ማስታወቂያ

programs top mid size ad

ደሞዝ ጭማሪ መጣ ቅንጡ ስልክ ግዙ

በቅርቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ግንባታ በተመለከተ ስራውን የሚሠራው ኤጀንሲ የስራ ሀላፊዎች በዚው በሸገር ሬዲዮ ላይ ቀርበው ሲጠየቁ የሠጡትን ምላሽ ሠምቸዋለው፡፡ ብዙዎቻችሁም ሠምታችሁታል ብዬ አስባለው፡፡ ከተነሱት ሀሳቦች እኔን በበለጠ የሳበኝን አዎ አጥፍቻለው ይቅርታ ማለት ይህን ያክል ተወግዟል እንዴ እንድል ያደረገኝን ጉዳይ ላንሳ፡፡ ቤት ‹‹የራስ ቤት›› ማግኘት ለአዲስ አበባ ህዝብ ምን ማለት እንደሆነ የምናወቀው ነውና ስለዚህ በማወራት ጊዜ ማጥፋት አልፈለኩም፡፡ አሁን አሁን ብዙ ልጆች ሲጫወቱት ባላየውም በፊት ሰኞ ማክሰኞ የሚባለው ጨዋታ ላይ ሰኞ ብለን የምንጠራት ቁራሽ ቦታ ዛሬ በሊዝ ዋጋ 65 ሺህ ብር እና ከዛም በላይ እያወጣች ስለሆነ ቤት መስራት የሚለው ሀሳብ ከብዙዎቻችን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የአጭርም ሆነ የረጅም ጊዜ እቅድ ውጪ ከሆነ ሠነባብቷል፡፡
እናም ቢያንስ የቤትን እድል በጋራ መኖሪያ ቤት ፕሮግራም በኩል ላግኝ በሚል ብዙ ሰው ከሚያገኛት እየሸረፈ ይቆጥባል፡፡ በሰኔ ወር መጨረሻም ቀኑን መናገር ካስፈለገም ሰኔ 29 እጣ ይወጣል፤ ባለ እድል ለመሆንም ተዘጋጁ የሚል ወሬ ተሠማ:: ብዙው ሰውም የተባለውን አመነ፡፡ ግን ቄሱም ዝም መፅሀፏም ዝም ሆነ በምትኩ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ከዚህ ቀደም የወጣውን እጣ የማስተላለፍ ፕሮግራም ተካሄደ፡፡
በጉጉት ቀኑን ሲጠብቅ ከነበረው ሰው ከፊሉ እንዴ መንግስትም እንደ አንዳንድ የግል ቤት እንገነባለን ብለው እንደሸወዱን ግለሰቦች መዋሸት ጀመረ እንዴ ሲል ተጠራጠረ፡፡ የተቀረው ደግሞ ለካ ማስተላለፍ ነው የተባለው በሚል የሰማውን ለማስታወስ በመሞከር የራሱን ጆሮ ተጠራጠረ፡፡እናም በባለፈው ውይይት ላይ ቤት አስተላላፊው መስሪያ ቤት ምነው ቃልህ ዞረ ሲባል እረ አልዞረም ቀድሞም ቢሆን እኮ እኔ አልተናገርኩም የተናገረው የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ፅህፈት ነው አለ፡፡ የግንባታ ፅህፈት ቤቱ ሀላፊም እኔ ስራዬ መገንባት እንጂ በዚህ ቀን በዚያ ቀን የማለትን ስልጣን ማን ሠጥቶኝ እኔ አልተናገርኩም ሲል አስተባበለ፡፡ እነዛ ባለቤት ያደርጉናል ብለን የምንጠብቃቸው ቢሮዎች እንዲህ ነው ብለው መፍትሔ መስጠታቸው ቀርቶ እርስ በእርስ መወነጃጀል ጀመሩ፡፡ ቀድሜ እንዳልኩአችሁ ጉዳዩ ቤት ነው፣ ያሉም አዲስ አበባ ላይ ታዲያ እሺ አንዱ በስተት ያውራ ሌላኛው ሲሰማ አይ ትክክል አይደለም ማለት የለበትም? ከጠፋስ በኋላ ይቅርታ ማለት ማንን ገደለ? መቼም ይህንን ለማድረግ ቢሮው በስራ ተጠምጄ ነው እንደማይል ተስፋ አደርጋለው ምክንያቱም ካልጠፋ ቀን ህዝቡ በሚጠብቅበት ሰሞን የቤት ማስተላለፍ ፕሮግራም አካሂዷልና፡፡
ወደ ሰሞኑ ሌላው ተመሳሳይ ጉዳያችን እንለፍ፡፡ ከዛ በፊት ግን የሰሞኑ የደሞዝ ጭማሪ ተቋዳሽ የሆናችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ ብያለው፡፡ አንድ ወዳጄ ምን እንዳለኝ ታውቃላችሁ፡፡ እንዲህ ነው መገጣጠም ደሞዝ በተጨመረ ማግስት ኢትዮ ቴሌኮም ምንም እንዳልተፈጠረ ቀለል አድርጐ የ4G አገልግሎትን ለማግኘት ስማርት ስልክ ከስማርት ስልክም 5S አይፎንና ጋላክሲ ግዙ አለን፡፡
በአዲሱ የደሞዝ ጭማሪ የምገዛውን አገኘው ነው ያለኝ፡፡... እያነቡ እስክስት ይሎታል ይህ ነው፡፡
ወደ ዋናው ጉዳያችን ስንመለስ ግን ቀድሞ ብዙ ነገር ቃል ተገብቶ ሲያበቃ የተባለው ጊዜ ሲደርስ እኔ አላልኩም አይኔን ግንባር ያርገው የምንባልበት ነገር እየበዛ የመጣ ይመስለኛል፡፡
ልክ እንደ ቤቱ ኢትዮ ቴሌኮምም ያለን ይህንኑ ነው፡፡ ያለፈውን 7 እና 8 ወር ዛሬ ኔትዎርክ አይሠራም ነገ ኢንተርኔት ተቋረጠ ሲባል ይሁን እያለ ሲጠብቅ የነበረው ህዝብ ነገ የሚያገኘውን የተሻለ አገልግሎት ተስፋ በማድረግ ነበር፡፡
ከዛሬ ነገም ስራው አልቆ ETH ከምትለው ፅሁፍ ጐን 4G የምትለውን ፅሁፍ የአዲስ አበባ ህዝብ በተንቀሳቃሽ ስልኩ ሲጠብቅ ኖሯል፡፡
ምክንያቱም ተነግሮታል መንግስት ያለውን አምኑአል፡፡
እናም ሲጠብቅ ከርሞ ትንሽ በመሀከል አገልግሎቱ ሲከፋና ሲጮህ ነገን ለማስተካከል ነው ሲባል እሺ ሲል ሠነበተ፡፡ ይጠናቀቃል ከተባለበት ጊዜ ከ1 ወር በላይ የዘገየው ፕሮጀክት ባለፈው ሳምንት ይፋ ሲደረግ ግን ያልጠበቅነውን ሌላ ነገር ሰማን፡፡
4G (የአራተኛ ትውልድ) ኔትዎርክ ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ ነው የሚሠጠው ይቅርታ የሚሸጠው ተባልን፡፡
በወቅቱ ስራ ሲጀመር አሁን ያለው ኔትዎርክ ያረጀና ያፈጀ ነው በአዲስ እና ዘመናዊ መተካት አለበት አዲስ አበባ የአራተኛውን ትውልድ ኔትዎርክ ያገኛል፤ የክልሎቹም የተሻለ ይሆናል ተባልን፡፡
እንዲያውም በኩራት By the way ይህ ኔትዎርክ በብዙዎቹ ሀገሮች ገና ብርቅ ነው፡፡ በጣም ያደጉ የሚባሉ ሀገሮች የሚጠቀሙበት ነውም ተብለናል፡፡
መቼም አልተባለም የሚል ወገን ይኖራል ብዬ አላስብም ምክንያቱም በየሬዲዬና ቴሌቪዝኑ፣ በየጋዜጦች እና መፅሔቱ ደጋግማችሁ አይታችሁቷል፡፡ ግን ከዚህ ሁሉ ጥበቃ በኋላ 4G ለአራት መቶ ሺህ ሰው ያውም በክፍያ ነው የሚሠጠው ተባለ፡፡ ይህም ቢሆን መቼ እንደሚጀምር ገና አልታወቀም ፕሮጀክቱ ያልቃል ከተባለበት ጊዜ ግን ተጨማሪ ከ1 ወር በላይ እስካሁን ተነስቶለታል፡፡

እናም ስንት የተጓጓለት እና የተጠበቀው ፕሮጀክት እንዲህ ሆኖ ተጠናቀቀ ተባልን፡፡ ቀድሞ እንደተወራው በዚህ አገልግሎት ከቀደሙት ሀገሮች ተርታ ተሠልፋቸዋል እንኳን ደስ ያላችሁ ከአፍሪካ ሀገሮች እስካሁን መስራት የጀመሩት 11 ብቻ ናቸው፡፡ በመጀመር የቀደመችን ደግሞ ደቡብ አፍሪካ ብቻ ነች ተባልን፡፡
ተቋሙ በዚህም አላበቃም በተንቀሳቃሽ ስልካችሁ ከ400 ሺህው ተጠቃሚዎች ውስጥ ለመግባትም ከአይፎን 5S እና ከዛ በላይ ከጋላክሲ S5 እና ከዛ በላይ እንዲሁም ሌሎችም ቅንጡ ስልኮች መያዝ አለባችሁ ብሎን እርፍ አለው ይህ ማለት እጃችሁ ላይ በትንሹ የ15 ሺህ ብር ስልክ ሊኖራችሁ ይገባል ማለት ነው፡፡
ስንት ጠብቆ ሁለት መቶ እና ሶስት መቶ ብር በደሞዙ ላይ ለተጨመረለት፣ ለሌላውም ከመንግስት ስራ ውጪ ላለውና ለሚበዛው ነዋሪም ትርጉሙ የማይመስል ነገር ነው፡፡ ቀድሜ ያነሳውት ወዳጄም እንዲህ ነው መገጣጠም ‹‹ደሞዝ ጭማሪ መጣ ቅንጡ ስልክ ግዙ›› ሲል በኑሮው ላይ የቀለደውም ለዚሁ ነው፡፡ አበቃው፡፡
 
ቁልፍ ቃላት
Tue, 08/12/2014 - 08:32