• United Bank S.C.

    ሕብረት ባንክ አ.ማ.

  • Slider Two

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Sldier Three

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ሸገር ወሬዎች እና ልዩ ወሬዎች

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ሀላፊው አቶ ፍፁም አረጋ በህንዳዊው ዲፕ ካማራ እና 2 ኢትዮጵያውያን የዳንጎቴ ሲሚንቶ ሰራተኞች ላይ በተፈፀመው ግድያ...

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ሀላፊው አቶ ፍፁም አረጋ በህንዳዊው ዲፕ ካማራ እና 2 ኢትዮጵያውያን የዳንጎቴ ሲሚንቶ ሰራተኞች ላይ በተፈፀመው ግድያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ማዘናቸውንና መንግስታቸው በወንጀሉ ፈፃሚዎች ላይ በአስቸኳይ ምርመራ በማድረግ ጉዳዩን ለፍትህ እንደሚቀርቡ መናገራቸውን አቶ ፍፁም በቲውተር ገፃቸው አስፍረዋል፡፡
 
ቢቢሲ አማርኛ ደግሞ ከጥቃቱ በኋላ በቦታው የተገኙ የዓይን እማኞች ነገሩኝ እንዳለው ከሆነ ጥቃቱ የተሰነዘረባቸው ሰዎች ይጓዙበት በነበረው ቶዮታ ላንድክሮዘር መኪና አካባቢ 17 የሚሆኑ የጥይት ቀለሃዎችን አይተዋል ብሏል፡፡
 
በኦሮሚያ ክልል በነበረው አለመረጋጋት የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ከባድ ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎች ላይ ጥቃት ተሰንዝሮባቸው እንደነበር ያስታወሰው የወሬ ምንጩ ሆኖም በአካባቢው ህብረተሰብና በፋብሪካው ሀላፊዎች መካከል በተደረገው ውይይት መልካም የሚባል ግንኙነት ተፈጥሮ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
 
ስራ አስኪያጁ በአካባቢው ህብረተሰብም ተወዳጅ ነበሩ ያለው የወሬ ምንጩ የአደአ በርጋ የኦህዴድ ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ድሪርሳ ታደሰ ስራ አስኪያጁና ሁለቱ ኢትዮጵያውያን የተገደሉት ጋቲራ በተባለ ቦታ መሆኑን እንደነገሩት ፅፏል፡፡
 
መረጃዎች እንደሚጠቅሙት የዳንጎቴ ግሩፕ ባለቤቱ ናይጄሪያዊው ቱጃር አሌኮ ዳንጎቴ ዛሬ አዲስ አበባ ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ዳንጎቴ የሚመጡት ቀድሞ በያዙት ዕቅዳቸው ይሁን በድንገት መረጃዎች ያሉት ነገር የለም፡፡
 

ምስክር አወል
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ትላንትና በአዲስ አበባ የተደረገው የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና የግብፅ ከፍተኛ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ለ15 ሰዓታት የዘለቀና በጣም ረጀም ነበርም ተባለ

ከቀኑ 6፡30 ገደማ የተጀመረው የሁለተኛው ከፍተኛ የሚኒስትሮቹ ስብሰባ ከሌሊቱ 9፡30 መጠናቀቁን የውጪ ጉዳይ መ/ቤት ቃል አቀባይ መለስ አለም ለሸገር ተናግረዋል፡፡በትላንትናው እለት የሶስቱ ሀገር ሚኒስትሮችና ልዑካኖቻቸው ተግባብተውባቸዋል ከተባሉ 4 ነጥቦች መሀከል ከዚህ ቀደም ግብፆች አማካሪው ባቀረበው የጥናት ማስጀመሪያ ሪፖርት ላይ አስተያየትም ሆነ ማብራሪያ ያለመቀበል ሀሳብ መለውጥ ይገኝበታል ተብሏል፡፡

ከግብፅ ወገን ታላቅ ተቃሞው ሲቀርብበት የነበረው የግድቡ ውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ጉዳይ ሌላው የሀገራቱ የልዩነት ነጥብ የነበረ ሲሆን በትላንትናው ስብሰባ ከስምምነት መድረሱን አቶ መለስ አለም ተናግረዋል፡፡የሶስትዮሽ የመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ማቋቋም እንዲቻል ቀጣዩን ስብሰባ ግብፅ ካይሮ ላይ ለማድረግ እና የሶስቱ ሀገር መሪዎች በዙር በተራ በአመት ሁለት ጊዜ በየሀገሮቻቸው መዲና መደበኛ ምክክር እንዲያደርጉ መስማማታቸውንም ሰምተናል፡፡በግብፅ ካይሮ የሚደረገውን ስብሰባ ቀነ ቀጠሮ በተመለከተ ወደፊት የሚነገር ይሆናል ተብሏል፡፡

የኔነህ ሲሳይ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

በቅርብ አመታት ውስጥ ብቻ ጠንክር፣ ጎፈር፣ ወርቁ፣ ቃኘው፣ በሻቱ የተባሉ እና ሌሎችም አናብስቶች ሞተዋል

በቅርብ አመታት ውስጥ ብቻ ጠንክር፣ ጎፈር፣ ወርቁ፣ ቃኘው፣ በሻቱ የተባሉ እና ሌሎችም አናብስቶች ሞተዋል…በንጉሱ ዘመን ግቢ ተከልሎላቸው ይኖሩ የነበሩ የአንበሳ ግቢዎቹ አንበሶች ጉዳይ አሳሳቢ ነው ሲሉ ምንጮች ለሸገር ተናገሩ፡፡ሸገር ከምንጮቹ እንደሰማው የቀለብ መስተጓጎል፣ የህክምና መጓደል እና እርጅና ተደማምሮ በቅርብ አመታት ውስጥ ብቻ ጠንክር፣ ጎፈር፣ ወርቁ፣ ቃኘው፣ በሻቱ የተባሉና ሌሎችም አናብስቶች መሞታቸውን ሰምተናል፡፡

ጉዳዩ ያሳስበናል ያሉ ወጣቶችም ስለ ሁኔታው ከ5 ዓመት ጀምሮ ለከንቲባ ጽ/ቤት አመልክተናል ያሉ ሲሆን ዛሬም ምክትል ከንቲባውን በአካል አግኝተው እንዳስረዷቸውና እሳቸውም ጉዳዩን የሚከታተል ኮሚቴ መመደባቸውን ሰምተናል፡፡መረጃውን ለሸገር የተናገሩት የቅርብ ምንጮች እንዳሉት አፋጣኝ መፍትሄ ካልተወሰደና መንግስት ጉዳዩን በትኩረት ካላየው የከተማዋ ብሎም የሀገሪቱ የቱሪስት መስህብ የሆኑት አንበሶች ጉዳይ አሳሳቢ ነው፡፡

ግቢው ለእድሳት ከመዘጋቱ በፊትም አንበሶቹን በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ አገር ቱሪስቶች በሰልፍ ጭምር ይጎበኛቸው ነበር ተብሏል፡፡ስለ ግቢው እድሳት መጓተት ስለ አንበሶቹ ወቅታዊ የጤና ሁኔታና የምግብ አቅርቦት እንዲነግሩን የጠየቅናቸው የግቢው ሀላፊ ዶ/ር ሙሴ ክፍሎም ጉዳዩን ከእርሳቸው ይልቅ የአንበሶቹን ሐኪም እንድንጠይቅ ነግረውናል፡፡

ሆኖም የሀኪሙን አድራሻ ማግኘት ያልቻልን ሲሆን መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ የሆነ አካል ሲኖር ምላሹን አካተን እናቀርባለን፡፡አንበሳ በተለይም ባለ ጎፈር አንበሳ በቀደሙት ጊዜያትና አሁንም ቢሆን የሀገራዊ ጀግንነት ምልክቶች መሆናቸውን የታሪክ ተመራማሪው አቶ አበባው አያሌው ለሸገር ተናግረዋል፡፡የታሪክ ተመራማሪው እንደነገሩን በተለይ ባለ ጥቁር ጎፈር አንበሶች በአፍሪካ ውስጥ የተለዩና ብቸኛ የኢትዮጵያ ዝርያዎች እንደሆኑ ነግረውናል፡፡

ምስክር አወል

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ኢትዮጵያ ውስጥ ለማምረት ከሚያስፈልገው ወጪ ይልቅ ምርቱ ተጠቃሚው ጋር እስኪደርስ የሚወጣው ገንዘብ ይበልጣል ተባለ

የአለም ባንክ እንዳለው ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ምርት ከተመረተበት ዋጋ ይልቅ ተጠቃሚው ጋር እስኪደርስ ብዙ ገንዘብ ይወጣበታል፡፡ለአብነትም አንድ ኩንታል ጤፍ በ2 ሺ 4 መቶ ብር በአማካይ እንደሚሸጥ ባንኩ ጠቅሷል፡፡

አንድ ኩንታል ጤፍ ለማምረት የሚያስፈልገው ገንዘብ ግን 9 መቶ 36 ብር እንደሆነ ባንኩ ይፋ አድርጓል፡፡ከአንድ ኩንታል ጤፍ አጠቃላይ የመሸጫ ዋጋ 81 በመቶ የአገልግሎት ክፍያ እንደሆነ ባንኩ እወቁት ብሏል፡፡የአለም ባንክ የኢትዮጵያን ምጣኔ ሐብት ይዞታ በተመለከተ ያዘጋጀውን ሪፖርት ዛሬ በሒልተን ሆቴል ይፋ አድርጓል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ በዘንድሮ የጎርጎሮሳውያን አመት የአጠቃላይ ብሔራዊ አገራዊ ሀብት (GDP) እድገቷ ስምንት በመቶ ገደማ ይሆናል ብሏል፡፡የዋጋ ግሽበቱ በአንድ አሃዝ ተገድቦ ይቆያል የሚል ትንበያውን ይፋ አድርጓል፡፡የአገሪቱ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት መጠንም ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ባንኩ በሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡

አገሪቱ እያቋቋመቻቸው ያሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰቱ ማደግ ምክንያት ይሆናሉ ብሏል፡፡የውጪ ምንዛሬ እጥረት ግን በቀጣዩ ፈተና እንደሆነ ሊቀጥል እንደሚችል የአለም ባንክ በሪፖርቱ አስፍሯል፡፡የአለም የነዳጅ መሸጫ ዋጋ መጨመርም በዘንድሮ የጎርጎሮሳውያን አመት የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ፈተና ሊሆን የሚችል ጉዳይ ነው ብሏል፡፡

ንጋቱ ረጋሳ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የተማሪዎች ሥነ-ምግባር አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ተናገረ

የሥነ-ዜጋና ሥነ-ምግባር ትምህርት የታለመለትን ውጤት አላመጣም ተብሏል፡፡ተማሪዎች በትምህርት አይነቱ የሚያስመዘግቡት ውጤትና በተግባር የሚያሳዩ ሥነ ምግባር እጅጉን የተራራቀ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ እንደሻው ጣሰው ተናግረዋል፡፡በመሆኑም ከወላጅ ጀምሮ ጠቅላላው ማህበረሰብ የልጆች ሥነ-ምግባር መሻሻል ላይ መስራት ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ትምህርት ቢሮም በከተማዋ ያሉ 1800 የሚደርሱ የሥነ-ዜጋ እና ሥነ-ምግባር መምህራንን ለተማሪዎች ሥነ-ምግባርና አገር ግንባታ በሚረዱ ሰነዶች ላይ ተከታታይ ስልጠናዎችን የሰጠ መሆኑንና ወደፊትም እንደሚቀጥልበት ተናግረዋል፡፡ከዚህም በተጨማሪ መምህራን ስለሚያስተምሩት ትምህርት በቂ እውቀት እንዲኖራቸውና ለተማሪዎች ምሳሌ የሚሆን ጥሩ ሥነ-ምግባር እንዲኖራቸው ለማስቻል የሚሰሩ መሆኑን የቢሮ ሀላፊ አቶ እንደሻው ተናግረዋል፡፡

በልጆች ሥነ-ምግባር ግንባታ ላይ የመገናኛ ብዙሃን ድርሻም የጎላ ነው ተብሏል፡፡

በየነ ወልዴ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ባለፈው አንድ ወር ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ስደተኞች ቁጥር ቀንሷል ተባለ

በወሩ 2 ሺህ 682 ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሲሆን አሃዙ በመጋቢትና በየካቲት ወራት ከመጡት ጋር ሲነፃፀር ከግማሽ በላይ ቅናሽ ማሳቱን ሰምተናል፡፡በየካቲት ወር 7 ሺ 200 በመጋቢት ወር ደግሞ 6 ሺ 996 ስደተኞች በተለይ ከጎረቤት አገራት ኢትዮጵያን አስጠልይን ብለው መምጣታቸውን የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛው የስደተኞች ኮሚሽን የኢትዮጵያ ቢሮ ነግሮናል፡፡

ባለፈው አንድ ወር ወደ ኢትዮጵያ የገቡትን ጨምሮ በኢትዮጵያ የሚገኙት ስደተኞች ብዛት 915 ሺ 73 መድረሱን ሰምተናል፡፡ከስደተኞቹ 57 በመቶዎቹም ከ18 አመት በታች የሆኑ ህፃናት ናቸው ተብሏል፡፡

በፈረንጆቹ አቆጣጠር ባለንበት 2018 በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች የምግብና መጠጥ፣ መኖሪያ እንዲሁም ህክምናን ለመሳሰሉ አገልግሎትች ማሟያ 335.8 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተብሎ የተነገረ ሲሆን እስካሁን ከለጋሾች የተገኘው 53 ነጥብ 5 ሚሊዮን ወይንም አጠቃላይ ከሚያስፈልገው 16 በመቶ ብቻ መሆኑን ከድርጅቱ ቢሮ ሰምተናል፡፡በኢትዮጵያ ያሉ ስደተኖች በስድስት ክልሎች በሚገኙ 26 የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ይኖራሉ፡፡

ንጋቱ ሙሉ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

አርብ አርብ ይካሄድ የነበረው የካቢኔ ስብሰባ ወደ ቅዳሜ መዛወሩን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ

ዶክተር አብይ ከሚኒስትሮች ፤ ሚኒስትር ዴኤታዎችና ዋና ዳይሬክተሮች ጋር ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ውይይት አድርገዋል፤ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በፊት በየሳምንቱ አርብ ጠዋት በስራ ሰዓት ሲካሄድ የነበረው የካቢኔ ስብሰባ ወደ ቅዳሜ ጠዋት መዛወሩን በውይይቱ ላይ ተናግረዋል፤በስብሰባ ላይ በማይገባ ክርክርና ጭቅጭቅ የሚባክኑ ሰዓቶችን ለመቀነስ ጥረት እንደሚደረግ መናገራቸውንም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት መረጃ አስፍሯል

ሚኒስትሮች አርብ በስብሰባ ስም ጊዜ ማባካን እንደሌለባቸው ማሳሰባቸውን ደግሞ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጽፏል፤እያንዳንዱ ሚኒስትር ከዚህ በኋላ ለስብሰባ ሲመጣ በቂ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባው የተናገሩት ዶክተር አብይ፤ “ሚኒስትር ሃሳብ አመንጪ እንጂ አቃቂር አውጭ አይደለም” ብለው መናገራቸው ተሠምቷል

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የስብሰባዎች መብዛትና መንዛዛት የመንግስት የስራ ጊዜ ላይ ተጽዕኖ እንዳለው ከዚህ ቀደም መናገራቸው ይታወሳል።በውጭ ሀገራት ባንኮች *የባንክ ሂሳብ* ወይም አካውንት ያላቸው ባለስልጣናት በአካውንቶቻቸው ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋልየባለስልጣናቱን አካውንት በማጣራቱ ተግባር ሀገራትም እየተባበሩ ናቸው ብለዋል

በቀጣይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልዩ ልዩ ቋሚ ኮሚቴዎች ከሚመለከታቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር የስራ ስምምነት እንዲፈጽሙ እና ስራውን በዚሁ አግባብ እንዲሰሩ አዘዋል፤
እያንዳንዱ የመንግስት ተሿሚ አሰራሩን ግልጽና ለህዝብ የማይደበቅ ማድረግ አለበትም ብለዋልጠቅላይ ሚኒስትሩ በውይይቱ ላይ የራሳቸውን ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርበዋል የተባለ ሲሆን የአመራር ጥበብን የተመለከተ ገለጻ ማድረጋቸውንም ሠምተናል

ባቀረቡት ጽሁፍ ላይ ስራን ከማቀድ ጀምሮ እስከሚጠናቀቅበት ጊዜ ድረስ በምን ያህል ጊዜና ወጪ መስራት እንደሚገባ አብራረተዋል ተብላል፤ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለስልጣናት ኢትዮጵያ አድጋለች ከማለት ባሻገር በተጨባጭ ህዝቡ ምን ያህል ተጠቅሟል የሚለውን መፈተሽና ማረጋገጥ እንዳለባቸው አሳስበዋል

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከውይይቱ በሁዋላ ባለስልጣናቱን በአጼ ሚኒሊክ፣ በአጼ ኃይለሥላሴ እና በደርግ ዘመን የተለያዩ ታሪካዊ ድርጊቶች የተፈጸሙባቸውና በቤተመንግስት የሚገኙ- እስካሁንም ድረስ ዝግ የነበሩ የተለያዩ ክፍሎችን አስከፍተው እንዲጎበኙ አድርገዋል።በዚህም ባለስልጣናቱ የነገስታቱን የግብር ቤቶች፣ አጼ ሀይለስላሴ የተገደሉበትንና የደርግ ጄኔራሎች የተረሸኑባቸውን ክፍሎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት ጎብኝተዋል።

ንጋቱ ረጋሳ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

አምስት የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ጡረታ ወጡ፡፡

ጡረታ እንደወጡ ከተጠቀሱት መካከል ጎምቱ የህወሀት መስራችና የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዮት ዋና ዳሬክተር ጄነራል አቶ ስብሃት ነጋ እንደሚገኙበት የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት አስታውቋል፡፡
 
ፅ/ቤቱ ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችው ማሻሻያ /ሪፎርም/ የተሳካ እንደሆነ የማድረጉ ስራ እንዲሁም ለህዝብ የልማትና ለውጥ ፍላጎት ተገቢ ምላሽ የመስጠቱ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያግዙ እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሚገኙ ጠቅሷል፡፡ከነዚህ እርምጃዎች መካከል ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ እያካሄዱት ያለው የካቢኔ ለውጥ ይገኝበታል ብሏል፡፡
 
ዶ/ር አብይ የተለያዩ የመንግስት ተቋማት በአዳዲስ ሀላፊዎች እንዲመሩ እያደረጉ ይገኛሉ ያለው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ከዚህ ስራ ጋር በተያያዘም ለበርካታ አመታት በመንግስት ሀላፊነት ቦታዎች ያገለገሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች በጡረታ እንዳያርፉ እየተደረገ ይገኛል ሲል ተነግሯል፡፡
 
በጡረታ እንዲያርፉ የተደረጉትም የህወሀት መስራች የነበሩትና የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዮት ዋና ዳሬክተር ጀነራል የሆኑት አቶ ስብሃት ነጋ/አብይ ስብሃትን ጨምሮ አምስት ናቸው፡፡ እነሱም ከፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ዶክተር ካሱ ኢላላ ፣ ከተቀናጀ የመሬት አጠቃቀም እቅድና ፖሊሲ ዝግጅት ፕሮጀክት አቶ በለጠ ተፈራ ፣ ከንግድና ኢንዱስትሪ የፖሊሱ ዕቅድ አፈፃፀም ክትትል አቶ ታደሰ ሀይሌ እንዲሁም ከፖሊስ ምርምር ማዕከል አቶ መኮንን ማንያዘዋል መሆናቸው ተገልፃል፡፡
 
ወደፊትም ለረጅም ጊዜ በመንግስት ሀላፊነት እየሰሩ ያሉ ሀላፊዎች በጡረታ እንዲያርፉ የማድረጉ ስራ ይቀጥላል ሲል ጽ/ቤቱ ተናግሯል፡፡

ንጋቱ ሙሉ
 
 
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

በኢትዮጵያና በቼክ ሪፐብሊክ መካከል ባለው የንግድ ግንኙነት የኢትዮጵያ ድርሻ ዝቅተኛ መሆኑ ተነገረ

በቼክ ኤምባሲ በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት እና በቼክ ሪፐብሊክ ንግድ ምክር ቤት ትብብር በተዘጋጀ የንግድ ልውውጥ መድረክ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ኤልያስ ገነቴ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ ወደ ቼክ ሪፐብሊክ ያደላ መሆኑ ተናግረዋል፡፡

ቼክ ከኢትዮጵያ የተቆላ ቡና ፣ የተፈተገ ሰሊጥ እና ሌሎችም ምርቶችን በብዛት ብትፈልግም ኢትዮጵያውያን አምራቾችና ላኪዎች ደረጃውን የጠበቀ አለም አቀፉን መስፈርት የሚያሟላ አቅርቦት ስለሌላቸው ሊገኝ የሚችለውን የውጪ ምንዛሬ እንዳያስገቡ እንቅፋት ሆኖባቸዋል ብለዋል ፕሬዝዳንቱ ፡፡የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አምራቾችና ላኪዎች የሚጠበቅባቸውን መስፈርት እንዲያሟሉ ለማስቻል እየሰራ መሆኑንም አቶ ኤልያስ ተናግረዋል፡፡

በማኒፋክቸሪግ ዘርፍ በአለም ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸው የቼክ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያደርጉ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤትና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተባብረው ሊሰሩ ይገባል ተብሏል፡፡በዝግጅቱ ላይ የተለያዩ የቼክ ሪፐብሊክ ኩባንያዎች ልምዳቸውን ያካፈሉ ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ለመስራት ያላቸውን ቀጥተኛ ፍላጎት አሳይተዋል፡፡

ማህሌት ታደሰ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ኒውትሪሽን ኢንተርናሽናል የተባለው አለም አቀፍ ድርጅት ዛሬ በሂልተን ሆቴል ኢትዮጵያ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ስኬትና ወደፊት ተስፋዎችን በተመለከተ ውይይት አካሂዷል

ኢትዮጵያ ሴቶች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ እና ጤናቸው እንዲጠበቅ የምታደርገውን ጥረት በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር የሆኑት ፊሊፕ ቤከር አድንቀዋል፡፡ የአንዲት አገር ዜጎች ጤናማና የዳበሩ ሆነው መገኘት ለተቀረው አለም ስኬት ነው ያሉት አምባሳደሩ ይህም የሚሳካው የተመጣጠነ ምግብ ለዜጎች በማቅረብ ነው ብለዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ከአምባሳደሩ በተጨማሪ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የእናቶችና የህፃናት ጤናና የተመጣጠነ ምግብ ዳይሬክተር ዶ/ር ኤፍሬም ታከለም ኢትዮጵያ በድህነት ቅነሳና የህፃናት ሞት ዙሪያ አመርቂ ስራዎችን ብትሰራም የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ግን መቀነስ አልቻለችም ብለዋል፡፡ ከአራት እናቶች አንዷ አሁንም ደም ማነስ እንደሚይዛት ተናግረዋል፡፡

ይህንንም በብሄራዊ የተመጣጠነ ምግብ ፕሮግራም ለመቀነስ መንግስት ቁርጥ አቋም ይዟል ብለዋል፡፡ኒውትሪሽን ኢንተርናሽናል ለዜጎች የተሻለ የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት እያደረገ ያለው ድጋፍም አድንቀዋል፡፡ኒውትሪሽን ኢንተርናሽናል እ.ኤ.አ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ቢሮውን በአዲስ አበባ ከከፈተ ወዲህ ከ90 ሚሊዮን የካናዳ ዶላር በላይ ድጋፍ እንዳደረገ ተናግሯል፡፡ኢትዮጵያ ኒውትሪሽን ኢንተርናሽናል ከተባለው ድርጅት ጋር በጥምረት መስራት ከጀመረች 20 አመታት ተቆጥሯል፡፡

ቴዎድሮስ ብርሃኑ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)
Sheger 102.1 AudioNow Numbers