• Slider One

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Slider Two

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Sldier Three

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ሸገር ወሬዎች እና ልዩ ወሬዎች

ጠቅላይ ሚንስተር ዶክተር አብይ እና አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ

ከእስር በመንግስት በልዩ ሁኔታ የተፈቱት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ዛሬ በጠቅላይ ሚንስትሩ ቤተመንግስት ከጠቅላይ ሚንስተር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር መገናኘታቸውን እና ለመንግስት ምስጋና እንዳቀረቡ፤በተለያዩ ጉዳዮችም እንደተነጋገሩ ሰምተናል።
 
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ብሔራዊ የሥርዓተ ምግብ መረጃ መተንተኛ ማዕከል ተመሰረተ

የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትና ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ጋር በመቀናጀት ተግባራዊ አደርገዋለው ያለው ብሔራዊ የሥርዓተ ምግብ መተንተኛ ማዕከል ምስረታ ይፋ የተደረገው ዛሬ በህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ ነው፡፡

ማዕከሉ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ በርካታ የሥርዓተ ምግብ መረጃዎችን ወደ አንድ ቋት በማሰባሰብ የመረጃ ትንተና ሥራ ይሰራል ተብሏል፡፡የአገሪቱን የሥርዓተ ምግብ ችግር መንስኤዎች መለየት፣ የተሻለ ውጤት ያመጡ የሥርዓተ ምግብ ፕሮግራሞችን መቀመርና ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓት የሚሆኑ መረጃዎችን ማቅረብ ማዕከሉ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራባቸው ጉዳዮች መሆናቸው ተነግሯል፡፡

በዓለም የምግብ ፖሊሲ ምርምር ተቋም ሙያዊ ድጋፍ የሚደረግለት ብሔራዊ የሥርዓተ ምግብ መረጃ መተንተኛ ማዕከል በአውሮፓ ህብረት የገንዘብ ድጋፍ የሚተገበር መሆኑን በመመስረቻ ፕሮግራሙ ላይ ተገኝተን ሰምተናል፡፡

ማህሌት ታደለ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የኢጋድ ሚኒስትሮች አስቸኳይ ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

በአስቸኳይ የተጠራው የሚኒስትሮቹ ካውንስል ስብሰባ 62ኛው መሆኑን ሊቀመንበሩ ወርቅነህ ገበየሁ ተናግረዋል፡፡የስብሰባው ዋና ዓላማም እ.ኤ.አ በ2015 በደቡብ ሱዳን ሀይሎች መካከል የተፈጠረውን የሰላም ስምምነት ባለመጠበቃቸው ውሳኔ ለማሳለፍ ነው ተብሏል፡፡

የአሜሪካ፣ የተባበሩት መንግስታት፣ የአውሮፓ ህብረት እንዲሁም የአፍሪካ ፀጥታና ሰላም አስከባሪ ሀይሎች በተገኙበት በዛሬው ስብሰባ ላይ ነፍጥ ያነሱ ሁለቱ ሀይሎች ከዚህ ቀደም የተሰጣቸውን ምክረ ሀሳብ እንዲቀበሉ ተጠይቀዋል፡፡ከ2 ዓመታት በፊት በተፈረመው የሰላም ስምምነት መሰረት ምንም አይነት ግጭት እንዳይቀጥልና በአደጋ ቦታ ላይ ያሉትም የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ እንዲደርሳቸው የሚጠይቅ ቢሆንም ሁለቱ ሀይሎች አንዱ በሌላኛው ላይ እያመካኘ ወደ ጦርነት የገቡት ወዲያውኑ ነበር፡፡

የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊቀመንበር ወርቅነህ ገበየሁ የአሁኑ የኢጋድ ሚኒስትሮች ስብሰባ የሚያሳልፈውን ውሳኔ እንዲቀበሉ በፅኑ አሳስበዋል፡፡ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ትናንት ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው ተሰምቷል፡፡

የኔነህ ሲሳይ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር አዲስ አበባ ደርሰዋል

የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር አዲስ አበባ ደርሰዋል፡፡ፕሬዝዳንቱ ወደ አዲስ አበባ የመጡት ከኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ለመምከር ነው ተብሏል፡፡የደቡብ ሱዳን የሰላም ድርድርና ንግግር ባለፈው በአዲስ አበባ የተካሄደ ሲሆን ፕሬዝዳንት ሳርቫ ኪር ወደ አዲስ አበባ የመጡት ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ይሁን ወይም ከተቃዋሚዎች ጋር በሚደረገው ድርድር ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ለመነጋገር ይሁን ለጊዜው አልታወቀም፡፡

የደቡብ ሱዳንን የሰላም ድርድር በሚያስተጓጉሉ የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ላይ አለም አቀፍ ማዕቀብ ለመጣል አሜሪካ ያቀረበችው የውሳኔ ሀሳብ ውድቅ መደረጉ ይታወሳል፡፡ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ከምክትላቸው ዶ/ር ሪያክ ማቻር ጋር በተነሳ ልዩነት ከፍተኛ ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ ከገቡ 4 አመታትን አስቆጥረዋል፡፡

የኔነህ ሲሳይ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

በድርድር ላይ ያሉት አገር አቀፍ ፓርቲዎች ድርድራቸውን ዛሬ መቀጠላቸው ተነገረ

ኢህአዴግን ጨምሮ 14ቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከ2 አመታት በፊት የጀመሩትን ድርድር ዛሬም እያካሄዱ መሆኑን ተነግሯል፡፡ ፓርቲዎቹ ቀደም ሲል በመረጧቸው 12 የመደራደሪያ ነጥቦች ላይ እየተነጋሩ ነው፡፡ከእነዚህም ውስጥ በ4ቱ ነጥቦች መወያየታቸውና ከስምምነት መድረሳቸው ተነግሯል፡፡

የአገሪቱ የምርጫ ህግ የምርጫ ቦርድ አደረጃጀትና የምርጫ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ድርድርም ማሻሻያ በማድረግና ባሉበት እንዲቀጥሉ በመስማማት የመረጧቸው አጀንዳዎች መኖራቸው ይነገራል፡፡ተደራዳሪ ፓርቲዎቹ በሞራል ካሳ ፈንድ፣ በሽብርተኝነት ትርጓሜና በሌሎቹም የፀረ ሽብር አዋጅ አንቀፆች ላይ ማስተካከያ ለማድረግ መግባባት ላይ መድረሳቸው ይነገራል፡፡

ፓርቲዎቹ በፀረ ሽብር ህጉ ላይ ከመግባባት ላይ የደረሱባቸው ጉዳዮች በባለሙያዎች ተደራጅተው እንዲቀርቡ ውሳኔ ማሳለፋቸው ይነገራል፡፡ፓርቲዎቹ ዛሬ የሚያደርጉት ንግግር ተደራጅቶ በሚመጣው ሰነድ ላይ ተወያይተው ውሳኔ ይሰጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ሰምተናል፡፡

የኔነህ ሲሳይ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ከደብረ ብርሃን በ20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ጫጫ ከተማ በተከሰተ የመኪና አደጋ የ18 ሰዎች ህይወት አለፈ

ትናንት ግንቦት 21 ቀን 2010 ዓ.ም ከደብረ ብርሃን ወደ አዲስ አበባ ሲጓዝ በነበረ አውቶብስ እና ከአዲስ አበባ ወደ ደብረ ብርሃን ሲያመራ በነበረ ሚኒባስ ሀይሩፍ ተሽከርካሪ መካከል በደረሰ ግጭት በሚኒባሱ ውስጥ ተሳፍረው የነበሩት 16 ሰዎችና አሽከርካሪው ሕይወታቸው ማለፉን የነገሩን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ ናቸው፡፡

በአደጋው በአውቶቡሱ ውስጥ ከተሳፈሩት ሰዎች መካከል የ1 ሰው ሕይወት ማለፉን የነገሩን ኢንስፔክተሩ ቀላልና ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቢኖሩም ቁጥራቸው ገና በትክክል አልታወቀም ብለውናል፡፡ከደብረ ብርሃን ወደ አዲስ አበባ ያመራ የነበረው አውቶቡስ መታጠፊያ ቦታ ላይ ሌላ መኪና ደርቦ ለማለፍ ሲሞክር ከሚኒባሱ ጋር ፊት ለፊት በመጋጨታቸው አደጋው ሊደርስ እንዳቻለም ከኢንስፔክተር አሰፋ ሰምተናል፡፡

ማህሌት ታደለ
 
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ከውጪ ተገዝተው የገቡ መድኃኒቶችና የህክምና መሳሪያዎች ለሆስፒታሎች እስኪከፋፈሉ ድረስ የሚከማቹበት መጋዘን ደረጃውን የጠበቀ አይደለም ተባለ

የመድሃኒት ፈንድ አቅርቦት ኤጀንሲ ገዝቶ የሚያከፋፍላቸው መድኃኒቶችና የህክምና መሳሪያዎችን ቆርቆሮ በቆርቆሮ በሆነ መጋዘን ውስጥ እንደሚከማቹ በመስክ ጉብኝቴ ተመልክቻለሁ ያለው በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ነው፡፡መድሃኒቶችና የህክምና መሳሪያዎቹ ቆርቆሮ በቆርቆሮ በሆነ መጋዘን ውስጥ መከማቸታቸው ደህንነታቸውና ፈዋሽነታቸው ተጠብቆ ወደ ሆስፒታሎች የመድረሳቸውን ነገር በእጅጉ አጠራጣሪ እንደሚያደርገው የቋሚ ኮሚቴው አባል ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የመድሃኒት ፈንድ አቅርቦት ኤጀንሲ የመጋዘን ጥበት አለብኝ በሚል ምክንያት በርካታ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን መድኃኒቶች ጥቅም ከሚሰጡት ጋር በአንድነት አስቀምጧቸው አይተናል ማለታቸውን ሰምተናል፡፡ ቋሚ ኮሚቴው ከኤጀንሲው በተጨማሪ የተለያዩ ጤና ጣቢያዎችን ሆስፒታሎንና ተያያዥ የጤና ተቋማትን በአካል ተገኝቶ ተመልክቻለሁ ያለውን የአሰራር ችግር እና በጎ ጎን በሚመለከት ዛሬ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከሌሎች የጤና ተቋማት ጋር እየተመካከረበት ነው፡፡

ቋሚ ኮሚቴው እንዳለው በጤና ጣቢያዎችና በሆስፒታሎችም ተገልጋዮችን ያማረሩ ውስብስብ ችግሮች አሉ፡፡ከ6 ወር በላይ ጓንት እና እጅግ አስፈላጊ የሆኑ መድሃኒቶች የሌሉባቸው ሆስፒታሎና የጤና ጣቢያዎች እንዳሉ በምክክሩ ወቅት ተነስቷል፡፡ ከመንግስት የጤና ተቋማት መድሃኒት እየተሰረቀ ወደ ግሎቹ እንደሚሄድና በጉዳዩም ላይ እርምጃ አለመወሰዱን ካነጋገርኳቸው ሰራተኞች ሰምቻለው ያለው ቋሚ ኮሚቴ መድሃኒትን በተመለከተ ከፍተኛ የቁጥጥር ሥርዓት ሊዘረጋ ይገባል ብሏል፡፡ ለችግሮቹና በምክክሩ ወቅት ለተነሱ ጥያቄዎች ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከሌሎች ተቋማት የተገኙ የስራ ሀላፊዎች መልስ ይሰጡባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ትዕግስት ዘሪሁን
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

“ከእስር ቤት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች እየለቀቅን ያለነው እስር ቤቱን ለመዝጋት አይደለም፤ እስር ቤትን ለማጥፋትም አይደለም...

“ከእስር ቤት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች እየለቀቅን ያለነው እስር ቤቱን ለመዝጋት አይደለም፤ እስር ቤትን ለማጥፋትም አይደለም፤ ቢጠፋልን ጥሩ ነው፤ የፖለቲካ ባህላችንን ለመቀየር ነው፤ መቻቻልን እንድንማር፤ መደማመጥ እንድንለምድ - ባለን አቅም ሁሉ ከመገፋፋት ባህል መውጣት አለብን በሚል የተወሰነ ነው - ቀላል ውሳኔ እንዳይመስላችሁ -ትልቅ ውሳኔ ነው፡፡

ዛሬ የኦሮሚያ ክልል በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ከአርባ ሺህ በላይ ሰዎችን ከእስር መፍታቱ፤ ሰዎች መንደር ውስጥ እንደሚያወሩት ቀላል ውሳኔ አይደለም፡፡ እውነት ነው ለአርባ ሺህ ነፍሶች ይቅርታ ማድረግ በሰው ልጆችም ሆነ፤ በፈጣሪ ፊት ጥሩ ስራ ነው፤ እነዚህ አርባ ሺህ ሰዎች ብቻ አይደሉም ነጻ የወጡት- ከእነዚህ አርባ ሺህ ሰዎች ጀርባ ሌሎች ሚሊየኖች አሉ፤ እነዚህ ሁሉ ናቸው ነጻ የወጡት…ትናንት ሲናቅ የነበረው ኦህዴድ - እየተናቀ - ዝቅ እየተደረግን እዚህ ደርሰናል፡፡ ከእናንተ በላይ ነን ሲሉን የነበሩትን ሁሉ ነጻ አውጥተናል - ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ አድርገናል፡፡

ለወገን በመቆርቆር መስራት ጥሩ ነው- መስራትና ማውራት ግን የተለያዩ ናቸው፡፡ እኔ ምንም ሳይጎድልብኝ የሰዎችን ትኩረት የሚስብ ንግግር ለአንድ ሰዓት ያህል ተዘጋጅቼ ሚዲያ ላይ በመውጣት ለሰላሣ ደቂቃ ላደርግ እችላለሁ፡፡ አራት ሰዓት ተዘጋጅቼ ለአንድ ሰዓት ጥሩ ንግግር ማሰማት እችላለሁ፡፡ ንግግር ግን ያው ንግግር ነው፡፡ ወደ ዳቦ አይለወጥም፡፡ ቁጭ ብሎ መናገር ለሰው አይከብድም፡፡ መስራት ነው የሚከብደው፡፡ ሰርቶ መሬት ላይ ትንሽም ይሁን ትልቅ ለውጥ ማምጣት ነው ከባዱ፡፡

ተሰዶ የነበረውን ብቻ አይደለም ነጻ ያወጣነው፤ ይህን ሀገር ከመበታተን አድነናል፡፡ ይሄ ለእኛ ትልቅ ታሪክ ነው - ለኦሮሞ ህዝብ ብቻ አይደለም ወደ ስልጣን የመጣነው፡፡ ምንም እንኳን ከኦሮሞ ህዝብ መካከል ብንወጣም፤ ሌሎች አሳንሰው እንደሚያዩን አይደለንም፡፡ ከኦሮሞ ህዝብ አልፈን ሀገር ማዳን የቻልን መሆናችንን እያረጋጥን ነው - እያሳየን ነው - ይሄ የሩቅ ዘመን ዘመን ታሪክ አይደለም- ያለፈው ወር ታሪክ ነው- ያለፉት ሶስት ሣምንታት፤ ያለፉት ሁለት ወራት ታሪክ ነው፡፡ ባለፉት ሁለት እና ሶስት ዓመታት በዚህ ሀገር ሲታይ የነበረ ታሪክ ነው”

ይህን ያሉት የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ - መስተዳድር አቶ ለማ መገርሣ ናቸው፡፡ ግንቦት 20ን አስመልክቶ በተዘጋጀ መድረክ ላይ አቶ ለማ መገርሳ ያደረጉትን ንግግር የተመለከተው ንጋሩ ረጋሳ ይህን አዘጋጅቷል…

ውድ የሸገር ቤተሰቦች፣ ሌሎች ማራኪ ፕሮግራሞቻችንን በቀላሉ እንድታገኙ ወደ ይፋዊ የYouTube ቻናላችን ጎራ ብላችሁ Subscribe እንድታደርጉ እንጋብዛለን፡፡ እናመሰግናለን!

አስተያየት ይፃፉ (1 Comment)

“ ኘ ” ን ያያችሁ አፋልጉኝ ተብላችኋል...

ቀደም ሲል በየአገልግሎት ሰጭ የመንግስት መስሪያ ቤቶች በስራ ሰዓት ሲደረጉ የነበሩ ማለቂያ ያልነበራቸው ስብሰባዎች የአገልግሎት ፈላጊዎች የመጉላላት ምክንያቶች የእሮሮ ምንጮች ነበሩ፡፡በከተማችን አንዱ ወረዳ “ ኘ ” የተሰኘችው ፊደል ከኮምፒዩተር መተየቢያው መጥፋቷ የተገልጋዮች መጉላያ ሆናለች፡፡

ወጣቱ ከዓመት በፊት የጋብቻ የምስክር ወረቀቱን ለመውሰድ ወደ ወረዳው ወሳኝ ኩነቶች ጽህፈት ቤት አመራ፡፡“ ኘ ” ፊደል ባለመኖሯ ሰነዱን ማሰራት አልቻለም፡፡ዛሬም ከአመት በኋላ ሰነዱን ለማሰራት ወደ ወረዳው ወሳኝ ኩነቶች ጽህፈት ቤት ቢመለስም “ ኘ ” ን የበላት ጅብ አልጮህ እንዳለ ነው፡፡

አሁንም የጋብቻ የምስክር ወረቀት ፈላጊውን ኧረ “ ኘ ” ወዴት ነሽ እያሰኘው መሆኑን ከስፍራው ደውሎ ነግሮናል፡፡

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የጠንቋይዋ ነገር…ጠንቋይዋ ከነባለቤቷ ተሰውራለች…

ቦታው አዲስ አበባ፣ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5፣ ግሩም ሆስፒታል አካባቢ ነው፡፡ የዛሬ 10 ዓመት አንዲት ሴት አንድን የዛን አካባቢ ነዋሪ ተጠግታ ሐብታም አደርግሃለሁ አለችው ይለናል ይህ የበየነ ወልዴ ዘገባ፡፡ እሱም፣ የአካባቢው ሰው እንደሚለው፣ የተገባለትን ተስፋ አድርጎ የሚኖርበትን የቀበሌ ቤት ለቅቆላት ኩሽና ውስጥ መኖር ጀመረ፡፡ግን ደግሞ እንዳለችው ሐብታም አልሆነም፡፡ ሴትየዋም ቤቱን የጥንቁልና ማካሄጃ አደረገችው፡፡ በሴትየዋ ድርጊት በተናደዱ የአካበቢው ነዋሪዎች ግፊት እና እሱም የምኖርበት ኩሽና ጠቦኛል ሲል ቤቴን ልቀቂልኛ ማለት ጀመረ፡፡
በዚህም ግጭት ተፈጠረ፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎች የሰውዬውን ወንድም ቁርስ ብላ ብላው ከበላ በኋላ ወዲያው ሞተ ነው የሚሉት፡፡ሐብትን አልሞ ቤቱን የሰጣት ሰውም ብዙም ሳይቆይ ከወገቡ በታች ፓራላይዝድ ሆነ፡፡ ፊዚዮቴራፒን ጨምሮ የተለያዩ ሕክምናዎች ቢሞከርም ሊድን አልቻለም ከትላንት በስቲያ አረፈ፡፡የአካባቢው ሰው የሰውዬውን አስክሬን ወደቤት ሊያስገቡ ሲሉ፣ “ይሄ አስክሬን “ቤቴ” አይገባም” አለች ሴትየዋ፡፡ ፖሊስ ሲጠራ ከነባለቤቷ ቤቱን ጥላ መሰወሯ ተነግሯል…አስክሬኑም ከመቀበሩ በፊት ተመርምሮ የምርመራ ውጤቱ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮምሽን ተልኳል፡፡

ቤቱ ሲፈረሽ የተለያዩ ነገሮች ተገኝተዋል - ብዛት ያላቸው ሳንቲሞች፣ የበግ ቀንዶች፣ የተለያዩ ሰዎች ፓስፖርቶች፣ የባንክ ደብተሮች…ሴትየዋ በሐምሌ 18 ቀን 2008 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ቀደምት ወፋ አቦዬ ገዳ ወረጊፍት አውልያ እና ወልዮች አንድነት ዓለማቀፍ እምነት ተቋም የእምነቱ አባል እና አያንቱ የሆነችበትን የምስክር ወረቀት ተቀብላለች፡፡ በእምነቱ መተዳደሪያ ደንብ መሰረትም ከእምነቱ ጋር በሚፃረረው የጥንቆላ ተግባር ላይ እንዳትሰማራ ግዴታ ገብታለች፡፡

የእምነት ተቋሙ በሕዳር 15 ቀን 2009 ዓ.ም ለአውቶብስ ተራ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ በላከው ደብዳቤ፣ “ሴትየዋ ተጠግታበት የነበረውን ቤት የራሷ በማስመሰል አስመዝግባ ላልተፈቀደላት አላማ እየተጠቀመች በመሆኑ ከእምነት ተቋሙ ማስናበቱን እና የሰጣትን ፈቃድ መሰረዙን” አስታውቋል፡፡ይህ ሁሉ እያለ ሟች ቤቱን ለማግኘት ሲከራከር ድጋፍ አለማግኘቱ እንደሚያሳዝናቸው የአካባቢው ሰዎች ይናገራሉ፡፡

የበየነ ወልዴን ሙሉውን ዘገባ ያዳምጡ…

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

“አያ ሙሌ ! ... የከተማው ባሕታዊ ! - አራተኛ ክፍል

የወሎው አበጋር ፣ ወድ ሐለቃ !ነቢዩ ወልደ እግዚአብሄር ! ”

ሙሉጌታ ተስፋዬ ! ... የቅኔ ሙሉ ጌታ ! “ ማንም ያልደረሰበት የራሱ ዓለም ያለውና ቀድሞ የሄደ ሰው ነው። ገና በአፍላ እድሜው ከልጅ እስከ አዋቂው በአክብሮት ‘አያ ሙሌ’ በማለት ይጠሩት ነበር”
ባለቅኔ ሙሉጌታ ተስፋዬ…

ሃሳበ ውቅያኖስ፤ የቋንቋ ባለፀጋ፤ ፈላስፋ፤ ሌሎችንም ብዙ ቅፅሎችን ደርድረን የማንጨርሰው ልሂቅ ነበር ! የአበበ ተካን አንድዬ ድንቅ አልበም ጨምሮ ለተለያዩ ድምፃውያን ጥልቅና ውብ ግጥሞችን አበርክቷል ! በሙዚቃ ሥራ ውስጥ የግጥም ዋጋና ፋይዳ ከፍ ያለ እንደሆነ ሰርቶ ያሳየና አቅጣጫ ያስቀየረ ድንቅ ገጣሚ ነበር፤
ባለቅኔው ሙሉጌታ ተስፋዬ ! “ወይ አዲስ አበባ” የራድዮ ፕሮግራም በዘፈንና ዘመን የፕሮግራም አንጓው የባለቅኔውን ሙሉጌታ ተስፋዬ ሕይወትና ሥራዎች በስፋት መዳሰስ ጀምሯል !
እነሆ አራተኛውን ክፍል…

ውድ የሸገር ቤተሰቦች፣ ማራኪ የአሁን እንዲሁም ቆየት ያሉ መሰናዶዎቻችንን በYouTube ቻናላችን ማዳመጥ እንድትችሉ በቀላሉ ሊንኩን በመጫን Subscribe ያድርጉ እናመሰግናለን::

አስተያየት ይፃፉ (1 Comment)
Sheger 102.1 AudioNow Numbers