• Slider One

  የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

 • Slider Two

  የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

 • Sldier Three

  የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ሸገር ወሬዎች እና ልዩ ወሬዎች

ነሐሴ 19፣2009 የሸገር ወሬዎቻችን

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

 • የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የወደፊት ታሳቢ የምርት አቅርቦትና ዝውውር ማከናወኛ መላ ሥራ ላይ ላውል ነው አለ፡፡ (ንጋቱ ረጋሣ)
 • የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት ደንብን ለማስከበር የሚወሰዱ የኃይል እርምጃዎች ምንም አይነት የህግ ማዕቀፍ የላቸውም አለ፡፡ (ቴዎድሮስ ብርሃኑ)
 • የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማት ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ሠራተኞችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ደንብ እያዘጋጀ ነው፡፡ (በየነ ወልዴ)
 • የኢትዮጵያ የእንስሣት እርባታ ባለሙያዎች ማህበር በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ላይ የበኩሌን ለመወጣት እድል ሊሰጠኝ ይገባል አለ፡፡ (አስፋው ስለሺ)
 • ለጤና ጐጂ ንጥረ ነገር ይዘዋል ተብለው የተጠረጠሩ አምስት የምግብ አይነቶች ናሙናቸው ከገበያ ተወስዶ ጥናት እየተደረገባቸው ነው፡፡ (ትዕግሥት ዘሪሁን)
 • ሰቆጣ ማይኒንግ የተባለውና በማዕድን ዘርፍ የተሰማራው ኩባንያ በኢትዮጵያ የብረት ማዕድን ለመሰማራት ግማሽ ቢሊየን ዶላር ማዘጋጀቱ ተሠማ፡፡ (ዮሐንስ የኋላወርቅ)
 • የኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅ የወጪ ንግድ መዳከም አንዱ ምክንያት አለም አቀፍ መስፈርትን አሟልተው አለመገኘታቸው ነው ተባለ፡፡ (ምህረት ስዩም)
 • ከአዲስ አበባ ታክሲ አሽከርካሪዎች ስለ ትራፊክ አደጋ የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ አሰጣጥ እውቀቱ ያላቸው ከ13 በመቶ አይበልጡም ተባለ፡፡ (ንጋቱ ሙሉ)
 • የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ካሣ ከፈልኩ አለ፡፡ (ንጋቱ ረጋሣ)
 • ኢትዮጵያ የአቮካዶ ምርት ለአውሮፓ ገበያ ማቅረብ ጀመረች ተባለ፡፡ (ቴዎድሮስ ብርሃኑ)
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መፃህፍት ኤጀንሲ ዘንድሮ ለአምስት ሚሊየን አንድ መቶ አሥራ ሦስት ሺ ሦስት መቶ ስልሣ ሰባት...

የብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መፃህፍት ኤጀንሲ ዘንድሮ ለአምስት ሚሊየን አንድ መቶ አሥራ ሦስት ሺ ሦስት መቶ ስልሣ ሰባት ተጠቃሚዎች አገልግሎት ሰጥቻለሁ አለ፡፡ ኤጀንሲው ለጥናትና ምርምር ሰዎች፣ ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎችና ለሌሎችም ጠቃሚዎች የንባብ አገልግሎት የሚሰጥበት ክፍል ጥበት ገጥሞት ብዛት ያላቸው ተገልጋዮች ማስተናገድ አለመቻሉንም ተናግሯል፡፡ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ እንዳለው አዳሙ ለሸገር ሲናገሩ ያለብንን የቦታ ጥበት ያስቀራል የተባለውና መንግሥት በሦስት መቶ ሚሊየን ብር የሚያስገነባው ባለ 13 ፎቅ ህንፃ በመጠናቀቅ ላይ ነው ፤ ህንፃው ወደ ሥራ ሲገባ በዓመት ከ11 ሚሊየን በላይ ተጠቃሚዎችን ማስተናገድ ይችላል ብለዋል፡፡

ኤጀንሲው ከንባብ አገልግሎቱ ባለፈ ዘንድሮ ከተለያዩ አድባራትና ገዳማት እንዲሁም መስጊዶች ከአንድ መቶ አሦስራ ሦስት ሺ በላይ ጥንታዊና ታሪካዊ የሥነ-ፅሁፍ ሐብቶችን በዲጂታል ካሜራና በማይክሮ ፊልም ሰብስቧልም ተብሏል፡፡ በኤጀንሲው በሚሰጠው የብሬል ንባብ አገልግሎትም ዘንድሮ 486 አይነስውራን ተጠቅመዋል ያሉት አቶ አዳሙ የአይነስውራን አንባቢያን ቁጥር በጣም አነስተኛ ነው ለዚህም አይነስውራኑ የቦታውን ርቀት በምክንያትነት ያነሳሉ፡፡ ወደፊት እነሱ በሚበዙበት ሥፍራ የብሬል ንባብ አገልግሎት ለመጀመርም ኃሣብ አለ ሲሉ ተናግረዋል፡፡


ወንድሙ ኃይሉ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ከዚህ ቀደም ወደ ሀገር ገብተው የማያውቁ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ጥራት ለመፈተሽ መቸገሩን የኢትዮጵያ ተስማሚነት ድርጅት ተናገረ

ከዚህ ቀደም ወደ ሀገር ገብተው የማያውቁ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ጥራት ለመፈተሽ መቸገሩን የኢትዮጵያ ተስማሚነት ድርጅት ተናገረ፡፡በዚህ ዓመትም ከቀረቡለት 26 ሺ የጥራት ፍተሻ ጥያቄዎች 39ኙን የማላውቃቸው ቴክኖሎጂዎች ስለሆኑ አልችልም ብዬ መልሼያለሁ ብሏል፡፡ለመጡት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች መፈተሻ መሣሪያ፣ የሰለጠነ የሰው ኃይልና የተዘጋጀ ደረጃም እንደሌለው ተናግሯል፡፡ኢትዮጵያ ወደ ሀገር በምታስገባቸውና ወደ ውጭ የምትልካቸው ምርቶች የጥራት ችግር ላይ መላ ለመፈለግ የጥራት ፈታሽ ድርጅቱ ከአምራች አስመጪና ላኪዎች ጋር ዛሬ እየመከረ ነው፡፡

አስመጪዎች ወደ ሀገር የሚያስገቧቸውን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ጥራት ለመፈተሽ ይችል ዘንድ ለሚያስመጧቸው እቃዎች ቀድመው እንዲያሳውቁትም ጠይቋል፡፡የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሻለ በልሁ እንዳሉት የሀገሪቱ ኢንዱስትሪዎች እየሰፉ ነው ከዓለም ወደ ሀገር የሚገቡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችም እየጨመሩ ነው፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ የጥራት ፈታሹ መሥሪያ ቤት አቅም አብሮ ካላደገ ፈተናው እየከበደ ይሄዳል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸው የግብርና ምርቶችና እንደ ቆዳና ጨርቃ ጨርቅ ያሉ የኢንዱስትሪ ውጤቶች የሚያስገኙት የውጭ ምንዛሬ ከዓመት ዓመት እያሽቆለቆለ ነው፤ ለዚህ አንዱ ምክንያት የአለም የዋጋ መዋዠቅ ነው ቢባልም የሚላኩ ምርቶች ከሌሎች ጋር በጥራት ተወዳዳሪ አለመሆናቸውና እሴት ተጨምሮባቸው አለመላካቸው ለገቢው መቀነስ ሌላው ምክንያት እንደሆነ ይነገራል፡፡የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር እንዳሉትም ከዚህ ቀደም ወደ ኖርዌና ጀርመን የተላከ ማር ስኳር ተቀላቅሎበት በመገኘቱ መመለሱን፣ የበርበሬና የገብስ ቆሎም አፍላ ቶክሲን አለባቸው ተብለው ከአለም ገበያ ተሰብስበው መመለሳቸውን አስታውሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ በማር ውስጥ ስኳር ስለመቀላቀልና አለመቀላቀሉ የመፈተሻ ቴክኖሎጂ አስመጥቶ ሥራ ጀምሯል ብለዋል፡፡በሌሎች ምርቶች ላይ ግን ተጨማሪ ፍተሻዎችን ካላደረግን ከዓለም ጋር ተወዳዳሪ መሆን አንችልም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ትዕግስት ዘሪሁን

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ሰቆጣ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በአማራ ክልል ከፍተኛ የሆነ የብረት ማዕድን እንዲያመርት ፍቃድ ተሰጠው

ሰቆጣ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በአማራ ክልል ከፍተኛ የሆነ የብረት ማዕድን እንዲያመርት ፍቃድ ተሰጠው፡፡ኩባንያው ለአሥር አመታት ስምንት መቶ አርባ ሺ ቶን የብረት ማዕድን ያመርታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ዛሬ በማዕድን ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር በተደረገ ስምምነት እንደተባለው ለኩባንያው ፈቃድ የተሰጠው በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ዋግ-ህምራ ዞን በሰቆጣና ዝቋላ ወረዳ ወይም በልዩ ስማቸው ደብረብርሃን ረታ ገነትና ደብረ ህይወት በተባሉ ቦታዎች ነው፡፡

አጠቃላይ ሥፋታቸውም 16 ካሬ ኪሎ ሜትር መሆኑ ተነግሯል፡፡ኩባንያው ለኢንቨስትመንትም 422 ሚሊየን ብር ወጪ እንደሚያደርግም ተሰምቷል፡፡ስምምነቱ ለ20 ዓመታት የሚፀና ሆኖ የፈቃድ ዘመኑ ሲጠናቀቅ በባለፈቃዱ ጥያቄ መሠረት በእያንዳንዱ የፈቃድ እድሣት ጊዜ ለ10 ዓመት ያልበለጠ ጊዜ ሊታደስ ይችላል ተብሏል፡፡ዛሬ ስምምነቱን ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳና የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ሉቺያኖ ፍራቶሊን ፈርመውታል፡፡

ዮሐንስ የኋላወርቅ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ነሐሴ 18፣2009 የሸገር ወሬዎቻችን

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

 • የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ከአውሮፓ ህብረት ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ፕሮጀክት ነድፎ በሴቶች ላይ የሚደርስን ጥቃት ለማስቆም እየሰራ ነው ተባለ፡፡ (ምህረት ስዩም)
 • የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት እግረ መንገድ የምሰጠው የትራንስፖርት አገልግሎት እየተወደደልኝ በመሆኑ አዳዲስና ዘመናዊ አውቶብሶችን ገዝቼ አሰማርቻለሁ አለ፡፡ (ምሥክር አወል)
 • በድምሩ ከ904 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የተለያዩ እቃዎች በህገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጡና ሊገቡ ሲሉ ተይዘዋል ተባለ፡፡ (ትዕግሥት ዘሪሁን)
 • የውጭ ሀገር ኩባንያዎች የኢትዮጵያን የጨርቃ ጨርቅ ኢንዲስትሪ እየተቀላቀሉ ነው ተባለ፡፡ (ወንድሙ ኃይሉ)
 • የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር በዋሉ 27 ግለሰቦች ላይ ከ8 እስከ 12 ቀናት የሚደርስ ተጨማሪ ቀጠሮ ሰጠ፡፡ (አስፋው ስለሺ)
 • የኢትዮጵያ ተስማሚነት ድርጅት ለአገሪቱ እንግዳ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን የጥራት ደረጃ መፈተሹ ችግር ሆኖብኛል አለ፡፡ (ትዕግሥት ዘሪሁን)
 • በአዲስ አበባ የፍጥነት ወሰን መቆጣጠሪያ ራዳር ሥራ ላይ ሊውል ነው፡፡ (ምህረት ስዩም)
 • ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ያለፈው የበጀት ዓመት እጅግ የተሳካ ተግባር ያከናወንኩበት ነበር አለ፡፡ (ምሥክር አወል)
 • ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መፃህፍት ኤጀንሲ ዘንድሮ ከ5 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ዜጐች አገልግሎት መስጠቱ ተናገረ፡፡ (ወንድሙ ኃይሉ)
 • ሰቆጣ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በአማራ ክልል ከፍተኛ የሆነ የብረት ማዕድን እንዲያመርት ፍቃድ ተሰጠው፡፡ (ዮሐንስ የኋላወርቅ)
 • የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ጋር የክፍያ አገልግሎት ስምምነት ተፈራረመ፡፡ (ንጋቱ ረጋሣ)
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

በኢትዮጵያ ፍትህ አጥተው የመከራከሪያ አቅም ሳይኖራቸው ድጋፍ ለሚፈልጉ ሴቶች በራሳቸው ፍትህን እንዲያገኙ ላደርግ ነው ሲል...

በኢትዮጵያ ፍትህ አጥተው የመከራከሪያ አቅም ሳይኖራቸው ድጋፍ ለሚፈልጉ ሴቶች በራሳቸው ፍትህን እንዲያገኙ ላደርግ ነው ሲል የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ተናገረ፡፡ማኅበሩ ዛሬ “የአንቺው ጠበቃ አንቺው” ብሎ የሰየመውን ሴቶች የህግ አገልግሎት ፈልገው ነገር ግን ጠበቃ ለማቆም የሚያስችል አቅም ሳይኖራቸው ቀርቶ ለሚያጋጥማቸው ችግር በራሳቸው ተከራክረው ፍትህ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል ያለውን አሰራሩን ተግባራዊ ለማድረግ ከሚመለከታቸው ጋር ሲመክር ነው ይህን የሰማነው፡፡

የኢትዮጵያ ህግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር በሀገሪቱ ያሉ ሴቶች በገንዘብ ችግር ምክንያት ፍትህ ማግኘት ላይ ከፍተኛ የተባለ ችግር ይገጥማቸዋል እስካሁንም ይህንን ለማስቀረት ማኅበሩ በራሱ ጠበቆችን በማቆም በደል ለደረሰባቸው ሴቶች ድጋፍ አድርጓል ተብሏል፡፡

ማኅበሩ በአዲስ አበባና በሌሎች አራት የሀገሪቱ ክልሎች ለሴቶች ነፃ የህግ አገልግሎትን ሲሰጥ እንደቆየ ተናግሮ እስካሁንም ቁጥራቸው ከ45 ሺ በላይ ለሚሆኑ ሴቶች ድጋፍ አድርጓል ተብሏል፡፡ማኅበሩ ዛሬ ባሰናዳው የምክክር አውደ ጥናት ሴቶች ለመብታቸው ራሳቸው ተከራካሪ እንዲሆኑና ፍትህ እንዲያገኙ በፍርድ ቤትም ለራሳቸው ጠበቃ ሆነው እንዲቆሙ “ያንቺው ጠበቃ አንቺው” የሚለውን አሰራሩን እንዳዘጋጀ ተናግሯል፡፡

ሴቶች እራሳቸውን ወክለው በፍርድ ቤት በሚያጋጥማቸው ጉዳዮች መከራከራቸው ለራሳቸው ነገሮችን መፈፀም እንዲችሉና የሚያጋጥሟቸውንም የፍትህ ጥያቄዎች እንዲመለሱላቸው ለማድረግ ያግዛል ተብሏል፡፡በአውደ ጥናቱ ከማኅበሩ ጋር በጋራ የሚሰሩ የፍትህ ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻዎች ምክክር እያደረጉ ነው፡፡

ምህረት ስዩም
አስተያየት ይፃፉ (1 Comment)

በአካባቢው የሚስተዋለውን ከፍተኛ የትራፊክ እንቅስቃሴ ለማቃለል ሲባል ሳሪስ የሚገኘው የአቦ አደባባይ እንደሚፈርስ ተነገረ

በአካባቢው የሚስተዋለውን ከፍተኛ የትራፊክ እንቅስቃሴ ለማቃለል ሲባል ሳሪስ የሚገኘው የአቦ አደባባይ እንደሚፈርስ ተነገረ፡፡ ከአቦ አደባባይ በተጨማሪ የጀርመን አደባባይም ሊፈርስ ይችላል መባሉንም ሰምተናል፡፡ለትራፊክ እንቅስቃሴ ማነቆ ሆነዋል የተባሉ አደባባዬችን እያፈረሰ በትራፊክ መብራት እየተካ የሚገኘው የአዲስ አበባ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ አሁን ደግሞ ተራው ሳሪስ የሚገኘው የአቦ አደባባይ መሆኑን ለሸገር ተናግሯል፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ገነቱ ደሣለኝ እንደነገሩን ከዚህ በፊት የከተማዋን የትራፊክ እንቅስቃሴ አስተጓጉለዋል ተብለው የተለዩ ስድስት አደባባዬች ፈርሰው በትራፊክ መብራቶች መተካታቸውን አስታውሰዋል፡፡ዳይሬክተሩ እንዳሉት ሳሪስ የሚገኘውን የአቦ አደባባይ ለማፍረስ የዲዛይን ሥራው እያለቀ ነው፡፡አደባባዩን ከማፍረስ በተጨማሪ በአካባቢው የታክሲ ፌርማት እንደሚገነባም ተናግረዋል፡፡

ሌላው ለትራፊክ እንቅስቃሴ መጨናነቅ ምክንያት እየሆነ መጥቷል የተባለውን የጀርመን አደባባይን ይፍረስ ወይስ አይፍረስ የሚለውን ለመወሰን ጥናት መጀመሩን ሰምተናል፡፡በአዲስ አበባ ከ80 በላይ አደባባዬች እንዳሉ ያስታወሱት አቶ ገነቱ ደሣለኝ ለትራፊክ ፍሰት ሲባል በተለይ ታሪካዊ አደባባዬች አይፈርሱም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በከተማዋ ከዚህ በኋላ አዲስ አደባባዬችን መገንባት እንደሚቆም አቶ ገነቱ ነግረውናል፡፡በአዲስ አበባ ከዚህ በፊት ለትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት ሆነዋል ተብለው የፈረሱት ስድስት አደባባዬች ሲሆኑ ከእነሱም ውስጥ 18 ማዞሪያ፣ ኢምፔሪያል ጃክሮስ፣ ለቡና ቦሌ ሚካኤል ይገኙበታል፡፡

ንጋቱ ሙሉ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

በአመቱ ባደረገው ጥናትና ድንገተኛ ፍተሻ ከ1 ሺ 445 በላይ የንግድ ድርጀቶች ህገ-ወጥ ንግድና የታክስ ማጭበርበር ተግባር...

በአመቱ ባደረገው ጥናትና ድንገተኛ ፍተሻ ከ1 ሺ 445 በላይ የንግድ ድርጀቶች ህገ-ወጥ ንግድና የታክስ ማጭበርበር ተግባር መፈፀማቸውን ደርሼበታለሁ ያለው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ነው፡፡የንግድ ማጭበርበር፣ የታክስ ስወራ፣ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያን ህጉ በማይፈቅደው መልኩ መጠቀም፣ ለቀረጥ ነፃ የተሰጠ መብትን ያለ አግባብ መጠቀምና ሌሎችንም ህገ-ወጥ ተግባራት ፈፅመዋል ያላቸውን ከ1 ሺ 445 በላይ የንግድ ድርጅቶች ላይም ድርጅቱን ከማሸግ ጀምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዱን በዓመቱ የሥራ አፈፃፀም ሪፖርቱ አስፍሯል፡፡

ከመካከላቸውም የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢ ሆነው ደረሰኝ የማይቆርጡ 927 ድርጅቶች ተጠርጣሪዎችም ተይዘው ጉዳያቸው ለተጨማሪ የወንጀል ምርመራ ለሚመለከተው አካል ተላልፏል ተብሏል፡፡ሌሎች 42 ድርጅቶችም ከሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ጋር ተያይዞ ማስታወቂያ ባለመለጠፋቸውና 33 ድርጅቶችም አመታዊ የቴክኒክ ምርመራ ባለማድረጋቸው ጉዳያቸው ለአስተዳደራዊ ቅጣት ለሚመለከተው ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ተልኳል፡፡38 ድርጅቶችም ያለንግድ ፈቃድ ሲሰሩ ተገኝተው እንዲታሸጉ መደረጉን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የንግድ ገቢ ግብር ሲሰበስብ ተደጋጋሚ ኪሣራ የሚያሳውቁ ምንም የንግድ እንቅስቃሴ አልነበረንም ብለው ሪፖርት የሚያደርጉና አነስተኛ የንግድ ትርፍ በሚያሣውቁ በ483 ድርጅቶች ላይ ጥናትና የመረጃ ማሰባሰብ ሥራም ከውኗል፡፡በ109 ድርጅቶች ላይ ድንገተኛ የሠነድ ምርመራ በማካሄድም ለኦዲት ጠቃሚ የሆኑ ሰነዶችን ማግኘቱንና የ106ቱን ለሂሣብ ምርመራ ወደ ኦዲት መላኩን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በሪፖርቱ ተናግሯል፡፡

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ህገ-ወጦችን በመያዝና መንግሥት ሊያጣ የነበረውን ገቢ በማሰባሰብ ተግባሩ ከጠቋሚዎች ያገኘው መረጃ 91 በመቶ ውጤታማ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብሏል፡፡ለጠቋሚዎቹም በዚህ ዓመት ብቻ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ እንደከፈለ ተናግሯል፡፡

ትዕግስት ዘሪሁን

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ነሐሴ 17፣2009 የሸገር ወሬዎቻችን

 • የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር አቅም የሌላቸው ሴቶች በራሳቸው ፍትህ እንዲያገኙ የሚረዳ ሥርዓት ልፈጥር ነው አለ፡፡ (ምህረት ስዩም)
 • የኢትዮጵያ ገቢያዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሥነ-ምግባር ችግር አሳይተዋል ያላቸውን ሰባ ሰባት ሠራተኞቹን ከሥራ ማባረሩን ተናገረ፡፡ (ትዕግሥት ዘሪሁን)
 • በ2009 በጀት አመት ከ5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ንፁህ ውሃ እንዲጠጡ አድርጌአለሁ ሲል የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ተናገረ፡፡ (ምህረት ስዩም)
 • በመላ ሃገሪቱ በ150 ወባማ ወረዳዎች የፀረ ወባ መድሐኒት ርጭት እየተካሄደ እንደሆነ ተነገረ፡፡ (አስፋው ስለሺ)
 • የምሥራቅ ኢትዮጵያን የህክምና ፍላጐት ለማሟላት የተገነባው የራዲዮ ቴራፒ (የካንሰር ህክምና ማዕከል) ግንባታው ተጠናቋል ተባለ፡፡ (ምሥክር አወል)
 • ከ1 ሺ 400 የሚበልጡ የንግድ ድርጅቶች በህገ-ወጥ ተግባራት ተሰማርተው በመገኘታቸው እርምጃ ተወስዶባቸዋል ተባለ፡፡ (ትዕግሥት ዘሪሁን)
 • ብሔራዊ ሎተሪ ያሰበውን ያህል ገቢ ዘንድሮ ማግኘት አልቻለም ተባለ፡፡ (ዮሐንስ የኋላወርቅ)
 • ሳሪስ የሚገኘው የአቦ አደባባይ ሊፈርስ ነው ተባለ፡፡ (ንጋቱ ሙሉ)
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የኮድ 3 ሚኒባስ ተሽከርካሪዎች በተመደቡበት መስመር ሳያቆራርጡ አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላል የተባለው የብረት ታፔላ ተቀየረ

የኮድ 3 ሚኒባስ ተሽከርካሪዎች በተመደቡበት መስመር ሳያቆራርጡ አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላል የተባለው የብረት ታፔላ ተቀየረ፡፡የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን በከተማዋ የታክሲ አገልግሎት ለሚሰጡ የኮድ-3 ሚኒባስ ተሽከርካሪዎች ታፔላውን የቀየርኩት ተሽከርካሪዎቹ እንደሌሎች ታክሲዎች ለእይታ በሚመች መልኩ እንዲሰቅሉት ነው ብሏል፡፡

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ምክትል ኃላፊ የሆኑት አቶ ምትኩ አስማረ የታፔላው መየቀር ለቁጥጥር ሥራው ምቹ ከመሆኑም በላይ ተሣፋሪዎችም የታክሲውን መሥመር በቀላሉ እንዲለዩት ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡ታፔላ የመቀየሩ አገልግሎትም ከነሐሴ 17 እስከ ነሐሴ 30 2009 ዓ.ም አንደሚሰጥም ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ተናግሯል፡፡

በፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን የትራንስፖርት አገልግሎት ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ተስፋዬ በላቸው በበኩላቸው ታፔላ የሚሰጣቸው ተሽከርካሪዎች ከተሰጣቸው ስምሪት ውጪ ወደ ክልል ከተሞች መሄድ አንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡

በየነ ወልዴ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

በኦሮሚያ ክልል በሐሰተኛ መንጃ ፈቃድ የሚያሽከረክሩ አሽከርካሪዎች የትራፊክ አደጋ ስጋት መሆናቸውን ቀጥለዋል ተባለ

በኦሮሚያ ክልል በሐሰተኛ መንጃ ፈቃድ የሚያሽከረክሩ አሽከርካሪዎች የትራፊክ አደጋ ስጋት መሆናቸውን ቀጥለዋል ተባለ፡፡ይህን ያለው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ነው፡፡የፖሊስ ኮሚሽኑ የትራፊክ ፖሊስ ደህንነትና ቁጥጥር የሥራ ሂደት ባለሙያ ምክትል ኮማንደር ንጉሴ ግርማ እንደተናገሩት የአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ዞኖችን ጨምሮ በተለይ ምስራቅ ሀረርጌና ወለጋ በሐሰተኛ መንጃ ፈቃድ የሚያሽከረክሩ ሰዎች አሁንም በብዛት አሉ፤ አደጋ ካደረሱም በኋላ ይሰወራሉ ብለዋል፡፡

በሐሰተኛ መንጃ ፈቃድ የሚያሽከረክሩትን የክልሉ ፖሊስ በተቻለው መጠን እየያዘ በፍርድ ቤት እንዲቀጡ እያደረገ ነው ያሉት ምክትል ኮማንደር ንጉሴ ግርማ የመንጃ ፈቃድ ቋት ወጥ የሆነና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ካልሆነ በስተቀር ችግሩን ለመቅረፍ ይቸግራል ብለዋል፡፡ሐሰተኛ መንጃ ፈቃድን ለመቆጣጠርም ሆነ ሌሎች የትራፊክ ደንብ ጥሰቶችን ለመቆጣጠር ቋሚ የፍተሻ ጣቢያ በክልሉ በተመረጡ ቦታዎች ለማድረግ እቅድ መኖሩን ባለሙያው ነግረውናል፡፡ በዚህ ዓመት በኦሮሚያ ክልል በደረሱ የትራፊክ አደጋዎች ከ1 ሺ 900 በላይ ሰዎች ህይወት የተቀጠፈ ሲሆን ካለፈው ዓመት ተመሣሣይ ወቅት ጋር ሲመሣከር በ280 ቅናሽ እንዳለው ሰምተናል፡፡

ንጋቱ ሙሉ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)
Leza Vote Banner
Sheger 102.1 AudioNow Numbers