• United Bank S.C.

  ሕብረት ባንክ አ.ማ.

 • Slider Two

  የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

 • Sldier Three

  የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ሸገር ወሬዎች እና ልዩ ወሬዎች

የዛሬ ጥቅምት 21፣2010 የሸገር ወሬዎቻችን

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

 • በኦሮሚያ ክልል የኤች.አይቪ ቫይረስ በደማቸው ከሚገኝ ሰዎች የፀረ ኤች.አይ.ቪ መድኃኒት የሚወስዱት ግማሽ ያህሉ ናቸው ተባለ፡፡ (ንጋቱ ሙሉ)
 • ከውጪ ሃገር የጨርቃ ጨርቅ ገበያ ባለፉት 3 ወሮች 31 ነጥብ 22 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኘ ተባለ፡፡ (ወንድሙ ኃይሉ)
 • በኦሮሚያ ክልል ባለፈው ዓመት የሥነ-ምግባር ጉድለት ባሳዩ ወደ ስድስት መቶ በሚጠጉ የትራፊክ ፖሊስ አባላት ላይ የተለያየ እርምጃ ተወስዷል ተባለ፡፡ (ንጋቱ ረጋሣ)
 • በደርግ ዘመነ መንግሥት በርካቶች እንዲገደሉና እንዲሰቃዩ አድርጓል በሚል በኢትዮጵያ በሌለበት የሞት ፍርድ ተላልፎበት የነበረው ሃምሣ አለቃ እሸቱ አለሙ በኔዘርላንድስ ፍርድ ቤት ጉዳዩ መታየት ጀመረ፡፡ (ንጋቱ ሙሉ)
 • ወላጆች ልጆቻቸውን በተለያዩ ሣይንሣዊና የቴክኖሎጂ ፕሮግራሞች ማሣተፍ አለባቸው ተባለ፡፡ (ቴዎድሮስ ብርሃኑ)
 • የሀገሪቱ የፊልም ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ተልኳል ተባለ፡፡ (ምሥክር አወል)
 • የኢትዮጵያ ብሔራዊ አክርድቴሽን ፅህፈት ቤት እውቅና የምሰጣቸው ላብራቶሪዎች ውጤት ከዚህ በኋላ በአለም አቀፍ ደረጃ ያለዳግም ፍተሻ ተቀባይነት ያገኛሉ ብሏል፡፡ (ትዕግሥት ዘሪሁን)
 • ከአዲስ አበባ ግብር ከፋዮች ባለፉት ሦስት ወራት የተሰበሰበው ገቢ ከዕቅዱ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ የቀነሰ ነው ተባለ፡፡ (ትዕግሥት ዘሪሁን)
 • የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ተሾመለት፡፡ (ምሥክር አወል)
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የከባድ ኮንስትራክሽን ማሽነሪ ማሰልጠኛ የሆኑ አራት ተቋማት ፍቃዳቸው ተሰረዘ፡፡

የከባድ ኮንስትራክሽን ማሽነሪ ማሰልጠኛ የሆኑ አራት ተቋማት ፍቃዳቸው ተሰረዘ፡፡ለማሰልጠኛ ተቋማቱ የሰጠኋቸውን ፈቃድ ሰርዣለሁ ያለው የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ነው፡፡በኦሮሚያ ክልል ጅማ ከተማ ሲሰራ የቆየው አጅሃፍና በቡራዩ ከተማ ሲያሰለጥን የነበረው ዲ.ኤስ የከባድ ኮንስትራክሽን ማሽነሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ፈቃዳቸው ከተሰረዙ መካከል ይገኙበታል፡፡

ቀሪዎቹ ሁለት ማሰልጠኛዎች በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ሲሆን ዘፍና ጵንኤል የሚል ስያሜ ያላቸው ማሰልጠኛዎች መሆናቸውን የነገሩን በትራንስፖርት ባለሥልጣን የኮሙኒኬሸን ዳይሬክተሩ አቶ ይግዛው ዳኘው ናቸው፡፡አራቱ የከባድ ኮንስትራክሽን ማሽነሪ ማሰልጠኛዎች ፈቃዳቸው የተሰረዘባቸው ማሟላት ያለባቸውን መስፈርቶች ይዘው ፈቃዳቸውን ለማሳደስ በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ማሳደስ ስላልቻሉ መሆኑን ሰምተናል፡፡

አቶ ይግዛው እንዳሉት አጅሃፍ፣ ዲኤስ፣ ዘፍና ጵንኤል የተሰኙ ማሰልጠኛ ተቋማት ለ2010 በጀት ዓመት ፈቃዳቸው በመሰረዙ ከዚህ በኋላ ከእነዚህ ተቋማት የሚመጣ የሥልጠና ሰርተፍኬት እውቅና አያገኝምና ተጠንቀቁ ተብላችኋል፡፡ማሰልጠኛ ተቋማቱ በመጪው ዓመት እንደ አዲስ የፈቃድ ጥያቄ አቅርበው በሰው ኃይልና በመሣሪያ የሚጠበቅባቸውን መስፈርት ካሟሉም ፈቃድ ሊሰጣቸው እንደሚችል አቶ ይግዛው ነግረውናል፡፡

ትዕግስት ዘሪሁን

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የዛሬ ጥቅምት 20፣2010 የሸገር ወሬዎቻችን

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

 • የተለያዩ የከባድ ኮንስትራክሽን ማሽነሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ፈቃዳቸውን መሰረዙን የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ተናገረ፡፡ (ትዕግሥት ዘሪሁን)
 • በኢትዮጵያ የተሽከርካሪዎች ብዛት እስከ 2009 ዓ.ም መጨረሻ ከ831 ሺ በላይ ደርሷል ተባለ፡፡ (ምስክር አወል)
 • የኢትዮጵያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባላት ቡድን ዘንድሮ ወደ ተለያዩ ሰባት ሀገራት ጉዞ ያደርጋል ተባለ፡፡ (የኔነህ ሲሣይ)
 • የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴና የኦህዴድ ድርጅታዊ ኮንፍረስ የተለያዩ ፖለቲካዊ ውሣኔዎችን ከስብሰባው በኋላ ያሳልፋል ተባለ፡፡ (የኔነህ ሲሣይ)
 • አርብ ዕለት በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ተጀምሯል፡፡ ምዝገባው ከመጀመሩ በፊት በኢትዮጵያ የተወለዱ ህፃናትም የልደት ሰርተፍኬት ይሰጣቸዋል ተብሏል፡፡ (ንጋቱ ሙሉ)
 • ሰባት ባለ በጀት መሥሪያ ቤቶች የፈፀሙትን ህጉን ያልተከተለ ግዢ እንዲያስተካክሉ ተነግሯቸዋል ተባለ፡፡ (ንጋቱ ረጋሣ)
 • በ2010 ዓ.ም ሩብ ዓመት ከ6 ሺ በላይ ሕፃናት የተለያዩ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት አገኙ፡፡ (ምህረት ስዩም)
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ስምንተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን በሂልተን ሆቴል እያካሄደ ነው

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ስምንተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን በሂልተን ሆቴል እያካሄደ ነው፡፡የምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ ከመደበኛ ጊዜው አንድ ዓመት ዘግይቶ ነው እየተካሄደ ያለው፡፡ጠቅላላ ጉባዔውን በወቅቱ ማካሄድ ያልተቻለው በሁለት አባል ምክር ቤቶች ውስጥ ተፈጥሮ በነበረው ችግር ምክንያት እንደሆነ ሰምተናል፡፡

አንዱ በአማራ ክልል የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ተፈጥሮ የነበረው ችግር እንደሆነ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አበበ ደበበ ለሸገር ተናግረዋል፡፡

የነበረው ችግር የአማራ ክልል የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ከሁለት ጊዜ በላይ ተመርጠዋል፣ እንዲሁም በጠቅላላ ጉባዔው ላይ መሳተፍ የሚገባቸው ሰዎች አልተሣተፉም የሚል ነው ብለዋል፡፡በሀገር አቀፉ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከቦርድ አባላት ምርጫ ጋር የነበረው ችግርም ሌላው እንደሆነ አቶ ደበበ አስታውሰዋል፡፡ 

የሁለቱ ምክር ቤቶች ችግር እስኪፈታ ድረስ ጠቅላላ ጉባዔው የሚካሄድበት ጊዜ እንዲራዘም በንግድ ሚኒስቴር በተወሰነው መሠረት እስካሁን ቆይቷል ብለዋል፡፡አሁን የምክር ቤቶቹ ችግር በመፈታቱ ጠቅላላ ጉባዔው ዛሬ እየተካሄደ እንደሚገኝ ነግረውናል፡፡የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን አፈወርቅ ለተሣታፊዎቹ የሁለት ዓመት የሥራ ክንውን ሪፖርት አሰምተዋል፡፡

ከሰዓት በኋላ ባለው ጊዜ ደግሞ ምክር ቤቱን ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት የሚመሩ ፕሬዝዳንት፣ ምክትል ፕሬዝዳንትና የቦርድ አባላት ምርጫ እንደሚካሄድ ሰምተናል፡፡

ንጋቱ ረጋሣ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የዛሬ ጥቅምት 17፣2010 የሸገር ወሬዎቻችን

 • በድህነት፣ በወላጆች ሞት፣ በቤተሰብ ግጭትና በሌሎችም ምክንያቶች በኢትዮጵያ ከሚገኙ 15 በመቶ ህፃናት በአስቸጋሪ ሁኔታ እንዲኖሩ እያደረጋቸው ነው ተባለ፡፡ (ምህረት ስዩም)
 • የብርን ዶላር የመግዛት አቅም መቀነስ ተከትሎ ብዙ ሰዎች የዋጋ ጭማሪ መታየቱ በኑሯችን ላይ ጫና እያሳደረ ነው ብለዋል፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው በበኩላቸው ቁጥጥሩን እናጠናክራለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡ (ምሥክር አወል)
 • በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች ከመጠን በላይ በተከማቸ ቆሻሻ ምክንያት በሚፈጠረው ሽታ መቸገራቸውን አንዳንድ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ (በየነ ወልዴ)
 • በ2008 ዓ.ም ሚኒስትሮች ምክር ቤት የገባው የመኖሪያ ቤቶች ልማትና ግብይት ረቂቅ አዋጅ አሁንም እዛው ነው ተባለ፡፡ መቼ እንደሚፀድቅ ባላውቅም ተግባራዊ ለማድረግ እየተጠባበቅኩ ነው ሲል የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ተናገረ፡፡ (ዮሐንስ የኋላወርቅ)
 • በ2009 ዓ.ም ከ480 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማግኘቱን ህብረት ባንክ ተናገረ፡፡ (ምህረት ስዩም)
 • ኢትዮጵያን ጨምሮ የአካባቢው አገሮች አባል የሆኑበት የናይል ተፋሰስ ልማት ነክ ስብሰባ በሩዋንዳ ኪጋሊ ተካሄደ፡፡ (የኔነህ ሲሣይ)
 • በተለያዩ ምክንያቶች በ1 ዓመት የዘገየው የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ጠቅላላ ጉባዔ እየተካሄደ ነው፡፡ (ንጋቱ ረጋሣ)
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

በቅርቡ የሥራ መልቀቂያ ያቀረቡት በሚኒስትር ማዕረግ የፖሊሲ ጥናት ምርምር ማዕከል ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ በረከት ስምኦን...

በቅርቡ የሥራ መልቀቂያ ያቀረቡት በሚኒስትር ማዕረግ የፖሊሲ ጥናት ምርምር ማዕከል ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ በረከት ስምኦን ጥያቄያቸው በመንግሥት ተቀባይነት ማግኘቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ ተናገሩ፡፡

በተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ በአባዱላ ገመዳ የሥራ መልቀቂያ ጉዳይ ግን እስካሁን ውይይት እየተደረገና ውጤቱም ገና መሆኑን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰምተናል፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት ዛሬ በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ተገኝተው ከአባላቱ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ ነው፡፡

አቶ በረከት የሥራ መልቀቂያ ጥያቄ ሲያቀርቡ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደምም በተደጋጋሚ ሥራ ለመልቀቅ አመልክተው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ይሁንና ጊዜው እንዳልሆነ ተነግሯቸውና ትግላቸውንም እንዲቀጥሉ በተደረገ ማግባባት እስካሁን ቆይተዋል ብለዋል፡፡አሁን ግን ከመንግሥት የሥራ ኃላፊነት መልቀቅ አለብኝ የሚል አቋም በመያዛቸው ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቷል ብለዋል፡፡

ትዕግስት ዘሪሁን

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ትናንትና ጋዜጠኞችን ሰብስቦ እንደተናገረው መገናኛ ብዙሃን ሥራቸውን...

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ትናንትና ጋዜጠኞችን ሰብስቦ እንደተናገረው መገናኛ ብዙሃን ሥራቸውን ሲሰሩ ህገ-መንግሥቱንና ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ብቻ መነሻ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል፡፡መገናኛ ብዙሃኑ አንድን ቡድን ለማስደሰት ብቻ መስራት የለባቸውም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘርዓይ አስገዶም ትናንት ሲናገሩ እንደሰማነው አብዛኛው የመገናኛ ብዙሃን የግል ስሜታቸውን ካለው እውነታ ጋር በማዛመድ እየሰሩ ነው ብለዋል፡፡ባለፉት 12 ወራት በሀገሪቱ በመገናኛ ብዙሃን የነበረውን አዘጋገብ ተመልክተናል ያሉት ዳይሬክተሩ አብዛኛው መረጃን በግልፅነትና በፍጥነት ለህብረተሰቡ እያደረሱ አይደለም፤ በማኅበራዊ ገፆች ተቀድመዋል ብለዋል፡፡

በተለይም በሀገሪቷ ላይ ችግር በተፈጠረ ጊዜ ህብረተሰቡ ጉዳዩን የማወቅ መብት አለውና በድፍረት ያንን የሚሰራ መገናኛ ብዙሃን ያስፈልጋል ሲሉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ከዚህ ቀደም የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ነገሪ ሌንጮ አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ነገሩን እያባባሱት ስለሆነ በህግ እንጠይቃቸዋለን ማለታቸው ይታወሣል፡፡

ባለሥልጣኑ መረጃ አልሰጥም የሚሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት ካሉ በህግ ማስገደድ ይቻላል አለበለዚያም ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልፆ መረጃውን ማስተላለፍ አማራጭ መሆኑን ዳይሬክተሩ አቶ ዘርዓይ አስገዶም ተናግረዋል፡፡

አስፋው ስለሺ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ጥቅምት 16፣2010 የሸገር ወሬዎቻችን

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

 • የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ድርጅት ባለፉት 3 ወራት ካሰብኩት በላይ ትርፍ አግኝቻለሁ አለ፡፡ (ወንድሙ  ኃይሉ)
 • የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ግብአትና ልማት ድርጅት ከ2007 በጀት ዓመት ጀምሮ 22 ሺ 266 ሜትሪክ ቶን የተዳመጠ ጥጥ ለ12 ፋብሪካዎች የ885 ሚሊዮን ብር የዱቤ ሽያጭ አከናውኛለሁ አለ፡፡ (አንተነህ ሃብቴ)
 • የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ጥገና የሚያደርግባቸው መንገዶች ዝግ ስለሆኑ የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር አማራጭ ያላቸውን መንገዶች እወቁት ብሏል፡፡ (ምህረት ስዩም)
 • በሚኒስትር ማዕረግ የፖሊሲ ጥናት ምርምር ማዕከል ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ በረከት ስምኦን ያቀረቡት የሥልጣን መልቀቂያ ጥያቄ በመንግሥት ተቀባይነት ማግኘቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ ተናገሩ፡፡ (ትዕግሥት ዘሪሁን)
 • የብሮድካስት ባለሥልጣን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ሁነቶችና ክስተቶችን በወቅቱና ግልፅነት በተላበሰ ሁኔታ እንዲዘግቡ ጠየቀ፡፡ (አስፋው ስለሺ)
 • በጥቁር አባይ የደብረ ብርሃን የቆዳ ፋብሪካ እንደ ፈረስና ዶሮ ካሉ እንስሣት የሚገኙ የቆዳ ውጤቶችን ማምረት ጀምሬአለሁ አለ፡፡ (ወንድሙ ኃይሉ)
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

እንኳን አደረሰን…

በግል ጥረት ሬዲዮ ጣቢያ ማቋቋም በጨለማ እንደመጓዝ ከባድ በነበረበት ወቅት፥ ለሬዲዮ ያለንን ፍቅር ብቻ ይዘን የጀመርነው ሸገር 102.1 ሬዲዮ አስር ዓመት ሞላው፡፡ህልማችን ምን ነበር? ተስፋችንና ፍላጎታችንስ? ሸገር አዲስ የሬዲዮ መላና አቀራረብ አዲስ የሬዲዮ ቃና ይዞ እንዲቀርብ ምኞታችን ነበር፡፡ ከተለመደው የተለየ፤ አለበለዚያማ ለምን? የምንል ደፋሮች ነበርን፡፡ ተስፋችን፥ ሕልማችንን የሚጋሩ ባለሙያዎች፣ ጣቢያውን የእኛ ብለው የሚያደምጡ አድማጮች ማግኘት ነበር፡፡

ሸገር የተመኘው ገለልተኛ፥ ኃላፊነት የሚሰማው፣ በአድማጮቹ የሚታመን፣ የመረጃና መዝናኛ ሬዲዮ ጣቢያ መሆን ነበር፡፡ ሸገር ቀድመው ረጅም ርቀት ከተጓዙትም ሆነ አብረው ሩጫ ከጀመሩት በተለየ መንገድ ለመጓዝ ሞክሯል፡፡

የሸገር እሴቶች ለጋዜጠኝነት ሙያዊ ብቃትና ስነምግባር እንዲሁም ለሙያ ነፃነት መከበር መቆም፤ እውነትን በትክክለኛነት፣ በሚዛናዊነትና በጨዋነት መናገር፤ የአድማጮቹን ፍላጎት፣ ባህልና ወግ ማክበር፤ ከማንም ጋር ያለመወገን፣ ለሁሉም እኩልና ፍትኃዊ ዕድል መስጠት ናቸው፡፡ የሸገር ሙያተኞች በእነዚህ አስር ዓመታት እነዚህን እሴቶቻቸውን በሚቻላቸው ጠብቀው ለመዝለቅ ሞክረዋል፡፡

ሸገር ስርጭቱን እንደጀመረ በተደጋጋሚ የሚመጡ አስተያየቶች፣ ምስጋናው እንዳለ ሆኖ፣ “አትደፍሩም፣ ትፈራላችሁ፣ እንዳንዴም ደፈር ማለት ያስፈልጋል” የሚሉ ነበሩ፡፡

በዚህ ረገድ የሸገርን አቋም ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡ ይህም ገለልተኛ ሬዲዮ ጣቢያ መሆንና አማካዩን ቦታ መያዝ ነው፡፡ ገለልተኝነት መቃወምም፣ መደገፍም አይደለም፡፡ የተለየ እምነት፣ አቋምና የፖለቲካ መስመር ማራመድም አይደለም፡፡ ወይንም ያለውን አቋም፣ እምነትና መስመር መቃወምም መደገፍም አይደለም፡፡ የሸገር ወገንተኝነት ከሕዝብ ጋር ነው፡፡ ሸገር የአድምጮቹን ፍላጎት ከግምት በማስገባት እርካታ ማግኘታቸውን ለማረጋገጥ ይሠራል፡፡ ለጋራ ጥቅም ለእድገትና ብልጽግና ይቆማል፡፡ ለአድማጮች የዕለት ተለት የሕይወት ፍላጎት የሚሆኑ የመረጃና የመዝናኛ ፕሮግራሞች በጥራት ለማዘጋጀትና ለማስደመጥ ይተጋል፡፡ ሸገር ወደፊትም በዚሁ አቋሙ ፀንቶ፣ በርካታ ወጣት ሙያተኞች አፍርቶ፣ ለፕሬስ ነጻነትና ለጋዜጠኝነት ስነምግባር ታማኝ ሆኖ፣ ለአገራችን ሚዲያ ዕድገት የድርሻውን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይቀጥላል የሚል እምነት አለን፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለሁላችሁም ልባዊ ምስጋና እናቀርባለን፡፡

ሸገር የናንተው ነው!

ወ/ሮ መዓዛ ብሩ - የሸገር ኤፍ ኤም 102.1 መሥራችና ሥራ አስኪያጅ
አስተያየት ይፃፉ (4 Comments)

ለዛ የምሳ ሰዓት ፕሮግራም ጥቅምት 14፣2010

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የተጀመረው የኩላሊት ንቅለ ተከላ በየወሩ መካሄድ መጀመሩን የኩላሊት ህመምተኞች እጥበት በጎ አድራጐት ድርጅት ተናገረ

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የተጀመረው የኩላሊት ንቅለ ተከላ በየወሩ መካሄድ መጀመሩን የኩላሊት ህመምተኞች እጥበት በጎ አድራጐት ድርጅት ተናገረ፡፡ከዚህ ቀደም በሦስትና በአራት ወር ልዩነት ህክምናው ይሰጥ እንደነበር ሰምተናል፡፡አሁን የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እራሱን በማደራጀት ህክምናውን በየወሩ መስጠት መጀመሩን ማኅበሩ ተናግሯል፡፡ልምድ ባላቸው ሀኪሞች የተሳካ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ተጠቃሚ የሆኑ የኩላሊት ህመምተኞች ቁጥርም 50 መድረሱን ሰምተናል፡፡

ኩላሊት የሰጡና የተቀበሉ ሰዎችም ዛሬ በኢትዮጵያ ሆቴል ዲያሊሲስ /የኩላሊት እጥበት ህክምና/ እያደረጉ ላሉ የማኅበሩ አባል ለሆኑ የኩላሊት ህመምተኞች ልምዳቸውን እያካፈሉ ነው፡፡ኩላሊት የሰጡትም ሆነ የተቀበሉትም ጤናማ ህይወት እየኖሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የኩላሊት ንቅለ ተከላ ተጠቃሚ የሆኑት ሰዎች ከዚህ ቀደም ህይወታቸውን ለማቆየት ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቀውን የኩላሊት እጥበት ህክምና እየወሰዱ መቆየታቸውን የተናገሩት የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አሰፋ ሌሎችም ህክምናውን እየወሰዱ ያሉ ህሙማንም  በመጪው ጊዜ ጤናማ ህይወት እንዲኖራቸው የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምናው ያስፈልጋቸዋል ብለዋል፡፡

እዚያ ለመድረስ ግን አሁን የጀመሩት የኩላሊት እጥበት ህክምና ሳይቋረጥ በህይወት መሰንበት ይጠበቅባቸዋልና ህብረተሰቡ በ8846 A ብሎ በመላክ የጀመረውን ድጋፍ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡ኩላሊታቸው ሙሉ በሙሉ ሥራ በማቆሙ ምክንያት የኩላት አጥበት ህክምና እንዲያገኙ ማኅበሩ ከ400 በላይ ለሆኑ አባላቱ በየሳምንቱ ለእያንዳንዳቸው 600 ብር የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል፡፡

ሥራ አስኪያጁ አቶ ሰለሞን እንዳሉት ማኅበሩ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ይሰጥ የነበረውን የኩላሊት እጥበት ድጋፍ በመጪው ጊዜ በመቐሌ፣ ሃዋሳ፣ ባህርዳር፣ ጎንደርና ድሬዳዋ ከተሞችም ለሚገኙ የኩላሊት ህመምተኞች ተመሳሳይ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅቱን ጨርሷል ብለዋል፡፡

ትዕግሥት ዘሪሁን
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)
Sheger 102.1 AudioNow Numbers