በአማራ ክልል ላጋጠሙ ሰብአዊ ቀውሶች፤ የረድኤት ድርጅቶችና የሚመለከታቸው ሁሉ እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ፡፡
በሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች በአማራ ክልል ያለው ሰብአዊ ቀውስ እየከፋ መጥቷል ተብሏል፡፡
ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ አሁንም ድረስ ክልሉ ከወታደራዊ ግጭት መውጣት ባለመቻሉ በሚሊዮኖች የምግብ እና የቁሳቁስ አስቸኳይ እርዳታ ይፈልጋሉ ተብሏል፡፡
ዛሬ በአዲስ አበባ ሸራተን አዲስ በጉዳዩ ላይ በተዘጋጀ ውይይት ላይ በክልሉ ያለው አሁናዊ ሰብአዊ ቀውስ በዝርዝር በማቅረብ የእገዛ ጥሪ ያቀረበው በክልሉ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ነው፡፡
የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የረድኤት ድርጅቶች፣ ሰብአዊ መብት ተከራካሪ ተቋማትም በተገኙበት በዚሁ ውይይት እንደተነገረው ማባሪያ ያጣው ወታደራዊ ግጭት፣ ከኦሮሚያና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ የተፈናቀሉ ወደ 600,000 የተጠጉ ሰዎች መፍትሄ አለማግኘታቸው እና ድርቅን ጨምሮ የተለያዩ ተፈጥሯዊ አደጋዎች የክልሉን ሰብአዊ ቀውስ የከፋ እንዲሆን አድርገውታል ተብሏል፡፡
የጤና ተቋማት፣ ት/ቤቶች በግጭቶች ምክንያት መውደማቸውና አንዳንዶችም በስጋት ምክንያት መዘጋታቸውን ሰምተናል፡፡
በዚህም ምክንያት 4.7 ሚሊዮን ህፃናት ከት/ት ገበታ ውጭ ናቸው ተብሏል፡፡
4,870 ት/ቤቶች መዘጋታቸው እና 5,379 ት/ቤቶች ደግሞ መውደማቸው በመድረኩ ላይ ተነግሯል፡፡
የጤና ተቋማትም በግብዓት እጥረት እየተፈተኑ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ከዚያም በላይ የደህንነት ስጋት የጤና ባለሞያዎችም በአግባቡ ስራቸውን እንዳይሰሩ ምክንያት ሆኗል ተብሏል፡፡
በስጋት ምክንያት በመኪና አደጋ የቆሰለ ሰው እንኳን ወደ ጤና ተቋም ሂዶ ለመታከም ያልቻለበት ጊዜ ነው ተብሏል፡፡
ሰብአዊ ቀውሱ የከፋ በመሆኑ መፍትሄ ለማበጀት የገንዘብና የቁሳቁስ እርዳታ ያስፈልጋል ያለው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረሙ ያልዘገየ እገዛ እንዲደረግ ጠይቋል፡፡
ይህን ማድረግ ካልተቻለ በአማራ ክልል ያለው ሰብአዊ ቀውስ ይበልጥ እንዳይወሳሰብ ስጋት አለኝ ብሏል፡፡
ትዕግስት ዘሪሁን
Comments