• United Bank S.C.

    ሕብረት ባንክ አ.ማ.

  • Slider Two

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Sldier Three

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ሸገር ወሬዎች እና ልዩ ወሬዎች

የኤርትራ መንግስት ከፍተኛ የልኡካን ቡድን ዛሬ ከረፋዱ 4፡00 ሰዓት አዲስ አበባ ይገባል

የኤርትራ መንግስት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሚመክር ልዑክ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚልክ ባስታወቀው መሰረት የሀገሪቱ መንግሥት ከፍተኛ የልኡካን ቡድን ዛሬ ከረፋዱ 4፡00 ሰዓት አዲስ አበባ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሀገሪቱ የሰማዕታት ቀን በዓል ላይ ባሰሙት ንግግር የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነትና እድገት በየበኩላችን የታገልንለት አላማ እንደመሆኑ መጠን በሚኖረን ግንኙነት ላይ በቀጥታና በጥልቀት ለመረዳዳት እንዲሁም የቀጣይ እቅድም ለማውጣት እንድንችል ወደ አዲስ አበባ ልዑክ እንልካለን ማለታቸው ይታወሳል።
በሁለቱ ሀገሮች መካከል ለሁለት አስርት አመታት የተቋረጠው ግንኙነት ዳግም የተጀመረው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የኢሕአዴግ ሊቀ መንበር ጓድ ዶ/ር አቢይ አህመድ ያቀረቡትን የሰላም ጥሪ ተከትሎ ነው።

ምንጭ:- EPRDF ይፋዊ Facebook

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ዶልፊን ሚኒባስ ውስጥ ሆነው ወደ አምቦ ሲጓዙ የነበሩ 14 ሰዎች በመኪና አደጋ የሞት እና የአካል ጉዳት ደረሰባቸው

ባሳለፍነው ቅዳሜ በተካሄደው ሰልፍ ላይ ድጋፋቸውን ሲሰጡ ቆይተው በደስታ እየጨፈሩ በፍጥነት በሚከንፍ ዶልፊን ሚኒባስ ውስጥ ሆነው ወደ አምቦ ሲጓዙ የነበሩ 14 ሰዎች በመኪና አደጋ የሞት እና የአካል ጉዳት ደረሰባቸው፡፡ ሚኒባሱ መንገዱን ለቅቆ በተቃራኒ አቅጣጫ ከሚመጣ ሲኖትራክ ጋር ተጋጭቶ በሚኒባሱ ውስጥ የነበሩ 3 ወንዶችና አንዲት ሴት ሲሞቱ፣ 4 ወንዶች ለከባድ፣ 6 ወንዶች ደግሞ ለቀላል የአካል ጉዳት ተዳርገዋል…

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.ወንድሙ ኃይሉ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

አሜሪካ የጥቃቱን ፈፃሚዎች ለመያዝ የኤፍ ቢ አይ ባለሞያዎችን ለመላክ ዝግጁ ነች

ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድን ለመደገፍ በወጣው ሰልፈኛ ላይ ጉዳት ያደረሱትን ተጠያቂዎች ለመለየት አሜሪካ እተባበራለሁ አለች፡፡የአሜሪካው ምክትል የንግድ ሚኒስትር ጊልበርት ካፕላን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ እንደነገርዋቸው አሜሪካ የጥቃቱን ፈፃሚዎች ለመያዝ የኤፍ ቢ አይ ባለሞያዎችን ለመላክ ዝግጁ ነች፡፡

ተጨማሪ፦ የቅዳሜውን የቦምብ ጥቃት ለመመርመር የአሜሪካ የፌድራል የወንጀል ምርመራ ቢሮ (ኤፍ ቢ አይ) መርማሪዎች አዲስ አበባ መግባታቸውን የፌድራል ፖሊስ ኮምሽነር ጄኔራል ዘይኑ ጀማል ተናገሩ…
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ደም ለግሰዋል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ለቅዳሜው የቦምብ ጥቃት ተጎጂዎች ያላቸውን ፍቅር፣ህብረት፣ አንድነት እና የጋራ ጥቅም ለመግለፅ በብሄራዊ ደም ባንክ ተገኝተው ደም ለግሰዋል፡፡ ደም በመለገስ ሕይወት እንታደግ!
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ሰበር ወሬ፣ አፈጉባዔ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል የደኢህዴን ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ

ሥልጣን በለቀቁት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ምትክ አፈጉባዔ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል የደኢህዴን ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ፡፡
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ሰበር ወሬ፣ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ከሥልጣናቸው በገዛ ፍቃዳቸው ስልጣናቸውን ለቀቁ

የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ሊቀ መንበር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ከሥልጣናቸው በገዛ ፍቃዳቸው መልቀቃቸው ተሰማ…የሥልጣን መልቀቂያቸውን አስቸኳይ ስብሰባ እያካሄደ ላለው የደኢህዴን ማእከላዊ ኮሚቴ ያቀረቡት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶ ከድርጅቱ ሊቀመንበርነት እና ሥራ አስፈፃሚነት ለቅቀዋል፡፡ አቶ ሽፈራው የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነው ይቀጥላሉ ተብሏል፡፡
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የቦምብ ጥቃት ተጎጂዎች መረጃ

ባለፉት 48 ሰዓታት ወደ ሕክምና ተቋማት ሄደው ከታከሙ 156 ተጎጂዎች፣ 114ቱ ሕክምና ተደርጎላቸው ወደ ቤታቸው ሄደዋል፡፡ 40ዎቹ አሁንም በሆስፒታል እየታከሙ ነው፡፡ የሕክምና ባለሞያዎች አደጋውን ተከትሎ ያሳዩት ታላቅ የሙያ እና የወገን ፍቅር ከምንጊዜው በላይ የሚያተጋን መሆኑን እንገልፃለን ሲሉ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር አሚር አማን በትዊተር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ፅሁፍ ገልፀዋል፡፡
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ ከአሜሪካ የንግድ ምክትል ሚኒስትር ጊልበርት ካፕላን ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች መነጋገራቸው ተሰማ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ መስሪያ ቤት ሸገር እንደሰማው አሜሪካ በኢትዮጵያ የንግድ ስራን የማስፋፋትና ፖለቲካዊ ግንኙነቱንም ለማስፋት ያቀደ ውይይት በሁለቱ ባለስልጣናት መካከል ተደርጓል፡፡ተሽከርካሪ አምራቾችን ጨምሮ በተለያዩ ስመጥር የአሜሪካ አምራች ኩባንያዎች የተካተቱበትን ልዑካን በመምራት አዲስ አበባ የመጡት ጊልበርት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ መክረዋል፡፡

አሜሪካ በኢትዮጵያ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የበለጠ የመሰማራት ፍላጎት እንዳላት የተሰማ ሲሆን በኢኮኖሚውና በንግድ ዘርፉ ስምምነቶች ይፈረማሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡በኢትዮጵያ ያሉ የአሜሪካ ኩባንያዎች የገጠማቸውን የውጭ ምንዛሪ እጥረትም በተመለከተ የንግድ ሚኒስትሩ ለወርቅነህ ገበየሁ ያነሱላቸው ሲሆን መፍትሄውን ለመፈለግ አገራቸው ጥረት እንደምታደርግ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስተዳደር ከተመሰረተ ወዲህ የበለጠ የንግድ ትስስሩን ለማሳደግ የአሜሪካ ባለፀጎች ኢትዮጵያ የመምጣት ፍላጎታቸው ማደጉንም ምክትል ሚኒስትር ካፕላን ተናግረዋል፡፡ቅዳሜ እለት በደረሰው አደጋ ልባዊ ሀዘን የተሰማቸው መሆኑን ለወርቅነህ ገበየሁ መንገራቸውን ከውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ሰምተናል፡፡

የኔነህ ሲሳይ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

በሰልፉ ላይ የሚንፀባረቀው ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው ያሉት የኮሚቴው ሰብሳቢ ያልተገባ ነገር የሚያደርጉ ሰዎችን ሰልፈኛው ሲመለከት ወዲያውኑ በአካባቢው ለሚገኙ ፖሊሶች ወይም የዝግጅቱ አስተባባሪዎች እንዲጠቆም ጠይቀዋል

በነገው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን በመደገፍ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ለሚካሄደው ሰልፍ ዝግጅቱ ተጠናቋል ተባለ፡፡የድጋፉ ሰልፉ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጉደታ ገላልቻ ዛሬ ለሸገር እንደተናገሩት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ነገ በመስቀል አደባባይ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡የድጋፍ ሰልፉ ያለ ምንም የፀጥታ ችግር እንዲካሄድ ከሚመለከታቸው ጋር ተወያይተናል ብለዋል፡፡
ከፌዴራል፣ አዲስ አበባ እና ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነሮች ጋር ውይይት መካሄዱን ነግረውናል፡፡ኮሚቴው ሰልፉን የሚያስተባብሩ ከሁለት ሺህ እስከ ሶስት ሺህ የሚደርሱ ወጣቶችን በዕለቱ በየአካባቢው እንደሚያሰማራም አቶ ጉደታ ነግረውናል፡፡ወጣቶቹ ሰልፈኞችን የማስተባበር እና ያልተገባ ነገር የሚያደርጉ ሰዎችን የመቆጣጠር ስራ ይሰራሉ ብለዋል፡፡

ሰልፉ እስከ አሁን ለተገኙ ድሎች ምስጋና የሚቀርብበት ብቻ ነው ያሉት አቶ ጉደታ ከዚህ ውጪ ግን የየትኛውንም ፖለቲካ ፓርቲም ሆነ ሌላ ወገን አቋም እንደማይንፀባረቅበት ተናግረዋል፡፡በሰልፉ ላይ የሚንፀባረቀው ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው ያሉት የኮሚቴው ሰብሳቢ ያልተገባ ነገር የሚያደርጉ ሰዎችን ሰልፈኛው ሲመለከት ወዲያውኑ በአካባቢው ለሚገኙ ፖሊሶች ወይም የዝግጅቱ አስተባባሪዎች እንዲጠቆም ጠይቀዋል፡፡

በአጠቃላይ አደራውን የሰጠነው ለህዝቡ ነው ሲሉ አቶ ጉደታ ተናግረዋል፡፡ሰልፉ ከነገ ቅዳሜ ጠዋት አንድ ሰዓት ጀምሮ በመስቀል አደባባይ ይካሄዳል ተብሏል፡፡ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በዙሪያዋ የሚገኙ ነዋሪዎችም ይሳተፉበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከአስተባባሪ ኮሚቴው ሠምተናል፡፡

ንጋቱ ረጋሳ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብዛት ላይ ከማተኮር ተላቀው ጥራት ላይ መስራት እንደሚኖርባቸው ተጠቆመ

በ33 የመንግስትና 5 የግል ዩኒቨርስቲዎች ላይ ተደረገ በተባለ ጥናት መሰረት ጥራት ያለው የትምህርት አሰጣጥ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው ተብሏል፡፡በመሆኑም ተቋማቱ ፊታቸውን ወደ ጥራት እንዲያዞሩ በጥናቱ ተመክረዋል፡፡የመምህራን ተነሳሽነት ያነሰ መሆን፣ ብቃት ያላቸው መምህራን በበቂ አለመኖር፣ የተማሪዎች ተሳትፎ ማነስና የመምህራንና የተማሪዎች የፈጠራ ክህሎት ማነስ ለትምህርት ጥራቱ መውረድ በምክንያትነት ተጠቅሰዋል፡፡

አሁን ያለው የትምህርት ተቋማት አስተዳደርም አጠቃላይ የትምህርት ጥራትን ሊያስጠብቅ የሚችል እንዳልሆነ በጥናቱ ተመልክቷል፡፡ለዚህም እውቀትና ክህሎትን መሰረት ያደረገ የትምህርት ተቋማት አስተዳደር ምደባ መፍትሄ ይሆናል ተብሏል፡፡የትምህርት ጥራት እቅዱም የሚመለከታቸው አካላትን ማሳተፍ ይኖርበታል ተብሏል፡፡ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ባዘጋጀው 17ኛው የጥናትና የምርምር መድረክ ላይ እንደሰማነው በኢትዮጵያ ሁሉም አቀፍ እድገት እንዲመዘገብ ጥናትና ምርምሮች ጉልህ ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡

ይህንን ሀላፊነቱን ለመወጣት የጥናትና የምርምር ስራዎችን የሚደግፍ ቢሮ አቋቁሜ እየሰራው ነው ያለው ዩኒቨርስቲው በጥናቱ እና ምርምር መድረኩ በትምህርት፣ ጤና፣ በግብርና፣ የአየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም በቢዝነስና ሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ 22 የጥናት ወረቀቶች ይቀርባሉ ብሏል፡፡በጥናትና ምርምር መድረኩ ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ እንዲሁም ከተለያዩ ድርጅቶች የተጋበዙ ምሁራን እየተሳተፉ ነው፡፡

በየነ ወልዴ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)
Sheger 102.1 AudioNow Numbers