#ቀይ ባህር
ማኤስክ የተሰኘው የመርከብ ጭነት አጓጓዥ ኩባንያ ወደ ቀይ ባህር አገልግሎቴ ልመለስ ነው አለ፡፡
ኩባንያው ቀደም ሲል የቀይ ባህር ቀጠና እና የባብኤል መንደብ መተላለፊያ ሰርጥ ይቅርብኝ ካሉ የመርከብ አጓጓዥ ኩባንያዎች አንዱ እንደነበር አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡
ማኤስክ ቀይ ባህር ለጊዜው ይቅርብኝ ያለው የየመኖቹ ሁቲ ታጣቂዎች በቀይ ባህር ተላላፊ መርከቦች ላይ ሲሰነዝሩ በቆዩት ጥቃት ፍራቻ ነው፡፡
ሁቲዎቹ ከእስራኤል ጋር አንዳች ግንኙነት ባላቸው እና መዳረሻቸውን የእስራኤልን ወደቦች ያደረጉ መርከቦችን እንደሚመቱ በተደጋጋሚ ሲዝቱ ቆይተዋል፡፡
ማኤስክ በቀይ ባህር ለሚተላለፉ መርከቦች አሜሪካ መራሹ ጥምረት ከለላ ለመስራት በመሰናዳቱ ወደ ቀይ ባህር መመለሴ አይቀርም ማለቱ ተሰምቷል፡፡
የሶማሊያ መንግስት ሰራዊት በሰሞኑ የጦር ውሎዬ በለስ እየቀናኝ ነው አለ፡፡
ጦሩ እስከ ትናንት ከሰዓት በነበሩት 24 ሰዓታት 80 ያህል የአልሸባብ ፅንፈኛ ቡድን ታጣቂዎችን መግደሉን አዛዦቹ እንደተናገሩ አናዶሉ ፅፏል፡፡
የመንግስት ጦር ፅንፈኛ ታጣቂዎቹን የገደለው ሙዱግ በተባለው ግዛት ባካሄደው ዘመቻ ነው ተብሏል፡፡
ከ2 ቀናት በፊትም የሶማሊያ መንግስት ጦር 130 የአልሸባብ ታጣቂዎችን ገድያለሁ ማለቱን ዘገባው አስታውሷል፡፡
የሶማሊያ መንግስት ጦር የአልሸባብ ፅንፈኛ ቡድንን ለመደምሰስ ታላቅ ዘመቻ ከጀመረ ከአመት በላይ ሆኖታል፡፡
ከፅንፈኛው ቡድን ጋር የሚካሄደው ውጊያ በጠቅላላው 16 አመታትን እንዳስቆጠረ ዘገባው አስታውሷል፡፡
የአዘርባጃን መንግስት ሁለት የፈረንሳይ ዲፕሎማቶችን አገሬን ለቅቃችሁ ውጡልኝ አላቸው፡፡
የአዘርባጃን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሁለቱን ፈረንሳውዠያን ዲፕሎማቶች ለማስወጣት የወሰነው በደፈናው ከዲፕሎማሲያዊ ተልዕኳቸው ተቃራኒ የሆነ ተግባር ሲፈፅሙ አግኝቻቸዋለሁ ብሎ እንደሆነ አናዶሉ ፅፏል፡፡
በአገሪቱ የሚገኙትን የፈረንሳይ አምባሳደር በማስጠራት ስለ ጉዳዩ አብራርቶላቸዋል ተብሏል፡፡
ዲፕሎማቶቹ ከአዘርባጃን ለቅቀው እንዲወጡ ከትናንት አንስቶ የ48 ሰዓታት ጊዜ እንደተሰጣቸው ታውቋል፡፡
በአሜሪካ የኮሎራዶ ግዛት ፖሊስ የቀድሞው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሪፖብሊካዊው የፖለቲካ ማህበር የፕሬዝዳንታዊ እጩ ፉክክር ውጭ እንዲሆኑ ባዘዙት ዳኞች ላይ የተሰነዘረውን ዛቻ እየመረመርኩት ነው አለ፡፡
ማጣራቱን የፌዴራል የምርመራ ቢሮ /FBI/ም እንደተቀላቀለው ቢቢሲ ፅፏል፡፡
የኮሎራዶጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀድሞው ፕሬዘዳንት ለሪፖብሊካዊው የፖለቲካ ማህበር ፕሬዘዳንታዊ እጩ ምርጫ እንዳይወዳደሩ 4 ለ3 በሆነ ድምፅ የወሰነው ባለፈው ሳምንት ነው፡፡
ውሳኔውን በደገፉት ዳኞች ላይ ለጊዜው ካልታወቀ ወገን ዛቻ ተሰንዝሮባቸዋል ተብሏል፡፡
የዴንቨር ፖሊስ ምርመራውን ከማካሄድ በተጨማሪ ለዳኞቹ የተጠናጀከረ ጥበቃ እያደረገ መሆኑ ተሰምቷል፡፡
ቀደምሲል ትራምፕ የግዛቲቱን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ በመቃወም ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤት እላለሁ ማለታቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz
Comments