በተለያዩ ምክንያቶች እና በተፈጥሮ አካል ጉዳተኛ የሆኑትን በሚደረገው ሀገራዊ ምክክርና ውይይት ላይ ሀሳብ እንዲሰጡ እድል ሊሰጣቸው ይገባል ተባለ፡፡ ይህን ያለው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የአካል ጉዳተኞችና የአረጋዊያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ አካል ጉዳተኞች በሃገራዊ ጉዳይ ላይ እንዲመክሩና እንዲያማክሩ እንድል ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል፡፡
በሚደረገው ሀገራዊ ምክክር ላይ ለአካል ጉዳተኞች እንቅፋት የሆኑትን ከወዲሁ በመለየትና በማውጣት በውይይቱ ላይ የነቃ ተሳታፊ እንዲሆኑ ሁኔታዎችን እንዲመቻቹ ኮሚሽነሯ ጠይቀዋል፡፡
ለዚህም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለምክክር እና ለውይይት የሚጠቀምባቸው አዳራሾች እና የመወያያ ስፍራዎች ምን ያህል ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ናቸው የሚለውን ማጤን አለበት ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የትራንስፖርትና የመሳሰሉ የአካል ጉዳተኞች ላይመቹ የሚችሉ ሁኔታዎችን መፍታት ከኮሚሽኑ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ያ ካልሆነ አካል ጉዳተኞች በምክክሩ ላይ የነቃ ተሳታፊ እንዳይሆኑ ስለሚዳርጋቸው እነዚህ ችግሮችን ኮሚሽኑ እንዲፈታ ኢሰመኮ ጠይቋል፡፡
በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞችን የተመለከተ ትክክለኛ ቆጠራ ባለመካሄዱ ትክክለኛ ቁጥራቸው በውል ባይታወቅም ከ20 ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያውያን የተለያየ የአካል ጉዳት እንዳለባቸው ይገመታል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz
Comments