ማስታወቂያ

programs top mid size ad

"ወደፊት ወይስ ወደኋላ"

አዲስ አበባ መሃል ፒያሳ (ምሽት 2፡30) ከሳምንት ቀኖች በአንዱ፡፡
ታክሲ ይዤ ከመጣሁበት ራቅ ያለ ሰፈር ፒያሳ ኪያብ ካፌ አካባቢ ወረድኩ፡፡ ወትሮ ለታክሲ መጫን እና ማውረድ በተከለከለበት በዚህ መስመር ሲመሻሽ ግን ህግ ገለመሌ ቦታ የላቸውም፡፡
ፒያሳ የቀን ወዟ የለም፡፡ ሲመሽ ሌላ ነች፡፡
የአላፊ አግዳሚውን እጅ እየሳሙ ዳቦ መግዣ የሚለምኑ ህፃናትም አይታዩም… ከጥዋት እስከማታ ፆም የማይውሉትና 'የአዲስ አበባ ሰው ቀን ቀን አይሰራም እንዴ?' የሚያስብሉን ካፌዎችም ቀሪ ተስተናጋጆቻቸውን ሸኝተው ለመዘጋጋት ያኮበኮቡ ይመስላል፡፡ ግር ግር እና ወከባው ጋብ ብሏል፡፡
ብቻ አራዳ ህንፃ ላይ ከተንጠለጠሉት መጠጥ ቤቶች የተደበላለቀ የዘፈን ድምፅ ይሰማል፡፡ ጥቂት የመንገድ ላይ ሸቃጮች "ቦርሳ በመቶ ብር ፤ ጫማ በእንዲህ ዋጋ ፤ ትራስ የአየር መንገዷን በ10 ብር…" እያሉ የምሽት ገበያ ይጠራሉ፡፡
የተቀቀለ እና የተጠበሰ እሸት በቆሎ የሚሸጡ ሴቶች እና  ወንዶች በየቦታው ይታያሉ፡፡
ወደ አዲሱ ገበያ የሚያደርሰኝን ታክሲ ለመያዝ በትሪያኖን ካፌ ሽቅብ ወጣሁ፡፡ቀደም ብሎ መዝነቡን የሚያሳብቀው የአስፓልት መንገድ እዚህም እዚያም ውሃ ቋጥሮ አረማመዴን በብልሃት አድርጎታል፡፡
ካዛንቺስ ፤ 22 ፤ መገናኛ ፤ 4 ኪሎ በዚያ መስመር የሚጠሩ ታክሲዎች ቤቱ ለመከተት የሚጣደፈውን አዲስ አበቤ እየሞሉ ይፈተለካሉ፡፡ ሲኒማ ኢትዮጲያ በር ላይ ደረስኩ፡፡ የምሽት ሁለት ሰአት ተኩሉን ፊልም የሚገቡ ጥቂት ሰዎችን አየሁ፡፡ ለምን አልገባም? የሚል ሀሳብ ሽው አለብኝ፡፡ ተረኛውን ፊልም አየሁት 'ሮማንስ ኮሜዲ' ይላል የተለመደ ነው ግን እንደው ግቢ ግቢ አለኝ አመነታሁም፡፡
እራሴን ትኬት ቆርጬ አገኘሁት፡፡
ለታሪካዊው ሲኒማ ኢትዮጲያ ባይተዋር ነኝ፡፡ በመንገዴ የማገኘው ቢሆንም እግር ጥሎኝ የገባሁበት ቀን ቢቆጠር ከአንድ እጄ ጣት አይበልጥም፡፡
ወደ ውስጥ ስገባ እንደ አዲስ የሰፈራ መንደር ሰው አለፍ አለፍ ብሎ ተቀምጧል፡፡ ከበሩ ብዙም ሳልርቅ ተቀመጥኩ፡፡ ከበስተጀርባዬ ሰው የለም፡፡ ከፊት ለፊቴ አንድ ሁለት ወንበር ዘሎ ሁለት ጥንዶች ተቀምጠዋል፡፡
አንዳንዶች ስልካቸው ላይ ተጠምደዋል፡፡ እዚህም እዚያም በጨለማ ውስጥ ብርሃኑ ይታያል፡፡ ትኬት ቆርጠው ገና የሚገቡት ቦታ እየመረጡ ይቀመጣሉ፡፡
ሰዓቱ ይሆን? እንጃ ግን ጥንድ ይበዛል፡፡
ከፊት ለፊቴ የተቀመጡት ጥንዶች አልፎ አልፎ ንግግራቸው ይሰማኛል፡፡ ቆየት እያለች ደግሞ ሴቲቱ እምቅ አደርጋ ትስቃለች፡፡
ፊልሙ ተጀመረ፡፡ ደቂቃዎች ተቆጠሩ፡፡ የፊልሙ ጭብጥ ገና ጭራው አልተያዘኝም፡፡ ሰሪ ነን ባዮቹን ለመታዘብ እየዳዳሁ መለስ እያልኩ ደግሞ እኔ ያልገባኝ ነገር ይኖር ይሆን? እያልኩም እየተመራመርኩ ጥቂት ቆየሁ፡፡
ወዲያው እንደኔው ትኬት ቆርጠው በገቡ ተደራሲያን የተዘጋጀ ፤ ሁለት ተዋንያን የተሳተፉበት ፤ ዳይሬክተር የሌለው ፤ ካሜራ ያልተደገነበት ፤ በጀት ያለተመደበለት ፊልም ተጀመረ፡፡ እኔ በተመልካችነት ተሰየምኩ፡፡
ከፊት ለፊቴ የተቀመጡት ጥንዶች ታዳሚውን በተለይ ደግሞ በቅርብ እርቀት ያለሁትን እኔን ከቁብም ሳይቆጥሩ አፍ ለአፍ ገጥመዋል፡፡ የስክሪኑ ብርሃን ሁለመናቸውን ያሳየኛል፡፡
የዚህ ፊልም ጭብጥ እንኳ አልጠፋኝም ግን ደግሞ ሃሳቤን በታተነው፡፡
የአቡጀዲው ፊልም ላይ እንዲህ ወዳለው ስሜት የሚገፋፋ ነገር አላየሁም፡፡ ዋና ገፀ ባህሪው አፈቀርኳት ያላትን ሴት በእጁ ለማስገባት ሲዳክር ከፊት ለፊቴ ያለው አንበሳ ግን እወዳጁ ከንፈር ላይ ጠንጠልጥሏል፡፡ መዳፎቹ መላ አካሏን ያካልላል፡፡ እንደማያባራ ገባኝ እንኳንስ ቀጥሎ አስካሁን ያየሁትም ለወሬ አልመች ብሎኛል፡፡
ጥንዶቹ ነገር አለሙን እረስተዋል፡፡ የስክሪኑ ፊልም ድንገት በፀጥታ የተዋጠ እንደው የጎረቤቶቼ ድምፅ ይቀጥላል፡፡ በትጋት ይሳሳማሉ፤ ይደባበሳሉ፤ ይነካካሉ፤ ያጎነታተላሉ እረፍት የላቸውም፡፡ ወጣቱ ከንፈሩን ከከንፈረሯ ሲያነሳ ወደ ሌሎች የተከለሉ ዞኖች ይሄዳል፡፡
ጭራው አልተያዘኝም ያልኩት ፊልም ከናካቴው ግራ ገብቶኝ ቁጭ አለ፡፡ ወደ 25 ደቂቃዎች አለፈ የአቡጀዲው ግርግር ከተጀመረ፡፡ ስልኬን አወጣሁና ሰዓት አየሁ 3፡15 ይላል፡፡
ከዚህ በላይ በዛ አይነት ሁኔታ ውስጥ መቀመጥ በራስ አናት ጥይት ከመስደድ አይተናነስም፡፡ ኮተቴን ሰብስቤ ውልቅ አልኩ፡፡
በምሽት ፕሮግራም ፊልም ለማየት ስገባ ይህ ሁለተኛ ቀኔ ነው፡፡ አቋርጬ እንድወጣ ስገደድ ደግሞ የመጀመሪያ ነው፡፡የሲኒማ ቤቶቻችን የምሽት ፕሮግራሞች ሁሉ እንዲህ ባለው መዳራት የታጀቡ ናቸው ብሎ ለመደምደም እንደ እኔ የአንድ ቀን ገጠመኝ ሳይሆን እዛ አካባቢ የቅርብ ሰራተኛ መሆን ወይም እንደ ጥናት አድራጊ መለስ ቀለስ ብሎ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ግን ፊልም አዘውታሪ ነኝ ባይ መሰል ገጠመኞችን ሊያካፍለን ይችላል፡፡
ከሲኒማ ቤቶች ጋር በተያያዘ በተለይ የ5 ሰዓት በሚባለው በረፋዱ የፊልም ፕሮግራም ተማሪዎች ከክፍል እየወጡ ከነመለዮአቸው መሽገው እንደሚውሉ ወላጆችም ትምህርት ቤቶችም ቅሬታ ሲያቀርቡ ሰምቻለሁ፡፡ አንድ መንግስት ያሰራው ሰፊ ጥናትም ይህንኑ ጉዳይ እንደችግር አንስቶታል፡፡
መሳሳም በምትለው ስስ ሃሳብ ብዙ ጥንዶች የሲኒማ ቤት ትዝታ ሊኖራቸው እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ አሁን ችግሩ ገዝፎ እና ተለጥጦ እዚህ ደረጃ ደርሷል እኔ እስካየሁት፡፡
ትላንት ብዙ ነውር የምንላቸው ነገሮች አሁን አሁን አደባባይ ተሰጥተዋል፡፡ እመንገድ ላይ ቆመው ፤ መብራት የያዘው ታክሲ እና የግል መኪና ውስጥም አቅላቸውን አስኪስቱ ለፍትወት የሚንገበገቡ ሰዎች ላይ ማፍጠጥ ተመልካቹን ፋራ ያስብለው ይሆናል እንጂ ምንም ሆኗል፡፡
በተለይ ታክሲ ውስጥ የመጨረሻው ወንበር አገልግሎቱ ፈርጀ ብዙ መሆኑን ለማየት ለጥቂት ቀናት ዞር ዞር ማለት እንደው በምንአልባት ባይቀናዎት እንኳ ረዳቶችን መጠየቅ ጉድ ያሰማል፡፡
ከሰሞኑ እንኳ ለ4ት የተቀመጥንበት የታክሲ ወንበር ላይ ጥጉን የያዙት ሁለት ጥንዶች እንዲሁ ሲቃበጡ በአግራሞት ባያቸው በመሃላችን የተቀመጠው አንዱ 'ምነው ጮክ ብለሽ አየሻቸው?' ብሎ ወዲህ አሳፍሮ ዝም አስብሎኛል፡፡
ጉድ ብዬ ቢሮ ይዤ የመጣሁት ወሬ 'የት ከርመሽ ነው?' አስብሎኝ ባልደረቦቼን ብዙ አስፈትፍቷቸዋል፡፡
             
ባልደረባዬ ቴዎድሮስ ወርቁ  እኔ የገጠመኝን ልንገርሽ ብሎ ቀጠለ፡፡
ቴዲ እና ወንድ ጓደኛው ምግብ ፈልገው 'ካፕል ሃውስ' ከሚባሉት ቤቶች ወደ አንዱ ይገባሉ፡፡ እነሱ ከተቀመጡባቸው ወንበሮች ጎን… ፊት ለፊት የተፋጠጡት ለጥንዶች የተዘጋጁት ወንበሮች በመጋረጃ ተጋረደዋል፡፡ መቼም ለምን? አትሉኝም…
ወንበሩ ላይ የተቀመጡት ሰዎች በመጋረጃ ውስጥ ቢሆኑም የእግራቸው እንቅስቃሴ ይታያል፡፡ ለስለስ ብሎ የተጀመረው ጉዳይ የግብግብ ያህል ይጦፋል፡፡ ቆየት ሲል የሲቃ ድምፅ ይሰማ ጀመረ፡፡
ቴዲ እና ጓደኛው ነገሩ 'ፊልም በነፃ' እምንለው አይነት ሆኖባቸው ነገሩን ይከታተላሉ፡፡ የሲቃ ድምፁ እየጨመረ ጭራሽ የወንድየው ሱሪ በእግሮቹ መሃል መሬት ወረደ፡፡ ይህኔ ማናጀር የተባለው ሰው መጥቶ መጋረጃውን ገልጦ ጥንዶቹ ክፍሉን ለቀው እንዲወጡ ይነግራቸዋል… ጎረምሳው ሱሪውን እየታጠቀ 'ወንድ አይደልህ? ምነው ብትታገሰኝ?' ብሎ ሰውየውን ገለማምጦ ሴቲቱን ይዞ ወጣ፡፡
ቴዲ ይህን ካወራኝ ብዙ ሳይቆይ ቦሌ እመንገድ ላይ፤ በጠራራ ፀሃይ ሰው በተሰበሰበት ሁለት ጥንዶች መኪና ውስጥ ወሲብ ሲፈፅሙ መያዛቸውን አየን ከሚሉ ሰዎች የዚያኑ ቀን ሰማን፡፡ አሁን ጉዳዩ በፍርድ ቤት ተይዟል፡፡
ጓዶች ነገሩ እንዴት ነው? ማንስ ይወቀስ? ወላጅ ፤ መንግስት ፤ ማህበረሰብ?
ለምን?
ምንስ መፍትሄስ አለ?
ብዙ ጥያቄ…መልሱን ግን አላውቅም፡፡
በ1950ዎቹ ከተፃፈው የእጓለ ገ/ዮሀንስ አንድ መፅሃፍ ላይ ያነበብኩትን ቃል በቃል ላስቀምጠውና ዞር ልበል፡፡
"በተፈጥሮ ዘይትነት ያለው ዛፍ አለ፡፡ ፍሬ ማፍራት ስለተሳነው ቅርንጫፎቹን ይቆርጧቸዋል፡፡ በነሱ ፈንታ አውለ ገዳም የምድረ በዳ ዛፍ በዘይቱ ግንድ ላይ ተቀጥሎ እንዲያድግ ይተከላል፡፡
ተቀፅላው የስሩ ህይወት ተካፋይ ስለሚሆን ዘይትነትም ያገኛል፡፡ ግን ፈርቶ መኖር አለበት፡፡ በቅርንጫፍነቱ መኩራት አይገባውም፡፡ ምክንያቱም ስር ቅርንጫፍን ይሸከማል እንጂ ቅርንጫፍ ስርን አይሸከምም፡፡
ለእኛ የተፈጥሮ ዘይትነት ያለው ዛፍ የሃገራችን ስልጣኔ ነው፡፡ ተቀፅላው በእሱ ላይ ተጣብቆ የስሩ ዘይት ተካፋይ መሆን አለበት ብቻውን ቢቆም የምድረበዳ ቅጠል ሆኖ ይቀራልና፡፡
….የባህል የኑሮ መልክ የጣእም ህይወት ችግርን የታሪክ ፀሃፊዎች ካልቸር ክራይሲስ ይሉታል፡፡ ሰው ለኑሮ ያለው ጣዕም ይለወጣል፡፡ ለሌላ ነገር ተምኔት ያድርበታል፡፡ አይቶት የማያውቅን ይናፍቃል፡፡ አብዛኛውን ግዜ ሊያገኘው የማይችለውን ይመኛል፡፡ በዚህም ምክንያት ይቸገራል፡፡
የዘመኑ ሰው ከነባሩ የኑሮ እና የሃሳብ ዘዴ ወጥቶ የገዛ ሕሊናው መርምሮ ባስገኘው ህግ ኑሮን ለመምራት ተነሳ፡፡ ከአሮጌው ወጥቶ ወደ አዲሱ ለመዘዋወር አመራ ግን አንዱን ወርውሮ ሁለተኛውን እስኪጨብጥ ባዶ እጁን ነበር፡፡
እዚህ ላይ መንፈስ ይቸገራል፡፡ እንዲህ ያለውን ዘመን ታሪክ ፀሃፊዎች ዘመነ ችግር ብለው ጠርተውታል፡፡
ባልሳሳት በእንዲህ ያለው ዘመን የምንኖር ይመስለኛል፡፡"
ቁልፍ ቃላት
Wed, 08/14/2013 - 11:48