ማስታወቂያ

programs top mid size ad

ቪዛ ከተመታላችሁ ጥገኝነት የምትጠይቁበት ሀገር ወዴት እንዳለ ልጠቁማችሁ

"ቪዛ ከተመታላችሁ ጥገኝነት የምትጠይቁበት ሀገር ወዴት እንዳለ ልጠቁማችሁ"

ኢትዮጵያ 11 በመቶ ማደጓን የምትጠራጠሩ . . .
ብር የመግዛት አቅሟ ተዳክሟል ብላችሁ በ100 ብራችን ላይ "የኛዋ ሁሴን ቦልት" ብላችሁ የቀለዳችሁ
በሃብታም እና ደሃ መሃል ያለው ልዩነት ተንቦረቀቀ ምናምን ያላችሁ

ወደኔ ኑ

የፕሌን ትኬት ሳትቆርጡ. . .
"እኔስ ሃገሬን. . ." መዝፈን ሳይጠበቅባችሁ
የኩበቱ ሽታ ሳይናፍቃችሁ. . .
አማርኛ ሳይጠፋችሁ . . . በ100 ብር ወር የምትኖሩበትን ሃገር ልጠቁማቹ

4 ኪሎ. . . ፓርላማ!

(ሰሞኑን ደግሞ ፓርላማ ፓርላማ ይለኛል ልመረጥ ነው መሰለኝ)

የፓርላማ ካፌን ደጅ መርገጥ እፈልግ ነበር፡፡ አልተመቸኝም፡፡ አመት ሙሉ ስመላለስበት ሻይ እንኳን መጠጣት ሳልችል ቆይቼ ቀኑ ደረሰ እና ባለፈው ገባሁ፡፡

ምን ላድርግ ስብሰባው ተንዛዛ፡፡ እኔ እርቦኛል ከጎኔ ያለው ጋዜጠኛ ወዳጄ "ሃኒ አሁንስ ሞረሞረኝ" ብሎ ወተወተኝ ሰዓቱም ወደ ሰባት እየቆጠረ ነው፡፡ ወተን ሄድን፡፡

የምግብ ሜኑው ካሸሯ መስታዋት ፊት ተለጥፋል፡፡

ሽሮ. . . . . . . . . . . . . . . . . 3 ብር
ሽሮ በቅቤ. . . . . . . . . .. . 4 ብር
ፓስታ 5 ብር ሩዝ. . . . . . 5 ብር
ሚስቶ. . . . . . . . . . . . . . . 8 ብር
ማህበራዊ. . . . . . . . . . . . .8 ብር
ክትፎ አስር ብር እንደሆነ አብሮኝ የነበረው ልጅ ነገሮኛል ግን አላረጋገጥኩም፡፡

ከመስታዋት ግድግዳው ላይ እንዲህ የሚል ማሰታወቂያም ተለጥፏል፡፡
"የዱቄት ዋጋ በመጨመሩ ምክንያት 50 ሳንቲም የነበረው የገብስ ዳቦ አንድ ብር ገብቷል" ይላል፡፡

እናንተ ሰፈር እንኳን የገብስ የስንዴ ዳቦም አንድ ብር በሚባል ዋጋ መሸጥ ካቆመ መቼና መቼ(ደሞስ እጅ አልሞላ ብላ ኡ ኡ ትሉ የለ እንዴ?)

በብዙ የመንግስት መ/ቤቶች በድጎማ ምክንያት የምግብ ዋጋቸው አንድ መንግስት ወደኋላ እንደሆኑ እንሰማለን፡፡ እነዚህ ቤቶች በአብዛኛው ለውጭው ህዝብ መግባት የተከለከሉ ናቸው፡፡
የፓርላማውም ተመሳሳይ ነው፡፡ አንድ ሰሞን ለጋዜጠኞችም ተከልክሏል ተብሎ ሰምቼ ነበር፡፡ እግዱ ተነስቶ ይሁን ተምረን ብቻ እንዴት እንደገባን ግን አልገባኝም፡፡

ባቻ ገባን. . . ዋጋውን እያየሁ ማመን አልቻልኩም፡፡

ውጪ ስንት እየከፈልን እንደምንበላ አስቡ? ሊያውም ጉንጭ አትሞላ ነገር. .. .

አንድ ሚስቶ እና አንድ ማህበራዊ አዘዝን፡፡ እራሳችንን ማስተናገድ ቢጠበቅብንም እጅ ታጥበን እስክንመጣ ምግቡ ጠረጴዛችን ላይ ተቀምጧል፡፡ (እዚህ መራጭ እና ተመራጭ ጥበቃ እና አለቃ እኩል ነው)

እንጀራው ፓ! (ግነት ከመሰላችሁ ምን ላድርግ? አልምል ነገር. . . ፎቶ እንዳላነሳ ስልኬም በእጄ የለ)

ትልቅ ፤እንደናንተ ሰፈሩ የ4 ብር እንጀራ ለመያዝ እስኪያስቸግር ያልሳሳ እና ነጭ እሚያምር እንጀራ ነው፡፡

ሚስቶ የተባለው . . . ቀይ እና አልጫ ስጋ ወጥ አለው(ብዙ የስጋ መረቅ ሳይሆን ብዙ ስጋ ያለው ነው፡፡ ይሔ አዛችሁ ከእንጀራው ስር ውሃ እንደሚያቀረውም እንዳይመስላችሁ)

ማህበራዊው የሌለው ነገር የለም፡፡ ክትፎ ፤ አይብ ፤ ስጋ ወጥ አልጫና ቀይ፤ ጎመን ፤ ምስር ፤ ሩዝ ፤ ፎሰሊያ ፤ ምናምን ምናምን. . .

እኛ ግን ሚስቶውን እንደበላን ጠገብን፡፡

በርግጥ ክትፎ እና አይቡን ከማህበራዊው ላይ አንስተናል፡፡

ስንጨርስ አንድ መግብ ማዘዝ እንዳለብን በቁጭት አወራን፡፡ ምሳችንን ጥርግ አድርገን 16 ብር ከፈልን፡፡ ወጣን፡፡

ስብሰባው ቀጥሏል. . . ሰዎቹ ሚላቀቁም አይመስልም፡፡ ትኩስ ነገር እንውሰድ ተባብለን ወደ አዳራሹ የቀረበ ሌላ ካፌ ገባን ፡፡

አንድ ወተት እና አንድ ሻይ ታዘዘ፡፡ በትልልቅ ማግ መጣልን፡፡ ለሁለቱ 3፡50 ከፈልን፡፡

19.50 አትሉም?

ለዘላለም የጠገብን ያህል ተሰምቶን ወደ ስብሰባው ገባን፡፡ ስራ ቀጠለ. . .

ቪዛ ካገኛችሁ ጥገኝነት ጠይቁ አላልኩም?

እኔም ልጠይቅ አሰብኩ አሰብኩ አሰብኩ እና "ሰው በምግብ ብቻ አይኖርም" የሚል ቃሉን አስታውሼ ወጣሁኝ፡፡

ቁልፍ ቃላት
Wed, 07/02/2014 - 12:41