top of page

ሚያዝያ 11፣2016 - የባህር ማዶ ወሬዎች

 

የፍልስጤም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሙሉ አባል አገር የመሆን ሕልም ተጨናገፈ፡፡

 

ፍልስጤምን የተባበሩት መንግስታት ሙሉ አባል ማድረጊያ የውሳኔ ሀሳብ ትናንት ለፀጥታው ምክር ቤት ቀርቦ እንደነበር አናዶሉ ፅፏል፡፡

 

የውሳኔ ሀሳቡ በምክር ቤቱ 12 አባል አገሮች ቢደገፍም አሜሪካ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብቷን ተጠቅማ ውድቅ አድርጋዋለች ተብሏል፡፡

 

በጉዳዩ ላይ ብሪታንያ እና ሲዊዘርላንድ ድምፀ ተአቅቦ ማድረጋቸው ታውቋል፡፡

 

አሜሪካ ከዚህ ቀደምም በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ለፀጥታው ምክር ቤት የቀረቡ የውሳኔ ሀሳቦችን ድምፅን በድምፅ የመሻር መብቷን ተጠቅማ በተደጋጋሚ ውድቅ ማድረጓ ለትውስታ ተነስቷል፡፡

 

ፍልስጤም አሁን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያላት ቦታ በጠቅላላ ጉባኤው የታዛቢነት ብቻ እንደሆነ ዘገባው አስታውሷል፡፡

 

እስራኤል በኢራን ኢስፍሐን ከተማ ድንገት ደራሽ የሚሳየል ጥቃት ሳትፈፅም አልቀረችም ተባለ፡፡

 

በከተማዋ ማለዳውን ከባድ ፍንዳታ መሰማቱን ታይምስ ኦፍ ኢስራኤል ፅፏል፡፡

 

ቢቢሲ እንደፃፈው ደግሞ የእስራኤል ሚሳየል ኢራንን መምታቱን ሁለት የአሜሪካ መንግስት ሹሞች ጭምር አረጋግጠዋል፡፡

 

በሚሳየል ጥቃቱ ስለደረሰ ጉዳት በዝርዝር የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡

 

በብዙ የኢራን ከተሞች የአውሮፕላን በረራዎች መታገዳቸው ታውቋል፡፡

 

ኢስፍሐን የኢራን የኒኩሊየር ማብለያ የሚገኝበት ስፍራ እንደሆነ ይነገራል፡፡

 

ኢራንም ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ሌሊት በእስራኤል ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሚሳየሎችን መተኮሷን ዘገባው አስታውሷል፡፡

 

የኢራን ጥቃት በሰው አልባ በራሪ አካላት ድሮኖችም የታገዘ እንደነበር ዘገባው አስታውሷል፡፡

 

ይሄን ተከትሎም እስራኤል ኢራንን መበቀሌ አይቀርም በሚል ስትዝት ሰንብታለች፡፡

 

የኢራን መገናኛ ብዙሃን ደግሞ ወደ ኢራን የተሰደዱ 3 ሰው አልባ በራሪ አካላት(ድሮኖች) በአየር መቃወሚያ ተመትተው መምከናቸውን እየዘገቡ ነው፡፡

 

የጦር ሹሞችም በኢአስፍሃን ያጋጠመን አንዳችም ጉዳት የለም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡

 

ከእስራኤል መንግስትም ሆነ ከአሜሪካው የመከላከያ መስሪያ ቤት ፔንታገን በይፋ የተባለ ነገር የለም፡፡

 

 

የየመን ሁቲዎች የጋዛው የእስራኤል ዘመቻ እስካልቆመ ድረስ በቀይ ባህር በሚተላለፉ የእስራኤል፣ የአሜሪካ እና የብሪታንያ መርከቦች ላይ ጥቃት ማድረሳችንን በጭራሽ አናቆምም አሉ፡፡

 

ሁቲዎቹ በቀይ ባህር ተላላፊ መርከቦች ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ ወራት አስቆጥረዋል፡፡

 

አሜሪካ እና ብሪታንያ ሁቲዎቹን ከጥቃት አድራሽነት እናቅባለን በሚል በይዞታቸው ላይ ድብደባ እየፈፀሙ ነው፡፡

 

ያም ሆኖ ሁቲዎቹ እስካሁን ከአቋማቸው ሸብረክ እንዳላሉ ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡

 

የየመን ሁቲዎች ርዕሰ ከተማዋ ሰንዓን ጨምሮ የአገሪቱን ሰሜናዊ ክፍል ያስተዳድራሉ፡፡

 

የኢራን ሁነኛ የጦር እና የፖለቲካ ሸሪኮች እንደሆኑም ይነገራል፡፡

 

 

እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ደቡባዊ ጠርዝ በምትገኘው ራፋ የጦር ዘመቻ እንድታካሂድ አሜሪካ ተስማምታለች መባሉን የዋይት ሐውስ ሹሞች ሐሰት ነው አሉ፡፡

 

እስራኤል በኢራን ላይ የምትወስደውን የአፀፋ እርምጃ ቅልብጭ ካደረገችው በምላሹ የራፋ ዘመቻዋን እንድታካሂድ አሜሪካ ፈቅዳላታለች የሚል ወሬ እየተናፈሰ መሆኑን አናዶሉ ፅፏል፡፡

 

እስራኤል የራፋ ዘመቻዋን እንድትተው ከየአቅጣጫው ተማፅኖ ሲቀርብላት ቆይቷል፡፡

 

ራፋ በእስራኤል ዘመቻ ከተለያዩ የጋዛ ክፍሎች የተፈናቀሉ ከሚሊዮን በላይ ፍልስጤማውያን ተፈናቃዮች የተጠለሉባት እንደሆነ ይነገራል፡፡

 

እስራኤል በራፋ ሙሉ ወታደራዊ ዘመቻ የምታካሂድ ከሆነ አሁንም በመባባስ ላይ የሚገኘውን ሰብአዊ ቀውስ ይበልጥ ያባብሰዋል የሚል ስጋት አለ፡፡

 

የእስራኤል የጋዛ  የጦር ዘመቻ ከመንፈቅ በላይ ሆኖታል፡፡


 የኔነህ ከበደ


 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

 

Telegram:  @ShegerFMRadio102_1

 

 

 

Yorumlar


bottom of page