንሲውን መጠየቅ አልያም ወደ የብዙሃን መገናኛዎች መረጃውን እንዲያጣሩ መጠየቅ አለባቸው ሲሉ ዶክተር ዘሪሁን ተናግረዋል፡፡

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር ዘሪሁን የዩኒቨርስቲ ምደባን በሚመለከትም ምደባ የተደረገ አስመስለው የሚያወሩ አካላት አሉ ነገር ግን ምደባው ገና ነው ብለዋል፡፡ከሣምንት በኋላ ሊለቀቅ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት ከ5 ቀናት በፊት ይፋ የተደረገ ሲሆን የ10ኛ ክፍል ከነሐሴ 25 በኋላ ይፋ ሊሆን እንደሚችል ኤጀንሲው መናገሩ ይታወሣል፡፡ሆኖም ባልኩት መልኩ ይፋ ያላደረኩት መረጃዎቹን ለመመልከት በሚያመች መልኩ በመጫን ላይ ስለሆንኩ ነው ሲል ኤጀንሲው ተናግሯል፡፡

ምሥክር አወል

 

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአብነት ትምህርት ረቂቅ ፖሊሲ አሰናድታ ዛሬ ከምሁራንና ከቤተክርስቲያን አባቶች ጋር እየመከረችበት ነው

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአብነት ትምህርት ረቂቅ ፖሊሲ አሰናድታ ዛሬ ከምሁራንና ከቤተክርስቲያን አባቶች ጋር እየመከረችበት ነው፡፡በኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት የዘመን አቆጣጠር፣ ሥነ-ፅሑፍና ኪነ-ጥበብ ባለውለታ የሆነው የአብነት ትምህርት በአሁኑ ወቅት የመጥፋት አደጋ ተጋርጦበታል ተብሏል፡፡

በመሆኑም መልካም ሥነ-ምርባር ያለው ሀገሩንና ባህሉን ጠንቅቆ የሚያውቅ ትውልድ የመፍጠር ኃላፊነት ያለባት ቤተክርስቲያኗ የአብነት ትምህርት ከዘመናዊው ትምህርት ጎን ለጎን የሚሰጥበትን ፖሊሲ ቀርፃ ተግባራዊ ለማድረግ መሰናዳቷን ብፅዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትሪያርክ ዘኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡

የአብነት ትምህርት ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥነ-ፅሁፍ፣ ኪነ-ጥበብና የዘመን አቆጣጠር ሁሉ መነሻ ነው ያሉት ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ በበኩላቸው ታላላቅ የአለም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይህን ተገንዝበው የግዕዝ ቋንቋን እያስተማሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ኢትዮጵያ ግን ለዚህ ባለቤት ሆና ሳለ ትምህርቱ እስኪጠፋ ድረስ ዝም የምንል ከሆነ የታሪክ ተወቃሽ እንሆናለን ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ጥንታዊንና ነባሩን የአብነት ትምህርት ከዘመናዊው ትምህርት ጋር ጎን ለጎን በማስተማር የላቀ እውቀት ያለው ትውልድ ለመቅረፅ ያስችላል የተባለለት ረቂቅ ፖሊሲ ቀርቦ ከሙህራንና ከሃይማኖት አባቶች ጋር ምክክር እየተደረገበት ነው፡፡

ትዕግሥት ዘሪሁን

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ኢትዮጵያ ለአንድ ወር በምትመራው የፀጥታው ምክር ቤት የፕሬዝዳንትነት ጊዜዋ የሰላም አስከባሪ ጉዳይ የውይይት አጀንዳ ይሆናል ተባለ

ኢትዮጵያ ለአንድ ወር በምትመራው የፀጥታው ምክር ቤት የፕሬዝዳንትነት ጊዜዋ የሰላም አስከባሪ ጉዳይ የውይይት አጀንዳ ይሆናል ተባለ፡፡በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ወኪል የሆኑት አንባሣደር ተቀዳ አለሙ የኢትዮጵያን የአንድ ወር የፀጥታው ምክር ቤት ሊቀ-መንበርነት የሥራ ጊዜ በሚመለከት መናገራቸው ተሰምቷል፡፡

በወር ተራው የኢትዮጵያ የፀጥታው ምክር ቤት የሊቀ-መንበርነት ጊዜ ብዙ ጉዳዮች ለነፃ ውይይትና ምክክር ይቀርባሉ መባሉም ተሰምቷል፡፡የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭና ቋሚ አባል ሀገር ሚኒስትሮች በአዲስ አበባ ከሚያደርጉት የፀጥታው ምክር ቤት ጉባዔ በተጨማሪ ዋሽንግተን ዲሲ ላይ የሚደረገውን ጉባዔ ኢትዮጵያ በሊቀ መንበርነት ትመራለች ተብሏል፡፡

በአሁኑ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭና ቋሚ አባላት በአዲስ አበባው ጉባዔያቸው ላይ በሶማሊያ፣ በሱዳንና በደቡባዊ ሰሃራ ጉዳይ አብዝተው ይመክራሉ ተብሏል፡፡በወር ተራው የፀጥታው ምክር ቤት የኢትዮጵያ የሊቀ መንበርነት ጊዜ በተለይም ግርግርና ሁካታ ባለባቸው ሀገሮች የሚሰማራውን የሰላም አስከባሪ ጦር ጉዳይ የተመለከተ የመነጋገሪያ አጀንዳው ቀዳሚ ይሆናል መባሉንም ሰምተናል፡፡

የኔነህ ሲሣይ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ነሐሴ 30፣2009 የሸገር ወሬዎቻችን

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

 • በአዲስ አበባ የሚገኙ የመንግሥትና የግል ተቋማት ቆሻሻን በአግባቡ አያስወግዱም ተባለ፡፡ ቴዎድሮስ ብርሃኑ
 • በግል ትምህርት ቤቶች መምህራንን በኮንትራት የሥራ ቅጥር ማስፈረም ሕገ-ወጥ ነው ተባለ፡፡ በየነ ወልዴ
 • በመጪዎቹ አስር ቀናት በአንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ጎርፍ የሚያስከትል ዝናብ ይኖራል ተብሎ ተተንብይዋል፡፡ ወንድሙ ኃይሉ
 • በኢትዮጵያ ተሽከርካሪዎች ከፍጥነት ወሰናቸው በላይ እንዳያሽከረክሩ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ በትውወቅ ላይ ነው፡፡ ንጋቱ ሙሉ
 • ዛሬ በመላው ኢትዮጵያ የንባብ ቀን ሆኖ ይውላል፡፡ ንጋቱ ሙሉ
 • የ10ኛ ክፍል ፈተና ውጤት በሚመለከት በማህበራዊ ሚድያዎች እየተሰራጩ ያሉ ወሬዎች ሀሰት ናቸው ሲል ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ተናግሯል፡፡ ምሥክር አወል
 • በኢትዮጵያ የፀጥታው ምክር ቤት ሊቀ መንበርነት ወር ተራ ወቅት የሰላም አስከባሪ ጉዳይ አጀንዳ ይሆናል ተብሏል፡፡ የኔነህ ሲሣይ
 • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአብነት ትምህርት ረቂቅ ፖሊሲ አሰናድታ ዛሬ ከምሁራንና ከቤተክርስቲያን አባቶች ጋር እየመከረች ነው፡፡ ትዕግሥት ዘሪሁን
 • የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ዩኒዶ /UNIDO/ ለዩኒቨርስቲ መምህራን ስልጠና መስጠት ጀመረ፡፡ ማህሌት ታደለ
 • የአለም የቱሪዝም ቀን መስከረም 17፣2009 በኦሮሚያ ክልል ይከበራል ተባለ፡፡ ምሥክር አወል
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የቅድስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በብዛት ለልብ ህመም ተጋልጠው ወደ እኛ የሚመጡት የከተማ ሰዎች ናቸው ብሏል

የቅድስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በብዛት ለልብ ህመም ተጋልጠው ወደ እኛ የሚመጡት የከተማ ሰዎች ናቸው ብሏል፡፡በሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የልብ ህክምና ተቋም አደራጁ አቶ ዩሱፍ አህመድ ናቸው በኢትዮጵያ ከተሞች የሚኖሩ ሰዎች በብዛት ለልብ ህመም ይጋለጣሉ በማለት ለሸገር የተናገሩት፡፡

ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ህክምና ክፍል የሚመጡ የልብ ህሙማን እየበዙ በመሆናቸው የቦታ ጥበት አጋጥሞ ተጨማሪ የልብ ህክምና ክፍል በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል መጀመሩንና ለዚህም በ6 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የልብ ህክምና ማሽን መተከሉን አቶ ዩሱፍ ተናግረዋል፡፡

በውጭ ሀገር የሚከናወነውን የልብ ህክምና ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ለማድረግ በመታሰቡም ባለ 250 አልጋው ትልቁ የልብ ህክምና ማዕከል ግንባታው እየተካሄደ ነው፤ ይህም በ4 ዓመት ጊዜ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደተጠበቀ አቶ ዩሱፍ ነግረውናል፡፡

ወንድሙ ኃይሉ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ድንበር ዘለል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ልጀምር ነው አለ

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ድንበር ዘለል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ልጀምር ነው አለ፡፡ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንዳለው ዘንድሮ በወጣቶች የተጀመረው ድንበር ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘመቻ እንደስያሜው ሁሉ ኢትዮጵያን ሊሻገር ይችላል አለ፡፡

ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የወጣቶች ተሣትፎና ንቅናቄ ዳይሬክተር ከአቶ ማቲያስ አሰፋ እንደሰማነው በዚህ ዓመት ወደ አፋር በመቶ ወጣቶች የተጀመረው ድንበር ዘለል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ውጤታማ በመሆኑ በአፍሪካ ሀገራትም ሊቀጥል ይችላል፡፡

ዳይሬክተሩ እንዳሉት ከሆነ ከ2010 ጀምሮ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ ፖሊሲ ፀድቆ ተግባራዊ ስለሚሆን እንዴትና በማን እንደሚመራ አገልግሎቱ ምን ጥቅም እንደሚያስገኝ በግልፅ ስለተቀመጠ ውጤታማነቱ ከአሁኑ የተሻለ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ወደ አፋር የተጓዘው የመጀመሪያው ድንበር ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃደኛ ቡድን ሰመራ ላይ ያጠናቀቀ ሲሆን የክልሉን ወጣቶችን ለሥራ አነሳስቷል ተብሏል፡፡

ይህን ድንበር የማይወስነውን አገልግሎት ከምስራቅ አፍሪካ በመጀመር ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትን እንዲያካትት ተደርጎ ፖሊሲ ተዘጋጅቶለታል ተብሏል፡፡

አስፋው ስለሺ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)
Sheger 102.1 AudioNow Numbers