• Slider One

  የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

 • Slider Two

  የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

 • Sldier Three

  የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ሸገር ወሬዎች እና ልዩ ወሬዎች

በተለያዩ ግንባታዎች ላይ የነበሩ 116 ሥራ ተቋራጮች የሥራ ውላቸውን አቋርጫለሁ ሲል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮንስትራክሽን ቢሮ ተናገረ

በተለያዩ ግንባታዎች ላይ የነበሩ 116 ሥራ ተቋራጮች የሥራ ውላቸውን አቋርጫለሁ ሲል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮንስትራክሽን ቢሮ ተናገረ፡፡የቢሮው ኃላፊ የሆኑት አቶ ዮናስ አያሌው እንዳሉት ከሆነ ከነዚህ ውስጥም በህግ የሚጠየቁም ይኖራሉ፡፡በአዲስ አበባ እስከ 900 ገደማ የሚደርሱ የመንግሥት ግንባታዎች እየተገነቡ ነው ያሉት አቶ ዮናስ በእነዚህ ግንባታዎች ላይ ከተማሰሩ ሥራ ተቋራጮች የአፈፃፀም ችግር ያለባቸውን ማስጠንቀቂያ በመስጠትና የአቅም ድጋፍ ለማድረግም ሞክረናል ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከአምና ጀምሮ የተለያዩ ድጋፍ ተደርጎላቸውም ሥራቸውን ማከናወን ያልቻሉ 116 ተቋራጮች ውላቸው ተቋርጧል ብለዋል፡፡የተለያዩ የቅድመ ክፍያዎችንም ይዘው የጠፉ እንዳሉም የተናገሩት አቶ ዮናስ እነዚህንም በህግ ተጠያቂ እናደርጋቸዋለን ብለዋል፡፡አንዳንዶቹም እስከ 90 በመቶ ግንባታቸውን አድርሰው መጨረስ ያልቻሉም እንዳሉ ሰምተናል፡፡

በአዲስ አበባ የተለያዩ ግንባታዎች መጓተት ይታይባቸዋል ያሉት አቶ ዮናስ ለእነዚህ ግን ተጠያቂዎቹ ሥራ ተቋራጮች ብቻ ሳይሆኑ አሰሪዎችም ናቸው ይላሉ፡፡በርግጥም የኮንስትራክሽን ግንባታ ውስብስብ ነው ያሉት ኃላፊው በተለይም በህንፃ ግንባታ የሚያስፈልጉ አንዳንድ ቁሣቁሶች ከውጪ የሚመጡና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ፈተና የሚሆኑባቸው እንደሚሆኑም ነግረውናል፡፡

ዮሐንስ የኋላወርቅ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ሐምሌ 4፣2009 የሸገር ወሬዎቻችን

 • በኢትዮጵያ የአልኮል መጠጥ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ41 በመቶ በላይ መሆኑን አንድ ጥናት አሣየ፡፡ (ንጋቱ ሙሉ)
 • በ2010፣ 2 ሺ 800 የጎዳና ተዳዳሪዎችና 400 ሺ የደሃ ደሃዎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮግራም መሰናዳቱ ተሠማ፡፡ (አስፋው ስለሺ)
 • የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 3ኛ መደበኛ ጉባዔውን ትላንት ጀምሯል፡፡ የአዲስ አበባ የውሃ ችግር በጉባዔው ላይ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል ይገኝበታል፡፡ (ምህረት ስዩም)
 • ኢህአዴግና ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚደራደሩበት ሰነድ ከዛሬ ጀምሮ ለፓርቲዎች ይሰራጫል ተባለ፡፡ (የኔነህ ሲሣይ)
 • በፖለቲካ ማኅበራት መካከል የሚካሄደው ድርድር በአምሥት ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል ተባለ፡፡ (የኔነህ ሲሣይ)
 • በግብር አወሳሰን የቀን ገቢ ግምት ላይ ቅሬታ ያላቸው አቤቱታ ማቅረብ እንደሚችሉ ተነገረ፡፡ (ምህረት ስዩም)
 • በአዲስ አበባ በተለያዩ ምክንያቶች የተሰጧቸውን የግንባታ ሥራዎች ማከናወን ያልቻሉ ከ100 በላይ ተቋራጮች ውላቸው ተቋርጦባቸዋል ተባለ፡፡ (ዮሐንስ የኋላወርቅ)
 • በአዲስ አበባ የሙያ ብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ፈተና ከቀጣዩ አመት አንስቶ በኢንተርኔት /በመረጃ መረብ/ አማካኝነት ሊሰጥ ነው፡፡ (ንጋቱ ረጋሣ)
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

መተሃራ ስኳር ፋብሪካ ላይ በደረሰው ንፋስና በረዶ የቀላቀለ ዝናብ ፋብሪካው ስኳር ማምረት ቢያቆምም የስኳር እጥረት እንደማይኖር ስኳር ኮርፓሬሽን ተናገረ

መተሃራ ስኳር ፋብሪካ ላይ በደረሰው ንፋስና በረዶ የቀላቀለ ዝናብ ፋብሪካው ስኳር ማምረት ቢያቆምም የስኳር እጥረት እንደማይኖር ስኳር ኮርፓሬሽን ተናገረ…ፋብሪካው ላይ በደረሰው የዝናብ አደጋ ለጊዜው ስኳር ማምረት ማቆሙን ያስታወሰው ስኳር ኮርፖሬሽን በስኳር አቅርቦት ላይ የተወሰነ ክፍተት ሊፈጠር ይችላል ብሏል፡፡ የኮርፖሬሽኑ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጋሻው አይችሉህም ለሸገር እንደተናገሩት በመታሀራ ስኳር ፋብሪካ ምርት ማቆም ምክንያት የስኳር አቅርቦቱ ላይ የተወሰነ ክፍተት ሊፈጠር ቢችልም ስኳር ኮርፖሬሽን ከ1 ሚሊየን ኩንታል በላይ ስኳር ስላለው ኃሣብ እንዳይገባችሁ ብሏል፡፡

የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በመስከረም ወር ሥራ ስለሚጀምር እንዲሁም የኩራዝ 2 እና የከሰም ስኳር ፋብሪካዎች ክረምቱን በሙሉ ስለሚያመርቱ እጥረት እንደማይፈጠር አቶ ጋሻው ተናግረዋል፡፡

የመተሀራ ስኳር ፋብሪካ ሰኔ 29 ቀን 2009 ዓ.ም ለሊት በደረሰበት ንፋስና በረዶ የቀላቀለ ዝናብ ለጊዜው ምርት ያቆመ ሲሆን ለፋብሪካው ተዘጋጅቶ የነበረው 40 ሺ ኩንታል ሸንኮራ አገዳ ወደ ከሰም ስኳር ፋብሪካ እየተጓጓዘ መሆኑን የስኳር ኮፖሬሽን የኮርፓሬት ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጋሻው አይችሉህም ለሸገር ተናግረዋል፡፡

ንጋቱ ሙሉ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ከሳውዲ አረቢያ የተመለሱ ኢትዮጵያውያን በማምረቻው ዘርፍ ገብተው እንዲሣተፉና ወደ ቅጥር እንዲመጡ መንገዶችን እንደሚያመቻች የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ተናግሯል

ከሳውዲ አረቢያ የተመለሱ ኢትዮጵያውያን በማምረቻው ዘርፍ ገብተው እንዲሣተፉና ወደ ቅጥር እንዲመጡ መንገዶችን እንደሚያመቻች የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ተናግሯል፡፡በኮሚሽኑ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነሩ ዶክተር በላቸው መኩሪያ ለሸገር እንደተናገሩት የማምረቻ ዘርፎች ያሏቸውን ሰፊ የሰው ኃይል ፍላጐት ለማሟላት ከሳውዲ አረቢያ ተመላሾችም እድሉን አግኝተው ወደ ቅጥር እንዲገቡ እናመቻቻለን ብለዋል፡፡ዶክተር በላቸው ተመላሾች በርከት ብለው በሚመጡባቸው ቦታዎች ዘርፉ በርካታ ሥራ ፈላጊዎችን እንደሚያስተናግድም ተናግረዋል፡፡

የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሠራተኛ ምልመላና ዝግጅት አካሄድ በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪያል ፓርክም ይተገበራልም ብለዋል፡፡የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ 9 የማምረቻ ሼዶች ያሉት ሲሆን ለ20 ሺ ሰዎች የሥራ እድል ይፈጥራል መባሉን ፓርኩ ከትላንት በስቲያ ሲመረቅ ተገኝተን ሰምተናል፡፡ኮምቦልቻና አካባቢዋ ለጂቡቲ በቅርብ ርቀት በመገኘቷ በርካታ የአካባቢው ወጣቶች በተለይም ሴቶች በህገ-ወጥ መልኩ በደላሎች ተታለው ወደ ሀረብ ሀገራት እንደሚሰደዱ ሸገር በአካባቢው ያነጋገራቸው ወጣቶች ነግረውታል፡፡

በሀገሪቱ በሁሉም መአዘናት እየተገነቡ ያሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን መንግሥት በሚመረቱ ምርቶች የውጭ ምንዛሬ ከማግኘት በተጨማሪ ለዜጎች ቀጥተኛ የሥራ ዕድል ይፈጥሩልኛል ብሎ በብርቱ አምኖባቸዋል፡፡ሀገሪቱን ተመራጭ የኢንዱስትሪ መዳረሻ ካደረጓት ነጥቦች አንዱና ዋነኛው በንፅፅር በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብና በትንሽ ሥልጠና ምርታማ መሆን የሚችል ሰፊና ወጣት የሠራተኛ ኃይል መኖሩ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ መናገራቸው ይታወሣል፡፡

በተለያዩ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች በሥራ ላይ የሚገኙ ሠራተኞች የክፍያ አንሶናል ጥያቄ ሲያሰሙ ይደመጣል ሆኖም መንግሥት የሠራተኞች ክፍያ ከልምድ፣ ከክህሎትና ምርታማነት ማደግ ጋር መጨመሩ የግድ ስለሚል መንግሥት የዝቅተኛ ክፍያ መጠንን ለመወሰን ጣልቃ እንደማይገባም ተናግሯል፡፡

መንግሥት የሠራተኛን ክፍያ ተጨባጭ ሁኔታ ከሚፈቅደው በላይ እንዲጨምር ግፊት ማድረጉ ወደ ሀገሪቱ በሚገባው የኢንቨስትመንት ፍሰት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል ብሎም እንደሚያምን ተሰምቷል፡፡

ምሥክር አወል
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ሐምሌ 3፣2009 የሸገር ወሬዎቻችን

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

 • በመተሃራ ስኳራ ፋብሪካ ምርት ማቆም ምክንያት የስኳር እጥረት እንደማይከሰት ስኳር ኮርፖሬሽን እወቁልኝ አለ፡፡ (ንጋቱ ሙሉ)
 • የጎማ ዛፍ ልማት እና ምርት ፕሮጀክት ዓመታዊ የማምረት አቅሙን በአሥር እጥፍ ማሳደጉ ተነገረ፡፡ (ንጋቱ ረጋሣ)
 • የመቐሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሣለኝ በተገኙበት ተመረቀ፡፡ (ንጋቱ ረጋሣ)
 • ከሳውዲ አረቢያ ተመላሾች በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሥራ እድል እንዲያገኙ መንገዶች ይመቻቹላቸዋል ተባለ፡፡ (ምሥክር አወል)
 • አራሜክስ በኢትዮጵያ ከሎጂክስ ኤክስፕሬስ ኩባንያ ጋር በመሆን ሥራ ጀመረ፡፡ (አስፋው ስለሺ)
 • በኢትዮጵያ ባለፉት 25 ዓመታት በወባ በሽታ የሚደርሰው ሞት በ94 ነጥብ 8 በመቶ መቀነሱን አንድ ጥናት አሳየ፡፡ (ንጋቱ ሙሉ)
 • የፋይናንስ እጥረትና የሥራ ተቋራጮች ችግር በከተማዋ የሚካሄዱ የቤት ግንባታዎች ለመዘግየታቸው ምክንያት መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተናገረ፡፡ (ምሕረት ስዩም)
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን በኤሌክትሪክ መቆራረጥ ሰበብ የውሃ ምርታችን የቀነሰ ነው አለ

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን በኤሌክትሪክ መቆራረጥ ሰበብ የውሃ ምርታችን የቀነሰ ነው አለ፡፡የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበኩሉ መስመሮቻችን ያረጁ ስለሆነ በቻይና የኤሌክትሪክ ኩባንያ በአዲስ በመተካት ላይ ነን ሲል ተናግሯል፡፡

ከውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የውሃ ማምረት ማሰራጨት ሲስተም ቁጥጥር ንዑስ የሥራ ሂደት ባለቤቱ አቶ ታደሰ ዘገየ እንደተናገሩት የኤሌክትሪክ አገልግሎቱ በአቃቂ ሁለትና ሦስት ሀ እና ለ የውሃ መገኛ ክፍል በየቀኑ ለረጅም ሰዓት እየተቋረጠ የአዲስ አበባ የውሃ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ እየተጐዳ ነው ብለዋል፡፡

በመብራቱ ችግር የውሃ ተጠቃሚዎች ከሁለትና ሦስት ቀን በላይ ውሃ እየተቸገረ ነው ያለው ውሃና ፍሳሽ ይህ የአቃቂው መስመር 210 ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ የሚያመርተው ነው እሱም ሲቋረጥ ጦር ሃይሎች፣ ቤተል፣ አለም ባንክ፣ አየር ጤና፣ ሰባተኛ፣ ሜክሲኮ፣ ሳር ቤት፣ ቄራ፣ ጐፋ፣ ሳሪስ፣ ስታዲየም፣ ካዛንቺስ አካባቢዎች በሙሉ ውሃ እያጡ ነው ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የኤሌክትሪክ አቅርቦት ሥራ ኃላፊው አቶ ኢሣያስ አማረን ስለ ችግሩ ጠይቀናቸው በእርግጥ መቆራረጡ እያጋጠመ ነው፤ ይህም የኤሌክትሪክ መስመሮቻችን ያረጁ በመሆናቸው ንፋስና ዝናብ እየበጣጠሳቸው የተፈጠረ እክል ነው፤ አሁን በቻይና የኤሌክትሪክ ኩባንያ በኩል የኮንክሪት ምሰሶዎችን እየተካን ነው ለሥራውም 168 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርገናል፤ ከስድስት ወር በኋላ የኤሌክትሪክ መቆራረጡ ችግር 90 በመቶ ይቀንሳል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ወንድሙ ኃይሉ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ሰኔ 29፣2009 የሸገር ወሬዎቻችን

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

 • የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት በኤሌክትሪክ መቋረጥ ምክንያት የውሃ ምርቴ እየቀነሰብኝ ነው አለ፡፡ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ችግሩን በመንፈቅ ውስጥ አቃልላለሁ ይላል፡፡ (ወንድሙ ኃይሉ)
 • በጣና ሃይቅ እየታየ ያለው የእምቦጭ አረም ሃይቅን ያደርቃል፣ የኤሌክትሪክ ማመንጫዎችንም ያውካል፣ ከዚህ ሂደት ጋር ቀጥታ ትስስር ያለውን የህዳሴ ግድብ እየገነባች ያለችው ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥንቃቄ ልታደርግ ይገባል ተብሏል፡፡ (ምሥክር አወል)
 • የሣውዲ አረቢያ መንግሥት የሰጠውን ተጨማሪ የአንድ ወር የምህረት ጊዜን በፍጥነት የመጠቀሙ ነገር በኢትዮጵያዊያን በኩል ድክመት እየታየበት ነው ተባለ፡፡ (የኔነህ ሲሣይ)
 • በየጊዜው የሚያሽቆለቁለውን የኢትዮጵያ የወርቅ ገበያ ለመታደግ እየተሰራ ነው ተባለ፡፡ (ዮሐንስ የኋላወርቅ)
 • የ2010 በጀት በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አጠር ያለ ምክክር ተደረገበት፡፡ (ትዕግሥት ዘሪሁን)
 • በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የኢንዶስኮፒ ሕክምና ባለሙያዎች ማሰልጠኛ ማዕከል ተከፈተ፡፡ (አስፋው ስለሺ)
 • በአዲስ አበባ በአንድ መኖሪያ ቤት ላይ ባጋጠመ የቃጠሎ አደጋ የአንድ ሰው ሕይወት አለፈ፡፡ (ወንድሙ ኃይሉ)
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ለዛ የምሳ ሰዓት ፕሮግራም ሰኔ 27፣2009

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የፍልስጤም አስተዳደር ከኢትዮጵያ ጋር የሁለትዮሽ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ለመመስረት ፍላጎት አንዳለው ተሰማ

የፍልስጤም አስተዳደር ከኢትዮጵያ ጋር የሁለትዮሽ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ለመመስረት ፍላጎት አንዳለው ተሰማ፡፡ወሬው የተሰማው ትላንትና በ29ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ የፍልስጤም አስተዳደር ፕሬዝዳንት መሐሙድ አባስ በጉባዔው ላይ በመገኘት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ ጋር በሁለትዮሽ የሚኒስትሮች ኮሚሽ ምክር ቤት መመሥረት ዙሪያ ሲነጋገሩ ነው፡፡

በ29ኛው የህብረቱ የመሪዎች ጉባዔ ላይ በመገኘት ፍልስጤም ነፃ ሀገር ለመሆን በምታደርገው ጥረት ውስጥ የአፍሪካ ህብረት ድጋፉን እንዲሰጣቸው የጠየቁት ፕሬዝዳንት መሐሙድ አባስ ሀገራት በእሥራኤል ላይ ተፅዕኖ በማድረግ የፍልስጤማውያንን ለነፃ መንግሥትነት የሚያደርጉትን ትግል እንዲደግፉ ጠይቀዋል፡፡የሁለት መንግሥታት ኃሣብን የምታራምደው ፍልስጤም በእሥራኤል መንግሥት ተወስዶብኛል የምትለውን መሬቷን ለማስመለስና ነፃ መንግሥት ለመሆን ትግል ከጀመረች 50 ዓመታት ሞልቷታል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ ጋር ትላንትና ፕሬዝዳንት መሐሙድ አባስ ባደረጉት የሁትዮሽ ንግግር ላይ በአፍሪካ ህብረት ተሰሚነት ያላት ኢትዮጵያ ትግላችንን ወደፊት እንዲሄድ ድጋፏን እንድትሰጠን እንፈልጋለን ሲሉ ፕሬዝዳንቱ መጠየቃቸው ተሰምቷል፡፡የኢትዮጵያ መንግሥት በፍልስጤምና በእሥራኤል መካከል የሰላም ስምምነት ተፈጥሮ ሀገራቱ እንዲኖሩ የኢትዮጵያ ፍላጎት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ ለመሐሙድ አባስ ተናግረዋል፡፡

ትላንትና በተጠናቀቀው 29ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ በኢትዮጵያና በፍልስጤም አስተዳደር መንግሥታት ሚኒስትሮች መሀከል የጋራ ኮሚሽን ለመመስረት የቀረበው ኃሣብ ከቀናት በፊት በኢትዮጵያና በሌሎች ሀገራት መሀከልም በተመሳሳይ ውይይት እንደተደረገበት ሰምተናል፡፡

የኔነህ ሲሳይ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ሰኔ 28፣2009 የሸገር ወሬዎቻችን

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

 • የደጋ ፍራፍሬ ችግኞችና የእንስሣት መኖ ለምትፈልጉ የአዲስ አበባ ግብርና ጽ/ቤት እኔ ዘንድ አለላችሁ ብሏል፡፡ (ወንድሙ ኃይሉ)
 • በኢትዮጵያ ደጋማ ቦታ የምትገኘው በቆጂ የውሀ ችግር ገጥሟታል ተባለ፡፡ የከተማዋ አስተዳደር ውሀ ለህብረተሰቡ ለማቅረብ በምናደርገው ጥረት ተወላጅ አትሌቶች እገዛ ያድርጉልን ብሏል፡፡ (አስፋው ስለሺ)
 • በሐምሌ ወር በረዶ የቀላቀለ ነጐድጓዳማ ዝናብ ይጠበቃል ተባለ፡፡ (ወንድሙ ኃይሉ)
 • የኢትዮጵያና የፍስሌጤም መንግሥት የጋራ ኮሚሽን ለማቋቋም ተነጋገሩ፡፡ (የኔነህ ሲሣይ)
 • ብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ክረምቱ የደም ለጋሾችን ቀንሶብኛል አለ፡፡ (ወንድሙ ኃይሉ)
 • የሀገራችን የሰኔ ወር የዋጋ ግሽበት 8 ነጥብ 8 በመቶ ሆኖ ተመዘገበ፡፡ (ንጋቱ ረጋሣ)
 • የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የውበትና መናፈሻ ዘላቂ ማረፊያ ልማት ኤጀንሲ በመዲናዋ የተወሰኑ ጎዳናዎች አካፋዮችንና አጥሮችን የማፈርሰው ወደ ስታንዳርድ ለመቀየር በማሰቤ ነው ሲል ተናገረ፡፡ (ምሥክር አወል)
 • ክረምት የመኪና አደጋዎች የሚደጋገሙበት ሆኖ የህክምና መስጫ ቦታ እጥረት ፈጥሮብኛል ሲል አቤት ሆስፒታል ተናገረ፡፡ (ወንድሙ ኃይሉ)
 • የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከዩኔስኮ አደገኛ መዝገብ ውስጥ ወጣ፡፡ (ንጋቱ ሙሉ)
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሜቴክ ከወሰዳቸው የስኳር ፕሮጄክቶች አንዱን አጠናቆ ሥራ ማስጀመሩን ተናገረ

የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሜቴክ ከወሰዳቸው የስኳር ፕሮጄክቶች አንዱን አጠናቆ ሥራ ማስጀመሩን ተናገረ፡፡በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እገነባቸዋለሁ ብሎ ሰባት የስኳር ፕሮጀክቶችን ወስዶ የነበረ ሲሆን በገንዘብ ችግር ምክንያት አራቱን ለቻይና ኩባንያዎች አስተላልፏል፡፡

ከህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ቢሮ ባገኘነው መረጃ እንደተባለው ከሰም፣ ወልቃይት፣ በለስ አንድ እና ሁለት እንዲሁም ኦሞ አንድ ሁለትና ሦስት ሜቴክ ሊገነባቸው የወሰዳቸው ፕሮጀክቶች ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ፋብሪካዎች ለመገንባት የሚጠይቀው ገንዘብ አጅግ ከፍተኛ በመሆኑ አራቱ ለቻይና ኩባንያዎች እንዲሰጡ ሆኗል፡፡ ቀድሞውኑ ገንዘቡስ ቢገኝ የመገንባት አቅምስ ነበራቸው የተባሉት የወሬ ምንጮች የገንዘብ እንጂ የሰው ኃይል ችግርስ አልነበረብንም ብለዋል፡፡ በኦሞ አንድ የስኳር ፋብሪካ በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር 250 ሺ ቶን ስኳር ያመርታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ፋብሪካው ያልቃል ከተባለበት ጊዜ አንድ አመት ያህል የዘገየ እንደሆነም ሰምተናል፡፡ በቅርቡም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሪፖርት ባቀረበ ጊዜ የኦሞ ቁጥር 1 መቶ በመቶ መጠናቀቁ የተነገረ ሲሆን የአሰሪው ሪፖርት ግን 93 ነጥብ 5 በመቶ ነው የተጠናቀቀው ማለቱ ይታወሳል፡፡

ዮሐንስ የኋላወርቅ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)
Sheger 102.1 AudioNow Numbers