ማስታወቂያ

programs top mid size ad

ስለ ባንዲራዋ

በአንድ ወቅት ወደ አንዱ የሀገራችን የገጠር አካባቢ ለስራ ጉዳይ በሄድኩኝ ጊዜ ከዋናው መንገድ ዳር በማስታወቂያ ቦርድ ላይ ተፅፎ ያየሁት ነው፡፡ ፅሁፍ ምን ማለት ነው የሚል ስሜትን ፈጥሮብኛል፡፡ መልዕክቱ ‹‹እንኳን አደረሳችሁ ሜዳ ላይ ከመፀዳዳት ነፃ የወጣንበት ክብረ በዓል›› ብሎ ከጐኑ ቀን ከነ ወርና ዓመቱ ተፅፏል፡፡

የአካባቢውን ሰዎች ስለዚህ መልክት ጠየኩኝ ሰዎቹም በኩራትና በራስ መተማመን በፊት እዚህ አካባቢ መፀዳጃ ቤት ብሎ ነገር የለም፡፡ መንገድ ላይ ነበር የምንፀዳዳው አሁን ሁሉም ነገር ተለውጦ እኛም በመፀዳጃ ቤት ብቻ መጠቀም ጀምረናል፡፡ አታያየትም ባንዲራዋን አሉኝ፡፡ ወደተሠቀለው ነጭ አነስተኛ ባንዲራ እየጠቆሙኝ፡፡

በዚህ ቦታ ስለ አካባቢ ፅዳት ለማስተማር የሄዱ ምግባረ ሰናይ ድርጅቶች በየመንገዱ መፀዳዳት ስላለው ችግር ካስተማሩ በኋላ ነዋሪው በየቤቱ መፀዳጃ ቤት እንዲቆፍር እስካሁን የጠፋውንም እንዲያፀዳ ምክር ሰጡት ህዝቡም በሀሳቡ ተስማምቶ ይህንን ማድረግ ጀመረ፡፡ በየአካባቢው የታሠበው መሠራቱ ሲረጋገጥ ነጭ ባንዲራ ይሠቀላል፣ ይህም ማለት መንገድ ላይ ከመፀዳዳት ነፃ ወጥተናል ማለት ነው፡፡ በጐዳናው ላይ የተሠቀለው ማስታወቂያም አካባቢው ሙሉ በሙሉ ነፃ መሆኑን ማረጋገጫ ነው፡፡ እውነት ነው አካባቢውን ላየው ማስታወቂያው ይገባዋል ያስብሏል፡፡ እነዚህን ሰዎች በዛች የገጠር ከተማ ይህንን ማድረጋችሁ ምን ጥቅም አለው ብላችሁ ስትጠይቁአቸው በጤናው በኩል ያለውን ፋይዳ ነግረዋችሁ ሲያበቁ የኛንም አካባቢ እንደ አዲስ አበባ ለማሳመር ነው ይሉአቸዋል፡፡ ይህንን እየሠማው አዲስ አበባን በምናቤ ሳልኩአት በየቦታው የሚፀዳዱባት አፊንጫን የሚበጥስ ሽታ ያላት እንጂ እነሱ የሚሉአትን አዲስ አበባን ማሰብ ተሳነኝ፡፡ እነሱ የሚያውቋት አዲስ አበባ ያቺ በቴሌቪዝን ላይ ያለቸው ነችና አይፈረድባቸውም፡፡ አሁን አሁንማ የአዲስ አበባ የፅዳት ነገር እኮ ጭራሽ እየባሠበት መንገድ ዳር መፀዳዳትም ነውር መሆኑ እየቀረ የመጣ ይመስላል፡፡ በአንድ ወቅት ስለዚሁ በአዲስ አበባ ስለሚታየው በየመንገዱ የመፀዳዳት ችግር ሀሳብ ተነስቶ ከጓደኞቼ ጋር ሳወራ አንደኛው ወገን ህዝቡ እሺ የት ይፀዳዳ የህዝብ መፀዳጃ ቤት በየቦታው የለ የሚል ሀሳብን አነሳ፡፡ ይህ ሀሳብ ሁሌም የሚባል የሚያሳምን ጐን ያለው ቢሆንም ከሁለተኛው ወገን የተነሳው ሌላኛው ሀሳብ ግን የበለጠ አሸንፎኛል፡፡ ትልቁ የኛው የአስተሳሰብ ችግር ነው፡፡

የሰው ልጅ በባህሪው የተለየ ነገር ካልገጠመው በቀር በፕሮግራም መመራት የሚችል ነው፡፡ ጠዋት ከቤታችን ስንወጣ ታጥበን ቁርስ ከአፋችን አድርገን እንደምንወጣው ለመፀዳዳት ቦታ አንሠጥም የትም ይምጣ የትም አስወግደዋለው ብለን ስለምናስብ ለመፀዳዳት የተገደበ ጊዜና ቦታ የለንም ትልቁ ችግራችን ያነው የሚል ነበር ሌላኛው ሀሳብ፡፡ እነዚህ ሀሳቦች እንዳሉ ቢሆኑም ግን ስለ አዲስ አበባ የፅዳት ነገር ስናስብ ብዙ ግራ የሚያጋቡ እንደ ስልጣኔ መለኪያ ተደርገው የሚወሠዱ ግን አሳፋሪ የሆኑ ተግባሮች ይታያሉ፡፡ አሁን አሽከርካሪዎች የትም ቦታ ይሁኑ ጐማቸው ላይ ውሃ ሽንት ይሽኑ ተብሎ የተደነገገ እኮ ነው የሚመስለው፡፡ በቅርቡ መሀል ፒያሳ አያሌው ሙዚቃ ቤት ከተደረደሩ ታክሲዎች የአንደኛው ሹፌር ተሳፋሪን እየጫነ እሱ ግን በበሩ ተከልሎ ጐማው ላይ ውሃ ሽንት ይሸናል፡፡ ይህ መሀል ፒያሳ ላይ ያየውት ነው፡፡ የዚህ ወጣት ሽንት ጐማውን አርሶ በመንገዱ ምፅዋት የሚጠይቁ አዛውንት የዘረጉአት ጨርቅን አቋርጦ ጉዞውን አቅም አጥቶ ፀሀይ ባደረቀው አስፋልት ተመጦ እስኪቆም ቀጠለ፡፡ ሹፌሩም ይቅርታ አላለም፤ ምፅዋት ጠያቄው አዛውንትም ለምን ብለው አልጠየቁም፡፡ እኔም ሆንኩ ሌላው መንገደኛም ምን አይነቱ ነው ከማለት ወጪ ለምን ብለን አልጠየቀንም መልሱ ምን አገባህ መሆኑ ስለሚታወቅ እናም በየጐዳው ሹፌሮቻችን ከመንጃ ፈቃድ ስልጠናው ጋር አብረው የሰለጠኑት ይመስል መኪናቸውን እያቆሙ ጐማቸው ላይ ይሸናሉ፡፡
ከዛ ወጪ ስድስት ኪሎ አካባቢ ነው ምሸት ጓደኛሞች ተሰብስበው ከአንድ አነስተኛ ግሮሰሪ ውስጥ አንድ ሁለት ይላሉ፡፡ የሚገርመው ነገር የሚበዙት ሽንታቸው ቢመጣም የግሮሰሪው መፀዳጃ ቤት ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኖ ቢታይም ከግሮሰሪው እየወጡ ከአስፓልት ዳር ይፀዳዳሉ፡፡ ይህንን እንደ ምሳሌ አነሳው እንጂ በየቦታው ብትሄዱ እንዲህ አይነት ሰዎች ሞልተዋል፡፡ እነዚህን ክፉ ልማዶች ሳስብ ችግሩ በቂ የህዝብ መፀዳጃ ቤት ያለመኖር ብቻ ሳይሆን የኛው አስተሳሰብ ነው ብዬ እንዳስብ ያደርገኛል፡፡ በህንፃ ላይ ህንፃ እየደራረብን አደግን የተለያዩ ዓለም አቀፍ ቢሮዎችን እየጠቀስን የነዚህ ሁሉ መቀመጫ ሆንን እያልን ከመኩራራት በፊት አስተሳሰባችን ላይ ያሉ እንዲህ አይነት ችግሮችን ማረሙን ማስቀደም ያለብን ይመስለኛል፡፡ በቅርቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመፀዳጃ ቤት ቀን ተከብሯል፡፡ በዚህ ቀን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት እንደተናገረው በአሁኑ ጊዜ ከዓለም ህዝብ ከ2 ነጥብ 5 ቢሊየን በላዩ የመፀዳጃ ቤት የለውም፡፡ የአካባቢ ፅዳት ችግርም በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮችን ከ260 ቢሊየን ዶላር በላይ ወይንም ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርታቸው 1 ነጥብ 5 በመቶውን ያክል እንዲያወጡ ያደርጋቸዋል ይላል በእለቱ የቀረበው ሪፖርት፡፡ እንደኔ ይህ ቁጥር የኛን ሀገርም ያጠቃለለ ቢሆንም መፀዳጃ ቤት እያለን እሱን ትተን በየጐዳናው መፀዳዳትናን አማራጭ ያደረግነውን ግን ያካተተ አይመስለኝም፡፡ ወደ ቀደመው ሀሳቤ ልመለስና በዛች የሀሳቤ መነሻ በነበረችው የገጠር መንደር ነጯ ባንዲራ ዝቅ የምትልባት ሲብስም የምትወርድበት አጋጣሚ አለ፡፡ በአካባቢው ከጊዜ በኋላ አልፎ አልፎ ከመንገድ የሚፀዳዳ ከታየ ባንዲራዋ ዝቅ ብላ እንድትውለበለብ ትደረጋለች፡፡

በቶሎ አስተካክሉ አደጋ ውስጥ ናችሁ ማለት ነው ከዛ ከባሰ ግን ባንዲራው እንዲወርድ ይደረጋል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ምንም መሻሻል አልቻላችሁም መልሳችሁ አካቢያችሁን አቆሽሻቹአል የሚል ትርጉም ነው ያለው፡፡ እንዲህ ሲሆን ዳግም ይሠባሰቡና ምንድን ነው የነካን ‹‹እረ በባንዲራው›› ይባባላሉ፡፡ ከዛም ተባብረው ሠርተው ባንዲራዋን መልሠው ያውለበልባሉ፡፡ የዚህች የአነስተኛ ገጠር ነዋሪዎች ልፋታችን ልክ እንደ አዲስ አበባ ውብ ለመሆን ነው ቢሉም እንደኔ ባንዲራዋ የወረደባት የምትመስለው አዲስ አበባ ከነሱ ልትማር የሚገባት ይመስለኛል፡፡ ቢያንስ እንደው ቢያንስ መፀዳጃ ቤት አጠገባችን እያለ እንዳላየና አልፈነው ጐዳና ላይ መፀዳዳትን የምንመርጥ ስልጣኔም የሚመስለን አዲስ አበቤዎች ክፉ አመላችንን እንተው ‹‹በባንዲራዋ ይዣችዋለው››፡፡
ቁልፍ ቃላት
Fri, 12/05/2014 - 11:41