ኬንያ ወቅታዊው ጎርፍ የገደላቸውን ዜጎች በብሔራዊ ደረጃ ልታስባቸው ነው፡፡
የሰሞኑ ጎርፍ ከ200 በላይ ሰዎች መግደሉን ቢቢሲ አስታውሷል፡፡
የጎርፍ ማቾቹ በነገው እለት በብሔራዊ ደረጃ ይታሰባሉ ተብሏል፡፡
በእለቱም የ100 ሚሊዮን የዛፍ ችግኝ ተከላ እንደሚከናወን ታውቋል፡፡
የችግኝ ተከላው በመጪዎቹ 10 አመታት በኬኒያ 15 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል የተያዘው ውጥን አካል መሆኑ ታውቋል፡፡
የችግኝ ተከላው የአየር ለውጥ ተፅዕኖን ለማቃለል ከፍተኛ ባለውለታ እንደሚሆን ታምኖበታል ተብሏል፡፡
በኬኒያ ወቅታዊው ጎርፍ የአየር ለውጥ ውጤት እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡
አሜሪካ ለእስራኤል ቦምቦችን ማቀበሏን በጊዜያዊነት እንዳቆመች የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦውስቲን አረጋገጡ ተባለ፡፡
ቀደም ሲል አንድ በስም ያልተጠቀሱ የአሜሪካ መንግስት ሹም ይሄንኑ ጉዳይ እወቁት ብለው ነበር መባሉ ተሰምቷል፡፡
የመከላከያ ሚኒስትሩ በአሜሪካ ኮንግረስ ኮሚቴ ፊት ቀርበው በሰጡት ምስክርነት ጉዳዩን አረጋግጠዋል ተብሏል፡፡
አሜሪካ ለእስራኤል ቦምቦቹን ማቀበሏን ያቆመችው በእስራኤል የራፋ ዘመቻ ምክንያት ነው፡፡
በጋዛ ሰብአዊ ቀውሱን ይበልጥ ያከፋዋል በሚል እስራኤል የራፋ ዘመቻዋን እንድትተወው ከየአቅጣጫው ስትጎተጎት ቆይታለች፡፡
እስራኤል ግን ሕልውናዬ ይቀድማል በሚል ምክንያት ለጥሪው ቁብ እንዳልሰጣት አልጀዚራ ፅፏል፡፡
በእስራኤል እና በደቡብ ሊባኖሱ የጦር ድርጅት (ሔዝቦላህ) መካከል ወሰን ተሻጋሪው መጠቃቃት እየከፋ ነው ተባለ፡፡
የጋዛው ጦርነት ከተቀሰቀሰ አንስቶ ሔዝቦላህ ወደ ሰሜናዊ እስራኤል ሮኬቶችን ከመተኮስ አልታቀበም፡፡
እስራኤልም በከባድ መሳሪያዎች እና በጦር አውሮፕላኖች ሊባኖስ ውስጥ የአፀፋ ጥቃት እየፈፀመች ነው፡፡
ሰሞኑን ደግሞ የእስራኤል የአየር ድብደባ ከፍቷል ተብሏል፡፡
የወሰን አካባቢ ነዋሪዎችም በብዛት እየወጡ ነው ተብሏል፡፡
ሔዝቦላህ የኢራን ሁነኛ የጦር አጋር እና የፖለቲካ ሸሪክ መሆኑ ይነገራል፡፡
በብራዚል የደቡባዊቱ ሪዮ ግራንዴ ግዛት ነዋሪዎች በሕይወት ዘመናችን እንዲህ ዓይነት ከባድ ጎርፍ አጋጥሞን አያውቅም አሉ፡፡
በግዛቲቱ የደረሰው ጎርፍ እና የውሃ መጥለቅለቅ በጥቂቱ 95 ሰዎችን መግደሉን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ከ130 በላይ የሚሆኑት ደግሞ የደረሱበት አልታወቀም ተብሏል፡፡
ወንዞች እና ሌሎች የውሃ አካላት ከአፍ እስከ ገደፋቸው ሞልተው በመፍሰሳቸው ሰፊ አካባቢ መጥለቅለቁ ታውቋል፡፡
መጥለቅለቁ የሰብአዊ ድጋፍ ተግባሩም በእጅጉ አዳጋች ማድረጉ ተሰምቷል፡፡
በጎርፉ ምክንያት 80 በመቶ ያህሉ የግዛቲቱ ነዋሪዎች ከንፁህ ውሃ ተቆራርጠዋል ተብሏል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Youtube: http://tiny.cc/ShegerFM1021Radio
Website: https://www.shegerfm.com/
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments