ማስታወቂያ

programs top mid size ad

መስከረም 4፣ 2014- ዕድሜያቸው ከ21 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች እና ህፃናት በስፖርት ውርርድ ጨዋታዎች እንዳይሳተፉ የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ከለከለ

ዕድሜያቸው ከ21 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች እና ህፃናት በስፖርት ውርርድ ጨዋታዎች እንዳይሳተፉ የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ከለከለ። 

አስተዳደሩ የስፖርት ውርርድ ጨዋታዎችን አስመልክቶ ያሻሻለውን መመሪያ ተግባራዊ ሊያደርግ መሆኑን ተናግሯል። 

የስፖርት ውርርድ ጨዋታ ጥብቅ በሆነ ህግ እና ስርዓት መመራት ይገባዋል ያለው የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ለቁጥጥ ያግዘኛል ያለውን የተሻሻለውን መመሪያ ቁጥር 172/2013 ይፋ አድርጓል።  

መመሪያው ከዚህ ቀደም ከ18 ዓመት በላይ የነበረውን በስፖርት ውርርድ የመሳተፊያ የዕድሜ ገደብ ወደ 21 ዓመት ከፍ አድርጎታል። 

ዕድሜያቸው ከ21 ዓመት በላይ ሆኖ ዩኒፎርም የለበሱ ተማሪዎች በምንም ሁኔታ በስፖርት ውርርድ ቤቶች መገኘት አይችሉምም ተብሏል። 

ይህን መመሪያ ጥሰው የሚገኙ አወራራጆች በቀጥታ ከስራቸው እንደሚታገዱ የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ገረመው ጋርጄ ተናግረዋል።  

በሌላ በኩል የስፖርት ውርርድ ቤቶቹ ከትምህርት፣ ከጤና እና ከእምነት ተቋማት ቢያንስ በ 5 መቶ ሜትር እንዲርቁ በመመሪያው ተደንግጓል። 

የሽልማት ጣሪያቸውም በ 1 ሚሊዮን ብር ተገድቧል። 

የስፖርት አወራራጅ ድርጀቶች ፈቃዳቸውን ለማደስ ይከፍሉ የነበረው 200 ብር ወደ 100,000 ብር ከፍ ማለቱም ተነግሯል። 

የስፖርት ውርርድ ጨዋታዎች ወጣቶችን ወደ ቁማር ሱስ እንዲሳሳ፤ ሳይሰሩ ገንዘብ ለማግኘትም እንዲጓጉ በማድረግ በርካታ ማህበራዊ ቀውስ እያስከተሉ ነውና ለምን ማስቆም አልተቻለም በሚል ከጋዜጠኞች ለተነሳው ጥያቄ  አስተዳደሩ የችግሩን ስፋት ለማወቅ ጥናት ማስጠናቱን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። 

የስፖርት ውርርድ ሙሉ በሙሉ ጎጂ ነው ማለት ስለማይቻል ጉዳቱን ቀንሰን ጥቅሙን የምናሳድግበት መንገድም በጥናቱ ተካቷል በለዋል።  

በመንግሥት ዩንቨርስቲዎች ተደርጓል የተባለው ይኸው ጥናት ለሚመለከታቸው የመንግሥት መስሪያ ቤቶች መላኩንም አቶ ገረመው ተናግረዋል።

ቁልፍ ቃላት
ምላሽ