top of page

ህዳር 17፣2017 - አዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ግቢ ውስጥ 1,200 ተመልካቾችን የሚይዝ የቴአትር አዳራሽ ያካተተ ህንጸ በመገንባት ላይ ይገኛል ተብሏል

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከሚገኙት 5 ቴአትር ቤቶች ውስጥ አራቱ (ሀገር ፍቅር፣ የህጻናትና ወጣቶች፣ የአዲስ አበባ ቴአትር እና ባህል አዳራሽ እና ራስ ቴአትር) በከተማ አስተዳደሩ ስር የሚገኙ ናቸው፡፡


ከእነዚህ #ቴአትር_ቤቶች ውስጥ ለኪነ ጥበብ ስራዎች ክፍት ሆነው አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት ሀገር ፍቅር እና የህጻናት እና ወጣቶች ቴአትር ቤቶች ብቻ ናቸው፡፡


የራስ ቴአትር ቤት አዳራሽ ከፈረሰ ከ10 ዓመት በላይ ሆኖታል፣ የአዲስ አበባ ቴአትር እና ባህል አዳራሽ ደግሞ ለእድሳት ተብሎ ስራውን ካቆመ በኋላ እድሳቱ ቢጠናቀቅም በልዩ ልዩ ምክንያቶች አሁንም የኪነ ጥበብ ስራዎች ወደ መድረኩ ሊመለሱ አልቻሉም፡፡

አሁን ላይ እነዚህን ስራ ያቆሙ ቴአትር ቤቶች መፍትሄ እንዲያገኙ የማድረግ እና የማስተዳደር ሃላፊነት የተሰጠው ‘’አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቴአትር ቤቶች አስተዳደር ድርጅት’’ የሚል ስያሜ የተሰጠው ተቋም እንቅስቃሴ መጀመሩን ሰምተናል፡፡


‘’ #ራስ_ቴአትር እና የአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ በስራ ላይ አለመሆናቸውን ተከትሎ ባለሙያዎቹ ስራቸውን የሚያቀርቡበት፣ ተመልካችም የኪነ ጥበብ ስራዎችን የሚታደምበት ቦታ አጥቷል ተብሎ የሚነሳው ሀሳብ አሁን ላይ ሙሉ ለሙሉ በሚነገረው ልክ አይደለም’’ በማለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቴአትር ቤቶች አስተዳደር ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ ባረከ ታደሰ አስተባብለውታል፡፡


‘’አሁን ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከዚህ ቀደም በነበረው መጠን የአዳራሽ እና የኪነ ጥበብ መሰናዶዎች ማቅረቢያ እጥረት የለም’’ ያሉን ዋና ስራ አስፈፃሚው በማሳያነትም በአዲሱ #የአድዋ መታሰቢያ ሙዝየም ህንጻ ላይ ብቻ 3 ለዚሁ አገልግሎት ተብለው የተዘጋጁ አዳራሾች መኖራቸውን እና ሌሎችም በመጠናቀቅ ላይ ያሉ አዳራሾች እንዳሉ አስረድተዋል፡፡


‘’ችግሩ የአዳራሽ እጥረት ሳይሆን የኪነ ጥበብ ባለሞያው ትያትር እና ሌሎች ዝግጅቶችን እያዘጋጀ ባለመሆኑ እንዲሁም የማዘጋጀት ፍላጎቱ ያላቸውም ቢሆን መጥተው እየጠየቁ ባለመሆኑ ነው’’ ብለዋል፡፡

ቴአትር መምህር እና አዘጋጅ ተሻለ አሰፋ(ዶ/ር)፤ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ቀደም ብሎ ከነበሩት የትያትር ቤቶች ቁጥር ውስጥ አሁን በስራ ላይ ያሉት ግማሾቹ ብቻ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡


ይህ ደግሞ በየጊዜው ቁጥሩ እየጨመረ ያለውን ቴአትር ባለሞያ የምጽፈውን እና የማዘጋጀውን ቴአትር የማሳይበት ቦታ የለም በማለት ወደኋላ እንዲሸሽ እያደረገው ነው ሲሉ ነግረውናል፡፡


ይሁን እንጂ አሉ ተብለው የሚነገሩት አዲስም ሆኑ ነባር አዳራሾች እንዲሁም በፓርኮች ውስጥ የተሰሩት አንፊ የቴአትር ማሳያዎች ለባለሞያው የተዘጉ ከመሆናቸው በተጨማሪም አብዛኛዎቹ ደረጃውን የጠበቀ #ቴአትር ለማዘጋጃነት የሚመቹ አይደሉም ይላሉ፡፡


የኪነ ጥበብ ባለሙያው ከዚህም በላይ ገፍቶ መሄድ እና መጠየቅ አለበት በሚለው ሃሳብ የሚስማሙ ቢሆንም ባለሞያዎች ቴአትር ለመለማመድ የተለያዩ የመንግስት አዳራሾችን በሚጠይቁበት ወቅት ክፍያ እንደሚጠየቁ እና አለፍ ሲልም ለጥያቄያቸው መልስ የሚሰጣቸው እንደማይኖር ተናግረዋል፡፡


አርቲስት ደበሽ ተመስገንም የትያትር መስርያ እና ማሳያ ቦታ ባለመኖሩ፣ ፍላጎቱም ብቃቱም ያላቸው ባለሞያዎች ከ10 ዓመት በላይ ያለስራ ተቀምጠዋል ሲል ነግረውናል፡፡


እንደተባለው የቴአትር ባለሞያዎቹ ሳይሰሩ ቀርተው ቢሆንም እንኳን ደመወዝ የሚከፍላቸው ቴአትር ቤትም ሆነ አዲሱ የቴአትር ቤቶች አስተዳደር ተከታትሎ የማሰራት፣ ሁኔታዎችን ማመቻቸት አለበት፣ ባለሞያዎቹ በዚህ ጉዳይ ተወቃሽ ሊሆኑ አይችሉም ብለውናል፡፡


‘’ #የኪነ_ጥበብ ማቅረቢያ እና መለማመጃ ቦታ እጥረት የለም’’ ያሉት አበባ ከተማ አስተዳደር ትያትር ቤቶች አስተዳደር ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ባረከ ታደሰ፤ ‘’በሌላ በኩል ደግሞ የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ በዋና መስርያ ቤቱ ግቢ ውስጥ 1,200 ተመልካቾችን የሚይዝ የቴአትር አዳራሽ ያካተተ ህንጸ በመገንባት ላይ ይገኛል’’ ሲሉም አስረድተዋል፡፡

ይህ ህንጻ ተጨማሪ 3 የሲኒማ አዳራሾችንም የያዘ ሆኖ አራቱም የከተማዋ ትያትር ቤቶች በጋራ እንዲጠቀሙበት ታስቦ እየተሰራ ያለ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡


ራስ ትያትርም ቢሆን አዲስ በተሰጠው ቦታ ላይ ግንባታውን ለማከናወን የተጀመረ ሂደት እንዳለ እና የቴአትር እና ባህል አዳራሽም በቅርቡ ወደ ቀደመ ስራው ይመለሳል ተብሏል፡፡


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


📌 YouTube: https://t.ly/9uH-g


📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s


Commentaires


bottom of page