ማስታወቂያ

programs top mid size ad

ታሪክን የኋሊት- ህዳር 14፣2013/ በኢትዮጵያ ታሪክ ብዙ አሰቃቂ የግፍና የግድያ ትውስታዎች ተመዝግበዋል

በኢትዮጵያ ታሪክ ብዙ አሰቃቂ የግፍና የግድያ ትውስታዎች ተመዝግበዋል፡፡ 

ነገር ግን ከዛሬ 46 ዓመታት በፊት የወታደራዊው አስተዳደር ደርግ በንፁሃን ዜጎች ላይ የፈፀመው ግድያ በአስቃቂነቱና በነውረኛነቱ ቀዳሚ ሆኖ ይጠቀሳል፡፡ 

በ1967 ህዳር 14 ቀን ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ አምባገነኑ ወታደራዊ መንግስት 60 የሚሆኑ የቀድሞው መንግስት ባለስልጣኖችንና ወታደራዊ መኰንኖች ያለፍርድ በግፍ ገደላቸው፡፡ 

በጥቂት መኮንኖችና በአብዛኛው የበታች ሹማምንት ስብሰብ የተዋቀረው ወታደራዊ ደርግ በእጃቸው መከላከያ የሌላቸውንና በቁጥጥሩ ስር ያደረጋቸውን ባለስልጣናትና ወታደራዊ መኮንኖችን ገድሎ በቀድሞው የአዲስ አበባ ወህኒ ቤት ግቢ ውስጥ በጅምላ ቀበራቸው፡፡

ወታደራዊ ደርግ የ66ቱን አመፅ በጠለፋና በአዝጋሚ ለውጥ ነጥቆ መስከረም 2 ስልጣኑን ከያዘ በኋላ አብዛኛው ታሪኩ የጭፍጨፋ ነው፡፡ የቀድሞ ኃይለ ስላሴ ባለስልጣኖች በአመፅ ግፊት ምክንያት በወታደሮች ቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡ 

አብዛኛዎቹ ሹማምንት ሃገራቸውን በጠላት ወረራ ጊዜ በአርበኝነት ደማቸውን ያፈሰሱ በዲፕሎማሲ ትግል ለሃገራቸው አንድነት፣ ክብርና ጥቅም የሰጡ፣ በሃገር ውስጥና ዓለም ዓቀፍ ወታደራዊ ተልዕኮ በክብር የተመሰገኑ ነበሩ፡፡ 

በአብዛኛው የመንግስት ፖለቲካ አስተዳደር ምን እንደሆነ ተሳትፎም ግንዛቤም ጨርሶ  ያልነበራቸው የደርግ አባላት “ሕዝብ በድለዋል” እያሉ በግል ስሜታቸው እየተነዱ በጅምላ አሰሩዋቸው፡፡ 

በባለስልጣናቱ ላይ አንዳችም ክስ አልተመሰረተባቸውም፡፡ እነሱው ከሳሽ እነሱው ፈራጅ በሆነው ስልጣናቸው የግድያ ውሳኔ ያሳለፉባቸው  በአንድ ቀን ስምምነት ነበር፡፡

ከደርግ አባላቱ ውሳኔ አንድ ቀን ቀደም ብሎ 53 ሹማምንት እንዲገደሉ በአንደኛ ምክትል ሊቀመንበሩ በሻለቃ መንግስቱ ኃ/ማርያም ፣ ለገዳይ ቡድኑ ኃላፊ ለኮሎኔል ዳንኤል አስፋው ትዕዛዝ ተሰጥቶ እንደነበረም ተረጋግጧል፡፡ 

ሁለት ጠቅላይ ሚኒስትሮችን ጨምሮ ሃገረ ገዥዎች ፣ የጦር ጄኔራሎች፣ ሚኒስትሮች ፣ ገበሬና ወታደሮች ለመገደላቸው የተሰጠው ምክንያት አብዩቱን ለመቀልበስ ይፈልጋሉ፤ ሕዝቡን በድለዋል የሚል ነበር፡፡

አቃቤ ሕግ ፣ ለፍርድ ቤት ባቀረበው ማስረጃ ግን ግድያው እንዲፈፀም የቀደመ ዝግጅት መኖሩን አረጋግጧል፡፡ 

ለሃገራቸው አንዳች የተለየ ተግባር መፈፀማቸው የማይታወቅላቸው የደርግ አባላት ውሳኔውን ሲያሳልፉ፣ የውጭ ጦር ተዋግተው ድል እንዳደረጉ ሁሉ በደስታ እየተፋከሩ እንደነበረ ተመልክቷል፡፡

በደርግ አባሎች በቅርቡ የተፃፉ ፅሁፎች፣ የደርጉ አንደኛም ሊቀመንበር የነበሩት ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ግድያውን እያበረታቱ ተሰብሳቢውን ስሜት ውስጥ ማስገባታቸው ይጠቁማሉ፡፡

ህዳር 14፣1967 ምሽት ላይ አብዛኛዎቹ በእድሚያቸው ከ57 ዓመት በላይ የነበሩት ባለስልጣኖች፣ ከታሰሩበት የቤተመንግስት የምድር ቤት እያወጡ ሁለት ሁለቱን እያቆራኙ አሰሩዋቸው፡፡ 

ከታሰሩበት በሽፍን መኪና ወደወህኒ ቤት ወሰዷቸው፡፡ በወህኒ ቤት ጉድጓድ ተቀፍሮ ጠመንጃ የወደሩ ወታደሮች ይጠባበቃሉ፡፡ በስፍራው እንደደረሱ ከመኪና እያስወረዱ በሩምታ ተኩስ ጨፈጨፏቸው፡፡ ሳይከሰሱ፣ ፍረድ ሳይታይላቸው በግፍ በጥይት ተደበደቡ፡፡ 

ገዳዮቹ የተኮሱትን የጥይት መጠን፣ ያስመዘገቡትን ሰነድ፣ አቃቤ ህግ በማስረጃነት  አቅርቧል፡፡ 

ደርግ፣ የሌተና ጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶምን አስክሬን ጨምሮ የ60ዎቹም አስከክሬን እዚያው ወህኒ ቤት ቀብሮ፣ ዘመድ አስከሬን እንዳይጠይቅ በአዋጅ ከለከለ፡፡ 

በዚህ የግፍ አገዳደልም የሃገር ጭንቅላትና ክብር በአንድ ምሽት ጠፋ፡፡ 

ኢህአዴግ፣ ደርግን አባሮ ስልጣን ከያዘ በኋላ ፣ የተገዳዮቹ ሹማምንት አፅም አስከሬን ከተቀበረበት ወጥቶ በቅድስት ስላሴ ካቴድራል በክብር አርፏል፡፡  በቀብራቸውም ላይ የግፍ አገዳደላቸውን የሚያመለክት ሐውልት ተቀርጿል፡፡ 

በዘር ማጥፋት ወንጀል ፣ የተከሰሱት የደርግ አባላት የሞትና የእስራት ቅጣት እንዲወሰንባቸው ካደረጉት ወንጀሎች አንደኛው ይኸው የህዳር 14 ጭፍጨፋ ነው።

ቁልፍ ቃላት
ምላሽ