ማስታወቂያ

programs top mid size ad

ታሪክን የኋሊት-ሐምሌ 7፣2013-“ጨለማው ሐምሌ ሰባት”

የዛሬው ቀን “ጨለማው ሐምሌ ሰባት” የሚል ስያሜ ወጥቶለታል፡፡

ስያሜው የወጣለት ፣ የዛሬ 42 አመት ፣ በዛሬው ቀን የኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክን ፣ የመካነ የኢየሱስን ቤተ ክርስቲያን ሀላፊንና ባለስልጣኖችን ፣ ወታደራዊው ደርግ በግፍ የገደለበት ቀን በመሆኑ ነው፡፡

ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ፣ ለአምስት አመታት አስሩዋቸው ፣ በእጁ ይዟቸው የቆዩትንና ፣ ጉዳት ሊያደርሱበት የማይችሉትን እስረኞች ፣ ገድሎ በጊዜው ባልታወቀ ስፍራ ቀበራቸው፡፡

በኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም  የሚመራው ወታደራዊ ደርግ  ፣ ሐምሌ 7 ቀን 1971 የሃይማኖት መሪዎቹን ብፅዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ፣ ርዕሰ ሊቃ ጳጳሳትና ፓትሪያርክ  ፣ ቄስ ጉዲና ቱምሳ የመካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ሀላፊ ፣ ከሌሎች ጋር ፣ ከእስር ቤት አውጥቶ ገደላቸው፡፡

ከነርሱም ጋር ፣ የንጉሡ የግቢ ሚኒስትር የነበሩት ፣ የ80 አመቱ አዛውንት ፣ ፀሐፊ ትዕዛዝ ተፈራወርቅ ኪዳነወልድ ፣ የትምህርት ሚኒስትር አቶ ሰይፉ ማህተመስላሴ፣ የቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ፕሬዝዳንት ደጃዝማች ካሳ ወልደማርያምና ሌሎች ሶስት ባለስልጣኖች ነበሩ፡፡

ደርግ በጊዜው ከአምስት አመታት እስር ቆይታ በኋላ ፣ለምን እንደገደላቸው ብቻ ሳይሆን ፣ መገደላቸውንም አላሳወቀም ነበር፡፡በኋላ እንደተረጋገጠው ፣ ወታደራዊ ደርግ ፣ የገደላቸውና የቀበራቸው በሰሜን አዲስ አበባ በሚገኘው የራስ አስራት ግቢ ነበር፡፡

ብፅዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሁለተኛው ፓትርያክ ሆነው ከመመረጣቸው በፊት ፣ የፓትርያልክ ፣ ብፅዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዩስ እንደራሴ ሆነው ሰርተዋል፡፡ የሐረር ሊቀጳጳስም ነበሩ፡፡

በዘመናዊ ትምህርት ጭምር ፣ የጠለቀ እውቀት እንዳለቸው የሚታወቅላቸው አቡነ ቴዎፍሎስ ፣ ደርግ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን መብት ለመዳፈር የሚያደርገውን እርምጃ አልተቀበሉም ነበር፡፡

ስልጣናቸው የሆነውን ጳጳሳት መሾም እንዳይችሉ ፣ ባዋቀራቸው በኮሚቴዎች በኩል አዘዛቸው ርሳቸው ግን “ በእኔ ጊዜ የቤተክርስቲያኗ ክብር አይደፈረም” ብለው ጳጳሳት ሾሙ፡፡ ብዙም ሳይቆይ እርሳቸውም የሾሟቸው ሶስቱንም ጳጳሳት አስሮ አቆያቸው፡፡

ቄስ ጉዲና ቱምሣ ፣ የፕሮቴስታንት ክርስቲያኖች ማህበርን በመምራት ላይ ነበሩ፡፡

ሃኃማኖትን ማዳከም እንደ አንድ ግቡ ያደረገው ደርግ ፣ ከስራቸው አስነስቶ ፣ ለጥቂት ጊዜ አስሮ ከፓትሪያርኩ ጋር ገድሎ ቀብሩዋቸዋል፡፡

ሌሎች አብረው የተገደሉት የአፄ ኃ/ሥላሴ ባለስልጣናትም ለአምስት አመት በእስር የቆዩ ናቸው፡፡ ደርግ ከስልጣን ከተባረረ በኋላ ፣ የሁሉም አስከሬን በድብቅ ከተቀበረበት ፣ ከራስ አስራተ ካሳ ግቢ ወጥቶ ፣ እንደየእምነታቸው በክብር አርፏል፡፡

ቁልፍ ቃላት
ምላሽ