መንግስታዊው የአዲስ አበባ የአካባቢ ጥበቃ ባልስጣን ተቋማት የአካባቢ ብክለት ፈፅመው መሆኑን ወይም አለመሆኑን ለማረጋገጥ ስሄድ ወደ ግቢያቸው እንኳን እንዳልገባ እየተከለከልኩ ነው አለ፡፡
መንግስታዊ ተቋማት ሳይቀር ስራዬን በአግባቡ እንድሰራ እየፈቀዱልኝ አይደለም ብሏል፡፡
የአካባቢ ተፅእኖ ግምገማ ሳይደረግባቸው የንግድ ፈቃድ እና የብቃት ማረጋገጫ የሚሰጡ ተቋማት ስራችንን እያወኩት ነውም ሲል ባለስልጣኑ ተናግሯል።
የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል ህጉን ተላልፈው በተገኙት ላይ ባለስልጣኑ የሚወስደውን እርምጃ ባለስልጣኑን የልማት አደናቃፊ አድርገው የሚቆጥሩት አንዳንድ ተቋማት እንዳሉም ተነግሯል።
የባለስልጣኑ የአካባቢ ጥበቃ የህግ ተከባሪነት ዳይሬክተር አቶ ለሜሣ ጉደታ በከተማዋ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ኢንዱስትሪዎች አይደለም የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ሊደረግባቸው ምን እንደሚያመርቱ እንኳን የማናውቅበት ደረጃ ላይ ደርሰናል ብለዋል።
በቦታው ግምገማ ለማድረግ ሲኬድም ለእኛ በራቸው ዝግ እየሆነ ተቸግረናል ብለዋል፡፡
የድምጽ ብክለት ደረጃውን ባለፉ ዳንኪራ ቤቶች ላይ የማሸግ እና ፍቃድ የመሰረዝ እርምጃ እየወሰድን ቢሆንም ንግድ ቢሮ ስራችንን ማገዝ ሲገባው እርምጃ በተወሰደበት ቤት ላይ በሌላ ሰው ስም ሌላ ፍቃድ እንዲሰጥ በማድረግ ስራችን ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ እንዲሆን አድርጓል ሲሉ አቶ ለሜሣ ጉደታ ነግረውናል።
ከንግድ ቢሮ ባለፈም ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ላልተደረገባቸው ምሽት ቤቶች እና ለከፍተኛ ድምፅ ብክለት አጋላጭ በሆኑ ትላልቅ ፎቆች ውስጥ ላሉ ዳንኪራ ቤቶች የብቃት ማረጋገጫ እየሰጠ መሆኑንም አቶ ለሜሣ ተናግረዋል።
ትናንት በጉዳዩ ላይ ውይይት ሲደረግ ቅሬታ የቀረበባቸው የተጠቀሱት ተቋማት የተገኙ ቢሆንም ምላሽ ግን ሳይሰጡበት አልፈዋል፡፡
ፍቅሩ አምባቸው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 YouTube: https://t.ly/9uH-g
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments