ማስታወቂያ

programs top mid size ad

ታሪክን የኋሊት፣ጷግሜ 3፣2008

የቴክሳሷን ግላቬስቶን ከተማና አካባቢዋን የመታው አውሎ ነፋስ

አሜሪካ በየዘመኑ በየጊዜው የተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎችን አስተናግዳለች፡፡

ስምና ዓይነታቸው የበዛ የአውሎ ነፋስ አደጋዎችም ተፈራርቀውባታል፡፡

በአሜሪካ ታሪክ እጅግ አስከፊ አደጋ አስከትሏል የሚባለው የቴክሳስ ግላቬስቶኑ የአውሎ ነፋስ አደጋ የደረሰው የዛሬ 116 ዓመት በዛሬዋ ዕለት ነበር፡፡

በ19ኛው ምዕተ ዓመት የቴክሳሷ ግላቬስቶን የአሜሪካ አብይዋ የንግድ ማቀለጣጠፊያ ማዕከል ነበረች፡፡

በዘመኑ ከአገሪቱ አብይ አብይ ወደቦችም አንዷ የመሆን ክብር ያገኘች ነበረች፡፡

በወቅቱ የቴክሳሷን ግላቬስቶን ከተማና አካባቢዋን የመታው አውሎ ነፋስ መነሻውን ከምዕራብ አፍሪካ ዳርቻ ከኬፕቬርዴ ያደረገ ነው ይባላል፡፡ ግምቱ ወደዚህ ያዘነብላል፡፡

ግላቬስቶን ከመድረሱ ከሳምንት በፊት መነሻውን የምዕራብ አፍሪካ ዳርቻ ያደረገው አውሎ ነፋስ የአትላንቲክ ውቅያኖስን ተመዝግዝጐ በማቋረጥ የካሪቢያኗን ደሴት ኩባን ደቡባዊ ምዕራብ መትቶ ወደ ፍሎሪዳ የባሕር ሰርፅ አለፈ፡፡

በዚህ ብቻ አልተገታም የመምዘግዘግና የጥፋት አቅሙም ፍጥነቱም ጨምሮ የሉዊዚያናና የሚሲሲፒን የባሕር ዳርቻዎች አዳረሰ፡፡

ኒው ኦርሊያንስን ሲያቋርጣት በሰዓት 160 ኪሎ ሜትር በሆነ ፍጥነት ሲሰግር የነበረው አውሎ ነፋስ ግላቬስቶንን ሲመታት ፍጥነቱ በሰዓት 233 ኪሎ ሜትር ደረሰ

አውሎ ነፋሱ የዛሬ 116 ዓመት በዛሬዋ ዕለት የመኖሪያ ቤቶችን ፍርስራሽ እንደ ወረቀት ያገለበልባቸው ያዘ፡፡

ዛፎችን ከነ ሥራቸው እየነቀለ ተሸክሞ ሮጠ፡፡

 

ድልድዮችና ትላልቅ ሕንፃዎችን ደረማመሳቸው፡፡ የኤሌክትሪክና የቴሌግራፍ መሥመሮችን ምንቅርቅራቸውን አወጣው፡፡

ከተማይቱን ወደ ፍርስራሽ ክምርነት ለወጣት፡፡ ብርቱው አውሎ ነፋስ ከ8 ሺህ በላይ ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉ ይነገርለታል፡፡

የሟቾቹ ብዛት ስምንት ሺህ ብቻ አይጠቅመውም የሚሉ ሰነዶች፤ አውሎ ነፋሱ የገደላቸውን ሰዎች ቁጥር ወደ 12 ሺህ ከፍ ያደርጉታል፡፡

የአሜሪካን ግዛቶች በመቱ አውሎ ነፋሶች ታሪክ ከፍተኛው ጨራሽም ፣ ደምሳሽም ተደርጐ ይቆጠራል፡፡

ያስከተለው የንብረት ጥፋትና የቁሳቁስ ውድመት፤ ከ6 ዓመት በፊት በነበረው የምንዛሪ አቅም ከ104 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተገምቷል፡፡

ጥፋትም ቢሆን የታሪክ አካል ነውና ከተማይቱ ታላቁ አውሎ ነፋስ የሚል ስያሜ የተሰጠው ቤተ መዘክር አቋቁማ ይኸው ይሄንንም አልፌያለሁ እያለች ነው፡፡

የኔነህ ከበደ

ቁልፍ ቃላት
ምላሽ