ማስታወቂያ

የሸገር ወሬዎቻችን

Sort by
ነባሪ
Post Date
2022-01-22
ሩሲያ ከባባድ ሚሳየሎቿን በኩባ እና በቬኒዙዌላ ለመትከል ማሰቧ ትዝታ አያረጅም ነገር ሆኗል፡፡  አዝማሚያው ዩክሬይንን በተመለከተ የአሜሪካ እና የሩሲያ የጦር አተካሮ ወደ አስፈሪ ደረጃ መሻጋገሩን ያሳያል ተብሏል፡፡ 
2022-01-22
የሱዳን ወታደራዊ መንግስት መሪ ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን 15 አዳዲስ ሚኒስትሮችን ሾሙ፡፡ አዳዲሶቹ ሚኒስትሮች ከባለሙያ ሲቪሎች የተውጣጣ እንደሆነ ዘ ኒው አረብ ፅፏል፡፡ ወታደራዊ መሪው ሲቪል ሚኒስትሮችን የሾሙት ወቅታዊውን የፖለቲካ ቀውስ ለማርገብ አልመው ነው ተብሏል፡፡ የጦር አለቆቹ ባለፈው ጥቅምት ወር ዳግም የመንግስት ግልበጣ ካደረጉ ወዲህ ህዝባዊ ተቃውሞው ያለ ማቋረጥ እንደቀጠለ ነው፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ቀደም ሲል ከጦር አለቆቹ ጋር የደረሱት ስምምነት ስራ ላይ ባለመዋሉ ስልጣን መልቀቃቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡ በሱዳን እየተባባሰ የመጣው ፖለቲካዊ ቀውስ ያለ ሁነኛ መፍትሄ እንዳለ አለ፡፡ እስካሁንም የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ ከ70 በላይ የተቃውሞ ሰልፈኞች መገደላቸው ይነገራል፡፡
2022-01-22
ሳውዲ አረቢያ መራሹ የጦር ጥምረት በየመን የሁቲ ታጣቂዎች ይዞታ የሚፈፅመውን የአየር ድብደባ አክፍቶታል ተባለ፡፡ በሳዳ ግዛት በአንድ እስር ቤት ላይ በፈፀመው ድብደባ በጥቂቱ 70 ሰዎች መገደላቸውን ኒውስ 18 በድረ ገፁ ፅፏል፡፡ በእስረኞች ላይ ሞት እና የአካል ጉዳት ያስከተለውን የሳውዲ መራሹን ጥምረት የአየር ድብደባ የመንግስታቱ ድርጅት በፅኑ ማውገዙ ተሰምቷል፡፡ ሳውዲ መራሹ ጥምረት ከሰንዓ የተባረሩትን የየመኑን ፕሬዝዳንት አብዱራቡ መንሱር አል ሐዲን ወደ መንበራቸው ለመመለስ አል ሁቲዎቹን መውጋት ከጀመረ ወደ 7 ዓመታት ሆኖታል፡፡ ጦርነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰብአዊ ቀውሱን እያባባሰው መምጣቱ ይነገራል፡፡
2022-01-22
የጋና መንግሥት ከትናንት በስቲያ የማዕድን ሥፍራ ፈንጂዎችን በጫነ ተሽከርካሪ ላይ በደረሰ ፍንዳታ የደረሰውን አደጋ ማጣራት ጀምሬያለሁ አለ፡፡ በትናንት በስቲያው ፍንዳታ 17 ሰዎች እንደሞቱ CGTN ፅፏል፡፡ በምዕራባዊ የአገሪቱ ክፍል በደረሰው አደጋ ከሞቱት በተጨማሪ በርካቶች ደግሞ አካላዊ ጉዳት እንደገጠማቸው ታውቋል፡፡ በርካታ ቤቶችም ወድመዋል ተብሏል፡፡ ፍንዳታው የደረሰው የማዕድን ማውጫ ሥፍራ ፈንጂ የያዘው ተሽከርካሪ ከሞተር ብስክሌት ጋር በመጋጨቱ ምክንያት እንደሆነ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡ የጋናው ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ አዶ አደጋውን እጅግ አሰቃቂ እና አሳዛኝ ነው ብለውታል፡፡
2022-01-20
ዓለም አቀፍ ትንታኔ የኮቪድ ወረርሽኝ ከተቀሰቀሰ ወዲህ፣ የዓለማችን 10 ቁንጮ ባለፀጎች በእያንዳንዷ ሴኮንድ 15000 ዶላር፣ ወይም በየቀኑ 1.3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እያገኙ ሀብታቸውን ከእጥፍ በላይ በማሳደግ፣ ድምር ሀብታቸውን ከ700 ቢሊዮን ዶላር ወደ 1.5 ትሪሊዮን ዶላር አሳድገዋል፡፡ የዓለማችን ባለፀጎች ሀብት በዚህ መጠን ሽቅብ ሲመነደግ፣ በተቃራኒው 99 በመቶ የሚሆነው የዓለማችን ሕዝብ ገቢ በወረርሽኙ የመጀመሪያ ሁለት ዓመታት በከፍተኛ ደረጃ ከመቀነሱም በላይ፣ ከ160 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ለድህነት እንደተዳረጉ ኦክስፋም ይፋ ያደረገው ሪፖርት አመልክቷል፡፡
2022-01-20
የዩክሬይን ጦርነት አይቀሬ እየመሰለ ነው፡፡ ብሪታንያ ትናንት በወረራ ስጋት ውስጥ ነች ላለቻት ዩክሬይን የጦር መሳሪያዎችን መላክ መጀመሯን አይ ኒውስ ፅፏል፡፡ ምዕራብ አውሮፓዊቱ አገር ወደ ዩክሬይን ልካቸዋለች ከተባሉት የጦር መሳሪያዎች መካከል ፀረ ታንኮች ይገኙበታል ተብሏል፡፡ ብሪታንያ አስቀድማ ወደ ዩክሬይን በላከቻቸው የጦር መኮንኖቿ አማካይነት በአገሪቱ ወታደሮች ስልጠና እየሰጠች ነው ተብሏል፡፡ የብሪታንያው የመከላከያ ሚኒስትር ቤን ዋለስ ወደ ዩክሬይን የላክናቸው የጦር መሳሪያዎች አገሪቱ ራሷን እንድትከላከል የታለሙ ናቸው ብለዋል፡፡ በዩክሬይ ድንበር ሰፍረዋል ከተባሉት 100,000 የሩሲያ ወታደሮች በተጨማሪ ሌሎች ደግሞ ወደ ቤላሩስ መላካቸው ተሰምቷል፡፡ የዩክሬይኑ የጦር ወሬ እና ፍጥጫ ከምንግዜውም በላይ እየበረታ መምጣቱ ይነገራል፡፡
2022-01-20
ሰሜናዊ ምዕራብ አፍጋኒስታንን የመታው መንታ ርዕደ መሬት በጥቂቱ 26 ሰዎችን መግደሉ ተሰማ፡፡ መንታዎቹ የመሬት መንቀጥቀጦች በርዕደ መሬት መለኪያ (ሬክተር ስኬል) 4.9 እና 5.3 ሆነው እንደተመዘገቡ ዘ ኢኮኖሚክ ታይምስ ፅፏል፡፡ ርዕደ መሬቱ በርካታ ሕንፃዎች እና መኖሪያ ቤቶችን ማፈራረሱ ታውቋል፡፡ ከ700 በላይ ቤቶችም በርዕደ መሬቱ ጉዳት አጋጥሟቸዋል ተብሏል፡፡ የመሬት ነውጡ የገደላቸው ሰዎች ብዛት ከተጠቀሰው በላይ እንደሚያሻቅብ ተገምቷል፡፡ አፍጋኒስታን የመሬት ነውጥ የሚደጋገምባት አገር እንደሆነች መረጃው አስታውሷል፡፡ በርዕደ መሬቱ ከፍተኛ ጉዳት የገጠማት ባዲጊስ የተባለችው ግዛት ነች ተብሏል፡፡
2022-01-20
የሱዳን የፀጥታ ኃይሎች በከፈቱት ተኩስ ከ7 ያላነሱ የተቃውሞ ሰልፈኞች መገደላቸው ተሰማ፡፡ በእርምጃው ከተገደሉት ሌላ ከመቶ በላይ የሚሆኑት ደግሞ አካላዊ ጉዳት እንደገጠማቸው CTV ኒውስ ፅፏል፡፡ የጦር አለቆቹ ዳግም የመንግስት ግልበጣውን ካደረጉ ወዲህ የተቃውሞ ሰልፉ እንደተጋገመ ነው፡፡ ትናንት በመዲናዋ ካርቱም እና በሌሎች ታላላቅ ከተሞች በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተካፈሉበት የጦር አለቆቹን የሚያወግዝ ሰልፍ ተካሂዷል፡፡ የትናንትናው እለት ከቅርብ ጊዜዎቹ ሁሉ በአንድ ቀን በርካታ የተቃውሞ ሰልፈኞች የተገደሉበት ነው ተብሏል፡፡ ሱዳንን ወደተሟላ የሲቪል አስተዳደር ለማሸጋገር ተጀምሮ የነበረው ሂደት የተስተጓጎለ ሲሆን ፖለቲካዊ ቀውስም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ነው፡፡
2022-01-17
አሜሪካ ሩሲያ ዩክሬይንን መውረሯ አይቀርም የሚል ክሷን እያጠናከረችው ነው፡፡ ዋሽንግተን፤ ሩሲያ ዩክሬይንን ለመውረር ሰበባ ሰበቦችን ለመፍጠር እየጣረች ነው ማለቷ ዘ ጋርዲያን ፅፏል፡፡ እንደውም ሩሲያ በጠብ አጫሪነት ልምድ ያካበቱ የጦር ባልደረቦቿን ወደ ምስራቃቂ ዩክሬይን ልካለች ማለቷ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡ ምስራቃዊ ዩክሬይን በአሁኑ ወቅት በትውልደ ሩሲያ አማፂያን እጅ እንደሚገኝ መረጃው አስታውሷል፡፡ በቀጠናው ጦር እና የጦር ወሬው እየበረታ ነው፡፡ ሩሲያ ዩክሬይንን ለመውረር ተሰናድታለች መባሉን በተደጋጋሚ ስታስተባብል ቆይታለች፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ዩክሬይን በሩሲያ የኮምፒዩተር መረጃ ማመሳቀል /የሐኪንግ/ ጥቃት ተፈፅሞብኛል እያለች ነው፡፡ ምዕራባዊያን ዩክሬይንን የኮምፒዩተር መረጃ ማመሳቀሉን ጥቃት ለመከላከል እንረዳሻለን እያሏት ነው፡፡
2022-01-17
በሊቢያ ከ600 በላይ ስደተኞች ተይዘው ታሰሩ፡፡ ስደተኞቹ የታሰሩት አያያዛቸው እንዲሻሻል በአደባባይ ሰልፍ በመጠየቃቸው ምክንያት እንደሆነ ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡ ያካሄዱትም ሰልፍ ፍፁም ሰላማዊ ነበር ተብሏል፡፡ ያም ሆኖ በመቶዎች የሚቆጠሩት ስደተኞች በሊቢያ የፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር በሚገኘው አይን ጋራ የማጎሪያ ማዕከል መታሰራቸው ተሰምቷል፡፡ የለቢያ የፀጥታ ኃይሎች ስደተኞቹን ከማሰር በተጨማሪ ዘግናኝ ድብደባ ፈፅመውባቸዋል ተብሏል፡፡ በአብዛኛው መነሻቸውን ከሰሐራ በስተደቡብ ያደረጉ ስደተኞች አውሮፓ ለመድረስ አልመው ሊቢያ እንደመሸጋገሪያ እየተጠቀሙባት መሆኑ ይታወቃል፡፡