ህዳር 13፣2017 - በሱዳን የቀጠለው ጦርነትን በመሸሽ፤ የሱዳን ዜጎች በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በኩል ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ቀጥለዋል ተብሏል
- sheger1021fm
- Nov 22, 2024
- 1 min read
በሱዳን ጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉ እና ከሌላም የአፍሪካ ሀገራት መጥተው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በኩል ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ስደተኞች ቁጥር ከ107,000 ተሻግሯል ተባለ፡፡
በሱዳን የቀጠለው ጦርነትን በመሸሽ፤ #የሱዳን_ዜጎች በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በኩል ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ቀጥለዋል ተብሏል፡፡
ወደ ክልሉ የሚገቡ ስደተኞች የሚበዙት የሱዳኑ ጦርነት ያፈናቀላቸው ይሁኑ እንጂ የሌሎች አፍርካ ሀገራት ዜጎችም እንዳሉበት ሰምተናል፡፡
በዚህም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በኩል ብቻ ያሉ ከሌላ ሀገራት የመጡ #ስደተኞች ቁጥር ቁጥር 107,222 መሆኑን ክልሉ ነግሮናል፡፡
እነዚህ ስደተኞች ሸርኮሌ፣ ኩርሙክ፣ ባምባሲ እና ኡራ በተባሉ አራት የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች እንደሚገኙም ሰምተናል፡፡

ለመሆኑ እነዚህ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣው የውጭ ሀገራት ስደተኞች ክልሉ እንዴት እያስተናገዳቸው ነው የደህንነታቸው ጉዳይስ?
ጸሀይ ጉዮ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሰላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ የሰላም ግንባታ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ሀላፊ ሲሆኑ፤ ‘’የውጭ ሀገራት ስደተኞቹ አለማቀፍ #የስደተኞች_አያያዝ_ስምምነትን ባከበረ መልኩ ተቀብለን እያስተናገድናቸው ነው’’ ብለውናል፡፡
‘’ስደተኞቹ የጤና እና መሰል ማህበራዊ አገልግሎቶችን የሚያገኙት ከዚሁ ክልል በመሆኑ የክልሉ መንግስት የተቻለውን እያደረገ ይገኛል’’ ሲሉም ሀላፊው ነግረውናል፡፡
በምግብ፣ በአልባሳትና በመጠለያ በኩል የተለያዩ ረጂ ድርጅቶች እያገዙ ቢሆንም በቂ ስላልሆነ ሌሎች ማገዝ የሚችሉ ይርዱን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከሱዳንና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተሰደው ከመጡ ስደተኞች በተጨማሪም #ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው ወደ ክልሉ የሚገቡትንም ደህንነታቸውን በጠበቀ መልኩ እያስጠለልን ነው ብለዋል አቶ ጸሀይ፡፡
ከሌሎች ሀገራት በመምጣት በኢትዮጵያ ያሉ ስደተኞች እና ስደተኝነት ጠያቂዎች ብዛት፤ ከአንድ ሚሊዮን መሻገሩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛው የስደተኞች ኮሚሽን (UNHCR) ሪፖርት ያሳያል፡፡
ከእነዚህ ከ1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ውስጥ 80 በመቶው ሴቶች እና ህፃናት መሆናቸው በሪፖርቱ ተነግሯል፡፡
ለስደተኞቹ ምግብ ጨምሮ የተለያዩ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት ከፍተኛ የበጀት እጥረት እያጋጠመ እንደሚገኝም UNHCR ከወራት በፊት አሳውቆ ነበረ፡፡
ማንያዘዋል ጌታሁን
Comentarios