ማስታወቂያ

programs top mid size ad

20 ዓመታት በጨዋታ- የቅዳሜ ጨዋታ ፕሮግራም ሐምሌ 1፣2012 20 ዓመት ሞላው - ሁላችንንም እንኳን ደስ ያለን

የቅዳሜ ጨዋታ ፕሮግራም ሐምሌ 1፣2012 20 ዓመት ሞላው፡፡ የቅዳሜ ጨዋታ አዘጋጆች በወጣትነታቸው በሬዲዮ ፍቅር የተጠመዱበትን የኢትዮጵያ ሬዲዮን የእሁድ ጠዋት ፕሮግራም ለዛን ይዞ፤ ዘመኑ የሚፈልገውን ቃና አክሎበት በ97.1 የFM ሬዲዮ ለ8 ዓመታት፣ በሸገር ሬዲዮ ለ12 ዓመታት ከእናንተ አድማጮቹ ጋር 20 ዓመታት በጨዋታ አሳለፈ፤ ለሸገርም እርሾ ሆኖ ቀጠለ፡፡ ጨዋታ አዲስ ጣዕም ይዞ ሸገርን ወለደ፡፡

የጨዋታ አዘጋጆች የዛሬ 20 ዓመት በአገራችን ሚዲያ ተዘንግቷል ብለው ያሰቡትን ኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ አጋምዶ፣ አዛምዶና አስማምቶ ያኖረውን የኢትዮጵያዊነት መንፈስ በትዝታ ዘአራዳ፣ በእንግዶች ጨዋታ፣ በድራማና የሥነጽሁፍ ትረካ በሙዚቃ አጣፍጦ በጥበብ አሳምሮ ቀጠሮውን ሳያዛንፍ 20 ዓመታት ከአድማጮቹ ጋር ዘለቀ፡፡

ሁላችንንም እንኳን ደስ ያለን፡፡

ሃያ ዓመታት በጨዋታ ሲያልፍ ሁልጊዜም በምቾት አልነበረም፡፡ በሚቀርቡት አንግዶች፣ በታሪክ ትውስታው፣ በአድማጭ መወቀሱ በባለስልጣን መከሰሱ አልቀረም፡፡ ይሄ ይበልጥ ወዳጅነታችንንም ሆነ ተግባራችንን አጠንክሮታል፡፡ የሬዲዮ ባህርይ ከአድማጩ ጋር ሲደሰት እየተደሠተ፣ ሲያዝንና ሲከፋ አብሮ እያዘነ መጓዝ ነውና ጨዋታም ከአድማጮች ስሜት ጋር አብሮ በሃዘንም በደስታም ተጉዟል ብለን አንገምታለን፡፡

የጨዋታ ዝግጅት ፈረንጆቹ Labour of Love የሚሉት ዓይነት ነው፡፡ የሬዲዮ ሥራ በፍቅር የሚሰሩት ሥራ ነውና እኛም ይሄ ብርሃን ዛሬም ከእኛ ጋር ነው ብለን እናምናለን፡፡ ብርሃኑ ሲጠፋ ይታወቃችኋልና፡፡ እንግድነታችሁን፣ ጽሁፋችሁን፣ ሙዚቃችሁን በደግነት ለሠጣችሁን ባለሙያዎች፣ ከእኛ ጋር በጨዋታ ሃያ ዓመታት የዘለቃችሁት አድማጮቻችን፣ በስፖንሰርሺፕ በማስታወቂያ የደገፋችሁን የእናንተ ከእኛ ጋር መቆየት ጉልበት ሆኖን ይሄው ሃያ ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ ከልብ እናመሰግናለን፡፡

ወቅቱ አብሮ በደስታና በፌሽታ ለማሣለፍ አመቺ አለመሆኑ እንጂ በአንድነት ለማክበር ምኞታችን ነበር፡፡ ይሄ ባለመሆኑ ከልብ እያዘንን አንኳን ሃያ ዓመታት በጨዋታ አሣለፍን ለወደፊቱም እንዲሁ አብረን እንድናሳልፍ ይሁን የሚለው ልባዊ ምኞታችን በያላችሁበት ቦታ ይድረሣችሁ፡፡

ቁልፍ ቃላት
ምላሽ