ማስታወቂያ

የሸገር ወሬዎቻችን

Sort by
ነባሪ
Post Date
2021-05-14
የእስራኤል ጦር ከባባድ የጦር መሳሪያዎችን እና ብዛት ያላቸው ወታደሮችን ጋዛ ሰርፅ ወሰን እያሰፈረ ነው፡፡ ይህም የእስራኤል ጦር በሰርፁ ከአየር እና ከሚሳየሎች ጥቃት በተጨማሪ በምድር ሀይል መጠነ ሰፊ ዘመቻ የማካሄድ እድቅ ሳይኖረው እንደማይቀር ግምት ማሳደሩን ቢቢሲ ፅፏል፡፡ ሐማስ ወደ እስራኤል ሮኬቶችን መተኮስ እንደቀጠለ ነው ተብሏል፡፡ የእስራኤልም የአየር እና የሚሳየል ጥቃት አላቋረጠም፡፡ በጋዛ በጥቃቱ የተገደሉት ፍልስጤማውያን ብዛት ወደ 103 አሻቅቧል፡፡ አረቦች እና አይሁዶች መሳ ለመሳ በሚኖሩባቸው የእስራኤል ከተሞችም እዚህም እዚያም ግጭቶች መፈጠራቸው በመረጃው ተጠቅሷል፡፡ በዚሁ የተነሳም ከ400 በላይ ሰዎች ተይዘው መታሰራቸው ተሰምቷል፡፡ እስራኤል በጋዛ ድንበር ሀይል ከማከማቸት በተጨማሪ ከ7000 የማያንሱ ተጠባባቂ ወታደሮቿን መጥራቷ ታውቋል፡፡ ሐማስ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ፍላጎት ቢያሳይም የእስራኤል ሹሞች ግን የተኩስ አቁም እንደማይኖር ተናግረዋል፡፡ ጦርነቱ እንዲቆም አለም አቀፍ ተማፅዕኖው መበርታቱ ተጨማሪ ያንብቡ
2021-05-14
በሕንድ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የጨረሳቸው ሰዎች ብዛት የሩብ ሚሊዮንን ወሰን አለፈ፡፡ በአገሪቱ በኮሮና ቫይረሱ የሚያዙ እና በበሽታው የሚሞቱ ሰዎች ብዛት በፍጥነት እያሻቀበ መምጣቱን ዩሮ ኒውስ ጽፏል፡፡ ካለፈው የካቲት ወር አንስቶ የወረርሽኙ ጥፋት እየተባባሰ መምጣቱን መረጃው አስታውሷል፡፡ የወረርሽኙ ከቁጥጥር ውጭ መሆን የአገሪቱን የጤና ሥርዓት በእጅጉ እየፈተነው ተብሏል፡፡ የእስትንፋስ መደገፊያ (ኦክስጂን) እና የሆስፒታል አልጋዎች እጥረቱ ለአገሪቱ ራስ ምታት ከሆነባት መሰንበቱ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡  
2021-05-12
በሱዳኗ ርዕሰ ከተማ ካርቱም ለተቃውሞ አደባባይ ከወጡት መካከል ሁለቱ በፀጥታ ሀይሎች ተተኩሶባቸው መገደላቸው ተሰማ፡፡ ሰልፈኞቹ አደባባይ የወጡት ከ2 አመታት በፊት በዛው ለተቃውሞ ሰፍረው በነበረ ሰልፈኞች ላይ በፀጥታ ሀይሎች በተወሰደ እርምጃ ያለቁትን ሰዎች ለመዘከር እንደሆነ አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡ የአሁኖቹ ሰልፈኞች አደባባይ የወጡት ያን ጊዜ ላለቁት ሰልፈኞች ፍትህ ለመጠየቅ ጭምር ነው ተብሏል፡፡ ሰልፈኞቹ ከ2 ዓመታት በፊት በሰልፈኞች ላይ እልቂት የፈፀሙት ተጠያቂ ይሁኑልን ማለታቸው ተሰምቷል፡፡ ይሁንና ምላሹ ጥይት እና አስለቃሽ ጋዝ እንደሆነባቸው በመረጃው ተጠቅሷል፡፡ በአሁኑ የፀጥታ ሀይሎች እርምጃ ከተገደሉት ሌላ 15 ያህሉ ደግሞ አካላዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል፡፡  ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ በሰልፈኞች ላይ ጥይት መተኮስ ተቀባይነት የሌለውና በሕግ የሚያስጠይቅ ወንጀል ነው ማለታቸው ደግሞ ቢቢሲ ፅፏፏል፡፡
2021-05-12
በሕንድ ጋንጄስ ወንዝ የታችኛው ተፋሰስ የሚገኘው የሰዎች አስከሬን ብዛት እየጨመረ መምጣቱ ተሰማ፡፡ ባለፉት ጥቂት ቀናት በወንዙ የታችኛው ተፋሰስ የ50 ሰዎች አስከሬን እንደተገኘ ቢቢሲ ፅፏል፡፡ እንደውም አንዳንድ የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ከወንዙ የወጣውን አስከሬን ብዛት ወደ 100 ያደርሱታል፡፡ ክስተቱ ግራ አጋቢ ሆኗል፤ ምክንያቱም አልታወቀም፡፡ አስከሬኑ ምናልባትም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የሞቱ ሰዎች ሳይሆን እንዳልቀረ ተገምቷል፡፡ በሕንድ ሰሞኑን በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ እና የሚሞቱ ሰዎች ብዛት እየጨመረ መምጣቱን መረጃው አስታውሷል፡፡ በአገሪቱ እስካሁን በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ብዛት ከ22 ሚሊዮን በላይ ሲደርስ 250,000 ያህል ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል፡፡
2021-05-11
ቱርክ ዳግም ከሳውዲ አረቢያ ጋረ እየተቀራረበች ነው ተባለ፡፡ የቱርኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቩ ሶግሉ ለይፋዊ ጉብኝት ሳውዲ አረቢያ መግባታቸውን ሬውተርስ ፅፏል፡፡ ሁለቱ አገሮች በተለያዩ ጉዳዮች ሲወዛገቡ እና ክፉ ደግ ሲነጋገሩ መቆየታቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡ እነ ሳውዲ አረቢያ ካታርን አግልለው በነበረበት ወቅት ቱርክ የዶሃ አለሁልሽ ባይ ነበረች፡፡ ጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ በቱርክ ኢስታምቡል በሚገኝ የሳውዲ ኤምባሲ በተገደለበት ወቅት የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ታይፕ ኤርዶአን ደግመው ደጋግመው ግድያው የታዘዘው በሳውዲ አረቢያ ከፍተኛ የስልጣን አካል ነው ማለታቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡ ሳውዲ አረቢያ ከቱርክ አጥቂ ሰው አልባ በራሪ አካላት (ድሮኖችን) ለመግዛት መፈለጓ ለሁለቱ አገሮች ዳግም መቀራረብ አንዱ ምክንያት ነው እየተባለ ነው፡፡
2021-05-11
በሩሲያ ካዛን ከተማ በአንድ ትምህርት ቤት በተከፈተ የእሩምታ ተኩስ 8 ሰዎች መገደላቸው ተሰማ፡፡ ከተገደሉት መካከል 7ቱ ሕፃናት ተማሪዎች እንደሆኑ ቢቢሲ አውርቷል፡፡ አንድ መምህርም እንደተገደለ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡ ከተኩስ በተጨማሪ በአካባቢው የፈንጂ ድምፅ መሰማቱ ተነግሯል፡፡ የእሩምታ ተኩሱን የከፈቱት ሁለት ሰዎች ናቸው ቢባሉም የፀጥታ ሀይሎች አንድን የ17 አመት ወጣት ተጠርጣሪን መያዛቸው ተሰምቷል፡፡ ጥቃቱ በምን ምክንያት እንደተፈፀመ የታወቀ ነገር የለም፡፡
2021-05-07
ሶማሊያ ከጎረቤት ኬንያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቴን አድሻለሁ አለች፡፡ ቀደም ሲል አገሪቱ ከኬንያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ያቋረጠችው ናይሮቢ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገባች አስቸግራኛለች በሚል እንደነበር ቢቢሲ አስታውሷል፡፡ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ወሰድ መለስ የሚበዛ ነው ተብሏል፡፡ ኬንያ እና ሶማሊያ በውቅያኖስ ዳርቻ የውሃ አካል ይገባኛል እየተወዛገቡ ነው፡፡ ሁለቱ አገሮች ሚወዛገቡበትና ከ100,000 ካሬ ኪሎ ሜትር የማያንስ የውቅያኖስ አካል የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ መገኛ መሆኑ ይነገራል፡፡ ኬንያ በደቡባዊ ሶማሊያ የአልሸባብ ፅንፈኛ ቡድንን ተፅዕኖ ለመገደብ በአፍሪካ ህብረት ሰራዊት (አሚሶም) ዕዝ ስር 4000 ወታደሮች እንዳሏት በመረጃው ተጠቅሷል፡፡  
2021-05-07
በየመን የደረሰ የጎርፍ መጠነ ሰፊ ሰብአዊ ቀውስ እና ቁሳዊ ውድመት እያደረሰ ነው ተባለ፡፡ ብዛታቸው በአሃዝ ባይጠቀስም በደፈናው በርካታ ሰዎች በጎርፍ አደጋው ለሞት እና ለአካል ጉድለት መዳረጋቸውን የተባበሩት መንግሥታትን የጠቀሰው ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡ ባለፉት ጥቂት ቀናት ሲጥል የነበረው ዶፍ ዝናብ በበርካታ ከተሞች መሰረተ ልማቶች እና ቤቶችን ማፈራረሱ ተሰምቷል፡፡ ኤደን፣ አብያን፣ ማሪብ እና ታይዝ በጎርፉ ከፍተኛ ጉዳት ከገጠማቸው ከተሞች መካከል ናቸው፡፡ ታሪካዊ ፋይዳቸው የጎላ ቅርሶችም ከፍተኛ ጉዳት አጋጥሟቸዋል ተብሏል፡፡ የመን ከ6 ዓመታት በላይ በውስብስብ ጦርነት ውስጥ እንደሆነች መረጃው አስታውሷል፡፡  
2021-05-06
በካናዳ እድሜያቸው ከ12 እስከ 15 የሆነ አዳጊዎች የፋይዘር ባዮንቴክ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ሊከተቡ ነው፡፡ አዳጊዎቹ እንዲከተቡ በጤና ሹሞች መወሰኑን አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡ ቀደም ሲል እንዲከተቡ የተወሰነው እድሜያቸው 16 እና ከዛም በላይ የሆናቸው እንደነበሩ መረጃው አስታውሷል፡፡ የአሜሪካ የምግብ እና የመድሃኒት መቆጣጠሪያ መስሪያ ቤትም የካናዳን ፈለግ ሊከተል እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ቀደም ሲል ፋይዘር እድሜያቸው ከ12 እስከ 15 በሆነ አዳጊዎች ላይ ክትባቱን መሞከሩ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡ በሙከራውም ክትባቱ ውጤታማነት እና ደህንነቱ ተረጋግጧል ተብሏል፡፡  
2021-05-06
የዚምባብዌ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት (ሴኔት) መንግሥታዊ ማሻሻያ አደረገ፡፡ የተሻሻለው ሕገ-መንግሥት ፕሬዝዳንቱ ዳኞችን እንዲሾሙ ይፈቅዳል መባሉን ቢቢሲ ፅፏል፡፡ በምርጫ ወቅት ፕሬዝዳንታዊ እጩዎች ተጣማሪ ምክትል ፕሬዝዳንት ይዘው እንዲቀርቡ የሚጠይቀውም አንቀፅ እንዲቀር ተደርጓል ተብሏል፡፡ የተሻሻለው ሕገ-መንግሥት 60 ሴቶች በየምርጫ ክልሉ ከሚደረገው ፉክክር ውጭ በኮታ ፓርላማ እንዲገቡ የሚፈቅድ እንደሆነ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡ ወጣቶችም በፓርላማው 10 መቀመጫዎችን ያገኛሉ ተብሏል፡፡ የፍትህ ሚኒስትሩ ዚያምቢ ዚያምቢ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያውን ታሪካዊ ሲሉ ጠርተውታል፡፡