• United Bank S.C.

  ሕብረት ባንክ አ.ማ.

 • Slider Two

  የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

 • Sldier Three

  የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ሸገር ወሬዎች እና ልዩ ወሬዎች

የኢትዮጵያ ብር የመግዛት አቅሙ ከዶለር አንፃር በ15 በመቶ ዝቅ እንዲል መደረጉ በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ የሚያስከትለው የዋጋ ግሽበት ሊጠና ነው ተባለ

የኢትዮጵያ ብር የመግዛት አቅሙ ከዶለር አንፃር በ15 በመቶ ዝቅ እንዲል መደረጉ በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ የሚያስከትለው የዋጋ ግሽበት ሊጠና ነው ተባለ፡፡የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኀበር ፕሬዝዳንት ኢንጂነር አበራ በቀለ እንዳሉት ከሆነ የብር የመግዛት አቅሙ ዝቅ እንዲል ከተደረገ ወዲህ ባለው አጭር ጊዜም ቢሆን የዋጋ ንረቱ ጐልቶ እየታየ ነው፡፡

በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩት የማኅበሩ አባሎችም የዋጋ ንረቱን እንዴት ብናደርግ ይሻል ይሆን ብለው ወደ ማኅበሩ ጥያቄ እያቀረቡ ነው ያሉት ኢንጂነር አበራ ማኅበሩም ከደንበኞቻችሁ ጋር  በደንብ ተነጋገሩ ከዚያም ካለፈ ከእኛም ጋር ቢሆን መፍትሔ እንፈልጋለን ብለናቸዋል ብለዋል፡፡

የዋጋ ግሸበቱ በተለይም አዲስ ኮንትራክት ወስደው ሥራ በጀመሩት ላይ ጫናው ይበረታል ሲሉም ተናግረዋል፡፡የዋጋ ማካካሻ መጠየቅ የሚቻለው አንድም ከ18 ወራት በላይ የሚወስድ ግንባታ ከዚያም ሲልያፍ ደግሞ ግንባታው ከተጀመረ 12 ወራት ያለፈው መሆን ያለበት ነው ያሉት ኢንጂነር አበራ ይህን መስፈርት የማያሟሉ ማካካሻ መጠየቅ ባይችሉም ጫናው ካለና ኮንትራክተሩ ከገበያ ማውጣት ስለሌለበት መፍትሄ የሚያገኙበት መንገድ ይኖራልም ብለዋል፡፡

በአጠቃላይም የዋጋ ለውጡ ምን ያህል እንደሆነና መፍትሃው ምን ሊሆን እንደሚችል ከጥናቱ በኋላ ይፋ እናደርጋለን ሲሉም ነግረውናል፡፡

ዮሐንስ የኋላወርቅ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያ እንደተደረገበት ከተነገረ ወዲህ በተለያዩ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ እየተደረገ ይታያል

የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያ እንደተደረገበት ከተነገረ ወዲህ በተለያዩ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ እየተደረገ ይታያል፡፡መንግሥት ምንም እንኳ የተደረገው የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያው ለዋጋ ጭማሪ የሚዳርግ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የለውም ቢልም ምርቶቻቸው ላይ ዋጋ የጨመሩ እንዲሁም የሸሸጉ ነጋዴዎች ተስተውለዋል፡፡

ለምሣሌም በግንባታ ዕቃዎች፣ በኤሌክትሮኒክስ ምርቶች፣ በመኪና ጎማና በመድኃኒት በመሳሰሉት ላይ ጭማሪው ታይቷል፡፡የውጭ ምንዛሪ ተመን ማሻሻያው ሰበብ ሆኖ በምርቶች ላይ ዋጋ እየተጨመረ ነው ምን እየሰራችሁ ነው ሲል ሸገር የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮን ጠይቋል፡፡

የቢሮው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በላይነህ ወልደሰንበት እንደሚሉት የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ከሌሎች መሥሪያ ቤቶች ጋር በጋራ በመሆን ከነጋዴዎች ጋር ዋጋ እንዳይጨምሩ በመመካከር እንዲሁም ይህን ተላልፈው በሚገኙት ላይ ደግሞ እርምጃ እየወሰደ ነው ብለዋል፡፡ከአስመጪዎች ጋርም ትናንት ምክክር ነበር ያሉት አቶ በላይነህ አንዳንዶቹ አስመጪዎችና አምራቾች እንደውም እኛ ሳንሆን ቸርቻሪዎች ናቸው ጭማሪ ያደረጉት ብለዋል ብለውናል፡፡

ከህብረተሰቡ ጥቆማ ካልደረሰን እኛ ብቻችንን ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉትን መቆጣጠር ይቸግረናል ያሉት አቶ በላይነህ መርካቶ ሲዳሞ ተራ፣ ተክለኃይማኖት፣ መገናኛ አካባቢዎች የተለያዩ ምርቶችን ሸሽገው የተገኙ ነጋዴዎች መደብራቸው ታሽጐ ምርመራ እየተካሄደባቸውም ነው ብለዋል፡፡የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያውን ሰበብ አድርገው በምርቶቻቸው ላይ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ካጋጠሟችሁ በ8588 ደውሉና ንገሩኝ ሲል የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ጥሪ አቅርቦላችኋል፡፡ 

ንጋቱ ሙሉ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ጥቅምት 14፣2010 የሸገር ወሬዎቻችን

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

 • የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የብርን የምንዛሪ ተመን ማስተካከያ አሳበው የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉት ላይ እርምጃ እየወሰድኩ ነው አለ፡፡ ሕብረተሰቡም በጥቆማ እንዲረዳው ጠይቋል፡፡ (ንጋቱ ሙሉ)
 • ትናንት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ወደ ጅቡቲ መሄዳቸው ተሰምቷል፡፡ ፕሬዝዳንት መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ ፎርማጆ በአዲስ አበባ የአንድ ቀን ቆይታቸው ከከፍተኛ ሹማምንት ጋር ተነጋግረዋል ተብሏል፡፡ (የኔነህ ሲሣይ)
 • የብር ምንዛሪ አቅም መቀነስ በግንባታው ዘርፍ ላይ ሊያስከትል የሚችለው ተፅዕኖ በመስኩ ማኅበር እየተጠና ነው፡፡ (ዮሐንስ የኋላወርቅ)
 • በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የኩላሊት ንቅለ ተከላ በየወሩ መካሄድ ጀመረ፡፡ (ትዕግሥት ዘሪሁን)
 • የያዝነው ጥቅምት ወር ነፋሻማ መሆኑ ለእሳት አደጋ መደጋገም ምክንያት ነው መባሉን ከእሣትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን ሰማን፡፡ (ወንድሙ ኃይሉ)
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ያለ አገልግሎት ያከማቿቸውን ንብረቶች ከብክነት ለመታደግ በሽያጭ...

የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ያለ አገልግሎት ያከማቿቸውን ንብረቶች ከብክነት ለመታደግ በሽያጭ እንዲያስወግዱና ገንዘቡንም ለመንግሥት እንዲያስገቡ ባለፈው ዓመት ትዕዛዝ ከተላለፈባቸው 108 መሥሪያ ቤቶችና ዩኒቨርስቲዎች መካከል 54ቱ አሁንም ንብረቶቹን ሸጠው ገንዘቡንም አላስረከቡም ተብሏል፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ከፍተኛ የንብረት ክምችት አላቸው ያላቸውን 108 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ዩኒቨርስቲዎች ንብረታቸውን እስከ ሰኔ ወር 2009 ዓ.ም ድረስ ሸጠው ገንዘቡንም ለመንግሥት ፈሰስ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር፡፡

በትዕዛዙ መሠረት 75 የፌዴራል መሥሪያ ቤቶችና 9 ዩኒቨርስቲዎች ያለ አገልግሎት ያከማቿቸውን ንብረቶች በሸያጭ ማስወገዳቸውን ሰምተናል፡፡ከመካከላቸውም 26 መሥሪያ ቤቶችና አንድ ዩኒቨርስቲ ያለ አገልግሎት ያከማቿቸውን ንብረቶች ሸጠው 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ለመንግሥት ገቢ ማድረጋቸውን ፤ ለመንግሥት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ሪፖርት እንዳደረጉ የነገሩን የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር  የሆኑት አቶ ሰለሞን ዐይንማር ናቸው፡፡

ቀሪዎቹ መሥሪያ ቤቶችም በሽያጭ ካስወገዷቸው ንብረቶች  ያገኙትን ገንዘብ መጠን ለአገልግሎቱ ሪፖርት ሲያደርጉ ይፋ እናደርጋለን ብለዋል አቶ ሰለሞን፡፡እስካሁን ያከማቿቸውን ንብረቶች በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ መሠረት ማስረከብ ያልቻሉ 33 የፌዴራልና 21 ዩኒቨርስቲዎች በአጠቃላይ 54 መሥሪያ ቤቶች ሽያጩን እንዲያከናውኑም የመንግሥት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ሙያዊ ድጋፍ እየሰጣቸው መሆኑን ከአቶ ሰለሞን ሰምተናል፡፡

በተያያዘም በየመንግሥት መሥሪያ ቤቱ የንብረቶችን ብክነት ለመታደግ አሁንም ክትትል ማድረጋችን ቀጥለናል ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ ለብክነት የተጋለጠ ከፍተኛ የንብረት ክምችት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን ጨምሮ 50 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ ጥናት እያደረግን ነው ብለዋል፡፡ከመካከላቸውም የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር፣ የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር፣ ትምህርት ሚኒስቴርና ሌሎችም ይገኙበታል ተብሏል፡፡

ትዕግሥት ዘሪሁን
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ባለፈው ክረምት ለመጠገን ሞክሬ መልሶ መፈራረስ...

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ባለፈው ክረምት ለመጠገን ሞክሬ መልሶ መፈራረስ ያሳየውን የከተማውን መንገድ በአዲስ መልክ መጠገን ጀምሬያለሁ አለ፡፡የህዝብ ግንኙነት ኃላፈው አቶ ጥዑማይ ወልደገብርኤል ለሸገር ሲናገሩ አምና በ350 ሚሊዮን ብር ወጪ ጥገና ተደርጐላቸው በክረምቱ ሰበብ መልሰው መፈራረስ ያሳዩትን መንገዶች እንዲሁም የእግረኛ መረማመጃዎችንና የኮብልስቶን መንገዶችን ለመጠገን ዘንድሮ ግማሽ ሚሊዮን ብር መድበን ሥራውን በሌሊት ማከናወን ጀምረናል ብለዋል፡፡

እስከ ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ለማጠናቀቅ ታስቦ ተጀምረ የተባለው የአዲስ አበባ መንገዶች ጥገና የተለይ በደቡብ አዲስ አበባ አቃቂ መስመር፣ ምዕራብ አዲስ አበባ አየር ጤና መስመር፣ ሰሜን አዲስ አበባ ድልበር መስመርን እንዲሁም በምሥራቅ አዲስ አበባ ሳሀሊተ ምህረት አካባቢ ሰፋ ያለ የጥገና ሥራ የሚከናወንላቸው ናቸው ተብሏል፡፡

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን በየሳምንቱ የሰራውን አፈፃፀም ይገመግማል ያሉት አቶ ጥዑማይ  በስራው ምንያት የሚቆፋፈሩ አካባቢዎች ይበዛሉ እነዚህንም ስፍራዎች በአንፀባራቂ ምልክቶች እየዘጋን ተለዋጭ መንገድ በማመቻቸት የጥገና ስራውን እናከናውናለን በማለትም ነግረውናል፡፡

ወንድሙ ኃይሉ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ጥቅምት 9፣2010 የሸገር ወሬዎቻችን

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

 • በአዲስ አበባ አቅራቢያ በኦሮሚያ ከተሞች የሚኖሩና በመዲናዋ የሚሰሩ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞች የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚ እንዳልሆኑ ተናገሩ፡፡ (ማኅሌት ታደለ)
 • ወደ ጎዳና ላይ የሚወጡ ሕፃናት ዋነኛ ምክንያታቸው የኢኮኖሚ ችግር ነው ተባለ፡፡ ህፃናትን ወደየቤታቸው ለመመለስ የተቋቋመ ብሔራዊ ኮሚቴ በ6 ወር የሰራሁት ሥራ የተሳካ ነው ብሏል፡፡ (አስፋው ስለሺ)
 • ያለ አገልግሎት የተከማቹ ቁሣቁሶችን ሸጠው ገንዘቡን ገቢ እንዲያደርጉ ከታዘዙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች 54ቱ ትዕዛዙን ሥራ ላይ ማዋል አልቻሉም ተባለ፡፡ (ትዕግሥት ዘሪሁን)
 • የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን በከተማዋ የመንገድ ጥገና ጀምሬያለሁ አለ፡፡ (ወንድሙ ኃይሉ)
 • በቢሾፍቱ ባለቤቱን በሹካ ወግቶ የገደለው በእሥራት ተቀጣ፡፡ (ማኅሌት ታደለ)
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

በ2009 ዓ.ም ግንባታቸው ተጠናቆ ሥራ የጀመሩት ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ቦታዎች ተመን ወጥቶላቸው...

በ2009 ዓ.ም ግንባታቸው ተጠናቆ ሥራ የጀመሩት ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ቦታዎች ተመን ወጥቶላቸው አገልግሎት እየሰጡ ነው ተባለ፡፡በመገናኛ ዘፍመሽ የተገነባው የመኪና ማቆሚያ ቦታ በሰዓት 6 ብር በማስከፈል አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡

የመኪና ማቆሚያው በአካባቢው የተገነባው የሚታየውን የተጨናነቀ የመኪና ፍሰት ለማስቀረት በመሆኑ በአካባቢው መንገዶች ዳር ላይ መኪና ማቆም የተከለከለ ሲሆን ህጉን ባለማክበር መኪና የሚያቆሙ ግለሰቦች እየተቀጡ እንደሆነ ከአዲስ አበባ የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ሰምተናል፡፡

ፓርኪንጉን በቋሚነት ለሚጠቀሙ ደንበኞችም በወርሃዊ የክፍያ ስርዓት እንዲስተናገዱ ይደረጋል ተብሏል፡፡የፓርኪንግ ቦታውን የሚያስተዳድረው የአዲስ አበባ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ሲሆን በቀን እስከ አራት ሺ ብር የሚደርስ ገቢ ከመኪና ማቆሚያ ስፍራው እየተገኘ ነው ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል በወሎ ሰፈር የተገነባው የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ግንባታው አልቆ ሥራ ቢጀምርም ወደ መኪና ማቆሚያው የሚያስገባው መንገድ በግንባታ ላይ በመሆኑ የሚጠበቀውን ያህል ተጠቃሚ አላገኘም ተብሏል፡፡ይህንንም ለማስተካከል መንገዱን ምቹ ማድረግና በአካባቢው ባልተፈቀደ ቦታ ተሽከርካሪያቸውን የሚያቆሙ ግለሰቦች ላይ ቁጥጥር ይደረጋል መባሉን ከፅህፈት ቤቱ ሰምተናል፡፡

ምህረት ስዩም

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ጥቅምት 10፣2010 የሸገር ወሬዎቻችን

 • ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እያለ የሚመጣውን የሙቀት መጠን ለመቀነስ መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በጋራ ሊሰሩ ይገባል ተባለ፡፡ (አስፋው ስለሺ)
 • ባለፉት አራት ወራት ብቻ በ525 መዝገቦች ለተከሰሱ ሰዎች በነፃ ጠበቃ ቆሞላቸዋል ተባለ፡፡ (ንጋቱ ረጋሣ)
 • የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር የተመሠረተበትን 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓል የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት አከናወነ፡፡ (የኔነህ ሲሣይ)
 • የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ለሴቶች እኩልነትና ተሣታፊነት ለማከናውናቸው ተግባራት ከተለያዩ አካሎች በተናጠል የሚያደረግልኝ ድጋፍ በቂ አይደለም አለ፡፡ (ቴዎድሮስ ብርሃኑ)
 • በአዲስ አበባ የተገነቡት ዘመናዊ የሕንፃ ውስጥ የመኪና ማቆሚያዎች ተመን ወጥቶላቸው አገልግሎት እየሰጡ ነው ተባለ፡፡ (ምህረት ስዩም)
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የኢትዮጵያ፣ የግብፅና ሱዳን የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሮች 16ተኛውን የሦስትዮሽ ብሔራዊ ኮሚቴ ከቢ.አር.ኤልና አርቴሊያ

የኢትዮጵያ፣ የግብፅና ሱዳን የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሮች 16ተኛውን የሦስትዮሽ ብሔራዊ ኮሚቴ ከቢ.አር.ኤልና አርቴሊያ የህዳሴ ግድብ ጥናት ቡድን ጋር ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ዝግ ስብሰባ ይዘዋል፡፡

የሦስቱ ሀገሮች የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሮች በአጥኚ ቡድኑ በሚቀርበው ጥናት ላይና ከዚህ ቀደም ባልተስማሙባቸው ጉዳዮች ላይ ይነጋገራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዛሬ ማለዳ በኢሊሌ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተነግሯል፡፡

ስምምምነት ላይ እንደሚደርሱም ይጠበቃል፡፡የግብፁ የውሃና መስኖ ሚኒስትር ዶክተር መሃመድ አብድልአቲ በፈረንሣዩ የአጥኚ ኩባንያ የቀረበውና ዋና ዋና አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ሦስቱ ሀገሮች እስካሁን መስማማት አልቻሉም፤ በጣምም ዘግይተናል ብለዋል፡፡

የአባይ ግድብ በግብፅና ሱዳን ላይ የሚያስከትለውን አካባቢያዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ እንዲሁም በግድቡ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ እየተደረገ ባለ ሁለት ጥናት ኩባንያው የጥናት ሥራውን እንዲያጠናቅቅ ተጨማሪ መዘግየቶች መኖር የለባቸው ሲሉም የግብፁ ሚኒስትር ተናግረዋል፡፡

ጥናቱ እንዲጠናቀቅ ሦስቱ ሀገሮች ቀድመው መስማማት ያሉባቸውን አንገብጋቢ ያሏቸውን ጉዳዮች ግን ለጋዜጠኞች ከመግለፅ ተቆጥበዋል፡፡ ግብፅ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን ዛሬ በኢሊሌ ሆቴል እያካሄዱት ባለው ዝግ ስብሰባ መስማማት በሚጠበቅባቸው ጉዳይ ላይ የሚያደርጉትን የምክክር ውጤት ከ10 ሰዓት በኋላ ይፋ ያደርጋሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡ 

ትዕግስት ዘሪሁን

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

በቅርቡ የተደረገውን የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያ ሰበብ በማድረግ በሸቀጦችና አገልግሎቶች ላይ ጭማሪ እንዳይኖር...

በቅርቡ የተደረገውን የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያ ሰበብ በማድረግ በሸቀጦችና አገልግሎቶች ላይ ጭማሪ እንዳይኖር ከአስመጪዎች ጋር ንግገር ሊደረግ መሆኑ ተሠማ፡፡የተመን ማሻሻያው ከተሰማ በኋላ በተለይ በኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች አሉ የሚሉ ጥቆማዎች መቀበሉን የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ለሸገር ተናግሯል፡፡

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የተደረገውን የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያ ምክንያት በማድረግ በሀገር ውስጥ ገብተው በመጋዘን ላይ ያሉና በሀገር ውስጥ ምርቶች ላይ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ህጋዊ እርምጃ እወስዳለሁ ማለቱ ይታወሣል፡፡

ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ተናግሮ ከሚደርሰው ጥቆማ በተጨማሪ የራሱንም ሠራተኞች ወደ ገበያው በማሰማራት እየተከታተለ መሆኑን አቶ እንዳልካቸው ፅጌ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ ለሸገር ተናግረዋል፡፡እስካሁን በተደረገው ክትትልም በተለይ በኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ተደርጓል የሚሉ ጥቆማዎች ተገኝተዋል ብለዋል፡፡

የውጭ ምንዛሬ ተመኑን ሰበብ በማድረግ በሸቀጦች ላይ ጭማሪ እንዳይደረግ ከአስመጪዎች ጋር ምክክር ሊደረግ መሆኑ ተሰምቷል፡፡የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን በገበያው ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ካጋጠማችሁ በነፃ የስልክ መስመር 8077ና 8478 ደውላችሁ አሳውቁኝ ብሏችኋል፡፡

ንጋቱ ሙሉ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

በኦሮሚያ ክልል መጀመሪያውኑ በሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የተቀጠሩና በተሰጠው የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ራሳቸውን...

በኦሮሚያ ክልል መጀመሪያውኑ በሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የተቀጠሩና በተሰጠው የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ራሳቸውን በማጋለጥ ይቅርታ የጠየቁ የመንግሥት ሠራተኞች ከመባረር አይድኑም ተባለ፡፡የኦሮሚያ ክልል በሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ተቀጥረው ሲሰሩ የቆዩ የመንግሥት ሠራተኞች ራሳቸውን እንዲያጋልጡ የአንድ ወር ጊዜ መስጠቱ ይታወሣል፡፡

በዚህ ጊዜ ውስጥም 6 ሺ 700 የመንግሥት ሠራተኞች ራሳቸውን በማጋለጥ ይቅርታ እንደጠየቁ የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ከዚህ ቀደም ለሸገር ተናግረዋል፡፡ከነሐሴ 22 እስከ መስከረም 22 ያለው አንድ ወር ደግሞ የጥቆማ ጊዜ እንደሆነ ዶክተር ቢቂላ ነግረውን ነበር፡፡

ዛሬ ስለዚሁ የጠየቅናቸው ዶክተር ቢቂላ መጀመሪያውኑ በሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የተቀጠሩና በተሰጠው የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ራሳቸውን በማጋለጥ ይቅርታ የጠየቁ የመንግሥት ሠራተኞች መባረራቸው አይቀርም ብለውናል፡፡ቀደም ሲል ግን ራሳቸውን የሚያጋልጡ የመንግሥት ሠራተኞች ከደረጃቸው ዝቅ ብለው ይመደባሉ እንጂ ከሥራ አይባረሩም ሲሉ ዶክተር ቢቂላ ነግረውን ነበር፡፡

ከተቀጠሩ በኋላ ሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ አቅርበው የደረጃ ዕድገትና ዝውውር ያገኙ ደግሞ በሚመጥናቸው ቦታ ይመደባሉ ብለዋል ዶክተር ቢቂላ፡፡በተሰጠው የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የቀረቡ ጥቆማዎችን መሠረት በማድረግም በየአካባቢው የማጣራት ሥራ ይሰራል ተብሏል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ በሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ሲሰሩ በቆዩ ተቀጣሪዎች ላይ ስለሚወሰደው እርምጃ የሚገልፅ መመሪያ ለሚመለከታቸው አስተላልፌያለሁ ብሏል፡፡

ንጋቱ ረጋሳ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)
Sheger 102.1 AudioNow Numbers