14 በመቶ ላይ ብቻ የተቆለፈበት የብድር ጣሪያ በተወሰነ ፐርሰንት ከፍ ማድረግ እንዲቻል መንግስት ተወያይቶ አቅጣጫ የሰጠበት ጉዳይ መሆኑንን የገንዘብ ሚኒስትር ድኤታው እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር ) ነግረውናል።
የኢትዮዽያ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ጥብቅ የገንዘብ ማሻሻያ ፖሊሲዎችን ተግብሯል።
የሀገር ውስጥ ብድር እድገትም በ14 በመቶ ጣሪያ ተገድቧል።
በዚህ መሰረት ሁሉም ንግድ ባንኮች የብድር ዕድገት ዕቅዳቸውን በዚህ የብድር ጣሪያ መሠረት እንዲያስተካክሉ ተነግሯቸው ቆይተዋል።
በዚህ ጉዳይና አጠቃላይ ለውጡ ምን ይመስላል ብለን የገንዘብ ሚኒስትር ድኤታውን እዮብ ተካልኝን(ዶ/ር) ጠይቀናል።
እሳቸው ለውጡ የተሳካ እንደሆነ ተናግረዋል።
ከብድር ገድቡ ጋር በተገናኘ ምን ለውጥ ይጠበቃል ኢኮኖሚው እንዳይፈዝና የመስሪያ ካፒታል እንዲቀርብ ምን ታሰበ ማለታችን አልቀረም።
የገንዘብ ሚኒስትር ድኤታው የባንኮች የገንዘብ የማበደር ጣሪያ ለማሻሻል እየተሰራ እንደሆነ ነግረውናል።
በዚህ ጉዳይም ውይይት እየተደረገ እንደሆነ እና በቅርቡም በብሔራዊ ባንከ በኩል እንደሚነገር አስረድተውናል።
አሁን 14 በመቶ ላይ ብቻ የተቆለፈበት የብድር ጣሪያ በተወሰነ ፐርሰንት ከፍ ማድረግ እንዲቻል መንግስት ተወያይቶ አቅጣጫ የሰጠበት ጉዳይ መሆኑንም ሚኒስትር ድኤታው ነግረውናል።
ባንኮች ከብድር ጋር በተገናኘ አምራች የሆኑ ዘርፎች ላይ እንዲያተኩሩ ተመክረዋል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለመንግሥት የሚሰጠውን የቀጥታ የብድር መጠን በእጅጉ በመቀነስ ባለፈው ዓመት ከተሰጠው ብድር 1/3ኛ እንዳይበልጥ እና መሠረታዊ በሆነ መልኩ እንዲገደብ ማድረጉን ተናግሯል።
ባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት ሲያጋጥማቸው ከብሔራዊ ባንክ በሚወስዱት የአስቸኳይ ጊዜ ብድር ላይ የሚከፍሉት የወለድ መጠን ከ16 በመቶ ወደ 18 በመቶ ከፍ እንዲል መደረጉም ታውቋል።
ተህቦ ንጉሴ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 YouTube: https://t.ly/9uH-g
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments