ማስታወቂያ

programs top mid size ad

መታሰር ያስፈራል?

ፍርሀተ- እስርቤት ወይም ፈረንጆቹ ስር የሰደደ፣ ምክንያት አልባ የሚሉት አይነት የመታሰር ፍርሀት(phobia) ገና ህክምናው እውቅና አልሰጠውም፡፡ ነገር ግን ሌሎች ህክምናው ቅጥ የለሽ ፍርሀት (phobia) ናቸው ከሚላቸው ጋር ሊዛመድ ይችላል፡፡ ለምሳሌ Cleithrophobia በተወሰነ ስፍራ ተቆልፎ መቀመጥ የሚፈጥረው የፍርሀት ዓይነት ነው፡፡ Claustrophobia የጠባብ እና የታጠረ ቦታ ፍርሀት ይባላል፤ Isoolophobia- ከሌላው ሰው የመነጠል ፍርሀት ነው፤ Monophobia - ለብቻ የመሆን ፍርሀት ይሉታል፤ Dikephobia ደግሞ ፍትህ የማጣት ፍርሀት ነው፡፡ ጠባብ ቦታ ተቆልፎ መቀመጥ ወይም የመንቀሳቀሻ ቦታ መወሰን፣ ከሚወዷቸው ሰዎች ተነጥሎ መቆየት፣ ለብቻ መሆን እስር ቤት ሰው ላይ የሚፈጥራቸው ገደቦች ናቸው፡፡

ገደቦቹ ደግሞ ለመፈራቱ ከበቂ በላይ ምክንያት ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ እስራትን ወይም ወደ እስር ቤት መላክን ‹የግል ነፃነት የሚቀንሱ እና የሚያሳጡ ቅጣቶች› ይላቸዋል፡፡ ከ ቀናት እስከ 25 ዓመታት የሚደርሱ የእስራት ቅጣቶች አሉ እንደወንጀሉ ዓይነትና ክብደት፡፡ ለመታሰር በህግ ፊት ጥፋተኛ ሆኖ መገኘት፣ ህግን የተላለፈ ወንጀለኛ ሆኖ መገኘት ያስፈልጋል፡፡ ከተራ ማጭበርበር እስከ የሰው ልጅ ህይወት ላይ አደጋ ማድረስ፤ አጥፊ መባል ፤‹ወንጀለኛ› ተበሎ መፈረጅን ይጠይቃል - እስራት፡፡ ወንጀለኛ መባል ማህበራዊ ተቀባይነትን ያሳጣል፡፡ የግል ነፃነትን ይነጥቃል፡፡ ያስፈራል፡፡ አላማውም ዜጎች ህግን እንዳይተላለፉ ማስተማር ነው፡፡ ወይም ማስፈራራት፡፡
የእስር ቤትን ደጃፍ ረግጠው የማያውቁ በርካታ ዜጎች እንዳሉ ሁሉ እስርቤትን ቤታቸው አድርገው የተመላለሱበትም ሞልተዋል፡፡ እንደውም የክረምት ዝናብ እና ብርድ ሽሽት ቀላል ወንጀል ሰርተው እስር ቤት ተጠልለው የሚያሳልፉ ዜጎች እንዳሉም ይወራል፡፡ ከእስር ቤት ውጪ ያለው ምቾት አልባ ህይወታቸው ይልቅ እስር ቤት እንደተሻለ መጠለያቸው የመረጡ አሉ፡፡ አሁን የምናወራው ግን እስር ቤትን እንደጦር እንደ ሲኦል ስለሚፈሩ ዜጎች ነው፡፡ ‹ከእስር ቤት ምኑ ነው የሚያስፈራችሁ?› ሲባሉ የሳቅ እና ስጋት ስሜት ስለሚቀላቅልባቸው፤ ስለሚሸብራቸው ሰዎች፡፡ ልባቸው ስለሚመታ፣እንባቸው ስለሚመጣ፣ ንብረት ልጆቻቸውን አደራ ስለሚሰጡ፣ እንዳላቀላቸው ስለሚቆጥሩ፡፡ አንዳንዶቹ ፍርሀቶች ሰዎች ስለ እስር ቤቶች ካላቸው አስፈሪ ምስል ጋር የተቆራኙ ናቸው፡፡ የጥቂቶቹ ፍርሀት እንዲህ ተሰብስበዋል፡፡
‹ወህኒ ወረደ /ወረደች› መባል
‹ፀጉር መላጨት› ሰው ሲፈረድበት ፀጉሩን ይላጫል የሚል እምነት አለ፡፡ ምን ያህል እውነት እንደሆነ እንጃ!
‹ የሻሞ/የሻማ አምጡ ይባላል፡፡› እስር ቤት ሲገባ የቀደሙ እስረኞች አዲስ ታሳሪዎችን ይጠይቃሉ የሚባል ገንዘብ ነው፡፡ እስር ቤት ውስጥ ገንዘብ አምጡ የሚል ጉልበተኛ እንዲኖር ፣ ወይም የገንዘብ ዝውውር ይፈቀዳል ማለት ነው?
‹ልጅ ሆኜ ሴት የምትታሰር አይመስለኝም ነበር፡፡ ካወቅኩ በኋላ ሴት ታስራ እንዴት ልትኖር እንደምትችል ይጨንቀኛል፡፡› ሴት እና ወንድ በአንድ እስር ቤት አብረው አይኖሩም፡፡ ይሄም የእስሩ ጊዜ በረዘመ ቁጥር የሚፈጥረውን ጭንቀት እና ጉድለት አስቡት፡፡
‹ አሰቃቂ ወንጀል የፈፀሙ ሰዎች መሀል ገብቶ እንዴት ደህንነት ይኖራል?›
‹ ስልክ መደዋወል፣ ኢንተርኔት መጠቀም የለም፡፡ እንዴት ይቻላል፡፡›
‹እዛ ሆኜ ብታመምስ፣ ብሞትስ፣ ጠያቂስ ባይኖረኝ?› በነገራችን ላይ መንግስት እስር ቤቶች ለታሳሪዎች ምቹ እንዲሆኑ የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡ የማሳከም ፣መድሀኒት እንዲያገኙ የማድረግ የመሳሰሉት፡፡ ታሳሪዎች ያቋረጡት ትምህርት ካለ እንዲማሩ ፤ ታሳሪዎች በአቅማቸው ሰርተው የእስር ጊዜአቸውን ሲጨርሱ ራሳቸውንም ማህበረሰባቸውንም እንዲጠቅሙም ይበረታታሉ፡፡ የረቀቀ ወንጀል ተምረው የሚወጡትም እንዳሉ ሆነው፡፡ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ግን እርስዎ ድንገት ‹ሊታሰሩ ነው› ቢባሉ የእስራት ወይም እስር ቤት ምኑ ያስፈራዎታል? ወደ እስር ቤት እያመሩ እንደሆነ ቢገባዎት መጀመሪያ የሚያደርጉት ምንድነው? በዚህ ሳምንት ስድስተኛ ሳምንት ‹ወፌ ቆመች› ድራማ የመታሰር ሀሳብ በአቶ አማረ ቤተሰብ ላይ የፈጠረውን ድራማ በመጠኑ ያገኛሉ፡፡ ቅዳሜ በሸገር ጨዋታ ላይ ከጨዋታ እንግዳ ቀጥሎ ያዳምጡት፡፡ ወይም በሸገር ድረገፅ ላይ በተመችዎ ጊዜ ያዳምጡት፡፡ የክፍል 6 የወፌ ቆመች ድራማ ‹ድንኳን ጣይ እና አስጣይ› በሚል ሳምንታዊ ርዕስ ቀርቦላችኋል፡፡ ድራማውን እያዳመጡ እየተዝናኑ ይወያዩበት፡፡
ቁልፍ ቃላት
Fri, 01/23/2015 - 13:13